Saturday, 17 October 2015 08:52

‘ለሽ’ እና “የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(15 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እሱዬው የመንግሥት ሠራተኛ ነው፡፡ እናላችሁ… ወደ ዶክተር ይሄድና… “ዶክተር መተኛት አቃተኝ…” ይለዋል፡፡ዶክተሩም… “እንቅልፍ አይወስድህም ማለት ነው?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡የመንግሥት ሠራተኛው ሆዬ ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው… “ማታ በደንብ አድርጌ እተኛለሁ፡፡ ጠዋትም አብዛኛውን ሰዓት ለሽ ብዬ ነው የምተኛው፡፡ አሁን የቸገረኝ ከሰዓት በኋላ መተኛት አልቻልኩም…” ብሎት አረፈ፡፡ እንዲህ እየተተኛ ነው ሦስት ዲጂቷ ላይ የሚደረሰው! ቂ…ቂ…ቂ…
የእንቅልፍ ነገር ከተነሳ አይቀር ይቺን ስሙኝማ… ሰውዬው መነሳት የነበረበትን ሰዓት አሳልፎ አርፍዶ ይተኛል፡፡ እናላችሁ… ጓደኝዬው እንደምንም ብሎ ይቀሰቅሰዋል፡፡ እናላችሁ … “አንተ ሰውዬ የማንቂያ ደወሉ ሲጮህ እንኳን አትሰማም!” ይለዋል፡፡ ሰውዬውም “አልሰማሁም…” ይላል፡፡
ይሄኔ ጓደኝዬው ግራ ይገባውና… “ደወሉ እንደዛ አገሩን ሲያደበላልቀው እንዴት ነው የማትሰማው?“ ይለዋል፡፡
ሰውዬው ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው… “እንቅልፍ ወስዶኝ እንዴት ልስማልህ!” አለውና አረፈው፡፡
እናማ የማንቂያ ደወሉ ሲደወል መነሳት አሪፍ ነው፡፡ ደግነቱ አንዳንዱ ቦታ መዶሻ መኖሩ! ቂ…ቂ…ቂ…
እንቅልፍ የሰሞኑ አጀንዳ ሆኖ ሰነበተ ብለን ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
እኔ የምለው…‘ለሽ’ እየተባለ እንዴት ተደርጎ ነው ስለ ስኬት ምናምን ማውራት የሚቻለው! ‘ለሽ’
ማለት በራሱ ‘ስኬት’ ካልሆነ በቀር፡፡
ስሙኝማ…የስኬት ነገር ካነሳን አይቀር…ይቺን ስሙኝማ…
በ4 ዓመት ዕድሜ ስኬት ማለት ሱሪ ላይ ፊኛ አለማቃለል ነው፡፡
በ12 ዓመት ዕድሜ ስኬት ማለት ጓደኞች ማፍራት ነው፡፡
በ16 ዓመት ዕድሜ ስኬት ማለት የመንጃ ፈቃድ መያዝ ነው፡፡
በ20 ዓመት ዕድሜ ስኬት ማለት ‘እነሆ በረከት’ ማለት ነው፡፡
በ35 ዓመት ዕድሜ ስኬት ማለት ገንዘብ ማግኘት ነው፡፡
በ50 ዓመት ዕድሜ ስኬት ማለት ገንዘብ ማግኘት ነው፡፡
በ60 ዓመት ዕድሜ ስኬት ማለት ‘እነሆ በረከት’ ማለት ነው፡፡
በ70 ዓመት ዕድሜ ስኬት ማለት መንጃ ፈቃድ መያዝ ነው፡፡
በ80 ዓመት ዕድሜ ስኬት ማለት ጓደኞች ማፍራት ነው፡፡
በ90 ዓመት ዕድሜ ስኬት ማለት ሱሪ ላይ ፊኛ አለማቃለል ነው፡፡
አሪፍ አይደል!
የምር ግን እኮ… አለ አይደል… እንቅልፍ ማለት ወንበር ላይ፣ ወይም ጠረጴዛ ላይ (አይ ይሄ ‘ሶሻል ሚዲያ’ የሚሉት ነገር!) ለሽ ማለት ብቻ አይደለም፡፡ የተኛውማ … በቃ ተኝቷል፡፡ ይልቁንስ በየቢሮው ዓይናችን ተገልጦ ‘ለሽ’ የምንል መአት አይደለን እንዴ! ድርጅቶች መሥሪያ ቤቶች ‘ለሽ’ ይሉ የለም እንዴ! “ማሳካት የተቻለው የዕቅዱን 29 በመቶ ብቻ ነው ማለት… እኮ ዓለም ዘጠኝ ብሎ ‘ለሽ’ የማለት ምልክት ነው፡፡እናማ… የተኛ ሰው የመዶሻ ድምጽም ሆነ የማንቂያ ደወል ስለማይሰማ አሪፍ አይደለም፡፡ የተኛ ድርጅት የመዶሻ ድምጽም ሆነ የማንቂያ ደወል ስለማይሰማ አሪፍ አይደለም፡፡ የተኛች አገር የመዶሻ ድምጽም ሆነ የማንቂያ ደወል ስለማትሰማ አሪፍ አይደለም፡፡አሀ…መስማት ሲያቅት እኮ ማሰብም ያቅታል፡፡ እግረ መንገዴን ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው ኑሮ ክፍት ይለዋል፡፡ ስለዚህ ከዚህ ሁሉ አንደኛውን ‘አሪ ቬዴርቺ’ ምናምን ብል ይሻላል ብሎ ይወስናል፡፡ እናላችሁ…ለማን ቢያማክር ጥሩ ነው…ለሚስቱ፡፡  
ታዲያላችሁ ‘አገሩን በእሪታ ታቀልጠዋለች’ ብሎ ነው መሰለኝ… “ራሴን ላጠፋ ስለሆነ የትኛውን
አካሌን በጥይት ልበለው?” ይላታል፡፡ ሚስት ሆዬ “ደረትህን በለው…” ትለዋለች፡
እሱም “ለምንድነው ደረቴን የምለው! ለምን ጭንቅላቴን አልለውም!” ሲላት ምን ብትለው ጥሩ ነው
“ጭንቅላትህማ ከሞተ ቆየ እኮ!” ተሸክመውት ቢዞሩ ጭንቅላት ሁሉ ‘ህይወት አለው’ ማለት እንዳልሆነ ልብ ይባል— በተለየ የደወሉን ድምጽ መስማት ካቆምን!ስሙኝማ…ዘንድሮ አንድ ችግሩ ምን መሰላችሁ…አይደለም ተኝተን፣ እንዲሁ ቁልጭ ብለንም መደማመጥ አልቻልንም፡፡ እናማ…ሁሉንም ነገር ከራሳችን ወገን ብቻ የማየት ነገር በዝቷል፡፡ ቦተሊከኛ ብትሉት ትክክሉ የእኔ መስመር ብቻ ነው፣ የሌሎቹ ውጉዝ ከመአርዮስ ነው አይነት ነገር ይልባችኋል፡፡ ምሁር በሉት ትክክሉ የእኔ ‘አናሊስስ’ ብቻ ነው፣ ሌሎቹ ብስለት የጎደላቸው ናቸው ምናምን ይላል፡፡ አርቲስት በሉት ፈልም ማለት የእኔ ብቻ ነው፣ የሌሎቹ ሁሉ የማይረባ ነው፡፡ ምን

አለፋችሁ ሁሉም… አለ አይደል… “ትክክሉ እኔ ብቻ ነኝ …” እያለ የት እንደሚደረስ ግራ አይገባችሁም!
አለ አይደል…ለእኛ እስከሆነ ድረስ ጉዳዩ ለሌላው ይመች አይመች ምንተእዳችን፡፡ለምሳሌ ታክሲ ላይ ትርፍ ሰው ሲጭኑብን… “ምን ያድርጉ፣ የሚናገራቸው የለ፡ አሁንማ መጫወቻ አደረጉን…” እንላለን፡፡ ከዛላችሁ የሆነ ቀን ታክሲ አቁሞ ልንገባ ስንል ረዳቱ “አባ ሞልቷል…” ይለናል፡፡ ይሄኔ ምን እንል መሰላችሁ… “አንድ ሰው መጨመር አቅቶህ ነው፡፡ ምድረ ውሪ ተሰብስቦ…” ምናምን ይባላል፡፡
እናማ…ሌላውን መተቸት እንጂ ትችት መቀበል የሚባል ነገር የለም፡፡ ራሳችን ላይ ግንዱ ተጋድሞ
ሌላው ያለችውን ስንጥር “አያችሁልኝ!” ማለት የማያሳፍር ነገር ሆኗል፡፡የመደማመጥን ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው በዕድሜ የገፉ ሀብታም አያት ሲሆኑ ለበርካታ ዓመታት የመስማት ችግር አለባቸው፡፡ እንደውም ጭርሱን ‘ጆሯቸው ስር መድፍ ቢፈነዳ አይሰሙም’ ወደሚባልበት ደረጃ ደረሱ፡፡ ታዲያ ለማንም ሳይነግሩ ሀኪም ዘንድ ይሄዳሉ፡፡ ሀኪማቸውም እያንዳንዷን ቃል ልቅም አድርገው መስማት የሚያስችላቸው መሣሪያ ገጠመላቸው፡፡ ቤትም ሲደርሱ ለማንም ትንፍሽ አላሉም፡፡ከአሥራ አምስት ቀናት በኋላ እንደገና ወደ ሀኪሙ ዘንድ ሄዱ፡፡ ሀኪሙም… “ለመሆኑ በደንብ መስማት በመቻልዎ የቤተሰቡ አባላት ደስ ብሏቸዋል?” ብሎ ይጠይቃቸዋል፡እሳቸውም… “ኧረ እኔ ለማንም አልነገርኩም፡፡ አሁንም እንደበፊቱ ምንም መስማት የማልችል ነው የሚመስላቸው፣” ይላሉ፡፡ አከታትለውም “እኔ ግን የሚናገሯትን እያንዳንዷን ነገር ስሰማ ነው የከረምኩት፡፡ ከሰማሁት ተነስቼም ባለፉት ሁለት ሳምንታት ኑዛዜዬን ሦስት ጊዜ ለውጫለሁ፣” ብለውት አረፉ፡እናማ… “አይሰሙም፣ አያዩም” ተብሎ የሚወራው ሁሉ በኋላ ኑዛዜ ማስለወጥ ያስከትላል፡፡እናላችሁ…ያለመደማመጥ ችግር ሥራ እንዳንሠራ ቆልፎ ይዞናል፡፡  አንዳንዴ ሚዲያ ላይ ነገሬ ብላችሁልኝ እንደሆነ አንዱ በሆነ ጉዳይ ላይ ሥራው ላይ አተኩሮ ይተቻል፡፡ የተተቸውን ሥራ የሠራው ሰው (ወይም ‘አድናቂው’) መልስ ሲሰጥ “ያቀረብከው ሀሳብ ትክክል አይደለም…” ምናምን ብሎ ሳይሆን…ትኩረቱ ሰውዬው ላይ ይሆናል፡፡ ‘እባክህ ድሮም እናውቅሀለን…’ አይነት ምላሽ ሆኖ ይቀርባል፡፡እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… አንዳንድ ጊዜ በሆኑ ሚዲያዎች ላይ ሰዎች ሲመላለሱ… አለ አይደል….የምትጠብቁትን ‘ቋንቋ’ ታጣላችሁ፡፡ በዚህም ሆነ በዚያ ምክንያት የሆነ ማማ ላይ አስቀምጣችሁት የነበረ ሰው፣ ወደ ‘መንደር’  ደረጃ ዝቅ ሲልባችሁ አሪፍ አይደለም፡፡በሁሉም ዘርፍ ብትሉ የአንዱን በጎ ጎን በአዎንታ ማየት ለምን እንደሚከብደን፣ ምን መስሎ እንደሚታየን አይገርማችሁም! ‘ቅዳሴው ሲያልቅበት ቀረርቶ ጨመረበት’ አይነት… ነገሩ ሁሉ ከሀሳብ ይርቅና ግለሰብ ደረጃ ይንሸራተታል፡፡ እንዳለፈው ጊዜ “ደጃዝማቸ እከሌ ማናቸው…” አይነት በ‘ሳውንድትራክ’ የታጀበ አዋጅ አይነገር እንጂ…በሁሉም ወገን ሀሳቡን ከመቃወም ይልቅ ግለሰቡን ማሳጣት ይቀናናል፡፡እናማ ‘ያለቦታው ለሽ’ ማለትና “የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ…” ማለትን የሚጠራረግ ተአምር ይላክልንማ! ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 6220 times