Saturday, 17 October 2015 09:21

የዮሃንስ ቡድን የት ሊደርስ ይችላል!?

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(4 votes)

      የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከመቼውም ጊዜ በላቀ ፈታኝ ሂደት ውስጥ ይገኛል፡፡ በዋና አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ለሚመሩት ዋልያዎች ዓመቱ በሴካፋ፤ በቻን፤ በአፍሪካ ዋንጫና በዓለም ዋንጫ ማጣርያና ዋና ውድድር ጨዋታዎች የተጨናነቀ ነው፡፡ ከ2 ዓመት በፊት ብሄራዊ ቡድኑ  ደርሶበት ወደነበረው የተሻለ የፉክክር ደረጃ  መመለሱን ለማረጋገጥ ወሳኞች ናቸው፡፡ በአራቱ ውድድሮች የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሚቀጥለው 1 ዓመት ውስጥ  ጨዋታዎች ያደርጋሉ፡፡ በሴካፋ አዘጋጅነት ከወር በሃላ ቡድኑ በቀጥታ  ይገባል፡፡ እስከዋንጫ ስለሚጠበቅ ቢያንስ ከምድብ እስከ ፍፃሜው 6 ጨዋታዎችን ሊያደርግ ይችላል፡፡  በቻን ደግሞ ከ2 የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ውጤት ወደ ዋናው ውድድር መግባቱ ይጠበቃል፡፡ ዋልያዎቹ በቻን ውድድር ከገቡ ቢያንስ የምድባቸውን 3 ጨዋታዎች ያደርጋሉ፡፡ ስለሆነም በሴካፋና በቻን የዋልያዎቹ ተሳትፎ እስከ 10  ጨዋታዎች  ይኖራሉ፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ለዋናው ውድድር ማለፍ ሳይታሰብ 4 ወሳኝ ፍልሚያዎችም ይኖሩታል፡፡  በዓለም ዋንጫ የመጀመርያ ዙር ቅድመ ማጣርያ 2 የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ውጤት ድረስ በአጠቃላይ በውድድር ዘመኑ 16  የነጥብ ጨዋታዎች ይጠብቃቸዋል፡፡ የወዳጅነት ጨዋታዎች  ከተጨመሩበት ዋልያዎቹ የሚሰለፉበት ግጥሚያ እስከ 20 ሊደርስ ይችላል፡፡ ከአገር ውስጥ የክለብ ውድድሮች ያልተጋጨ ፤ በተደራጀ እና የተሟላ ቡድን ስብስብ እንዲሁም በተጠኑ የውድድር ፕሮግራሞች መስራት ያስፈልጋል፡፡ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከፍተኛ በጀት ፤ የዝግጅት ደረጃና ትኩረት በሁሉም ባለድርሻ አካላት መኖር አለበት፡፡
ዋና አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ  ቡድናቸውን እየገነቡ ናቸው፡፡  በ31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ፤ በ5ኛው ቻን ፤ በ21ኛው የዓለም ዋንጫ የማጣርያ ጨዋታዎች እንዲሁም በ38ኛው የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሻምፒዮና በሚኖረው  ሙሉ ተሳትፎ በሃላፊነታቸው ለመጠየቅ በቂ ነው፡፡ የዮሃንስ ቡድን  የት ሊደርስ ይችላል የሚለው ወቅታዊ ጥያቄ ይሆናል፡፡  ዋልያዎቹ በተጨናነቀው ውድድር ዘመን የተመቻቸላቸው የታሪክ ሁኔታ በሴካፋ ዞን የበላይነትን የመመለስ ክብር ነው፡፡ በ38ኛው የሴካፋ ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ አዘጋጅነት ዋንጫውን  ማንሳትና ለ5ኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮሺፕ ቻን ውድድር ቢያልፉ የሚሳካ  ይሆናል፡፡  የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ዋልያዎቹን በ2017 እኤአ ጋቦን ለምታስተናግደው 31ኛው  የአፍሪካ ዋንጫ ይጠብቃል፡፡ ምድባቸውን በመሪነት አጠናቅቀው ማለፋቸው  እቅዱ ነበር፡፡ ተግባራዊነቱ አጠያያቂ የሚሆን ነው፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ ከአልጄርያ የሚገጥመውን ከባድ ፉክክር ከግምት ውስጥ ማስገባት ነበረበት፡፡ ዋልያዎቹ  በምርጥ ሁለተኛ ደረጃ ለማለፍ  ለሚችሉበት ሁኔታ  በምድብ ማጣርያው የቀሯቸውን 4 ጨዋታዎች በሜዳቸው ሆነ ከሜዳ ውጭ ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል ፡፡ ለዋልያዎቹ ራሽያ በ2018 እኤአ ለምታስተናግደው ለ21ኛው ዓለም ዋንጫ ለማለፍ ያለውን እድል በተመለከተ ግን ምንም ማለት አይቻልም፡፡ ዋልያዎቹ በመጀመርያው የቅድመ ማጣርያ የደርሶ መልስ ጨዋታዎቻቸው ኮንጎን ጥሎ ማለፍ ቢችሉ እንኳን ከዚያም በምድብ ማጣርያው ሊገጥሟቸው የሚችሏቸውን አገራት ከወዲሁ ስለማይታወቁ  የሚጠብቃቸውን ሁኔታ መገመት አዳጋች ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ2008 ዓም የውድድር ዘመን በሚኖረው የተጨናነቀ ሂደት ዋና አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ሩብ ዓመት በቆዩበት ሃላፊነታቸው ይፈተናሉ፡፡ ከሳምንት በፊት በሰጡት መግለጫ እነዚህን ፈተናዎች ለመወጣት ሁለት ብሄራዊ ቡድኖች ያስፈልጉኛል ብለዋል፡፡ ባለፉት 5 ወራት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ያለፈባቸውን ሂደቶች እና ቀጣይ  አቅጣጫዎችን ማት ተገቢ ነው፡፡
ዮሃንስና የዋልያዎቹ  ሽግግር
በሙያቸው የኢንስትራክተር ደረጃ ያላቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ  መስራት ከጀመሩ 5 ወራት አልፈዋል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ በቻን፤ በአፍሪካ ዋንጫ፤ በዓለም ዋንጫ ማጣርያዎች እና በአቋም መፈተሻ 5 ጨዋታዎች አድርጓል፡፡ ከነጥብ ጨዋታዎቹ 1 ሲያሸንፍ፤ 1 አቻ ወጥቶ 1 ተሸንፏል፡፡ በወዳጅነት ጨዋታዎች 1 አቻ ወጥቶ 1 አሸንፏል፡፡ የዮሃንስ  ቡድን ባለፈባቸው የነጥብ ጨዋታዎች  የተለያዩ አወዛጋቢ ሁኔታዎች ነበሩት፡፡ ዋና አሰልጣኙ  በተጨዋቾች ሽግግር፤ በወዳጅነት ጨዋታዎች አለማግኘት፤በአንጋፋ ተጨዋቾች መቀነስ፤በግብ ማስቆጠር ችግር፤ የገጠሟቸውን አስጨናቂ ሁኔታዎች እና መሰናክሎች ተጋፍጠው ቡድናቸውነ ማዋቀር ቀጥለዋል፡፡ ከእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ጋር በፈፀሙት የቅጥር ውል መሰረት በሃላፊነቱ ተጨማሪ 1 ዓመት ከመንፈቅ የሚቆዩ ይሆናል፡፡ በፌደሬሽኑ እንደ ግብ የተቀመጠው በ2017 እ.ኤ.አ. ጋቦን ለምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ማለፍና በ2016 እኤአ ሩዋንዳ ለምታስተናግደው 5ኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ቻን ውድድር መብቃት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የቅጥር ኮንትራቱ ሊራዘም የሚችልባቸው እድሎች ሰፊ ናቸው፡፡ ዋና አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ብሄራዊ ቡድኑን በክፍለ አህጉራዊ፤ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች በሚያደርጋቸው የማጣርያ ውድድሮች ይዘው ሲቀርቡ  አንዳንድ ለውጥ መፍጠራቸውን ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ በመጀመርያ ደረጃ የተረከቡት ብሄራዊ ቡድን  በጣም ስኬታማ ከነበረው የሰውነት ቢሻው ስብስብና በፖርቱጋላዊው ማርያኖ ባሬቶ  የውጤት መዳከም ደረጃው ቀንሶ የነበረ ነው፡፡  ቀድማዋቸው ከነበሩት አሰልጣኞች በነጥብ ጨዋታ ብዙ ነጥቦች በመሰብሰብ የተሻሉ ናቸው፡፡ የ58 ዓመቱ ማርያኖ ባሬቶ በነጥብ ጨዋታ 1.05 እንዲሁም አስቀድሟቸው የነበሩት የ63 ዓመቱ ሰውነት ቢሻው 1.35 ነጥብ ያስመዘግቡ እንደነበር ያሰላው የትራንስፈርማርከት ድረገፅ፤ ዮሃንስ ሳህሌ በአንድ  ጨዋታ 1.50 በማስመዝገብ ነጥብ የተሻሉ መሆናቸውን ያመለክታል፡፡ ዋና አሰልጣኙ ቡድኑን በሽግግር ወቅት ይዞ በመጓዝ አንዳንድ ውጤቶች አሳይተዋል፡፡  ረዳት አሰልጣኝ ሆኖ የሚሰራው ፋሲል  ተካልኝና የግብ ጠባቂዎቹ አሰልጣኝ  አሊ ረዲ ዋልያዎቹ  የሽግግር ወቅቱን ስኬታማ ለማድረግ በሚወጡት ሚናቸው ይጠቀሳሉ፡፡ በዓለም ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ ዋልያዎቹ 3ለ1 በሆነ የደርሶ መልስ ውጤት ስዋቶሜን አሸንፈው ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ቢችሉም ዋና አሰልጣኙ ፤ በቡድናቸው ዙርያ ብዙ ችግሮች እንዳሉ የጠቆሙ አስተያየቶችን ሰጥተዋል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ከሜዳ ውጭ በአርቴፊሻል ሜዳ ሲጫወት እንደሚከብደው፤ በሜዳውም ከሜዳው ውጭም ጎል የማግባት እድሎችን ሊጠቀም አለመቻሉ እና የዝግጅት ውጥረት እና የውድድሮች መደራረብን ጠቅሰዋል፡፡
ዋና አሰልጣኝ ዮሃንስ ባለፈው ሳምንት  በሰጡት መግለጫ ፡፡ “ቡድኑ ዘጠና በመቶ አዲስ ነው። ከሰውነት ቢሻው ቡድን ሁለት ተጫዋቾች ብቻ ናቸው የቀሩት (ሽመልስ እና ስዩም)። እንደ ቢንያም በላይ ያለ አንድም ጊዜ በፕሪምየር ሊጉ ተጫውቶ የማያውቅ ተጫዋችም በዚህ ወሳኝ ጨዋታ ላይ ተጠቅመናል። እነ ሳልሃዲን እና ጌታነህም መጀመሪያ ለብሔራዊ ቡድኑ ሲጫወቱ በርካታ ዕድሎችን ያባክኑ ነበር፤ በኋላ ልምድ እያገኙ ሲመጡ ነው ግብ ማስቆጠር የጀመሩት። ስለዚህ ያን ሁሉ ጫና ተቆጣጥረው እንደዚህ አይነት ጨዋታ በመጫዎታቸው ልጆቹ ከመወቀስ ይልቅ መመስገን ይገባቸዋል፤” ብለዋል። ብሄራዊ ቡድኑ ከያዙበት ጊዜ አንስቶ ትልቁን ውሳኔ ያሳለፉበትን ሁኔታ ያመለከተ ገለፃ ነበር፡፡ የቀድሞዎቹን የዋልያዎች ስብስብ ከቋሚ ተሰላፊነት ውጭ ማድረጋቸው ነው፡፡ የስፖርት ቤተሰቡ ይህን ውሳኔ ተከትሎ በቡድኑ ሳይካተቱ የቀሩትን የሳልሃዲን ሰይድ እና ጌታነህ ከበደን ስም እያነሳ በተለያዩ መድረኮች ተቃውሞውን ቢያሰማም አሰልጣኙ በአቋማቸው ፀንተዋል፡፡ ይህን በተመለከተ በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሲናገሩም “ብሔራዊ ቡድን የማንም ርስት አይደለም። እነ ሳልሃዲን እና ጌታነህ ቡድኑ ውስጥ እንዳይካተቱ ያደረጋቸው አቅማቸው ነው። በፊት ሃገራችን ውስጥ አጥቂ ስለሌለ የነሱን ልምድ መጠቀም አለብን ብዬ እንደተናገርኩ አስታውሳለሁ። ምንም አይነት የፊፋ ካሌንደር የሚከተል የወዳጅነት ጨዋታ ማድረግ ባለመቻላችን ከሃገር ውጪ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ያሉበትን ደረጃ ማወቅ አልቻልንም። በሲሼልስ ጨዋታ ሜዳ ውስጥ ስናያቸው ጎል ከመሳት በተጨማሪ ሌሎች እንቅስቃሴዎቻቸው አጥጋቢ ሆኖ አላገኘሁትም። በየክለቦቻቸውም በተቀያሪ ወንበር ላይ ነበር ጨዋታዎችን ሲያሳልፉ የነበሩት፤ በዚህ ምክኒያት ተጫዋቾቹን ቡድኑ ውስጥ አላካተትኳቸውም። ካሉት ልጆች ጋራ ተወዳድረው ተሸለው ከተገኙ ግን ይሄ ብሔራዊ ቡድን ለማንም ክፍት ነው።” ብለዋል፡፡
የዮሃንስ ሽግግር አምበሎችና ግብ አዳኞች የቀድሞ፤ ነባርና አዳዲስ  ዋልያዎች
በዋልያዎቹ የሽግግር ወቅት ከታዩ ሁኔታዎች የመጀመርያው የአምበልነቱ ሃላፊነት ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ብዙ ጨዋታ ያደረገው ተጨዋች ለ11 ዓመታት የክለቡ አምበል የነበረው ደጉ ደበበ ሲሆን 51 ጊዜ የአገሩን ማልያ ለብሶ ተጫውቷል፡፡ ከደጉ ደበበ በኋላ በዋልያዎቹ ዋና አምበልነት በባሬቶ ጊዜ ብርሃኑ ፋዲጋ፤ ከዚያም ሳላዲን  ሰኢድ እንዲሁም ሳላዲን በርጌቾ ነበሩ፡፡ በዩሃንስ ሳህሌ ዘመን ደግሞ የአምበልነቱን ክብር በሃይሉ አሰፋ እና ስዩም ተስፋዬ እየተፈራረቁበት ናቸው፡፡ በሃይሉና ስዩም ከቀድሞ የዋልያዎቹ አባላት መካከል የነበሩ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል የብሄራዊ ቡድኑ የአጥቂ መስመርም በሽግግሩ ተፅእኖ ካረፈባቸው መስመሮች የሚጠቀስ ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ የምንግዜም ከፍተኛ ግብ አግቢ ሳላዲን ሰኢድ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ባለፉት 5 ዓመታት ጨዋታዎች ያስመዘገባቸው 13 ጎሎች ናቸው፡፡ ዮርዳኖስ አባይ፤  አዳነ ግርማ፤ ጌታነህ ከበደ፤ ኡመድ ኡክሪ፤ ታፈሰ ተስፋ ለቡድኑ ብዛት ያላቸውን ጎሎች በማስመዝገብ ተከታታይ ደረጃ ነበራቸው፡፡ በዮሃንስ ሳህሌ በሚመራው ቡድን ግን እነዚህን የቀድሞ እና ከፍተኛ ልምድ ያላቸውን አጥቂዎች በስብስቡ አላካተተም፡፡ የቡድኑ ጎሎች እየተገኙ ያሉት ከአጥቂዎች አይደለም፡፡ ከተከላካይ እና ከአማካይ መስመር ተጨዋቾች ነው፡፡ በተለይ ከቀድሞዎቹ ሽመልስ በቀለ፤ ከነባሮቹ ዳዊት ፍቃዱ ከአዳዲሶቹ ዋልያዎች ደግሞ ጋቶች ፓኖምና ራምኬሎ ሎክ  በግብ አዳኝነታቸው ይጠቀሳሉ፡፡  በዮሃንስ የቡድኑ ስብስብ የቀድሞዎቹን ዋልያዎች  በአዳዲስ እና አሰላለፍ ውስጥ ባልነበሩ ነባር ዋልያዎች ተተክቶ ፍፁም እየተቀየረ መጥቷል፡፡ በግብ ጠባቂ ቦታ የቀድሞዎቹ ዋልያዎችን ጀማል ጣሰው እና ሲሳይ ባንጫን በመተካት አዲሱ ዋልያ ታሪኩ ጌትነት ቋሚ ተሰላፊነቱን አረጋግጧል፡፡ በተከላካይ መስመር የቀድሞዎቹን ዋልያዎች  እነ አበባው ቡጣቆ፤ ደጉ ደበበንና አይናለም ሃይሉን በመተካት አዳዲሶቹ ዋልያዎች ሳላዲን በርጌቾ፤ ጋቶች ፓኖም፤ አስቻለው ግርማና.. ገብተዋል፡፡ በአጥቂ መስመር በቀድሞዎቹ ዋልያዎች አዳነ ግርማ ፤ ሳላዲን ሰኢድ፤ ኡመድ ኡክሪ እና ጌታነህ ከበደን የቀየሩት አዳዲስና ነባር ዋልያዎች ደግሞ ዳዊት ፍቃዱ፤ ቢኒያም አሰፋ እና ራምኬል ሎክ ናቸው፡፡ በአማካይ መስመር ከቀድሞዎቹ ዋልያዎች በርከት ያሉት አሁንም በዮሃንስ ስብስብ የሚገኙ ሲሆን እነሱም ስዩም ተስፋዬ፤ በሃይሉ አሰፋ፤ ሽመልስ በቀለ እና ዋሊድ አታ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ብሄራዊ ቡድኑን ከተረከቡ በኋላ ካከናወኗቸው  ተግባራት ትልቁ የቡድኑን ሽግግር መስራታቸው ነው፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቡድኑን እንደአዲስ በማዋቀር ውጤታማ ቡድን መገንባት እንደቻሉ ይስተዋላል፡፡ በተለይ በአሰልጣኝ ሰውነት እና ባሬቶ ዘመን የነበሩ የዋልያዎቹን ቁልፍ ተጨዋች በመቀነስ በአዳዲሶቹ መተካታቸው በአንጋፋዎቹ ሲመራ የነበረው ቡድኑ አሁን ላይ በወጣቶቹ ውጤታማ እንዲሆን አድርገዋል፡፡ በተከላካይ  ዘካርያስ ቱጂ፣ አስቻለው ታመነ፣ እንዲሁም ተካልኝ ደጀን  ፤ በመሃል  ጋቶች ፓኖም እና ፍሬው ስለሞን ፤በአጥቂ አስቻለው ግርማ ፣ ራም ኬሎክ እንዲሁም ባዬ ገዛኸኝ የዋልያዎቹ ቡድኑን ያጠናከሩ እና በዮሃንስ  የተፈጠሩ አዳዲስ ዋልያዎች ናቸው፡፡
በ38ኛው የሴካፋ ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ
2015 እኤአ ኢትዮጵያ
38ኛው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ አገራት ሻምፒዮና ከወር በኋላ በኢትዮጵያ  አዘጋጅነት ይካሄዳል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የዞኑ ሻምፒዮና 1 ወር ቢቀረውም  መስተንግዶውን በከፍተኛ ደረጃ በሚያሟሙቅ አቅጣጫ እየሰራበት አይደለም፡፡ የውድድሩ ልዩ ምልክት እና ሎጎ፤ ጨዋታዎች የሚካሄዱባቸው ስታድዬሞች ተለይተው አልታወቁም፡፡ ተሳትፏቸውን ከገለፁት 3 አገራት ኡጋንዳ፤ ሩዋንዳ እና ታንዛኒያ ባሻገር ሌሎቹ የዞኑ አባል አገራት ማረጋገጫ አላቀረቡም፡፡ እነዚህ እና ሌሎች ሁኔታዎች በኢትዮጵያ በሚዘጋጀው 38ኛው የሴካፋ ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ ስኬታማነት ላይ ጥያቄዎች ይፈጥራሉ፡፡
በ5ኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ቻን
2016 እኤአ ሩዋንዳ
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ2016 እኤአ ሩዋንዳ ለምታዘጋጀው 5ኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ቻን ውድድር ለማለፍ በመጨረሻው የማጣርያ ምዕራፍ ላይ ይገኛል፡፡ ዋልያዎቹ በዚህ ምእራፍ የደርሶ መልስ  ጨዋታቸውን ከብሩንዲ ጋር የሚያደርጉ ሲሆን የመጀመርያው ጨዋታ ከሜዳው ውጭ ተደርጎ የመልሱ ጨዋታ ከሳምንት በኋላ በአዲስ አበባ  ሃላፊውን አገር ይወስናል፡፡ በምስራቅ አፍሪካ አገር ለመጀመርያ ጊዜ በሚካሄደው የቻን ውድድር ዞኑ በሁለት ቡድኖች የሚወከል ነው፡፡  ከብሩንዲ እና ከኢትዮጵያ የደርሶ መልስ ፍልሚያ ባሻገር ሌላው ጨዋታ ኡጋንዳ ከሱዳን የሚያደርጉት ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያና ብሩንዲ   በተገናኙባቸው ሁለት የሴካፋ ጨዋታዎች በ2000 እኤአ 1ለ0 እንዲሁም እና በ2001 እኤአ በመደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 2ለ2 ከተለያዩ በኋላ በመለያ ምቶች 5ለ3 ያሸነፈችው ኢትዮጵያ ነበረች፡፡
በ31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ
2017 እኤአ ጋቦን
በ2017 እኤአ ጋቦን በምታዘጋጀው 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሚሳተፍበት የምድብ ማጣርያ በምድብ 10 ከአልጄርያ፤ ከሌሶቶ እና ከሲሸልስ ጋር መደልደሉ ይታወቃል፡፡ ከ2 ዙር የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች በኋላ አልጄርያ በ6 ነጥብ እና በ4 የግብ ክፍያ መሪነቱን ስትይዝ ዋልያዎቹ በ4 ነጥብ እና 1 የግብ ክፍያ በሁለተኛ ደረጃ እየተከተሉ ናቸው፡፡ ከምድቡ ለ31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ሰፊ እድል ያላት አልጄርያ ናት፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቀሪዎቹ 4 የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች ከአልጄርያ ጋር ከሜዳው ውጭና በሜዳው፤ ከሌሶቶ ጋር ከሜዳው ውጭ እንዲሁም ከሲሸልስ ጋር በሜዳው ይጫወታል፡፡ የምድቡን መሪነት በማግኘት በአፍሪካ ዋንጫው ቀጥታ ተሳትፎ ለማግኘት ዋልያዎቹ በተለይ በአራቱ ጨዋታዎች መሸነፍ የለባቸውም፡፡ በተለይ ከአልጄርያ ጋር በሚያደርጓቸው የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ከፍተኛውን ነጥብ መውሰድ ከቻሉ ተስፋ ይኖራቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከአልጄርያ አቻው ጋር በታሪክ በ6 ጨዋታዎች ተገናኝቷል፡፡ 1 ድል፤ 2 አቻ ሶስት ሽንፈትም አስተናግዷል፡፡ ምድቡን በመሪነት መጨረስ ካልሆነለት ቡድኑ ለ31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ የሚችለው በምርጥ ሁለተኛነት ከጨረሰ ነው፡፡ ከ14 ምድቦች በምርጥ ሁለተኛነት ለማለፍ ሁለት አገራት እድል ይኖራቸዋል፡፡ በምድብ ማጣርያው የሁለት ዙር ጨዋታዎች ከተደረጉ በኋላ ባስመዘገቡት ነጥብ መሰረት ከየምድቡ  ምርጥ ሁለተኛ ሁኑት በወጣላቸው ደረጃ መሰረት፤ ከምድብ 6 ሞሮኮ በ6 ነጥብ እና በ4 የግብ ክፍያ አንደኛ ደረጃ ላይ ናት፡፡ ከምድብ 7 ናይጄርያ በ4 ነጥብ እና በ2 የግብ ክፍያ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ፤ በምድብ 10 የምትገኘው ኢትዮያ በ4 ነጥብ እና 1 የግብ ክፍያ ከላይቤርያ፤ ዚምባቡዌ እና ዛምቢያ ጋር ሶስተኛ ደረጃን ተጋርተው ፉክክራቸውን ይቀጥላሉ፡፡
በ21ኛው የዓለም ዋንጫ
2018 እኤአ ራሽያ
በዓለም ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተገናኘው  ከስዋቶሜ ፕሪንስፒ ጋር ነበር፡፡ ዋልያዎቹ በደርሶ መልስ 3ለ1  በሆነ ውጤት ስዋቶሜ ፕሪንስፒ ጥለው ካለፉ በኋላ  ወደ ሌላው የመጀመርያ ዙር ማጣርያ መግባት ችለዋል፡፡ በ2018 እኤአ ለሚስተናገደው 21ኛው የዓለም ዋንጫ ማለፍ የሚቻለው ደግሞ የመጀመርያ ዙር ማጣርያውን በደርሶ መልስ ጨዋታዎች አልፎ በምድብ ማጣርያ መሰረት ነው፡፡ ከኮንጎ ጋር ከሜዳው ውጭ እና በሜዳው ካደረገ በኋላ በሚመዘገብ ውጤት የሚወሰን ይሆናል፡፡  በአፍሪካ ደረጃ አምስት የዓለም ዋንጫ ወኪል ብሄራዊ ቡድኖች የሚለዩበት የምድብ ማጣርያ የመጨረሻው ምዕራፍ ሃላኖቹ ገኙበት ነው፡፡  ከኢትዮጵያ ሌላ ከምስራቅ አፍሪካ ከምድብ ማጣርያው በፊት ለሚገኘው የመጀመርያ ዙር የደርሶ መልስ ማጣርያ መብቃት የቻሉት ሌሎቹ አገራት ኬንያና ታንዛኒያ ናቸው፡፡ በቅድመ ማጣርያቸው ኬንያ ኬፕቨርዴን እንዲሁም ታንዛኒያ ማላዊን ጥለው ማለፍ ችለዋል፡፡ ኢትዮጵያ የዓለም ዋንጫ የመጀመርያ ዙር ማጣርያ ተጋጣሚ ከሆነችው ኮንጎ ጋር  በተለያዩ ውድድሮች ሶስት ጊዜ ተገናኝታለች፡፡ 1 ድል፤ 1 አቻ እና አንድ ሽንፈት ተመዝግቧል፡፡

Read 4070 times