Saturday, 17 October 2015 09:26

ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር በደ/ ሱዳን 18 አዳዲስ ግዛቶችን ሊያቋቁሙ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  - አማጺው የሰላም ስምምነቱን አፍርሼ ወደ ጦርነት እመለሳለሁ ብሏል
                 
    የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር የአገሪቱ ግዛቶች ቁጥር ከ10 ወደ 28 ማደግ አለበት ሲሉ ያስተላለፉት አወዛጋቢ ውሳኔ፣ ባለፈው ማክሰኞ ልዩ ስብስባውን ባከናወነው የአገሪቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተቀባይነት ማግኘቱን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
የፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር የግዛት ቁጥር ጭማሬ እርምጃ፣ ከአለማቀፉ ማህበረሰብ በስፋት ተቃውሞ ሲገጥመው እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ ኢጋድም የፕሪዚዳንቱ ውሳኔ በምክር ቤቱ ተቀባይነት ማግኘቱ በአገሪቱ ተቀናቃኝ ሃይሎች መካከል የተፈረመውን የሰላም ስምምነት የሚጻረር ነው ሲል እንደተቸው ገልጧል፡፡
ውሳኔው ተግባራዊ የሚሆነው የደቡብ ሱዳን ፓርላማ ካጸደቀው በኋላ እንደሚሆን የጠቆመው ዘገባው፣ አንዳንድ የአማጺው ሃይል አባላትም ውሳኔው የማይሻር ከሆነ የሰላም ስምምነቱን አፍርሰው ዳግም ወደ ትጥቅ ትግል እንደሚገቡ ማስጠንቀቃቸውን ገልጧል፡፡
የአማጺው ሃይል አመራሮች የፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬርን ውሳኔ ህገ መንግስታዊ ያልሆነና ባለፈው ነሃሴ ወር በሁለቱ ሃይሎች መካከል ከተፈረመው የሰላም ስምምነት ያፈነገጠ ነው ሲሉ መተቸታቸውን የዘገበው ደግሞ ሱዳን ትሪቢዩን ነው፡፡ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር ከሁለት ሳምንታት በፊት በአገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ በኩል የአገሪቱን ግዛቶች ቁጥር ለማሳደግ መወሰናቸውን ይፋ ማድረጋቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ በወቅቱም ይህን ያልተጠበቀ ውሳኔ ያስተላለፉት ለደቡብ ሱዳን ህዝቦች ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እንደሆነ ማስታወቃቸውን ገልጧል፡፡
ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር ደቡብ ሱዳን 10 ግዛቶች ያሏት አገር ናት የሚለውን የህገ መንግስቱ አንቀጽ 162 እንዲያሻሽሉ ለአገሪቱ ህግ አርቃቂዎች ጥሪ ማስተላለፋቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

Read 2489 times