Saturday, 24 October 2015 08:39

የነገው የታንዛኒያ ምርጫ በአገሪቱ ከፍተኛ ውጥረት ፈጥሯል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

- በ4 ተከታታይ ምርጫዎች ያልተሸነፈው ገዢው ፓርቲ፣ ዘንድሮ ከባድ ፈተና ገጥሞቷል
- ነገ የሚካሄደው የኮንጎ ብራዛቪል ህዝበ ውሳኔ ከወዲሁ የ4 ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል
   ነገ ሊከናወን የታቀደውና በአገሪቱ የምርጫ ታሪክ ከፍተኛ ውጥረት የታየበት እንደሆነ የተነገረለት ምስተኛው የታንዛኒያ ምርጫ፤ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ስጋት የፈጠረ ሲሆን የገዢው ፓርቲና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ደጋፊዎች ጎዳና ላይ ወጥተው በተጠንቀቅ እንደሚገኙ አልጀዚራ ዘገበ፡፡የአገሪቱ ፖሊስ በተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ደጋፊዎች መካከል ግጭት እንዳይፈጠር በመካከላቸው ገብቶ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፣ ምንም እንኳን የአገሪቱ መንግስት ታጣቂዎችን የመለመሉ ፓርቲዎች ግጭትና ብጥብጥ እንዳያስነሱ በተደጋጋሚ ቢያሳስብም፣ ብዙዎች ግን ከዚህ በፊት እንደተከሰተው ሁሉ በነገው ምርጫም ግጥትና ጥቃት ይፈጸማል ብለው እንደሰጉ ገልጧል፡፡ታንዛኒያ የመጀመሪያውን የብዙሃን ፓርቲ ምርጫ እ.ኤ.አ በ1992 እንዳካሄደች ያስታወሰው ዘገባው፣
ከዚያ በኋላ በተካሄዱት አራት ምርጫዎች በአሸናፊነቱ የዘለቀው ቻማ ቻማ ማፒንዱዚ የተባለውና አሁንም ድረስ በስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡ገዢው ፓርቲ በዚህ አመት የታንዛኒያ አራት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምረት ከሆነው ኡካዋ የተባለ ተቀናቃኙ በተለየ ሁኔታ ጠንካራ ፉክክር እንደገጠመው የጠቆመው ዘገባው፣ የጥምረቱ አባላት ከሆኑት ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ሁለቱ በአገሪቱ በትልቅነታቸው ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን የያዙ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ፈተናው ከባድ ሊሆንበት እንደሚችል ገልጧል፡
በሌላ በኩል የኮንጎ ብራዛቪል ፕሬዚዳንታዊ የስልጣን ዘመንና የእድሜ ገደብ ህጎች ይሻሻሉ ወይስ
አይሻሻሉ የሚለውን ለመወሰን በነገው ዕለት ህዝበ ውሳኔ እንደሚካሄድ የዘገበው ቢቢሲ፣ ህዝበ ውሳኔው በስልጣን ላይ ያሉትን ፕሬዚዳንት ዴኒስ ሳሶ ንጉኤሶን ህጉ ከሚፈቅድላቸው ውጪ በምርጫ ተሳትፈው በስልጣን ላይ እንዲቆዩ ለማድረግ የታቀደ ህገወጥ ተግባር ነው በሚል ጉዳዩን ተቃውመው በመዲናዋ ብራዛቪል ባለፈው ማክሰኞ ሰልፍ በወጡ ተቃዋሚዎች ላይ ፖሊስ በወሰደው የተኩስ እርምጃ አራት ሰዎች መሞታቸውን ገልጧል፡፡በአገሪቱ የአጭር የጽሁፍ መልዕክትና የኢንተርኔት አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ መቋረጡንና ህዝበ ውሳኔው እስከሚካሄድ ድረስ ህዝባዊ ስብሰባ ማድረግ መከልከሉን የጠቆመው ዘገባው፣ አብዛኛዎቹ የመዲናዋ ሱቆች ተዘግተው እንደሰነበቱና ህዝቡም  ግጭት ይከሰታል በሚል ስጋት በየቤቱ እንደተከከተ አስረድቷል፡፡ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ፤የፕሬዚዳንታዊ የስልጣን ዘመንና የዕድሜ ገደብ በማሻሻል፣ ግልጽነት ያለው ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ገለልተኛ የምርጫ ኮሚሽን በሌለበት ሁኔታ ምርጫን ማካሄድ በኮንጎ ብራዛቪል የከፋ አደጋና ቀውስ ሊያስከትል ይችላል ሲል ስጠንቅቋል፡፡የአገሪቱ መንግስት በቅርቡ በፖለቲካ ታጋዮች ላይ ህገወጥ እስር መፈጸሙ ያሳስበኛል ያለው
ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል፣ መንግስት ህገመንግስቱን በህገወጥ መንገድ ለማሻሻል እደረገ ያለው
እንቅስቃሴ ለአገሪቱ ብቻም ሳይሆን ለአካባቢው ሰላም ጭምር አደጋ መሆኑን አበክሮ
አስጠንቅቋል፡፡  

Read 1867 times