Saturday, 24 October 2015 08:44

ሰሜን ኮርያ ለ4ኛው የኒዩክሌር ሙከራ እየተዘጋጀች ነው

Written by 
Rate this item
(8 votes)

   የደቡብ ኮርያ ብሄራዊ የስለላ አገልግሎት ተቋም፣ ሰሜን ኮርያ አራተኛውን የኒዩክሌር ሙከራ ለማድረግ እየተዘጋጀች እንደሆነ የሚያረጋግጥ መረጃ እንዳገኘ ሊ ቾኤል የተባሉት የአገሪቱ ከፍተኛ የህግ ጉዳዮች ባለስልጣን መናገራቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘገበ፡፡የደቡብ ኮርያ ብሄራዊ የስለላ አገልግሎት ተቋም፣ ኒዮንግዮን በተባለው የሰሜን ከርያ ዋነኛ የኒዮክሌር ጣቢያ ላይ ባደረጋቸው የክትትል እንቅስቃሴዎች፣ አገሪቱ የኒዩክሌር ሙከራ ለማድረግ እየተዘጋጀች እንደሆነ አረጋግጧል ብለዋል  ባለስልጣኑ፡፡ሰሜን ኮርያ የደቡብ ኮርያ የኒዩክሌር ሙከራውን ለማድረግ ብትዘጋጅም በቅርቡ ተግባራዊ እንደማታደርገው ባለስልጣኑ ቢናገሩም፣ የስለላ ተቋሙ የህዝብ ጉዳዮች ሃላፊ ግን የተባለው ነገር እውነት ስለመሆኑ ማረጋገጫ ከመስጠት
እንደተቆጠቡ ዘገባው ገልጧል፡፡ሰሜን ኮርያ ሁሉንም የአቶሚክ ነዳጅ ማምረቻ ማዕከላቷን ደረጃ እንዳሳደገችና እንደገና ስራ እንዳስጀመረች ባለፈው ወር ላይ ማስታወቋን ያስታወሰው ዘገባው፣ ይህም አገሪቱ ለአራተኛ ጊዜ የኒዩክሌር ሙከራ ለማድረግ ትችላለች የሚል ጥርጣሬ መፍጠሩን አስረድቷል፡፡ሰሜን ኮርያ የኒዩክሌር ፕሮግራሟን እንድታቋርጥና በምላሹም የተጣሉባት ማዕቀቦች እንዲቀነሱላት ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንምከር በሚል፣ ባለፈው ሳምንት አሜሪካና ደቡብ ኮርያ በጋራ ያቀረቡላትን ሃሳብ ውድቅ እንዳደረገችውም ዘገባው አስታውሷል፡፡ሰሜን ኮርያ እ.ኤ. በ2006፣ በ2009 እና በ2013 ሶስት የኒዩክሌር ሙከራ ማድረጓንና በዚህም ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የኢኮኖሚና የንግድ ማዕቀቦችን እንዳስጣሉባት ዘገባው
አክሎ ገልጧል፡፡

Read 4257 times