Saturday, 24 October 2015 08:41

የዋልያዎቹ 2ኛው የቻን ተሳትፎ ነገ በአዲስ አበባ ይወሰናል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(3 votes)

     የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን  በታሪኩ ለ2ኛ ጊዜ በቻን ውድድር ላይ የሚሳተፍበትን እድል በሜዳው
ሊወስን ነው፡፡ ዋልያዎቹ በአገር ውስጥ ተጨዋቾች ብቻ በሚካሄደው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ የመጨረሻ የማጣርያ የመልስ ጨዋታ ላይ በአዲስ አበባ ስታድዬም ነገ የሚገናኙት ከብሩንዲ ጋር ነው፡፡
ሁለቱ ቡድኖች ከሳምንት በፊት የጦርነት ቀጠና በሆነችው የኦጋዱጉ ከተማ የመጀመርያ ጨዋታቸውን ያደረጉ ሲሆን ብሩንዲ  2ለ0 እንዳሸነፈች ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በመጀመርያ ጨዋታ ቡድናቸው ከሜዳው ውጭ ግጥሚያውን ያደረገበት ሁኔታ እንዳላስደሰታቸው ለሶካ አፍሪካ ተናግረዋል፡፡ በዚሁ ጨዋታ የብሩንዲ የፀጥታ ኃይሎች  በመትረየስ፤ በሮኬት መቃዋሚያ እና ሌሎች ከባባድ መሳርያዎች በስታድዬም አድርገውት የነበረው ጥበቃ ለማንኛውም ቡድን የሚያስጭንቅ እንደነበር ሶካ አፍሪካ በዘገባው አትቷል፡፡ ዋልያዎቹ በነገው እለት የብሩንዲ አቻቸውን የሚያስተናግዱት የገጠማቸውን የ2ለ0 ውጤት ለመቀልበስ ሲሆን፤ ነገ በአዲስ አበባ ስታድዬም በሚደረገው የመልስ ጥለው ለማለፍ ቢያንስ በሶስት ንፁህ ጎሎች ማሸነፍ ይኖርባቸዋል፡፡ የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ የሚመሩት የግብፅ ዳኞች ሲሆኑ፣ ኮሚሽነሩ ሱዳናዊ መሆናቸው ታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ በቻን  ለመጀመርያ ጊዜ
የተሳተፈው. በ2013 እ.ኤ.አ ውድድሩን ደቡብ አፍሪካ ባዘጋጀችበት ወቅት ነበር፡፡ ዋልያዎቹ በ3ኛው የቻን ውድድር በምድብ ‹‹3›› ከጋና፣ ሊቢያና ኮንጎ ተደልድለው የነበረ ሲሆን፤ በሶስቱም ጨዋታዎች ተሸንፏል፡፡ ውጤቱም በሊቢያ 2 ለ0 ፣ በኮንጎ  1ለ0  እንዲሁም በጋና 1 ለ0 የተሸነፈባቸው ሲሆኑ፤ ያለምንም ነጥብ ከምድቡ አራተኛ ሆኖ መጨረሱ ይታወሳል፡፡ በ2016 እ.ኤ.አ 4ኛው የቻን ውድድር በሩዋንዳ አስተናጋጅነት የሚደረግ ይሆናል፡፡በሌላ በኩል በ2020 እኤአ ላይ የሚዘጋጀውን 6ኛውን የቻን ውድድር ኢትዮጵያ እንደምታስተናግድ  ያስታወቀው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን  አህጉራዊ ሻምፒዮናውን ማዘጋጀት ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የማስተናገድን አቅም እንደሚያዳብር፤ የስፖርት ቱሪዝምን በማስፋፋት ከፍተኛ ጥቅም እንደሚያስገኝና የብሄራዊ ቡድኑን ልምድ የሚያጠናክር ነው ብሏል፡፡
በአገሪቱ ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች መገንባታቸው፣ ሆቴሎች መስፋፋታቸው፣ የተረጋጋ ሠላም መኖሩና የመሰረተ ልማት መስፋፋቱ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማስተናገድ አነሳስቶናል በማለት
የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ጁኔይዲን ባሻ ተናግረዋል፡፡ በተያያዘ ዜና  እግር ኳስ ፌደሬሽኑ የ2025ቱን የአፍሪካ ዋንጫ  ለማዘጋጀት ጥያቄ መቅረቡንና መልሱን በመጠባበቅ ላይ እንደሆነ ሲታወቅ፤ በ2017 እኤአ የሚካሄደውን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔም እንደሚያዘጋጅ አስታውቋል፡፡

Read 3685 times