Saturday, 24 October 2015 09:56

“…ደጅ ብቅ ብዬ ነፋስ ይምታኝ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(25 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሦስት ወንድ ልጆች ሁሉም በተለያየ ከተማ ሥራ ይይዙና ይሳካላቸዋል፡፡ በዕድሜ ለገፋችው እናታቸው ስጦታ ይልካሉ፡፡ ሦስቱም ተገናኝተው ያወራሉ፡፡
አንደኛው ልጅ… “በጣም ትልቅ የሆነ ቤት ሠራሁላታ!” ይላል፡፡
ሁለተኛው ልጅ… “እኔ ደግሞ መርሴዲስ ቤንዝ ገዝቼ ከሾፌር ጋር ላኩላት፣” ይላል፡፡
ሦስተኛው ልጅ ፈገግ አለና እንዲህ አለ… “እኔ ከሁላችሁም የተሻለ ስጦታ ነው የላኩላት፡፡ እማዬ መጽሐፍ ቅዱስ እንደምትወድ ታውቃላችሁ፣ ደግሞም አጥርታ የማየት ችግር ስላለባት ማንበብ እንደማትችል ታውቃላችሁ፡፡ መጽሐፍ ቅዱሱን እንድታነብላት ተናጋሪ ወፍ ላኩላት፡፡ ይህች ወፍ መጽሐፍ ቅዱሱን ጠንቅቃ እንድታነበንብ ለማድረግ 20 ባህታውያን 10 ዓመት ፈጅቶባቸዋል፡፡ እኔም ለአሥር ዓመት በየዓመቱ የ100‚000 ዶላር ስጦታ ለመስጠት ቃል ገብቻለሁ፡፡ እማዬ የምትፈልገውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ስትጠቅስ ወፏ በቃሏ ታነበንብላታለች፡፡”
ትንሽ ቆይቶ እናትየው ለሦስቱም የምስጋና ደብዳቤዎች ላከች፡፡
ለመጀመሪያው ልጅም… “ያሠራህልኝ ቤት በጣም ትልቅ ነው፡፡ የምጠቀምበት አንዱን ክፍል ብቻ ነው፣ ግን ሙሉ ቤቱን ማጽዳቱ አደከመኝ፣” ብላ ትጽፋለች፡፡
ለሁለተኛው ልጅ ደግሞ… “ዕድሜዬ ስለገፋ የትም ቦታ እንደማልሄድ ታውቃለህ፡፡ ስለዚህ መኪናውን አልጠቀምበትም፡፡ ሾፌሩ ደግሞ መለቲ ቢጤ ነው፣” ብላ ጻፈችላት፡፡
ለሦስተኛው ደግሞ እንዲህ ስትል ላከችለት፡፡ “የልቤን ያወቅህልኝ አንተ ብቻ ነህ፡፡ ወፏ እንዴት እንደጣፈጠችኝ አልነግርህም፡፡”
ስጦታ ስትልኩ የሚባለውንና የማይባለውን ለዩማ፡፡
የምር ግን…ስለ ተናጋሪዋ ወፍ ተግባር ልጁ ትክክለኛውን መረጃ ለእናቱ ስላልነገረ እናትየው ወፏን በመሰልቀጣቸው አይፈረድባቸውም፡፡ እንደውም ሌላ ወፍ ቢጨምርላቸው አሪፍ ነው፡፡ ትክክለኛ መረጃ ስለ አለመስጠት ስናወራ የማስታወቂያዎቻችን ነገር አይመጣባችሁም! ችግሩ ትክክለኛ መረጃ አለመስጠቱ ብቻ ሳይሆን የተሳሳተ መረጃ መስጠቱ ነው፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…በቃ እዚህ አገር ማስታወቂያዎች ያለ ‘ቆንጆ’ ሴት ላይሠሩ ነው! አሀ… ቆንጆ ሴት ሲያይ ሁሉም ሰው ስለ ምርቱ ወይም ስለ አገልግሎቱ አይደለማ የሚያስበው፡፡ አንዳንድ ጊዜማ የሚለበሰው ልብስ ሁሉ… አለ አይደል…“የምር ይህ ማስታወቂያ ምንን ለማሳየት ነው፣ ልጅቷን ነው ምርቱን?” ያስብላል፡፡
እግረ መንገዴን…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ለነገሩ እኮ የቁንጅና መለኪያዎቻችን ‘እነሱው (‘ፈረንጆቹ’ እንደማለት) ባስቀመጡልን’ ከሆነ ሰነበተ፡፡ አሀ…ልክ ነዋ…
“ሞንደል ያለች ሴት ወይዘሮ…”
“የደስ ደስ ያላት ጎራዳ…”
“ደም ግባት ያላት፣ ሞላ ያለች…”
“ጉንጮቿ ትንቡክ፣ ትንቡክ የሚሉ…”
“እንትኗ እንዲህ ገልበጥ፣ ገልበጥ የሚል…”  ምናምን አይነት የውበት መለኪያዎች ነበሩን፡፡ ማስታወቂያዎች ላይ እነኚህን ‘መለኪያዎች የሚያሟሉ’ ሴቶች ስንት ጊዜ ነው የሚገጥሙን!
በነገራችን ላይ የቁንጅና ነገር ካነሳን አይቀር…ሀሳብ አለን፡፡ የቁንጅና ውድድሮች በመድረክ ላይ ብቻ መሆናቸው ቀርቶ ሌላም ይታከልበት፡፡ ተወዳዳሪዎች ሁሉ ጧት ከእንቅልፋቸው ሲነሱ በሌሊት ልብሳቸው፣ ውሀ እንኳን ሳይነካቸው (ቢቻል ቅቤዋ ሳትፈታ)  በትክክል ወደ መወዳደሪያ አዳራሽ ቢሄዱ አሪፍ ነው፡፡ እውነተኛዋ መልክ የምትወጣው ያኔ ነዋ! ‘ፋውንዴሽን’ የለ፣ ማስካራ ነው ምናምን የሚሉት ነገር የለ፣ መልክ እግዜር እንደፈጠራት ቁልጭ ትላለች፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
የምር ግን…አለ አይደል…ማስታወቂያዎቻችን የፈጠራ ድርቅ ያስቸገራቸው ይመስላል፡፡ አዲስ ነገር… አለ አይደል… “እንዴት አይነት አሪፍ ፈጠራ ነች…” የምንልባቸው ማስታወቂያዎች ካየን ከራረምንሳ፡፡ አንዳንድ ጊዜ እኮ የአንዱን ማስታወቂያ ከሌላው ለመለየት ሁሉ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ የምር ግን…አለ አይደል… አልፎ፣ አልፎ ተስፋ የሚሰጡ ሙከራዎች አሉ፡፡ ግን በቃ ይሄ የፈረደበት ‘ኮምፒዩተር አኒሜሽን’ የአእምሮን ሥራ የተሻማው ነው የሚመስለው፡፡
‘ፈረንጆቹ’ ዘንድ እኮ ከዋና ፕሮግራሞች ይልቅ ቁጭ ብለው ማስታወቂያ ያያሉ የሚባለው ማስታወቂያዎች ፈጠራ የሚታይባቸው ስለሆኑ ነው፡፡
የማስታወቂያ ባለሙያዎቻችን… አለ አይደል...የፈጠራውን ነገር፣ የሰለቹ አይነት አቀራረቦችን የመደጋገሙ ነገርን ቢያስቡበት አሪፍ ነው፡፡
የምር ግን… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ብዙ ግራ የሚያጋቡን ነገሮች አሉ፡፡ አለ አይደል…ማስታወቂያዎቹ በቅፅሎች ምናምን ተሞልተው ማጋነኑ ይበዛና አይደለም አሁንም፣ ወደፊትም እንደዛ አይነት ምርት የማይመረት ነው የሚመስለው፡፡ ልክ ነዋ….ስንትና ስንት ፋብሪካ ያንኑ ምርት አገር ውስጥ እያመረተ ለገበያ በሚያቀርብበትና ከውጪም በሚገባባት አገር የአንዱ ፋብሪካ ውጤት ብቻ አገሩን በሙሉ የተቆጣጠረው ሲያስመስሉት አሪፍ አይደለም፡፡ ‘ኤቲካል’ እንደሚባለውም አይደለም፡፡
‘ሀያ አራት ሰዓት አገልግሎት እሰጣለሁ’ የሚለው የጤና ተቋም ሁለት ሰዓት ሳይሞላ፣ አይደለም የህክምና ባለሙያዎቹ፣ የጥበቃ ሠራተኞቹ እንኳን የት እንዳሉ አይታወቅም፡፡ ማስታወቂያውን ሰምቶ ለአስቸኳይ ህክምና ወደዛ ተቋም የሄደው ሰው ለሚደርስበት መጉላላት ተጠያቂው ማነው!
‘አንዴ ካደረጉት ለብዙ ዓመታት ሀሳብ የለም’ ምናምን አይነት ማስታወቂያ የተባለለት ጫማ በሁለት ወሩ ሦስት ቦታ ሲሰነጠቅ ገንዘቡን የከሰከሰው ሸማች አቤት የሚለው ለማን ነው!
‘በሰባት ሰዓት በሮች ይከፈታሉ’ ተብሎ በማስታወቂያው ‘የተደሰኮረለት’ ዝግጅት ላይ ሰዉ እስከ ዘጠኝ ሰዓት በፀሀይ ሲንቃቃ ለመዋሉ ተጠያቂው ማን ነው!
በነገራችን ላይ እኮ በብዙዎቹ አገሮች የተሳሳተ መረጃ በማስታወቂያ መልቀቅ እዳ አለበት፡፡
አንድ ሁለቱን ለመጥቀስ ያህል…ኤይርቦርን የተባለ እንደ ተጨማሪ ምግብነት የሚያገለግል የእጽዋት ውጤት በማስታወቂያው የተነሳ ለብዙ ዓመታት ከፍተኛ ሽያጭ ነበረው፡፡ ማስታወቂያው ላይ ባክቴሪያና ጀርሞችን እንደሚያጠፋ ኢንፉልዌንዛና ጉንፋንን እንደሚከላከል ተጠቅሷል፡፡ በስተኋላ ማስታወቂያው ላይ የተባለው ነገር ሁሉ ውሸትና ማጋነን መሆኑ ይረጋገጣል፡፡ አምራች ድርጅቱ ክስ ተመስርቶበት 23.3 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት ሲፈረድበት በኋላም ሌላ ተጨማሪ 7 ሚሊዮን ዶላር ተበይኖበታል፡፡
ሌላ ደግሞ…አክቲቪያ የተባለ እርጎ ከሌሎች እርጎዎች የተለየ ነገር ሳይኖረው ልክ ተጨማሪ የምግብ ይዘት እንዳለውና ይህም በሳይንስ እንደተረጋገጠ አምራች ድርጅቱ በማስታወቂያ ያስነግራል፡፡ ሰዉም እውነት እየመሰለው ይገዛል፡፡ ሆኖም በኋላ ሲመረመር ምንም አይነት የተለየ ይዘት የለውም፡፡
እርጎውን የሚያመርተው ኩባንያ ላይ ተጠቃሚዎች ተሰባስበው የማታለል ክስ ያቀርቡበታል፡፡ በፍርድ ውሳኔውም 45 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍል ይፈረድበታል፡፡
ይልቅ እኛዋ እዚቹ አገር ቢመጡ ይሻላቸው ነበር፡፡ “ሀያ አራት ሰዓት እገኛለሁ ብለህ አልተገኘህም…” ብሎ ልክ ነዋ…የምን ክስ፣ የምን ቅጣት ነው!
እናማ…በሌሎች ስፍራዎች ማስታወቂያ ለማሳመር ተብሎ የሚነገሩ ማስታወቂያዎች ውሎ አድሮ ጣጣ አላቸው፡፡
ስሙኝማ… አንድ ምርት ሲተዋወቅ የሌሎቹን ማስታወቂያ ያልተነገራቸውን ተመሳሳይ ምርቶች መብትም መጠበቅ ያለበት አይመስላችሁም! ልክ ነዋ…አንዳንዴ እኮ በተዘዋዋሪ እየተነገረን ያለው “ከእኛ ምርት በስተቀር የሌሎቹ ቀሺም ነው…” የሚል አይነት ነው፡፡
ደግሞላችሁ…አሁን፣ አሁን ደግሞ…
“በተመሳሳይ ምርቶች እንዳትታለሉ…”
“ምርታችንን አስመስለው የሚሠሩ መኖራቸው ተደርሶበታል…”
“ተመሳሳይ ምርቶች ገበያ ውስጥ ስለገቡ ከመገዛታችሁ በፊት የምርታችን መለያ መኖሩን አረጋግጡ…” አይነት ማሳሰቢያዎች በዝተዋል፡፡ እኔ የምለው… ይሄ ሁሉ ምርት ‘ተመሳሳዩ’ የሚሠራ ከሆነ በቃ…አገር ሁሉ እንደፈለገው ሆኗል ማለት ነዋ! ጥያቄ አለን…ይሄ ሁሉ ምርት በተመሳሳይ የሚሠራ ከሆነ…አለ አይደል…በሚዲያ… “እከሌ የተባለው ድርጅት እንትና የተባለውን ድርጅት ምርት አስመስሎ ሲሠራ ተደረሰበት…”
“እከሌና እከሌ የተባሉ ግለሰቦች እንትና የተባለውን ድርጅት አስመስለው በመሥራት ሲያከፋፍሉ ተገኝተው ጉዳያቸው እየተጣራ ነው…”
“እንትን የተባለውን ምርት በድብቅ አስመስለው እየሠሩ ሲሸጡ የተገኙ ፍርድ ቤት ቀርበው የገንዘብና የእስራት ቅጣት ተበይኖባቸዋል…”
ምናምን አይነት ነገሮች የማንሰማሳ!
በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ማሳነሱ ትክክል አይመስለኝም፡፡
እናማ…ብዙ የበሰሉ ማስታወቂያዎች እንዲኖሩን እንፈልጋለን፡፡ “ማስታወቂያ እስኪያልቅ ደጅ ብቅ ብዬ ነፋስ ይምታኝ…” ማለታችን ቢቀርልን አሪፍ ነው፡፡ ማስታወቂያ በመጣ ቁጥር… “እስቲ ጣቢያውን ለውጠው…” ማለታችን ቀርቶ… “እስቲ አንዴ ዝም በሉ፣ ማስታወቂያዎቹን እንስማበት/እንይበት…” የምንልበት ጊዜ ይፍጠንልንማ፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 6438 times