Saturday, 24 October 2015 10:07

ንፁሁ እና ብርሃናማው ስፍራ (A Clean, Well-Lighted Place)

Written by  ደራሲ - ኧርነስት ሄምንግዌይ ተርጓሚ - አሸናፊ አሰፋ
Rate this item
(5 votes)

(ኧርነርስት ሄምንግዌይ እ.ኤ.አ ከ1909 እስከ 1961 ዓ.ም የኖረ አሜሪካዊ የአጫጭር እና የረዣዥም ልብ-ወለዶች ደራሲ እና ጋዜጠኛ ነበር፡፡ ድርሰቶቹም፣ በጀብድ የተሞላ ህይወቱም ብዙዎች ላይ ተፅእኖ አሳድረዋል፡፡ በ1953 በThe Old Man and The Sea የፑልቲዘር፣ በ1954 ደግሞ በስነ-ፅሁፍ የኖቤል ተሸላሚ ነበር፡፡ በስሙ በጠቅላላው አስር ረዣዥም ልብ-ወለዶች፣ አስር አጫጭር ልብ-ወለዶች፣ አምስት ልብ ወለድ ያልሆኑ ስራዎች ታትመዋል፡፡ የኧርነስት ሄምንግዌይ አባት እራሱን ነው ያጠፋው፡፡ ኧርኒም እራሱን ነው የገደለው፡፡ “ነፍስ ሄር” ብለናል፡፡)
በጣም መሽቷል፡፡ መሸተኛው ሁሉ ሄዶ አንድ ሽማግሌ ብቻ ነው የቀረው፡፡ ሽማግሌው የግሮሰሪው ሰገነት ላይ የዛፎቹ ቅጠሎች የኤሌክትሪኩን ብርሃን ከልለው የተፈጠረው ጥላ ስር ተቀምጧል፡፡ ቀን፣ ቀን መንገዱ አቧራማ ነው፤ ማታ ማታ ጤዛው አቧራውን ያሰክነዋል፡፡ ሽማግሌው አምሽቶ መጠጣት ይወዳል፤ ሁሌም እንደአመሸ ነው፡፡ አካባቢው ጭር ብሏል፡፡ ፀጥታ ሰፍኗል፡፡ ሽማግሌው ጆሮው ባይሰማም የቀኑ ሁካታና የዚህ ሰዓት ፀጥታ ልዩነት ይታወቀዋል፡፡ ግሮሰሪው ውስጥ ያሉት ሁለቱ አስተናጋጆች ሽማግሌው ሞቅ እንዳለው ገብቷቸዋል፡፡ ጨዋ ደንበኛቸው ቢሆንም በጣም ሲሰክር ሂሳብ ሳይከፍል ነው የሚሄደው፡፡ ሁለቱም እያዩት ነው፡፡
“ባለፈው ሳምንት እራሱን ለማጥፋት ሞክሮ ነበር፡፡” አለ አንዳቸው፡፡
“ለምን?”
“ተስፋ ቆርጦ፡፡”
“በምን?”
“በምንም፡፡”
“በምንም እንደሆነ በምን አወክ?”
“ብዙ ገንዘብ አለዋ፡፡”
አስተናጋጆቹ በሩን ተጠግተው፣ ሰገነቱ ላይ ያለው ሽማግሌ እንዲታያቸው ሆነው ነው የተቀመጡት፡፡ ጠረጴዛዎቹ ሁሉ ባዶ ናቸው፡፡ የኤሌክትሪኩን ብርሃን የከለለው ዛፍ በነፋሱ በቀስታ ይወዛወዛል፡፡
ሽማግሌው ጥላው ስር እንደተቀመጠ በሚጠጣበት ብርጭቆ፣ የብርጭቆ ማስቀመጫውን አንኳኳ፡፡ ወጣቱ አስተናጋጅ በፍጥነት ወደ ሽማግሌው ሄደ፡፡
“ምን ፈልገህ ነው?”
“ብራንዲ አምጣልኝ”
“ትሰክራለህ፡፡” አለ አስተናጋጁ፡፡ ሽማግሌው አየው፡፡ አስተናጋጁ ብራንዲውን ሊያመጣ ሄደ፡፡
“ሌሊቱን እዚሁ ማንጋቱ ነው፡፡” አለ ለጓደኛው፡- “እንቅልፌ መጥቷል፡፡ አንድም ቀን ከዘጠኝ ሰዓት በፊት ተኝቼ አላውቅም፡፡ ምነው ባለፈው ሳምንት እራሱን የማጥፋት ሙከራው ተሳክቶ ቢሆን ኖሮ፡፡”
የብራንዲ ጠርሙስና የብርጭቆ ማስቀመጫ ይዞ ወደ ሽማግሌው በረረ፡፡ ማስቀመጫውን አስቀመጠ፡፡ ብርጭቆውን በብራንዲ ሞላው፡፡
“ባለፈው ሳምንት ሞተህ ቢሆን ኖሮ አሪፍ ነበር፡፡” አለ ጆሮው ለማይሰማው ሽማግሌ፡፡ ሽማግሌው ጣቱን ወደ ብርጭቆው እየጠቆመ፡- “ትንሽ ጠብ አድርግበት፡፡” አለ፡፡
ጢም አድርጐ ሞላው፡፡ ብራንዲው ብርጭቆውን እያጠበ መጨረሻ የቀረበው የብርጭቆ ማስቀመጫ ላይ ፈሰሰ፡፡ “አመሰግናለሁ፡፡” አለ ሽማግሌው፡፡ አስተናጋጁ ብራንዲውን ይዞ ወደ ግሮሰሪው ተመለሰ፡፡ ባልደረባው ጋ ሄዶ ተቀመጠ፡፡
“ሰክሯል፡፡” አለ፡፡
“ሁሌ እንደሰከረ ነው፡፡”
“ለምን ይሆን ግን እራሱን ለመግደል የሞከረው?”
“እኔ ምን አውቄ፡፡”
“ምንድነው ያደረገው?”
“በገመድ ታነቀ፡፡”
“ማን አተረፈው ታዲያ?”
“የእህቱ ልጅ፡፡”
“ለምን ብላ?”
“ለነብሱ ሳስታ ነዋ፡፡”
“ምን ያህል ብር አለው?”
“ብዙ አለው፡፡”
“ሰማንያ አመት ይሆነዋል፡፡”
“እኔም ሰማንያ ይሆነዋል ባይ ነኝ፡፡”
“ምናለ ወደ ቤቱ ቢሄድ፡፡ አንድም ቀን ከዘጠኝ ሰዓት በፊት ተኝቼ አላውቅም፡፡ አሁን ምን ይሉታል እስከ ዘጠኝ ሰዓት መቆየት?”
“የሚያመሸው ስለሚመቸው ነው፡፡”
“ብቸኛ ነው እሱ፤ እኔ አይደለሁም፡፡ አልጋ ውስጥ ሆና የምትጠብቀኝ ሚስት አለችኝ፡፡”
“እሱም ሚስት ኖሮት ያውቃል፡፡”
“አሁን ሚስት አያስፈልገውም፤ ምንም አታደርግለትም፡፡”
“እንዲያ ማለት አትችልም፡፡ ሚስት ብትኖረው ነገሮች ይሻሻሉ ይሆን ይሆናል፡፡”
“የእህቱ ልጅ አለች፤ እሷ ትንከባከበዋለች፡፡”
“ይገባኛል፤ እሷ ናት ከገመዱ ያዳነችው፡፡”
“የሱን ያህል ማርጀት አልፈልግም፡፡ የጃጀ ሰው በጣም ያስጠላል፡፡”
“ሁሌ አይደለም፡፡ ይኼ ሽማግሌ ፅዱ ነው፡፡ አንዳችም ሳያንጠባጥብ ነው የሚጠጣው፣ እንዲህ እንኳ ሰክሮ አንዲትም አላንጠባጠበም፡፡ እየው እስኪ፡፡”
“ላየው አልፈልግም፡፡ ወደ ቤቱ እንዲሄድ ብቻ ነው የምፈልገው፡፡ በስራ ለሚደክሙ ሰዎች ግድ የለውም፡፡”
ሽማግሌው አይኑን ከብርጭቆው ላይ አንስቶ ወደ አደባባዩ ተመለከተ፤ ከዚያ አስተናጋጆቹን አያቸው፡፡
“ብራንዲ፡፡” አለ ወደ ብርጭቆው እየጠቆመ፡፡
“አልቋል፡፡” አለ ቀሽም ሰዎች ሰካራምን ወይ የውጪ ዜጋን በሚያናግሩበት ለፍዳዳ ቅላፄ፡-
“ተጨማሪ የለም፡፡ ዘግተናል፡፡”
“ብራንዲ፡፡” አለ ሽማግሌው፡፡
“የለም፡፡ አልቋል፡፡” አስተናጋጁ ጠረጴዛውን በፎጣ እየጠረገ፤ ጭንቅላቱን በአሉታ ነቀነቀ፡፡
ሽማግሌው ካለበት ተነሳ፤ በእርጋታ የብርጭቆ ማስቀመጫዎቹን ቆጠረ፤ ከቆዳ ቦርሳው ውስጥ ገንዘብ አውጥቶ የመጠጡን ከፈለ፡፡ ጉርሻም ትቶአል፡፡
አስተናጋጁ፤ ሽማግሌው መንገዱን ይዞ ቁልቁል ሲሄድ አየው፡፡ ቢንገዳገድም በኩራት ነበር የሚራመደው፡፡
“ምናለ ትንሽ ቢቆይና ቢጠጣ?” አለ ያልቸኮለው አስተናጋጅ፡፡ ሻተሮቹን እየዘጋጉ ነበር፡- “ገና ስምንት ተኩል አልሆነም፡፡”
“ወደ ቤቴ ሄጄ መተኛት እፈልጋለሁ፡፡”
“አንዲት ሰዓት ምን ማለት ናት?”
“ለሱ ምንም፣ ለእኔ ግን ብዙ ነገር ናት፡፡”
“አንድ ሰዓት፣ አንድ ሰዓት ነው፡፡”
“አንተ ራስህ እንደ ሸመገለ ሰው ነው የምታወራው፡፡ ጠርሙስ ገዝቶ ቤቱ ወስዶ መጠጣት ይችላል፡፡”
“አንድ ሰዓት፣ አንድ ሰዓት ነው፡፡”
“አንድ አይደለም፡፡”
“እሱስ አንድ አይደለም፡፡” አለ፤ ተስማሚ ሚስት ያለችው አስተናጋጅ፡፡ ስለቸኮለ እንጂ ይህን አጥቶት አይደለም፡፡ ሽማግሌው ላይም ብዙ መጨከን አልፈለገም፡፡
“ቆይ አንተስ? ከተለመደው ሰዓትህ በፊት ወደ ቤትህ ስትሄድ አትፈራም?”
“ይህቺ እንኳ ስድብ ሳትሆን አትቀርም?”
“አይደለችም ጓዴ፤ እየቀለድኩ ነው፡፡”
“አልፈራም፡፡” አለ የቸኮለው አስተናጋጅ፡- “በራሴ እተማመናለሁ፤ ሙሉ በሙሉ በራሴ እተማመናለሁ፡፡”
“ወጣት ነህ፤ በራስህ ትተማመናለህ፤ በዚያም ላይ ባለ ስራ ነህ፡፡” አለ በእድሜ ከፍ ያለው አስተናጋጅ፡- “ሁሉም ነገር አለህ፡፡”
“አንተስ ምን አጣህ?”
“ከስራዬ በስተቀር ምንም የለኝም፡፡”
“እኔ ያለኝ ሁሉ አለህ፡፡”
“የለኝም፡፡ አንድም ቀን በራሴ ተማምኜ አላውቅም፡፡
 በዚያም ላይ ወጣት አይደለሁም፡፡”
“መዘላበዱን ተውና ካፌውን ዝጋ፡፡”
“ካፌው ውስጥ ማምሸት ከሚፈልጉ ሰዎች አንዱ ነኝ፡፡” አለ በእድሜ ከፍ ያለው አስተናጋጅ፡- “ወደ አልጋቸው ለመሄድ ከማይጣደፉት ጋር አብሬ ማምሸት እፈልጋለሁ፡፡ የምሽቱን ጨለማ የሚያሸንፍ ብርሃን ከሚፈልጉ ሰዎች ጋር አብሬ ማምሸት እፈልጋለሁ፡፡”
“እኔ ደግሞ ወደ ቤቴ እና ወደ አልጋዬ፡፡”
“በጣም የተለያየን ሰዎች ነን፤ እኔ እና አንተ፡፡” አለ እድሜውን ገፋ ያደረገው አስተጋጅ፡-
“ወጣት መሆን እና በራስ መተማመን ብቻ አይደለም የሚለያየን፡፡ ወጣትነትም በራስ መተማመንም በጣም ደስ የሚሉ ነገሮች ናቸው፡፡ ሁሌም ግሮሰሪውን በጊዜ ዘግቼ የማልሄደው፣ የግሮሰሪውን ድባብ የሚፈልግ የሆነ ሰው ከመጣ ብዬ ነው፡፡” “ወዳጄ፤ ሌሊቱን ሙሉ ክፍት የሆኑ ቡና ቤቶች አሉ እኮ፡፡”
“አልገባህም፡፡ ይህ ፅዱ እና አስደሳች ግሮሰሪ ነው፡፡ ብርሃናማ ነው፤ ብርሃኑ በጣም ይማርካል፡፡ ሌላው ደግሞ የዛፎቹ ጥላ አለ፡፡”
“ደህና እደር፡፡” አለ ወጣቱ አስተናጋጅ፡፡
“ደህና እደር፡፡” አለ ሌላኛውም፡፡ የግሮሰሪውን መብራት አጠፋ፡፡ ወሬውን ግን ከራሱ ጋር ቀጠለ፡፡ ‘ዋናው ነገር ብርሃን መኖሩ ነው፡፡ ቦታው ፅዱ እና ማራኪም መሆን አለበት፡፡ ሙዚቃ አያስፈልግም፡፡ ሙዚቃ ጨርሶ አያስፈልግም፡፡ ቡና ቤት ስትገባ ክብር አይኖርህም፡፡ ድሮስ ቡና ቤት ውስጥ በዚህ ሰዓት ምን ይጠበቃል፡፡ ምንድነው የሚያስፈራው? ፍርሃት አይደለም፤ ስጋትም አይደለም፡፡ ከሁሉም በላይ ጠንቅቆ የሚያውቀው ምንምነት ነው የሚቀፈው፡፡ ምንምነት በሁሉም ቦታ ተንሰራፍቷል፡፡ ሰው እራሱ ምንም ነው፡፡ ይህ ነው በቃ፡፡ ይህን ሊያስወግድ የሚችለው ብርሃን ነው፤ ንፅህናም ያስፈልጋል፣ ነገሮችም ቦታ፣ ቦታቸውን መያዝ፣ መሰናዳት አለባቸው፡፡ ሰዎች እየኖሩበት አይታወቃቸውም፣ እሱ ግን አበጠርጥሮ ያውቀዋል፡፡ ሁሉ ነገር ምንም - በምንም ነው፡፡ ምንም፡፡ ምንም፡፡ ምንም፡፡ ምንም፡፡ ምንም፡፡ ምንም፡፡ ምንም፡፡ ምንም፡፡ ምንም፡፡ ምንም፡፡ ምንም፡፡ ምንም፡፡ ምንም፡፡ ምንም፡፡ ምንም፡፡ ምንም፡፡ ምንም፡፡ ምንሞች ምንምነትን አመስግኑ፤ ምንም ከእናንተ ጋር ነውና፡፡’ ፈገግ አለ፡፡ እራሱን ቡና ቤት ውስጥ ነው ያገኘው፡፡
“ምን ልቅዳልህ?” አለ መጠጥ ቀጂው፡፡
“ምንም ቅዳልኝ፡፡”
“ሌላ ንክ ደሞ መጣ፡፡” ብሎ ወደ ነበረበት ተመለሰ፡፡
በመጨሻ የሚጠጣ አዘዘ፤ ተቀዳለት፡፡
“ቡና ቤታችሁ ብርሃኑ ደማቅ እና ማራኪ ነው፡፡ ፅዱ ግን አይደለም፡፡” አለ አስተናጋጁ፡፡
መጠጥ ቀጂው መልስ አልመለሰም፡፡ በዚህ ሰዓት ከመጣ ሰው ጋር ማውራት አያዋጣም፡፡
“ሌላ ልቅዳልህ?” ጠየቀ መጠጥ ቀጂው፡፡
“አመሰግናለሁ፤ አልፈልግም፡፡” ሂሳቡን ከፍሎ ወጣ፡፡ ቡና ቤቶች ያስጠሉታል፡፡ እንደ ፅዱ እና ብርሃናማ ግሮሰሪ አይሆኑም፡፡ አሁን እቤቱ ገብቶ አልጋው ላይ ይዘረራል፡፡ በስንት መከራ ከነጋ በኋላ እንቅልፍ ይወስደዋል፡፡ ችግሩ እንቅልፍ - አልባነት (Insomania) እንደሆነ እራሱን አሳምኗል፡፡ የኔ ችግር ብቻ አይደለም፤ ይኼኔ ስንቶቹ በእንቅልፍ አልባነት እየተሰቃዩ ነው ብሎ እራሱን ያፅናናል፡፡
(ምንጭ፡- THE SHORT STORY፡ JOHNSON & HAMLIN: 1966)


Read 3654 times