Saturday, 31 October 2015 08:47

ብሄራዊ ቡድኖቹ ከፌደሬሽኑ ውጭ በሽልማት መበረታታት አለባቸው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

• ወጣቶቹ ሉሲዎች ለዓለም ዋንጫ ቢያልፉም ባያልፉም መነቃቃት ፈጥረዋል
• ሎዛ አበራ በዱራሜ ብዙ መሰሎችን አነቃቅታለች
• ዋልያዎቹ ቻን በመግባት ታሪክ ደግመዋል

በዓለም U-20 የሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ለመሳተፍ 1 ጨዋታ የቀራቸው ወጣቶቹ ሉሲዎች  ቢያልፉም ባያልፉም ከፍተኛ መነቃቃት ፈጥረዋል፡፡ በሌላ በኩል በሩዋንዳ ለሚካሄደው 5ኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ቻን ውድድር ያለፉት  አዳዲሶቹ ዋልያዎችን የነባሮቹን ታሪክ በመድገም ተሳክቶላቸዋል፡፡ ሁለቱ ብሄራዊ ቡድኖች ከእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ከሚያገኙት የማበረታቻ ክፍያዎች ባሻገር በሚሳተፉባቸው የውድድር መድረኮች በሞራል እንዲገቡ እና ሌሎች ተከታይ ትውልድን ለማነቃቃት በሚያስችሉ ሽልማቶች መበረታት እንዳለባቸው  እየተገለፀ ነው፡፡  8ኛው የዓለም U-20 የሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ በፓፓዋ‬ ኒው ጊኒ አስተናጋጅነት በሰኔ ወር መጨረሻ የሚካሄድ ነው፡፡  ከሳምንት በፊት የአፍሪካን አህጉር የሚወክሉትን ሁለት አገሮች ለመለየት የመጨረሻው ዙር ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታዎች
ተደርገዋል፡፡ አዲስ አበባ ላይ የተገናኙት ኢትዮጵያ እና ጋና  በአቻ ውጤት  2-2 ሲለያዩ፤ በሌጎስ ደግሞ ናይጄርያ  2ለ1 ደቡብ አፍሪካን አሸንፋለች፡፡ ከሳምንት በኋላ  ደቡብ አፍሪካ ናይጄርያን እንዲሁም ጋና ኢትዮጵያን በሜዳቸው በሚያስተናግዱባቸው ሁለት የመልስ ጨዋታዎች ውጤት አፍሪካን የሚወክሉት ቡድኖች ይታወቃሉ፡፡በአፍሪካ ዞን ለU-20 የሴቶች ዓለም ዋንጫው በተሰጠው የሁለት ብሄራዊ ቡድኖች ኮታ  ባለፉት 6 ወራት ከቅድመ ማጣርያው አንስቶ 19 አገራት ተሳትፈውበታል፡፡ ለመጨረሻው  ምዕራፍ የደረሱት ኢትዮጵያ፤ ጋና፤ ናይጄርያ እና ደቡብ አፍሪካ ናቸው፡፡ በሁለት ዙር ቅድመ ማጣርያዎች ኢትዮጵያ ካሜሮንን 2ለ1 እንዲሁም ቡርኪናፋሶን 2ለ0 ፤ ጋና ደግሞ ሴኔጋልን 8ለ0 እና ጊኒን 3ለ0 በሆኑ
የደርሶ መልስ ውጤቶች አሸንፈዋል፡፡  በ8ኛው የU-20 የሴቶች ዓለም ዋንጫ ላይ መሳተፋቸውን
ያረጋገጡት  አዘጋጇን ፓፓዋ ጊኒ ጨምሮ 9 አገራት ናቸው፡፡ ከአውሮፓ ዞን ፈረንሳይ ፣ ጀርመን ፣
ስፔንና ስዊድን፤ ከኤሽያ ዞን ጃፓን፣ሰሜን ኮርያ እና ደቡብ ኮርያ እንዲሁም ከኦሽኒያ ዞን
ኒውዝላንድ ናቸው፡፡ ሎዛ  በኮከብነት አንፀባርቃለችየኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች  የሴቶች ብሄራዊ ቡድን በአምበልነትና በግብ አዳኝነት የምትመራው ከዱራሜ የ19 ዓመቷ ሎዛ አበራ ናት፡፡  በከንባታ ዞን የምትገኘውን ዱራሜ ከተማ በቅርቡ የጎበኘው የአዲስ አድማስ ባልደረባ አለማየሁ አንበሴ፤ በከተማዋ የሴቶች እግር ኳስ በከፍተኛ ደረጃ መነቃቃት እንደሚታይበት ገልፆልኛል፡፡ በወቅቱ አካባቢውን ለጎበኙ የጋዜጠኞች ቡድን የዱራሜ ሴት ወጣቶች የኳስ ግጥሚያ ማሳየታቸውን የጠቆመው የዝግጅት ክፍላችን ባልደረባ፤ በሰውነታቸው ጠንከር ያሉ፤ ከፍተኛ ቅልጥፍና እና ነፃነት የሚታይባቸው መሆናቸውን
ተገንዝቧል፡፡ የዱራሜ ሴት ወጣቶች የከተማው ጀግና ሆና የወጣችውን ሎዛ አበራ እየተከታተሉ መሆናቸውንም በተጨማሪ ገልፆ፤ ሴቶችን ለማብቃት በከተማው የሚደረጉ እንቅስቃሴዎቹን ጋዜጠኞቹ ሲጎበኙ በእግር ኳሱ ከፍተኛ መነቃቃት መኖሩን በገሃድ መመልከታቸውን ለስፖርት አድማስ አብራርቷል፡፡ ለነገሩ ሎዛ አበራ አድናቆት ያተረፈችው በትውልድ ከተማዋ ብቻ አይደለም፤ በአዲስ አበባ እና በባህርዳር ስታድዬሞች የተገኙ ስፖርት አፍቃሪዎች፤ በሬድዮ እና በቴሌቭዥን ጨዋታዎችን ሲከታተሉ የነበሩ ኢትዮጵያውያን እና ኮሜንታተሮችን ቀልብንም እንደገዛች ሰንብታለች፡፡ የጋና ጋዜጦችም ስለ ሎዛ አበራ ብዙ ፅፈዋል፡፡ አንዱ ሮዛና ሌላው ደግሞ በአያቷ ስም እየጠቀሳት በጥቋቁር ልፅልቶቹ ላይ ስላስቆጠረቻቸው 2 ጎሎች በስፋት በማውሳት የፃፉት ሚሰዲያዎቹ በመልሱ ጨዋታ የምትሰራውን ታሪክ በከፍተኛ ስጋት እየተጠባበቁት ይገኛል፡፡ በአጠቃላይ ሎዛ አበራ የአገሪቱን የሴቶች እግር ኳስ  አቅም እና የወደፊት ተስፋዎች በማንፀባረቅ ላይ ትገኛለች፡፡ ከጋና ጋር ከሚደረገው የመጨረሻው የመልስ ጨዋታ በፊት ወጣቶቹ ሉሲዎች  ከ3 የምዕራብ አፍሪካ ቡድኖች ጋር ባደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች 6 ጎሎችን ያመዘገበችው 10 ቁጥሯ ሎዛ አበራ ናት፡፡ በ6 ጎሎቿም የአፍሪካ ዞን ማጣርያን በኮከብ ግብ አግቢነት እየመራች ነው፡፡ ካሜሮን ላይ 2፤ ቡርኪናፋሶ ላይ 2 እንዲሁን ጋና ላይ ሁለት ጎሎችን አስቆጥራለች፡፡  በ5 ጎሎች የምትከተላት የናይጄርያዋ ቺንዎንዱ ኢዞሆ ናት፡፡ ባለፉት 6 ወራት 19 የአፍሪካ ቡድኖች በማሳተፍ በተደረጉት 30 የማጣርያ ጨዋታዎች 89 ጎሎች የተመዘገቡ ሲሆን በአንድ ጨዋታ በአማካይ 2.97 ጎሎች ሲቆጠሩ እንደነበር ታውቋል፡፡
በኩማሲ ከፍተኛ ጀግንነት የሚጠበቅባቸው ወጣቶቹ ሉሲዎችየኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን «የአባይ ፈርጦች» በሚል ቅፅል  ስም ወጥቶለታል፡፡ ለዋና ብሄራዊ ቡድን በማሰብም ወጣቶቹ ሉሲዎች እየተባሉም ነው፡፡ የወጣቶቹ ሉሲዎች  ሥነ ልቦና ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ መሆኑ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች የታየ ነው።  ከጋና ጋር 2ለ2 ከተለያዩበት የመጀመርያ ጨዋታ በኋላ ዋና አሰልጣኝ አሥራት አባተ ቡድናቸው በሜዳው የተሸነፈው ከልምድ ማነስ ብቻ መሆኑን አስተያየት ሰጥቷል፡፡ ግብ አዳኟ ሎዛ አበራ በበኩሏ ሁለት ጎሎችን ብታስቆጥርም የተገኙትን የግብ አጋጣሚዎች ባለመጠቀማቸውና  በሜዳቸው በመሸነፋቸው ብዙም አልተደሰተችም፡፡ ብናሸንፍ የተሻለ ነበር ያለችው፡፡  ወጣቶቹ ሉሲዎች
በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ኢትዮጵያን ለዓለም U-20 የሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ ለማብቃት በኩማሲ
በሚያደርጉት የመልስ ጨዋታ ከፍተኛ ጀግንነት ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡ ከሜዳቸው ውጭ  ከሳምንት በኋላ በሚደረገው ወሳኝ የመልስ ጨዋታ ላይ ወደ ወጣት ሴቶች የዓለም ዋንጫው የሚያልፉት በማንኛውም ውጤት ተጋጣሚያቸውን ማሸነፍ ከቻሉ ነው፡፡ በመልሱ ጨዋታ አቻ የሚለያዩ ከሆነ ግን 1ለ1 እኩል መውጣት አይሆናቸውም፤ አቻ ቢለያዩ እንኳን ከሜዳው ውጭ ብዙ ባስቆጠረ በሚለው ደንብ የማለፍ  ዕድል የሚኖራቸው 3ለ3 እና ከዚያም በላይ  ውጤት ማስመዝገብ ከቻሉ ብቻ ነው፡፡ እንደ አዲስ አበባው የመጀመርያ ጨዋታ በተመሳሳይ 2ለ2 በመልስ ጨዋታ በመለያየት መደበኛ ጨዋታ ክፍለ ጊዜ ካጠናቀቁ ደግሞ በመለያ ቶች ውጤት የማለፍ እድላቸውን ይወስናሉ፡፡በአጠቃላይ አሁን የደረሱበት ምዕራፍ ወጣቶቹ ሉሲዎች ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ በአገሪቱ የሴቶች እግር ኳስ በስፋት እንዲሰራ የተወሰነ መነቃቃት መፍጠራቸውም እንደ ትልቅ ውጤት መታየት ይኖርበታል፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ከጋና ጋር ከተደረገው ጨዋታ በፊት ለመላው የቡድኑ አባላት ከ5 እስከ 18ሺ ብር የሚደርስ የማበረታቻ ሽልማት ያበረከተውም ይህንኑ በመረዳት ይመስላል፡፡ ወጣቶቹ ሉሲዎች አስቀድመው ባካሄዷቸው የማጣርያ ግጥሚያዎች ካለፉባቸው ውጣውረዶች አንፃር ገና ብዙ ድጋፍ እና ማበረታቻ እንደሚያስፈልጋቸው ማንም ባለድርሻ አካል ይገነዘበዋል፡፡ በሶስቱ የማጣርያ ምዕራፎች ያስመዘገቧቸው ውጤቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለወጣት ሴቶች ዓለም ዋንጫው  ባያልፉም እንኳን በማጠቃለያው ተጨማሪ የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸው በቀጣይ ውድድሮች ያገኙትን ልምድ አዳብረው እንዲቀጥሉበት የሚያነሳሳቸው  ይሆናል፡፡ ቡድኑ ለዓለም ዋንጫ የሚያልፍ ከሆነ ደግሞ በኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ አዲስ ታሪክ ሆኖ የሚመዘገብ
አበት ምዕራፍ ስለሚሆን በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ፤ በመንግስት እና በሌሎች ባለድርሻ አካላት ዳጎስ
ያለ የምስጋና ሽልማት መሰጠት አለበት፡፡ በቀጣይ ዋናው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን
በእነዚህ ወጣቶች ላይ በአስተማማማኝ መሰረት ላይ እንዲገነባ ማበረታቻዎቹ አስፈላጊ ይሆናሉ፡፡
በአዲስ አበባ አየር የተጎሳቆሉት ጥቋቁር ልዕልቶቹ ለ4ኛ ጊዜ…የጋና ወጣት ሴቶች ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ መሱድ ዱአማሲ አዲስ አበባ ላይ ከመጫወታቸው በፊት ብዙም ከማያውቁት ባላጋራ ቡድን ጋር እንደሚገናኙ በመጥቀስ ቡድናቸው በመከላከል ላይ የተመሰረተ አጨዋወት እንዲከተል የነበራቸውን ፍላጎት ገልፀው ነበር፡፡ ዓላማችን ለአራተኛ ተከታታይ ጊዜ በፊፋ U-20 የሴቶች ዓለም ዋንጫ መሳተፍ ነው በማለት ከመጀመርያው ጨዋታ በፊት የተናገሩት ዋና አሰልጣኙ በአዲስ አበባው ጨዋታ 2ለ2 ከተለያዩ በኋላ ግን ቡድናቸው መልካም የግብ አጋጣሚዎችን አለመጠቀሙን አንስተው ፤ ተጨማሪ ጎሎች ብናስቆጥር የመልስ ጨዋታውን በቀላሉ የምንወጣበት ሁኔታ ይፈጠር እንደነበር በቁጭት አስተያያት መስጠታቸው ተዘግቧል፡፡ በአዲስ አበባ ከፍተኛ አልቲትዩድ በቡድናቸው ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩንም
በተጨማሪ የገለፁት ዋና አሰልጣኙ ከጨዋታው በኋላ ስድስት ተጨዋቾች ከድካማቸው ማገገም
የቻሉት በህክምና ቡድናቸው ከፍተኛ ድጋፍ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡የጋና ሚዲያዎች ጥቋቁሮቹ
ልዕልቶች ባላቸው ከፍተኛ ልምድ ተጠቅመው የወጣት ሴቶች ዓለም ዋንጫ ተሳትፏቸውን
እንደሚያረጋገጡ በመግለፅ ላይ ናቸው፡፡ በርግጥም ጋና በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ልምድ እንዳላቸው የውጤት ታሪካቸው ያመለክታል፡፡  የጋና ወጣት ሴቶች ብሄራዊ ቡድን በፊፋ U-20 የዓለም ሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ ለ3 ጊዜያት በ2010፡ በ2012 እና በ2014  እኤአ  በማለፍ  በምድብ ጨዋታዎች ተሳትፎ ነበረው፡፡  በአንፃሩ በወጣት ሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ላይ 5 ጊዜ በመሳተፍ በ3 ተከታታይ ውድድሮች በ2010፡
በ2012 እና በ2014 እኤአ ለሶስት ጊዜያት ሻምፒዮን ለመሆን ችለዋል፡፡ስለ ፊፋ ሀ 20 የዓለም
ሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) U-20 የዓለም ሴቶች እግር ኳስ ዋንጫን የመሰረተው በ2002 እኤአ ሲሆን በ2014 እኤአ ላይ ለ7ኛ ጊዜ ውድድሩ በካናዳ ሲካሄድ ሻምፒዮን ለመሆን
የበቃችው ጀርመን ነበረች፡፡ አሜሪካ እና ጀርመን ባለፉት 7 U-20 የዓለም ሴቶች እግር ኳስ
ዋንጫዎች እኩል ሶስት ጊዜ ሻምፒዮን ሆነውበታል፡፡ በ2004, 2010, 2014 እኤአ ሻምፒዮን
የሆነችው  ጀርመን በ2012 እኤአ ሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም በ2002 እና በ2008 እኤአ ላይ ሶስተኛ
ደረጃዎችን በማግኘት  የከፍተኛ ውጤት ክብረወሰኑን ይዛለች፡፡ አንድ ጊዜ ሻምፒዮን ለመሆን
የበቃችው ደግሞ በ2006 እኤአ ያሸነፈችው ሰሜን ኮርያ ናት፡፡ ከአፍሪካ አገራት ናይጄርያ በ2010
እና በ2014 እኤአ ሁለተኛ ደረጃዎችን እንዲሁም በ2012 እኤአ ሶስተኛ ደረጃ በማግኘት በከፍተኛ
ውጤት ደረጃዋ ከዓለም በአራተኛ ደረጃ ተቀምጣለች፡፡በዓለም ዳርቻ የምትገኘው አዘጋጇ ፓፓዋ ኒው ጊኒ
8ኛው የፊፋ U-20 የዓለም ሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ የሚስተናገደው
በፓፓዋ ኒው ጊኒ ይሆናል፡፡ በወጣት ሴቶች የዓለም ዋንጫው ከ6 የፊፋ ኮንፌደሬሽኖች
የተውጣጡ 16 ብሄራዊ ቡድኖች ይሳተፉበታል፡፡ ከሶስት ዓመታት በፊት ለውድድሩ  አዘጋጅነት
በመጀመርያ ዙር ያመለከቱት ኖርዌይ፤ ሪፖብሊክ ኦፍ አየርላንድና ደቡብ አፍሪካ ነበሩ፡፡ ደቡብ
አፍሪካ በፊፋ አባል አገራት በተካሄደው ምርጫ የመስተንግዶው እድል ብታገኝም ግልፅ ባልሆኑ
ሁኔታዎች አዘጋጅነቷን ላለመቀበል በመወሰኗ ፊፋ ለሌሎች አገራት የአዘጋጅነት እድል ድጋሚ ጥያቄ
አቅርቧል፡፡ በዚህ እድል ለመጠቀም  ፓፓዋ ኒው ጊኒ  ከአውሮፓዋ ተወካይ ስዊድን ጋር ለመፎካከር አመልክታ ከ1 ዓመት በፊት የአዘጋጅነቱን እድል አግኝታለች፡፡ ከአውስትራሊያ አህጉር ባሻገር በስተሰሜን የምትገኝው  ፓፓዋ ኒው ጊኒ 7.1 ሚሊዮን ህዝብ ያላት በኦሽኒያ ዞን የምትመደብ ደሴት አገር ናት፡፡ በዓለም ብዙ ቋንቋዎች ካሉባቸው አገራት አንዷ ሆና በምትጠቀሰው ፓፓዋ ጊኒ ከ848 በላይ ቋንቋዎችን መኖራቸውን የሚጠቅሱ መረጃዎች በአሁኑ ጊዜ ህዝቦቿ 12 የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩ መሆናቸውን  ያመለክታሉ፡፡ በዋና ከተማዋ ፖርት ሞስቤይ በሚገኙ አራት ስታድዬሞች የወጣት ሴቶች ዓለም ዋንጫውን ለማዘጋጀት በጉጉት እየተጠባበቀችም ትገኛለች፡፡
የአዳዲሶቹ ዋልያዎች ገድል…በሩዋንዳ ለሚካሄደው 5ኛው  ሻምፒዮንሺፕ የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ቻን ማለፉን ያረጋገጠው የኢትዮጵያ  ብሄራዊ ቡድን  በአዳዲሶቹ ዋልያዎች እና በዋና አሰልጣኙ ዮሃንስ ሳህሌ ተስፋ ማድረግ እንደሚቻል አመላክቷል፡፡  ብሄራዊ ቡድኑ በጥር ወር በአዘጋጅነት በሚሳተፉበት
የሴካፋ ሻምፒዮና እንዲሁም በአፍሪካ ዋንጫ እና በዓለም ዋንጫ ማጣርያዎች በሚኖራቸው ተሳትፎ
በቻን ውድድር መግባታቸው በክፍተኛ ደረጃ የሚያጠናክራቸው ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወደ ቻን ውድድር ማለፉን ያረጋገጠው ከቡርንዲ አቻው ጋር በአዲስ አበባ ስታዲየም ባደረገው የመልስ ጨዋታ 3 ለ 0 በሆነ ውጤት በማሸነፉ ነው። ጎሎቹን ያስቆጠሩት በ37ኛው
ደቂቃ ስዩም ተስፋዬ እንዲሁም በ73ና 79ኛው ደቂቃ ላይ ጋቶች ፓኖም ነበሩ። ዋልያዎቹ ቡርንዲ
ላይ ተደርጎ በነበረው ጨዋታ 2 ለ 0 በሆነ ውጤት መሸነፋቸውን በሜዳቸው በመቀልበስ በድምሩ
3 ለ 2 በማሸነፍ ታሪክ መስራታቸው የሚደነቅ ነው፡፡በመጪው ጥር ወር ሩዋንዳ በምታስተናግደው የአገር ውስጥ ተጫዋቾች ብቻ ከሚሳተፉበት  16 ብሄራዊ ቡድኖቹ 15 አገራት ተሳትፏቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ከሰሜን ዞን ሞሮኮና ቱኒዚያ ለሁለተኛ
ጊዜ፤ ከምዕራብ ዞን 1 ማሊ ለ3ኛ፣ ናይጄርያ ለ2ኛና ለጊኒ ለመጀመርያ ጊዜ፤ ከምዕራብ ዲሪ ሪፖብሊክ ኮንጎ ለ4ኛ እና ኒጀር ለ2ኛ ጊዜ፤ ከመካከለኛው ዞን እና ጋቦን ለ3ኛ ጊዜ፤ ከመካከለኛውና ምስራቅ ዞን አዘጋጇን ሩዋንዳና ኢትዮጰያ ለ2ኛ ኡጋንዳ ለ3ኛ ጊዜ፤ ከደቡብ ዞን  ዚምባቡዌ ለ4ኛ ጊዜ ዛምቢያበ እኩል ለ2ኛ ጊዜ ለአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ቻን ውድድር
ማለፋቸው ነው፡፡  በቀረው የአንድ ብሄረዊ ቡድን ኮታ  አይቬሪኮስት ከጋና በሚያደርጉት የመልስ
ጨዋታ ሃላፊው ይወሰናል፡፡

Read 4379 times