Print this page
Saturday, 31 October 2015 09:29

የፖለቲካ ቅኔያችን -ሰ“ው እኮ እውነት ይመስለዋል!”

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(13 votes)

“ታጋሽ ህዘብ”ን የሚሸልም የአውሮፓ ድርጅት የለም??
የሙስና “ኔትዎርክ”፣ የቴሌን ኔትዎርክ አጣጥፎት ሄደ!!

   አንዲት “ነቄ” እናት ናቸው አሉ፡፡ ቀለም ባይዘልቃቸውም ነገር ቶሎ ይገባቸዋል፡፡ (ፖለቲከኞቻችን እኮ ነገር ቶሎ አይገባቸውም!) በዚያ ላይ ልጆቻቸው ሁሉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ናቸው፡፡ እናላችሁ ----- ልጆቻቸውና የኮሌጅ ጓደኞቻቸው ቤት ውስጥ ሰብሰብ ብለው ስለ ትምህርታቸው የሚወያዩትን አዘወትረው ይሰማሉ፡፡ ልጆቹ ከሚማሯቸው የትምህርት ዓይነቶችም ጋር ከጊዜ ብዛት ተላምደው ብዙዎቹን በስም ያውቋቸዋል፡፡ አንድ ቀን ታዲያ ልጆቻቸው ተሰብስበው ሲያጠኑ ጣልቃ ገቡና፤“እኔ የምላችሁ --- ከናንተ ውስጥ አንድም እንኳ ጉምሩክ የሚባል ትምህርት የሚማር የለም?” ሲሉ ጠየቁ፡፡ (“ነቄነታቸው” ከኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት አላዳናቸውም ማለት እኮ ነው!)
በነገራችን ላይ በመንግስት አሰራር ላይም ሆነም በህዝብ ኑሮ ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የሚያስከትለው የሙስና ወንጀል፣ በዋናነት የአመለካከት ጉዳይ እኮ ነው፡፡ (እንደ አደንዛዥ ዕጽ የሙስና ቴራፒ ወይም ተሃድሶ ማዕከል ሳያስፈልገን አይቀርም!) ከምሬ እኮ ነው የምላችሁ --- ከየመንግስት መ/ቤቱ በሙስና እየተጠረጠሩ የሚከሰሱ ከፍተኛ የመንግስት ሹማምንት ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ነው፡፡ (ገና እኮ ያልተነቃባቸውም አሉ!) ሰሞኑን እንኳን የኤርፖርቶች ድርጅት ከፍተኛ ኃላፊዎችን ጨምሮ 15 ሰራተኞች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው መከሰሳቸው  ተዘግቧል፡፡ (ከቴሌ ኔትዎርክ የሙስና ኔትዎርክ በለጠ እኮ!) እኔማ ትንሽ በዛ ያለ ገንዘብ ይንቀሳቀስበታል በሚባል የመንግስት መ/ቤት ባለፍኩ ቁጥር “ስንቱ ተብልቶ ይሆን?” የሚል ስጋት ይንጠኝ ጀምሯል፡፡ (ከፍተኛ ሙስና = የድህነት አረንቋ!)
እኔ የምለው ግን ወዳጅ አገር ኮሙኒስት ቻይና----የ1ለ5 ጥርነፋ ብቻ ነው እንዴ የምታውቀው? ሙሰኞችን በ1ለ5 ጠርንፎ መቆጣጠርስ እንዴት አልተቻለም? (ገንዘብ ምን የማይበጣጥሰው መረብ አለ?) ከምሬ ነው የምላችሁ----ሙስናን ለመዋጋት “ረዳት መንግስት; ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡ (የተቃዋሚዎች የጸረ-ሙስና ግብረ ሃይል ቢቋቋምስ?)   
ወደ ዛሬ አጀንዳችን ለመግባት በቅርቡ የነገርኳችሁን አንድ ቀልድ ልደግመው ነው፡፡  ለምን መሰላችሁ? የፖለቲካ ወጋችን ማጠንጠኛ በመሆኑ ነው፡፡ ቀልዱን በአጭሩ ላስታውሳችሁ፡-አንድ የአገራችን ልማዳዊ ነጋዴ፤(የልምድ አዋላጅ እንደሚባለው!) “ደንበኛ ንጉስ ነው!” የምትለዋን ታዋቂ የቢዝነስ ጥቅስ፣ባሸበረቀ ቀለም አፅፎ እሱቁ ግድግዳ ላይ ፊት ለፊት ለጥፏታል፡፡ አንድ ስልጡን ደንበኛ፤ ወደ ሱቁ እንደገባ፣ ዓይኑ እዚያች ጥቅስ ላይ ያርፍና በመደነቅ፣ግሩም ጥቅስ እንደሆነች ለባለሱቁ ይነግረዋል፡፡ ባለሱቁ (ነጋዴው) ምን ቢል ጥሩ ነው?፤“ሰው እኮ እውነት ይመስለዋል!” ይሄኔ ደንበኛው በሃፍረት ተሸማቆ ከሱቁ ውልቅ አለ፡፡ ዳግም ላይመለስ በሆዱ እየማለ፡፡ (በጥቅሷ ተሸውዶ፣“ንጉስ” ለመሆን የዳዳው ደንበኛ አለቀለት!)   
ብዙ ነገራችንን ብትመረምሩት፣ “ሰው እኮ እውነት ይመስለዋል” በሚል ቅኔያዊ መልዕክት አምሮና ተውቦ የተጠቀለለ ነው፡፡ (የስጦታ እቃ በሉት!!) የቅኔውን ፍቺ የምናውቀው መቼ መሰላችሁ? ተጠራጣሪ ወይም አጥብቆ ጠያቂ ስንሆን ብቻ ነው፡፡ ቅኔያዊ ንግግር ወይም መልዕክት በማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ህይወታችን ውስጥ የተለመደ ቢሆንም የፖለቲካውን ያህል ግን አይበዛም፡፡    
እስቲ እንደው ዝም ብላችሁ-----የአገራችንን የፖለቲካ ፓርቲዎች ስም ልብ ብላችሁ ተመልከቱልኝ፡- ኢህአዴግ፣ ኢዴፓ፣ አንድነት፣ ኦፌዴን፣ መድረክ፣ አረና ወዘተ---- በሁሉም ፓርቲዎች ስም ውስጥ የጋራ የሆነው ነገር ምን መሰላችሁ? “ዴሞክራሲ” የሚለው ቃል ነው፡፡ እውነት ግን ፓርቲዎቹ ዲሞክራሲያዊ ናቸው? አጥብቆ መጠየቅ የግድ ይላል፡፡ ገና “በስማችሁ ውስጥ ዲሞክራሲ የሚለውን ቃል ማካተታችሁ ----“ ስትሏቸው፣እንደ ልማዳዊ ነጋዴው፤ “ሰው እኮ እውነት ይመስለዋል!” ብለው ሊገላግሏችሁ ይችላሉ፡፡ (እነሱም እኮ “ልማዳዊ ፓርቲዎች” ናቸው!)
አውራው ፓርቲ ኢህአዴግ፤ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ተመስርቶ የማየት ፅኑ ምኞት እንዳለው ደጋግሞ ሲነግረን እንደነበር አይዘነጋም፡፡ (ምኞት ሆኖ ቀረ እንዴ?) በተግባር ግን እንኳንስ ለጠንካራዎቹ ለደካሞቹም ፊት አልሰጠም፡፡ ጭርሱኑ ከ2002 ምርጫ በኋላ “አሁን ያሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዳግም እንዳያንሰራሩ” ተግቶ መሥራት እንዳለበት ራሱን አሳመነ፡፡  እናላችሁ…ኢህአዴግ “ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ያስፈልገኛል” እያለ በከንቱ ሲያደርቀን፣“ግን ከልብህ ነው?” ብንለው፤“ሰው እኮ እውነት ይመስለዋል” ብሎ እንደ ነጋዴው እቅጯን ይነግረን ነበር፡፡ (ባለመጠየቃችን ተሞኘን!)
አውራው ፓርቲ የ97 ምርጫ እልሁን በተወጣበት በ2002 ምርጫ ማግስት፣ (ከ96. ምናምን ውጤት በኋላ ማለት ነው!) ምን አለ? (ቃል ገባ እንጂ!) “ምንም እንኳን ተቃዋሚዎች ድምጽ አግኝተው ፓርላማ ባይገቡም መንግስት በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የሚያወያይበት መድረክ ያመቻቻል” ብሎ ነበር፡፡ ሆኖም ግን የ2007ቱ የግንቦት ምርጫ “ከች” እስኪል ድረስ ከተቃዋሚዎች ጋር የተባለው ውይይት አልተካሄደም፡፡ (በምስጢር ተካሂዷል ካልተባለ በቀር!?) በዚህም የተነሳ ብዙዎች ኢህአዴግን ወይም መንግስትን “ቃል አባይ” ብለው መንቀፋቸው አይቀርም፡፡ ግን እኮ ያኔውኑ ኢህአዴግን “ከምርህ ነው?” ብንለው ኖሮ፣ እቅጯን ይነግረን ነበር - “ሰው እኮ እውነት ይመስለዋል” በማለት፡፡ (ስንቴ ተሸወድን!)
ከአምስት ወይም ስድስት ዓመታት በፊት ልማታዊ መንግስታችን፣በቀጣዩ ዓመት የበቆሎ ምርት ለውጭ አገራት ኤክስፖርት እንደምናደርግ ገልፆልን ሲያበቃ፣ ጊዜው ሲደርስ ግን እኛው ራሳችን  የበቆሎ እጥረት ገጥሞን ከውጭ ገዝተን አረፍነው፡፡ (ጠ/ሚኒስትሩ በአንድ ስብሰባ ላይ “ኤክስፖርት; የሚለውን ቃል ስንቴ እንደሚጠሩት ማወቅ እፈልጋለሁ!) እናላችሁ--- መንግስት በቆሎ ኤክስፖርት እናደርጋለን የሚል ቃል ገና ከአፉ እንደወጣው፤ “ይሄ ነገር ከምር ነው?; ብንለው ኖሮ፣ “ሰው እኮ እውነት ይመስለዋል” ይለንና ከአጉል ጉጉት እንድን ነበር፡፡  
ከሦስት ዓመት በፊት አንድ ትልቅ የመንግስት ባለስልጣን በሙስና ዙሪያ ለሚዲያ በሰጡት ቃለምልልስ፤ “አገሩን የሚወድ ሰው፣ የአገሩን ሃብት በሙስና አይዘርፍም!” የሚል ለጥቅስ የሚበቃ አባባል ተናግረው ነበር፡፡ ብዙም ሳይቆዩ ግን እሳቸውም በከፍተኛ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ዘብጥያ ወረዱ፡፡ አሁን እንግዲህ ሰውየው ዋሹን ብለን ሃጢያታቸውን ልናበዛባቸው ነው አይደል? ጥፋቱ ግን የሳቸው ሳይሆን የጋዜጠኞቹ ነው፡፡ አጥብቀው አልጠየቋቸውም እንጂ “የተናገሩትን ከልብዎ ያምኑበታል?” ቢባሉ ኖሮ፣ በእርግጠኝነት፤ “ሰው እኮ እውነት ይመስለዋል” ሲሉ እቅጩን በነገሯቸው ነበር፡፡
አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች “የምንታገለው - የምንታሰረው… የምንሰደደው… የምንሞተው… የኢትዮጵያን ህዝብ ነፃ ለማውጣትና አገሪቱን በዲሞክራሲ ለማንበሽበሽ ነው” ሲሉ አልሰማችሁም? ያውም እስኪሰለቻችሁ ነዋ! ይሄን ባሉ ማግስት ግን ለፓርቲ ስልጣን ሲራኮቱና አገር እስኪታዘባቸው ድረስ እርስ በርስ ሲወነጃጀሉ አይተናቸዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ዋሽተውናል ብለን ልንወቅሳቸው አንችልም፡፡ ለምን ቢሉ? አልጠየቅናቸውማ፡፡ “የምንታገለው የኢትዮጵያን ህዝብ ነፃ ለማውጣትና አገሪቱን በዲሞክራሲ ለማንበሽበሽ ነው” ያላችሁት ከምራችሁ ነው ወይ ---- ቢባሉ ኖሮ፤“ሰው እኮ እውነት ይመስለዋል!” ብለው ይገላግሉን ነበር፡፡
 በሥራ ባህርያቸው የተነሳ ስለ ሴት ልጅ እኩልነት፣ ሴትን ልጅ ማስተማርና በኢኮኖሚ ማብቃት ስላለው ፋይዳ፣ በየመድረኩና በየሚዲያው ሲደሰኩሩ የምንሰማቸው ባለ ብዙ ድግሪ ሃላፊዎችና ዳይሬክተሮች ደግሞ አሉላችሁ፡፡ እኒህ ሃላፊዎች ቤት ሲገቡ ሚስቶቻቸውን በመጨቆንና ረግጦ በመግዛት የሚወዳደራቸው የለም (ሻምፒዮን በሏቸው!) እንዲህ ያሉት ወንዶች አጥብቆ ጠያቂ እያጡ ነው እንጂ ከመድረክ እንደወረዱ የሚጠይቃቸው ቢያገኙ እኮ ስለ ሴቶች መብት መከበር የተናገሩትን ሁሉ …”ሰው እኮ እውነት ይመስለዋል!” ብለው ኩም ያደርጉት ነበር፡፡
ህብረተሰቡ በአገሩ ምርት እንዲኮራ በየመድረኩ የካድሬ ዓይነት ቅስቀሳ የሚዳዳቸው፣ አስመሳዮችን ታዝባችሁልኛል? አብዛኞቹ እኮ በአውሮፓ ምርት ነው የሚኮሩት፡፡ እናም----መድረክ ላይ ሲቀሰቅሱ እንኳን በውጭ አገራት  አልባሳትና ጫማ አጊጠው ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ብዙ ጊዜ ለሰላ ትችትና ነቀፋ ይጋለጣሉ፡፡ ሆኖም ደህና ጠያቂ ጠጋ ብሎ፤“በአገራችን ምርት እንኩራ! ስትሉ ከልባችሁ ነው?; ቢላቸው፤በእርግጠኝነት፤ “ሰው እኮ እውነት ይመስለዋል” ይሉ ነበር፡፡
“የኢትዮጵያን ሲኒማ በአንድ ደረጃ ከፍ ያደረገ አዲስ የአማርኛ ፊልም” የሚል ማስታወቂያ ሰምተን “ጉዳቸውን እናይላቸዋለን” እንልና በእልህ ወደ ፊልም ቤት እናመራለን፡፡ እንደፈራነውም በፊልሙ “ቀሽምነት” እርር ድብን ብለን ገና ከማለቁ በፊት አቋርጠን እንወጣለን፡፡ ግን እኮ ከሁሉ አስቀድመን የፊልሙን ባለቤቶች፤“በማስታወቂያው ላይ የምትሉትን አምናችሁበት ነው?” ብለን ብንጠይቃቸው፤ “ሰው እኮ እውነት ይመስለዋል” በማለት ከድካምና ከብሽቀት ያድኑን ነበር፡፡
አንዳንድ የዳያስፖራ ኢንቨስተሮች ደግሞ አገር ውስጥ እንደገቡ፣ ለየሚዲያው በሚሰጡት ኢንተርቪው፤በአገራቸው ኢንቨስት ለማድረግ የተነሳሱት ለትርፍ ሳይሆን ሳይማር ላስተማራቸው ወገናቸው፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ውለታውን ለመመለስ በማሰብ እንደሆነ ይደሰኩራሉ፡፡ ከአንድ ከሁለት ዓመት በኋላ ግን ሠራተኞቻቸው በአስተዳደር በደል እንዲሁም በቂ ደሞዝና ጥቅማጥቅም በመከልከል ፍርድ ቤት ገትረዋቸው ይታያሉ፡፡ እኛም በአንዳንድ ቃል አባይ የዳያስፖራ ኢንቬስተሮች እናዝናለን፡፡ ከዚህ ሁሉ ግን ኢንተርቪው ሲሰጡ፤“ኢንቨስት ያደረጋችሁት እውነት ሳይማር ላስተማራችሁ ወገናችሁ የሥራ ዕድል በመፍጠር ውለታውን ለመመለስ  ነው?” ተብለው ቢጠየቁ፤“ሰው እኮ እውነት ይመስለዋል” የሚል መልስ ይሰጡ ነበር፡፡
እናላችሁ…ከመንግስት ጋር በሉት ከግል ባለሃብቶች፣ ከኪነጥበብ ባለሙያዎች ጋር በሉት ከፖለቲከኞች ወዘተ መግባባት ያቃተን፣ እያንዳንዱ ንግግር ከጀርባው ወይም ከውስጡ ያዘለውን “ሰው እኮ እውነት ይመስለዋል” የሚል ቅኔያዊ መልዕክት እየዘነጋን ነው፡፡ ስለዚህም ሁልጊዜ ከአንድ  መልካምና ተስፋ ሰጪ ንግግር በኋላ፣ “ሰው እኮ እውነት ይመስለዋል” የሚል ያልተነገረ ግን እንደተነገረ መቆጠር ያለበት መልዕክት መኖሩን ልብ እንበል!!
በመጨረሻ አንድ ጥያቄ አለኝ፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር ችሎ፣የአገልግሎት አሰጣጥ ጉድለቶችን በዝምታ አልፎ፣ለዓመታት በታክሲ ወረፋ ተሰቃይቶ፣የመንግስት ሚዲያ በገዛ ሬዲዮና ቴሌቪዥኑ የሚልኩበትን ያፈጠጠ ፕሮፓጋንዳ---የካድሬዎችን ቅዠት ሰምቶ---ያለምሬት ለአምላኩ ብቻ እየጸለየ የሚኖር ቻይና ታጋሽ ህዝብን የሚሸልም የውጭ ድርጅት እንዴት የለም? (መኖርማ አለበት!!) የለም ከተባለም ደግሞ በቃ ሰሞኑን ለኢትዮ ቴሌኮም የሸለመው የአውሮፓ ድርጅት፣ እኛንም ይሸልመን - ለታጋሽነታችን!! (ቴሌን ጭምር እኮ ነው ችለን የምንኖረው!)  

Read 6275 times