Saturday, 31 October 2015 09:36

ባተሌው

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(12 votes)

     የጥበብ ካራማን ለመካደም ካቀረቀረ ሰዓታት ነጉደዋል፡፡ እድፍ ያጎፈረውን ሪዙን በስለታም ጥፍሮቹ ቆፈር ቆፈር አደረገና ማውጠንጠኑን ቀጠለ። ከባተሌ አእምሮ የሚቀዳን ኑዛዜን በባዕድነት ከዳር ቆሞ ለመለፈፍ ወገቡን ሸብ አድርጓል። ሐሳብ ነጥፎበት እየተንገላታ ነው። ሐሳብ ማመንጪያ ይሆነው ዘንድ ሲጋራውን ለኮሰ። ብዕሩ ግን ሊቃናለት አልቻለም። ትንሽ መስመር እንደሄደ ቆም ይላል። ከእዚህ ቀደም የእርሱ ያልሆነውን አቋም ለመጻፍ መዳዳቱ ነው ፈተናውን ያበዛበት። ምን ይጻፍ። ደሞስ ስለ ባተሌ ምን ይጻፋል። የሚያውቀውን ሴጣን እንዴት ይሸንቁጠው። መጣጥፉን በትግል እንዲህ ብሎ ጀመረ፡-
****
ጥበብ ከባተሌ ጋር ኖራ አታውቅም፤ ባተሌ ፀሐፊ የጥበብን ጭን ለመሞቅ የሚያስችል የአንበሳ ልብን አልታደለም፤የአጎጥጓጤዎቿን ቆብ ለማፍተልተል ጣቶቹ ይሰንፉበታል፤ ስስ ከንፈሯን ሊጎርስ ሲንደረደር ልጋጉ ድንቅፍቅፍ ያደርገዋል፤ ገና በሩቁ ከዓይኑ እንደገባች ወንድነቱ ይከዳዋል፡፡ ባተሌ ፀሐፊ ግጥሙ ዘማዊት ጥበብ ናት፡፡ ዘማዊት ጥበብ ስሜት ላበረረው ሁሉ ጭኗን  የምታጋራ ለጋስ ነች። ይኸው ቀዝቃዛ ጭኖቿ ላይ ተንተርሼ ለልቧ እንቶ ፈንቶ አፈቀላጤ ሆኜ እማስናለሁ፡፡
****
ከሰንበሌጥ የሚሳሳውን ግድግዳ እያሳበረ የሚመጣ ድምጽ ከመጣጥፉ አስተጎጓለው፡፡ ተጎራባቹ ላጤ ሴት፣ ሙዚቃ ዝግ አድርጎ መክፈት አይሆንላትም፡፡ ለስላሳ ዜማው የዶለዶመ ስሜቱን ለማሾል  ሲታገለው ይሰማዋል። ክንድ በማይሞላ ሽንጥ ልክ የተቀለሰችውን ጎጆውን ከላይ እስከታች በዓይኑ ደባበሳት፡፡ ምንም የረባ ዕቃ አይታይም። የተከፈተ ድስት፣ወለሉ ላይ በብተና የተዘሩ ካልሲዎች፣ እኩሌታው የተሰነጠቀ ክብ መስታወት፣ባልዲ ውስጥ የተዘፈዘፉ ሸሚዞች፣ምስቅልቅል ያለ ሻንጣ… የቤቷን አስቀያሚነት አለቅጥ አጋነውታል። በእዚህ ሰዓት ስለጽዳት ማሰብ ቅንጦት ነው፡- ለባተሌው፡፡
ሥራውን ከለቀቀ ድፍን አንድ ወሩ ነው። ጠዋት አፉ ላይ ኩርማን ዳቦ ጣል አድርጎ ሲጭር ይውላል፡፡ ለምን እንደሚጭር ግን ለራሱ ገብቶት አያውቅም፡፡ ሲለው ሥጋው ይሰለጥንበታል፡፡ በለስ ሲቀናው ደግሞ በነፍሱ ቅኝ ይገዛል፡፡ ከእዚህ ድብታ፣ ከእዚህ እሳትና ውኃ ጨዋታ ለመንቃት መውተረተር ከጀመረ ሰነባበተ፡፡ ድሮ ድሮ፣ የእርጥባንን እርዳታ ሳይሻ ጥበብን ሲከውን እንደመተንፈስ ነበር፡፡ ሲውል ሲያድር ግን ነገሩ ሁሉ ተገለባበጠ፡፡ ሥጋው ሲቆራመድ ምናቡ ከዳው፡፡ ሆድ ኦና ሆኖ መጠበብ የሚሉት ጨዋታ አልጥም አለው፡፡ ቀፈት ሲወጠር ምናብ ይፋፋል ከሚሉት ወገን ነው፡፡ ለመጠበብ ለሥጋ መባተል ግድ ሆነበት፡፡ ግን አልቻለም፡፡ ቅለቱ፣ መዝናናቱ ሁሉ እንደጉም በነነበት፡፡ ማስታወሻ ደብተሩ ላይ እንደተደፋ፣ አንዲት መስመር ቅኔን ለማፍልቅ ምጥ እንደሆነበት ጀምበር ትገባለች፡፡
የተለቀቀው ሙዚቃ አሁንም ዝግ አላለም፡፡ ላጤዋ ሴት አብራ ማዜም ጀመረች፡፡
ደሞ እንደወንዶቹ ዘራፍ ማለት ልልመድ
ወተት ብቻ እኮ ነው መገፋት የሚወድ፣
አትዘባበቱ ቀን ጣለው ብላችሁ
ፊታችሁ ቆሞ  ታገኙታላችሁ፣
ባተሌውና ላጤዋ ተጎራባችነታቸው በቋፍ ነው፡፡ በረባው ባልረባው ይቆራቆሳሉ፡፡ ለግሳጼ አንደበቱን አላወሰ፡-
”እህት……..አልበዛም……”
 ”ኡኡኡኡኡ…ድንቄም…እኛም አላልንም”
”ምን ማለት ነው.... ”
”እምቡላውን ግፎ ሲያብድ የሚያድረው ማን ሆነና.............ኧረ ተውኝ ……..አመዳም እድሌ ነው እዚህ የሚያልከሰክሰኝ..”  የላጤዋ የእምባ ሳግ ከተለቀቀው ዜማ በላይ ጆሮውን አደነቆረው፡፡                         
ባተሌው በሐሳብ ወደትናንት ተወረወረ፡፡ በእርግጥም ትናንት ምሽት ከልክ በላይ ወሳስዶ ነበር፡፡ ሁሌም የቃል ፊትአውራሪነቱ ይከነክነዋል፡፡ ብዕሩን ከወረቀት ጋር በሚያወዳጅበት ቅጽበት ደርሶ ብጹዕ መሆን ይቃጠዋል፡፡ እንደ ፈሪሳዊያን በፊደል በቃል የሚታበይ ግብዝ መሆኑን የሚያውቀው ግን እንዲህ እንዳሁኑ ማልዶ ነው፡፡
የተኛበት ፍራሽ አለቀጥ ቀፈፈው፡፡ ማምለጫ የለም። ምርጫው ከአስቀያሚው እውነታ ጋር መጋፈጥ ነው። መዳፉ ላይ የጨበጣቸውን ወረቀቶች በንዴት ወለሉ ላይ በተናቸው፡፡
“ከመጻፍ በፊት ማንበብ ይቅደም፡፡” በውስጡ መፈክር ቢጤ አልጎመጎመና ጸጸቱን ማባረሪያ ይሆነው ዘንድ አንዱን ሽንጣም መጽሐፍ አፈፍ አድርጎ አነሳ፡፡ ዓይኑን በሽንጣሙ መጽሓፍ ገጾች ዙሪያ ገባ ላይ ማንከራተት ጀመረ። በመጽሐፉ ሆድ ዕቃ ላይ የተነጠፉት የቃላት መንጋ ፌዝ ሰላም አልሰጥህ እያለ ተፈታተነው። በተለይ በተለይ የምሳሌው ተሳልቆ ተጋኖበታል።
ሁለት የቡዲሂስት መነኩሴዎች ለመንፈሳዊ ጉዞ ማልደው እየገሰገሱ ነው፤ጥቂት ኪሎሜትሮችን ፈቀቅ እንዳሉ ከመንገዳቸው ላይ አጓጉል አሳቻ ሥፍራ አጋጠማቸው፤አሳቻውን ሥፍራ እንደ ደሴት የከበበ ረግረግ አለ፡፡ ለመሻገር እየተንደረደሩ ባለበት ቅጽበት አንዲት መልከመልካም ኮረዳ እርዳታቸውን ለመጠየቅ ቀረበቻቸው፤
”እኔ ፈጽሞ ይህንን አልሞክረውም፤ሃይማኖቴ አይፈቅድልኝም፤ ሌላ የሚረዳሽ ሰው ፈልጊ” አለ፤ አንደኛው መነኩሴ፡፡
የሌላኛው መነኩሴ ምላሽ ግን ከባልንጀራው ጋር የማይገጥም ነበር፡፡
“ግድ የለም እኔ አሻግርሻለሁ፤ነይ……ነይ ከጀርባዬ ላይ ተሳፈሪ” አለና ቀናኢ መስተንግዶውን ጋበዛት፡፡
ኮረዳዋ በቀናው መነኩሴ እርዳታ ረግረጉን ሥፍራ ተሻገረች፡፡
ከሰዓታት ጉዞ በኋላ ኮረዳዋን ያልተሸከማት መነኩሴ፤ዝምታውን እንዲህ ብሎ ሰበረው፤
“ምነው ባልንጃራዬ? ኮረዳን መሸከም ውግዝ መሆኑን ዘንግተኽው ነው? እኔ እኮ ለሃይማኖታችን ክብር ብዬ ነው ከድርጊቱ የታቀብኩት” አለ ፌዝ በተሞላ ገጽታ፡፡
ለኮረዳዋ ቀና ትብብር ያደረገው መነኩሴ ምላሽ ግን ያልተጠበቀ ሆነ፤
“ወዳጄ እኔ ኮረዳዋን የተሸከምኳት ከሰዓታት በፊት ነው፤ አንተ ግን እስካሁኗ ቅጽበት ድረስ ተሸክመሃት አበሳህን ትቆጥራለህ” ብሎ ተሳለቀበት፡፡ላጤዋ በለኮሰችበት ትናንትነት የአሁን ቅጽበትን መዳመጡን ሲያስብ ልግመኛው መነኩሴ መንትያው ሆነበት። ጠቢቡ መነኩሴ ከባልንጀራው ላይ ያሰወነጨፈው ስላቅ ከወስጡ ዘልቆ ሲያመው ተሰማው፡፡ ራሱን በራሱ ለመፈጣጠም ሲያወጣ ሲያወርድ ቤቱ ታዛ ላይ በማንአለብኝነት የተንጠለጠለች ገመድ ድንገት ውል አለችበት። ማን እንደአጠመዳት ሊነገረው የደፈረ ባልንጀራ አላገኘም።የሰናፍጭ ቅንጣት የምታክል ድፍረት ቢኖርህ ኖሮ እስካሁን አትዘገየም ነበር። ፍጠን ፍጠን።የሚል ሹክሽክታ በደመነፍሱ ጉሮኖ ሲስተጋባ ተሰማው። ሽንጣሙን መጽሓፍ ወደ ጎን ገፋ አድርጎ ጎኑን ካሳረፈበት የጥጥ ፍራሽ ላይ እምር ብሎ ተነሳ እና ወደ ገመዷ በረረ፡፡
ላለፉት ቀናት ስታበረግገው የነበረችው ገመድ ግን ከስፍራዋ ተፈናቅላለች። የሰናፍጭ ቅንጣት የምታክለውን ወኔውን ሰለላት፡፡ ከገመደ ጋር አብራ የውኃ ሽታ ሆናለች፡፡ፊቱን ወደ መጣበት አቅጣጫ መለሰ አደረገ፡፡ ከዳጃፉ ላይ ፍልቅልቅ ኩታራ ነግሶበታል፡፡ የጨቅላው መዝናናት በውስጡ ያቆጠቆጠውን ጨለምተኝነት ሲደፍቀው ይሰማዋል፡፡ በጨቅላው መዘዝ ስለብሩህነት፣ ስለ ቅለት ብዕሩን ከወረቀት ሊወዳጅ ወደ ጎጆው አቀና፡፡

Read 4423 times