Saturday, 07 November 2015 09:25

ለዳገት የጫንከው ሜዳ ላይ እንዳይደክም፣ ማልዶ መነሳት

Written by 
Rate this item
(14 votes)

     ከኤዞፕ ተረቶች አንዱ እንዲህ ይላል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ የሀብታም ጌታ አገልጋይ፤ ከቤት ጠፍቶ ወደ ዱር ይሄዳል። እዚያም አንድ ባዶ ዋሻ ያገኝና እዚያው ለመኖር ይወስናል፡፡ ሆኖም ገና አንድም ቀን ሳያድር የዚሁ ዋሻ ባለቤት የሆነው አያ አንበሶ ከች ይላል፡፡ አገልጋዩ ሰው በጣመ ደነገጠ፡፡ “አለቀልኝ!” ብሎ ተስፋ በመቁረጥ ካሁን አሁን ዘሎ ደቆሰኝ እያለ ይጠባበቅ ጀመር፡፡ ሆኖ አያ አንበሶ ዘሎ ሰውዬው ላይ ሳይወጣ ቀረ፡፡ ሰውዬው ደርቆ ተገርሞ ያስተውለዋል፡፡
ይልቁንም ማጥቃቱን ትቶ ያባበጠ መዳፉን ወደ አየር ከፍ አድርጐ እያቃሰተ አሳየው። ሰውዬው ትኩር ብሎ ሲያይ አንዳች የሚያክል እሾክ ተሰቅስቆበታል፡፡ ስለዚህ ቀስ ብሎ እየሳበ ነቀለለት፡፡ የቆሰለውንም አሠረለት፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቁስሉ ሙሉ በሙሉ ዳነለት፡፡
አያ አንበሶ ምሥጋናው ወሰን የሌለው ሆነ፡፡ ስለሆነም ሰውዬውን ጓደኛ አደረገው፡፡ ዋሻውም ቤታቸው ሆነ፡፡
ጊዜ እየረዘመ ሲሄድ ግን ሰውዬው ወደ ዘመዶቹ መሄድ ፈለገ፡፡ አያ አንበሶን ተሰናብቶ ወደናፈቃቸው ወዳጅ ዘመዶቹ ሄደ፡፡ ከሰው ጋር ሲቀላቀል ግን አንዳንድ ሰዎች ከጌታው ጠፍቶ መሄዱን አስታውሰው እጁን በገመድ አስረው ወስደው ለጌታው አስረከቡት፡፡
ጌታውም ለሌሎች መቀመጣጫ ይሆን ዘንድ በአደባባይ የትርዒት ሸንጐ ላይ ለአውሬዎች እንዲጣልና ህዝብ እንዲያየው አዘዘ፡፡ በዚያ የፍልሚያ ቀን አውሬዎች ሰውዬው ላይ ተለቀቁበት፡፡ ከነዚህ አውሬዎች መካከል አንድ ግዙፍ አንበሳ ይታያል፡፡ ያ አገልጋይ ሜዳው ላይ ተጥሎባቸዋል፡፡
ግዙፉ አንበሳ ቀድሞ ወደ ሰውዬው አመራ፡፡ “ደቆሰው በቃ!” ሰባበረው በቃ!” ይላል ህዝቡ፡፡
የሆነው ግን የተገላቢጦሽ ነው፡፡ አንበሳው ሰውዬው እግር ሥር አጐንብሶ በፍፁም አክብሮትና ፍቅር ይተሻሸው ገባ! ደስተኝነቱ ፊቱ ይ ያበራል!ይህ አንበሳ የጥንቱ የዋሻ ጓደኛው አያ አንበሶ ነው!
ተመልካቹ ሁሉ፤ “ሰውዬው ምህረት ሊደረግለት ይገባል!” እያለ ጮኸ!
የከተማው ከንቲባ ከአውሬ የዚህ ዓይነት ምሥጋናና ደግነት በማየታቸው ተደስተው፣
“ሁለቱም በነፃ ይለቀቁ” ብለው አወጁ!
*   *   *
ከአንበሳ መዳፍ እሾክ የመንቀል ያህል ደግነት ለመሥራት መጣር ትምህርትነቱ ኃያል ነው፡፡ አንበሳና ሰው የመቀራረብና አብሮ የመኖር ደረጃ ሲደርስ፣ ሰውና ሰውማ ማንም ይሁን ማን ተስማምቶ መኖር ሊያቅተው አይገባም፡፡ መቻቻል በቁም ትርጉሙ ስንወስደው የማይስማሙ ወይም የሚቃረኑ ኃይሎች፣ ቡድኖች ወይም ግለሰቦች መኖራቸውን ያሳያል፡፡ ምንም ያህል ተፃራሪ ቢሆኑ የሀገር ጉዳይን
አማክለው ካዩት፤ የጋራ መድረክ አያጡም፡፡ ባለሙያውና ፖለቲከኛው የጋራ ቦታ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ፖለቲከኛውና ፖለቲከኛው (የተለያየ ፓርቲ አባል ቢሆኑም) የጋራ መቻቻያ ሊኖራቸው ግድ ነው፡፡ ከመቀራረብ መደፋፈር መወለድ የለበትም፡፡ ተባብሮ አብሮ መሥራት እንጂ ምሁሩን ማግለል ሊያስከትል የሚችለውን ችግር ግምት ውስጥ ማስገባት በዓለም ታሪክ የታዩትን ታላላቅ ስህተቶች
ከመፈፀም ያድነናል! ለጠብ አለመቸኮል ተገቢ ነው፡፡ “ወዳጅና ወዳጅ የተጣሉ እንደሆን መታረቅም አይቀር፣ እንደ ጥንቱም አይሆን” የሚለውን ግጥምም አለመዘንጋት ነው!
ገሀድ ዕውነት በአደባባይ ሲወራ ለመስማት አብዛኛው ህዝብ ይናፍቃል፡፡ ብዙ ከመፈንደቅና ያለልክ የሀዘን ማቅ ከመልበስ ይሰውረን!
አንዳንድ ምሁራን የለውጥ እርምጃ (ተሃድሶ) (Reformism) ወደ አብዮት ያመራል ይላሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ “አብዮት እንዳይፈጠር ታኮ ይሆናል” ይላሉ፡፡ እንደየአገሩ ልዩ ባህሪ ግብዓቶቹ ወሳኝነት አላቸው የሚሉት ወገኖች ደግሞ እንደየሁኔታው ሁለቱን አካሄዶች
ያሞግሷቸዋል ወይም ይሽሯቸዋል፡፡ ዞሮ ዞሮ ፀሐፊው ሀንቲንግተን እንደሚለው፤ ከተሀድሶ እርምጃ ጋር የሚያያይዙት የአብዮት ችግሮች አንድም የምሁር መገለል፣ አንድም የገበሬ መከፋት ናቸው፡፡ በሀገራችን የአቀባባይ ከበርቴዎችና የቢሮክራሲ ደላሎች አደጋ ብዙ ሊሸሸግ ቢሞከርም ዛሬ አደባባይ መውጣቱ ዘግይተንም ቢሆን ዐይናችንን መግለጣችንን ይጠቁማል፡፡ እንግዲህ ኔትዎርኮቹን ሁሉ መፈተሽ ነው
ቀሪው ጐዳና! ስብሰባዎቻችን የተሞሉት “ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮህ” በሚለው ስላቅ ከሆነ መንፈሳቸው አስቂኝ ይሆናል፡፡ ሙሰኛው የፀረ ሙስና ተናጋሪ ሲሆን ምፀቱ አስገራሚ ነው፡፡ የትላንቱን ታሪክ ከዛሬው ሁኔታ የሚያላትመው ደስኳሪ ከውይይት ይልቅ ድንፋታን የሙጥኝ ሲል፤ “ይቺ አገር ወዴት እየሄደች ነው?” ብሎ መሸሞር ግድ ይሆናል፡፡ ሀቅ አይነቀን፡፡ ግልጽነት አይመመን፡፡ ወገናዊነትን፣
ዘረኝነትን፣ ፅንፈኝነትን፣ ትምክህተኝነትን እናስወግድ ካልን ከልብ እናስወግድ!
በዱሮው ዘመን፤ “ጉዟችን ረዥም፣ ትግላችን መራራ” ይባል ነበር፡፡ መንፈሱ ለየቅል ቢሆንም፤ የአሁኑም ዘመን ትግል መራራና ረዥም መሆኑ አልቀረም፡፡ “ለዳገት የጫንከው ሜዳ ላይ እንዳይደክም፣ ማልዶ መነሳት!” የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ 

Read 6758 times