Saturday, 07 November 2015 10:09

38ኛው ሴካፋ ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

    38ኛው የምስራቅ እና መካከለኛው የእግር ኳስ ሻምፒዮና ‹‹ሴካፋ ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ›› በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ህዳር 11 እንደሚጀመር ይጠበቃል፡፡ ከሴካፋ ምክር ቤት አባል አገራት ኬንያ፤ ኡጋንዳ፤ ታንዛኒያ፤ ዛንዚባር፤ ሱዳን፤ ደቡብ ሱዳን፤ ጅቡቲ፤ ሶማሊያ፤ ሩዋንዳ እና ብሩንዲ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ኤርትራ ስለሚኖራት ተሳትፎ በይፋ የተገለፀ ነገር ባይኖርም በቀነ ገደቡ ምላሽ ባለመስጠቷ ተሳትፏዋ መሰረዙን ዘገባዎች አውስተዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያያይዞ በ2013 እኤአ ላይ ናይሮቢ ባዘጋጀችው ውድድር ላይ 24 የኤርትራ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች መጥፋታቸው ታውሶ፤ በቅርቡ የኤርትራ ቡድን ዋና አሰልጣኝ እና 10 ተጨዋቾች በዓለም ዋንጫ ከቦትስዋና ጋር ከነበራቸው ቅድመ ማጣርያ በኋላ ከሆቴል በመጥፋታቸው ሴካፋን በከፍተኛ ደረጃ አሳስቦታል፡፡ ከተሳትፎ ለመታገዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል ተብሏል፡፡  
የምክር ቤቱ ዋና ፀሃፊ ኒኮላስ ሙንሶኜ በተጋባዠነት ለመሳተፍ የማላዊ እግር ኳስ ፌደሬሽን ብቻ  በደብዳቤ ሴካፋን  እንደጠየቀ ገልፀዋል፡፡ ከደቡብ አፍሪካ ዚምባቡዌ እና ዛምቢያ ከምዕራብ አፍሪካ አይቬሪኮስት  ለመሳተፍ ስላላቸው ፍላጎት  ግን ለማብራራት አልተቻለም፡፡
ሻምፒዮናውን ባህር ዳር ስታድዬም እንደሚስተናገድ ተገልፆ የነበረ ቢሆንም የሴካፋ ምክር ቤት በአዲስ አበባ ስታድዬም እንዲካሄድ መወሰኑን የገለፁት ዋና ፀሃፊው ለተቀላጠፈ መስተንግዶ  እንደሆነ ተናግረዋል። በተያያዘ    በ38ኛው የሴካፋ ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ ዋዜማ የሴካፋ ምክር ቤት አዲስ ፕሬዝዳንት ምርጫ በሚካሄድ ኮንግረስ ይወሰናል፡፡ ምክር ቤቱን ላለፉት 8 ዓመታት  የመሩት የታንዛኒያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ሊዮዳር ቴንጋ ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ወስነዋል፡፡ የኢትዮጰያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት የሆኑት ጁነዲን ባሻ፤ የቀድሞው የኡጋንዳ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ላውረንስ ሙሉዊንዳ፤ የሩዋንዳ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት  ቪንሰንት ናዛሚውታ እና የሱዳን እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ካህማል በምርጫው  ይፎካካራሉ፡፡
በሌላ በኩል ዋልያዎቹ ለሴካፋ እና ለአለም ዋንጫ ማጣሪያ ዝግጅት ገብተዋል፡፡ ዋና አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ 23 ተጨዋቾችን ጠርተዋል፡፡፡ ሁሉም በአገር ውስጥ ክለቦች የሚጫወቱ ናቸው። ዋልያዎቹ የዛሬ ሳምንት  በዓለም ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ መጀመርያ ጨዋታ በአዲስ አበባ ኮንጎ ብራዛቪልን የሚያስተናግዱ ይሆናል፡፡ የመልስ ጨዋታው ከ3 ቀናት በኋላ ነው፡፡
ፊፋ ለ2015 የሰጠው 750ሺ ዶላር
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር በየዓመቱ ለአባል አገራቱ በሚሰጠው የፋይናንሻል እገዛ ፕሮግራም ለ2015 እኤአ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን 750ሺ ዶላር ተበርክቶለታል፡፡ በ2014 እኤአ ላይ ከነበረው ድጋፍ በ200ሺ ዶላር ብልጫ የታየበት ነው፡፡ ዘንድሮ ለፉትሳል፤ ቢች ሶከር እና ለመሰረተልማት ግንባታ ምንም የበጀት ድጋፍ ያላደረገው ፊፋ ባለፈው ዓመት ለመሰረተ ልማት 2000 ዶላር ለግሶ የነበረ ሲሆን ቦነስ  የሰጠው ደግሞ 200ሺ ዶላር ነበረ፡፡
በፊፋ የድጋፍ በጀቱ ዝርዝር 2015 \2014
ለወጣት እግር ኳስ
    154 860 ዶላር \23500 ዶላር
ለወንዶች ውድድሮች 104000 \30500
ለሴቶች እግር ኳስ 141600 \45500
ለቴክኒካል እድገት ስራዎች
    56000 \57200
ለዳኞች 37000 \31000
ለህክምና 12540 \3250
ለእቅድና አስተዳደር 118000 \43000
ለውድድሮች መስተንግዶ
    52000 \6230
ለማርኬቲንግ እና ኮምኒኬሽን
    36000\ 7820
ለሌሎች 3800

Read 4829 times