Saturday, 07 November 2015 10:19

ከገዳም ህይወት ወደ ሞዴሊንግ ሙያ የገባችው ኢትዮጵያዊት

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(19 votes)

በ1974 ዓ.ም ወላይታ ሶዶ ውስጥ ነውየተወለደችው፡፡ “ፎኮላሬ ሙቭመንት”በተባለ የካቶሊክ ድርጅት ውስጥ
ገዳማዊት ሆና ማደጓን ትናገራለች ።በአፍሪካ አገራት ተምራለች፡፡ በአሁኑወቅት የፋሽን ከተማ በሆነችው የጣሊያኗ
ሮም ኑሮዋን የመሰረተችው ሞዴልና ዲዛይነር ሰናይት ማሪዮ፣ በቅርቡ ወደአገሯ በመጣች ወቅት ከአዲስ አድማስ
ጋዜጠኛዋ ናፍቆት ዮሴፍ ጋር ተገናኝታበህይወቷ እንዲሁም በሞዴሊንግናዲዛይኒንግ ሙያዋ ዙሪያ በስፋት
አውግታለች፡፡ ለመሆኑ ከገዳም ህይወትወጥታ እንዴት ወደ ሞዴሊንግ ሙያ ገባች?
የ33 ዓመቷ ሞዴልና ዲዛይነር፣ ሁሉንምዘና ብላ ትተርካለች፡፡


• በወላይታ የፋሽን ትርኢት ለማቅረብ እየተዘጋጀች ነው
• የድንጉዛንና የጀርመን ባንዲራ መመሳሰል ጥያቄ አስነስቷል
• ከዕውቅ የጣሊያን ዲዛይነር ጋር ለመስራት ተስማምታለች


እንዴት ነው ወደ ጣሊያን የሄድሽው?
ወደ ጣሊያን የሄድኩት በትዳር ምክንያት ነው፤ ባል አግብቼ፡፡ ባለቤቴ ጣሊያናዊ ነው፡፡
መቼ ነው ያገባሽው?
በፈረንጆቹ በ2009 ዓ.ም ነው የተጋባነው፡፡ ሰርጋችን እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከባሌና ከአምስት ዓመት ወንድ ልጄ ጋር በጣሊያን ነው የምንኖረው፡፡
ወደ ኋላ ልመልስሽና የልጅነት ህይወትሽን አጫውቺኝ -----
በልጅነቴ ወላይታ ሶዶ ከተማ ውስጥ ከካቶሊኮች ጋር ነው ያደግሁት፤ገዳማዊ ነበርኩኝ፡፡ ከዚያ ነፃ የትምህርት እድል አግኝቼ ቋንቋ ለመማር ወደ ኬንያ ሄድኩኝ፡፡ በመቀጠል በኡጋንዳ ሶሲዮሎጂ ኤንድ ሶሻል አንትሮፖሎጂ ተማርኩኝ፡፡ በዚህ የትምህርት ዘርፍ ዲግሪዬን ካገኘሁ በኋላ ወደ ወላይታ ተመልሼ በግል ኮሌጆች ውስጥ ሶሲዮሎጂ ማስተማር ጀመርኩኝ፡፡ “Introduction to sociology” የተሰኘ ኮርስ በተለያዩ የጤና ተቋማት ውስጥ እሰጥ ነበር፡፡  አግብቼ ጣሊያን ከሄድኩ በኋላ ለማስተርስ መማር ጀምሬ ነበር፤ሆኖም መውለድም መጣ፤ ጣሊያንኛ ቋንቋም ከበደኝ፡፡ አንዳንድ ስራዎችን ለመስራት ብሞክርም አልቻልኩም፣አቋረጥኩት፤  ወደፊት ያቋረጥኩትን ለመማር አስቤአለሁ፡፡  
ለማስተርስ ምን ነበር ማጥናት የጀመርሽው? ሶሲዮሎጂ ነው ወይስ --?
ከሶሲዮሎጂ የተለየ ትምህርት ነበር የጀመርኩት። ጣሊያን እንደሄድኩኝ አንዳንድ የኢንተርንሽፕ ስራዎችን ከምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) ጋር እሰራ ስለነበር፣ ቀልቤ ወደ ግብርናው ተሳበና ጀመርኩኝ፤ግን ባልኩሽ ምክንያቶች ሳይመቸኝ ቀርቶ ተቋረጠ፡፡ ወደ ግብርናው ዘርፍ ቀልቤ የተሳበው አንደኛ የፋኦ ዋና ጽ/ቤት ሮም ስለሆነና ፋኦም በግብርና ዘርፍ ላይ የሚሰራ በመሆኑ ነው። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ አገራችን ግብርና መር ኢኮኖሚ የምትከተል በመሆኑ ነው፡፡ ትምህርቱን አጥንቼ አገሬ ላይ ብሰራበት ውጤታማ ልሆን እንደምችል አስቤ ነበር፡፡  ያቋረጥኩት ትምህርት “Science of Agriculture” ይባላል፡፡
ከአገርሽ ውጭ በአፍሪካና አውሮፓ የመኖር እድል ገጥሞሻል፡፡ በማታውቂው ባህል ውስጥ መኖር አልከበደሽም?
ኦ… እሱ በጣም አስቸጋሪ ነበር፡፡ ኬንያ የሄድኩት ገዳማዊት ሆኜ ነበር፡፡ እዛ እንደሄድኩኝ የገጠመኝን የባህል ግጭት (Cultural shock) ልነግርሽ አልችልም፤ፈተናው በጣም አስቸጋሪ ነበር። ጣሊያን ስሄድ ደግሞ የባሰ ሆነ፤ምኑንም መልመድ አልቻልኩም፡፡ እንደውም ኬንያ የነበረውን ጊዜ ማመስገን ጀመርኩኝ፡፡ ለምን ብትይ----ምንም ሌላ ባህል ቢሆንና ምግቡም የተለየ ቢሆን ቢያንስ አፍሪካዊ ስለሆንኩኝ … የቆዳዬ ቀለምም ከነሱ ጋር ስለሚመሳሰል ትንሽ ይሻል ነበር፡፡ ቀላል ነው ለማለት ሳይሆን ጣሊያን ከገጠመኝ በጣም ይሻላል፡፡ ጣሊያን በአብዛኛው ነጮች ናቸው፤ ሁሉም አንቺን ነው የሚያዩሽ፤በዚያ ላይ ቶሎ አይግባቡሽም፡፡
ኢትዮጵያዊነትሽን ሲያውቁ የተለየ ስሜት ያሳዩሽ ነበር ?
አዎ፤ እሱ እንዳለ ነው፡፡ የተለያየ ቦታ ለስራ ስሄድ፣ከየት ነሽ ሲሉኝ፣ ኢትዮጵያን ስጠራ፣ ጥሩ ስሜት አላይባቸውም ነበር፡፡ አንዳንዴ አውቀው የት ነው ኢትዮጵያ ይላሉ፤ግን በደንብ ከነሽንፈታቸው ያስታውሷታል፡፡ እኔ አልበሳጭም፡፡ ብቻ--- በባሌ ብርታት ሁሉንም ለመድኩት፡፡  ባለቤቴ በደንብ ይንከባከበኝ ነበር፡፡
ከባለቤትሽ ጋር እንዴት ነው የተዋወቃችሁት?
ባለቤቴ ኢትዮጵያን በደንብ ያውቃታል፤ለበርካታ አመታት በሥራ ተመላልሷል፡፡
ምን ዓይነት ሥራ?
ወላጅ አልባ ህፃናትን ይረዳና ያስተምር ነበር፡፡ ይህን የሚሰራው ደግሞ እኔ በተወለድኩባት ደቡብ አካባቢ ነው፡፡ ያደግሁበትን ሁኔታ ስለሚያውቅ በደንብ ይንከባከበኝ ነበር፡፡ ብቸኝነት እንዳይሰማኝ የተቻለውን ሁሉ ያደርግ ነበር፡፡ እንደዛም ሆኖ ግን ለመልመድ በርካታ ጊዜ ወስዶብኛል፡፡ ሰው ቤቱን ዘግቶ ነው የሚቀመጠው፣ ሰላም ካላልሽ ሰላም አይሉሽም፤ ሻይ ቡና እንጠጣ ብሎ ያንቺን በር የሚያንኳኳ የለም፤ህዝቡ ሲሮጥ ሲዋከብ ነው ውሎ የሚያድረው፡፡ እሱ ስራ ሲሄድ በር ቆልፌ፣ ብቻዬን አገሬንና ቤተሰቤን ስናፍቅ እውል ነበር፡፡ ቤት  ውስጥ ምግብ አብስዬ መመገብ እንኳን ትልቅ ፈተና ነው፡፡ ከማብሰያ እቃቸው ጋር መግባባት አቅቶኝ ብዙ ተሰቃይቻለሁ፡፡ እኔ ያደግሁት ወላይታ ሶዶ ነው፤ መካከለኛ ኑሮ ባለው ቤተሰብ፡፡ ምግብ የማበስለውም እንጨት እያነደድኩኝ ነበር፤ስለዚህ እዚያ ሄጄ ጦጣ ብሆን አይግረምሽ ---- (ረጅም ሳቅ!)
አሁን ግን ኑሮውንም ባህላቸውንም ለምደሽ----የአባትሽን ስም ሁሉ በባለቤትሽ ለውጠሻል----?
ብዙ ሰው የሚሸወድበት ነገር ቢኖር ይሄ ነው፡፡ በእርግጥ ማሪዮ የሚለው የጣሊያን ስም ነው ፤ግን እኔ የምጠራው በወላጅ አባቴ ስም ነው፡፡ አባቴ እዚያው ወላይታ ከጣሊያን ካቶሊኮች ጋር እየሰራ ስላደገ ስሙን ማሪዮ ብለው አወጡለት፡፡ የወላጅ አባቴ ስም ማሪዮ ነው፡፡ እኔ ዜግነቴንም ስሜንም አልቀየርኩም፤ የቀንም የሌሊትም ህልሜ አገሬ ናት፡፡ ባለቤቴ እራሱ እዚህ ያለው አካልሽ እንጂ መንፈስሽ አይደለም ይለኛል፡፡ ስሜም አልተቀየረም፤ ያው ሰናይት ነው። ላለፉት 10 ዓመታት በጣሊያን ብኖርም ዜግነቴን አልቀየርኩም፤መቀየርም አልፈልግም፡፡ እነሱም በዚህ የተነሳ የሆነ ስሜት አላቸው፡፡
ምን ዓይነት ስሜት?
ኢትዮጵያዊ ነኝ ካልሽ ቅድም እንደነገርኩሽ የት ነው ሁሉ ይሉሻል ግን ኢትዮጵያን መቼም አይረሷትም። ከባለቤቴ ጋር አንዳንድ ጊዜ ስንከራከር፣“አንቺ ለምንድነው ሽንፈት የማትወጂው? ሁሌ የበላይ ነኝ ብለሽ ትችይዋለሽ?” ይለኛል፡፡ በተለያየ ስራ ከጣሊያኖች ጋር ስንገናኝና ስንነጋገር፤ “እኛ ለመሆኑ---ምን አላችሁና ልንወስድባችሁ መጣን?” ይሉኛል። እኔም፤ “መቼም ውሃ ልትቀዱ አልመጣችሁ” እላቸዋለሁ፡፡ ምን ፈልገው ወደ አገራችን እንደመጡ እኛም እነሱም እናውቃለን፤ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙም አልከራከራቸውም፡፡
በመጨረሻ ያ ሁሉ ብቸኝነትና ቤት ውስጥ መዋል ቀርቶ አደባባይ በሚያውለው የሞዴሊንግ ሙያ ላይ ለመሰማራት በቅተሻል፡፡ ለመሆኑ እንዴት ወደዚህ ሙያ ገባሽ? በልጅነትሽ ሞዴል የመሆን ፍላጎት ነበረሽ?
ወደ ሞዴሊንግ የገባሁት በጣም በሚገርም አጋጣሚ ነው፡፡ እዚህም አዲስ አበባ እያለሁ ነው ስሜቱን በሰዎች ግፊት ያወቅሁት፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ወላይታ ሶዶ እንደጨረስኩኝ ሀዋሳ መምህራን ኮሌጅ ገብቼ ዲፕሎማዬን ከያዝኩ በኋላ እዛው ደቡብ ገጠር፣ ውሃና መብራት በሌለበት መንደር ውስጥ ለአንድ ዓመት ሰርቻለሁ፡፡ ከዚያ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማታ ማታ በግሌ ፍልስፍና መማር ጀመርኩኝ፡፡ ማታ ከክፍል ስወጣ፣ግማሽ መንገድ በእግሬ፣ ግማሽ መንገድ በአውቶቡስ ነበር የምሄደው፡፡ እና ያኔ መንገድ ላይ ሰዎች ያበሽቁኝ ነበር፡፡
ምን እያሉ?
 ለምሳሌ ፒያሳ ከሆንኩኝ ረጅም ስለሆንሽ እስኪ እይልን፤ለገሀር ስንት ቁጥር አውቶብስ ቆማለች ይሉኛል፡፡ አንዳንዶቹ እስኪ ሰማይ ቤት ስለኔ ምን ይወራል አዳምጭልኝ ሲሉኝ፤ ሌሎቹ ደግሞ ይህን ቁመት ለምን ታባክኝዋለሽ፣ለምን ሞዴል አትሆኚም? ይሉኝ ነበር፡፡ ይሄኔ ፍላጎት እያደረብኝ መጣ፡፡ ከዚያ ፕሮፌሽናል ያልሆነች ሞዴል ጓደኛ ነበረችኝ፤ ቀለል ቀለል ያሉ የሞዴል ስራዎችን ትሰራ ስለነበር ይሄን ነገር ለምን አብረን አንሰራም አልኳት። እሷም ሞዴሊንግ ኤጀንሲ አላቸው ከሚባሉ ሰዎች ጋር አገናኘችኝ፡፡ እነሱ ኢትዮጵያዊያን ናቸው ግን ኤጀንሲያቸው ሆላንድ ነው ያለው፡፡ በዚያን ጊዜ እዚያ አገር ሄዶ የመስራቱ እድል ጠባብ ነበር፡፡ አንደኛ ለሞዴሊንግ እንግዳ ነኝ አላውቀውም፤ሁለተኛ የኢኮኖሚ አቅሜ ለዚያ የሚያበቃ አልነበረም፤ ስለዚህ በመፃፃፍ ደረጃ ብቻ ቀረ፡፡ ፍላጎቱና ሀሳቡ ቢዳፈንም ግን ጠፍቶ አልጠፋም ነበር፡፡
ከዚያስ?
ከዚያማ ኬኒያ ለቋንቋ ትምህርት ሄጄ ነበር አላልኩሽም? በዚያን ሰዓት ያንን የተዳፈነ ፍላጎት የሚያነቃቃ ነገር መጣ፡፡ አንድ ቀን በኬንያ ናይሮቢ ከተማ ውስጥ አንድ ፓርክ ሳቋርጥ፣ የ“ኢማኒ ሞዴሊንግ ኤጀንሲ” ባለቤት ታዋቂ ሞዴልና የኤጀንሲው ማናጀር አይታ ጠራችኝና፤ ኢትዮጵያዊት ነሽ? ብላ ጠየቀችኝ፡፡ አዎ ስላት፣ የሁሉም አገር ሞዴሎች አሉኝ፤ ኢትዮጵያዊ ሞዴል ነበር የሚጎድለኝ፤ስለዚህ አብረሽኝ ስሪ አለችኝ፣ እኔም የመስራት ፍላጎት እንዳለኝ ነገርኳትና መስራት ጀመርን፡፡ እኔን በቀጥታ ወደ ሥራ አልነበረም ያስገባችኝ፤ ከማሰልጠን ነበር የጀመረችው። ምክንያቱም ፍላጎቱ እንጂ አረማመዱን፣ ዲሲፕሊኑን-----ምኑንም አላውቀውም ነበር። እውነት ለመናገር ብዙ ለፍታብኛለች፤ብዙ ተቸግራብኛለች። ለመጀመሪያ ጊዜ ከእርሷ ጋር ነው ስራም የጀመርኩት።
የመጀመሪያ ስራሽ ምን ነበር?
ስራ የጀመርኩት በራሷ ኤጀንሲ ውስጥ ነው። ፎቶዎቼን እየወሰደች እያስተዋወቀች እዚያው ናይሮቢ ውስጥ ስራ ጀመርኩኝ፡፡ ከዚያ የቋንቋ ትምህርቴን ጨርሼ ወደ ኢትዮጵያ ስመለስ፣ በዘርፉ የተደራጀና በጥሩ ሁኔታ የሚሰራ ኤጀንሲ በማጣቴ ስራውን መቀጠል አልቻልኩም፡፡ ወደ ጣሊያን ስሄድ በሶሲዮሎጂ ለመስራት በጣም ተቸገርኩኝ፡፡ የአፍሪካ ዲግሪ በመሆኑ ከእነሱ አገር ዲግሪ ጋር ለማመጣጠን እንደገና አንድ ዓመት መማር አለብሽ፤ብቻ ብዙ ፈተና አለው፡፡ እንደነገርኩሽ ቋንቋውም ሌላ ፈተና ሆነ። በዚህ ምክንያት በተማርኩበት ሶሲዮሎጂ ቀርቶ ሱቅ ውስጥ  ለመቀጠር እንኳን ቋንቋው ችግር ሆነ። በኋላ አሰብኩና ከብቸኝነቱም እንዲገላግለኝ፣ እንደ ሆቢም ይሆነኛል በማለት “ግላሞር” በተሰኘ ኤጀንሲ ውስጥ ለሞዴሊንግ ተመዘገብኩኝ፡፡ መስፈርቱን አሟላሁ፤ያ ማለት አካላዊ መስፈርቱን እንጂ ፕሮፌሽናል የሆነውን ነገር ብዙም አላውቀውም ነበር፡፡ እንደነገርኩሽ ኬንያ ኢማኒ አሰልጥናኛለች፤ ግን በቂ አልነበረም፤በተለይ “catwalk” የሚባለውን አረማመድ በደንብ አልችለውም ነበር፡፡ እናም ምንም ክፍያ አንከፍልሽም፤ ግን መስራት ትችያለሽ አሉኝ፡፡ ልምዱን እፈልገው ስለነበር ስራውን ሳላቅማማ ጀመርኩት፡፡
ከነሱ ጋር ስሰራ ሌሎች የራሳቸው ኤጀንሲ ያላቸው ሰዎች እይታ ውስጥ መግባት ጀመርኩኝ፡፡ ከዚያም አዲስ ዓመት ሲመጣ የሚወጡ ካሌንደሮች ላይ መስራት ጀመርኩ፡፡ በአብዛኛው የሰራሁት የካሌንደር ስራዎችን ነው፡፡ እኔ ሞዴሊንጉን ዘግይቼ ነው የጀመርኩት፡፡ እዚያ አገር ከልጅነትሽ ጀምረሽ ታዋቂ ሆነሽ ካልዘለቅሽ በስተቀር እድሜሽ ከ25 እያለፈ በሄደ ቁጥር ሥራው አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ይህን በማሰብ ሙያውን ለመቀጠል ምን ማድረግ አለብኝ አልኩና… ዲዛይኒንግ መማር ወሳኝ መሆኑን ተረዳሁ። ጣሊያን ውስጥ በበርካታ የፋሽን ትርኢቶች ላይ ብካፈልም የኢትዮጵያ አልባሳት በትርኢቱ ላይ ሲታዩ አላጋጠመኝም፤ ነገር ግን ጣሊያን ውስጥ ኢትዮጵያዊ ዲዛይነሮች እኮ አሉ፡፡ እናም ዲዛይኒንግ መማሬ እንደሚጠቅመኝ አሰብኩ።
የዲዛይኒንግ ትምህርቱን ተማርሽ ማለት ነው -?
 አሁን ሶስተኛ ዓመት ነኝ፤ ግን ስራውን ጀምሬዋለሁ። ከትውልድ አካባቢዬ ከወላይታ ልጀምር ብዬ የወላይታ ድንጉዛን በተለያየ መልኩ ለበጋ በሚመች ዓይነት እየሰራሁ እያስተዋወቅሁ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ወደ አገር ልብስ እየተሸጋገርኩ ነው፡፡ የእኛ አገር ልብስ እኮ መቶ በመቶ ኮተን (ጥጥ) ስለሆነ ለሙቀትም ለብርድም ጊዜ አመቺ ነው፡፡ የሌላውን አገር ልብስ ብትወስጂ በሙቀት ጊዜ ላይሽ ላይ ሊቀልጥ የሚደርስ፣ በቅዝቃዜ ጊዜ ላይሽ ላይ በረዶ የሚሆን ነው፡፡ ስለዚህ የአገራችን የተለያዩ የብሄር ብሄረሰብ ልብሶች በልዩ ልዩ ዲዛይን ተሰርተው እንደነ ሚላኖ ባሉ የፋሽን ሳምንቶች ላይ ቢቀርቡ፣ከየትኛውም የአገር ልብስ እንደሚበልጡ እምነቱ አለኝ፡፡ ትምህርቱንም በቅርቡ እጨርሳለሁ። በነገራችን ላይ የራሴን ልብሶች ዲዛይን የማደርገው ራሴ ነኝ፡፡ አሁን የተለያዩ አገር ልብሶችን እየሰራሁ፣ የተለያዩ የፋሽን ሳምንቶች ላይ አቀርባለሁ፡፡ በቅርቡ የታወቀች ጣሊያናዊት ዲዛይነር አግኝቼ፣ ከእርሷ ጋር በስፋት ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡ ክላውዲያ ዳና ትባላለች፡፡
ስምምነታችሁ የኢትዮጵያን የባህል አልባሳት ዲዛይን ለማድረግ ነው?
የጣሊያንንና የኢትዮጵያን ቀላቅለን ለመስራት ነው ያሰብነው፡፡ ምክንያቱም ለምሳሌ ድንጉዛን ብትወስጂ ሙሉ ለሙሉ ልልበስ ብትይ፣ ከውፍረቱ የተነሳ ሙቀቱን መቋቋም አይቻልም፤ ስለዚህ ከላይ ሳሳ ያለ የጣሊያን ልብስ አድርገን፣ ከስር በቁምጣና በአጭር ቀሚስ መልክ፣ በቦርሳ፣ በስካርፍ---ብንሰራ እንዴት እንደሚያምር አልነግርሽም፡፡ እሷ ደግሞ ሮም ውስጥ የታወቀች ዲዛይነር ስለሆነች እውቅናዋን ተጠቅሜ፣ የአገራችንን የባህል አልባሳት በሰፊው ለማስተዋወቅ አስቤያለሁ፡፡ እሷም በቅርቡ አልባሳቱንና አገሪቱን ለመጎብኘት ትመጣለች። ጣሊያኖች ደግሞ በእኛ ስለሚቀኑ የእኛ ሁሉም ነገር ወደነሱ ቢሄድ ደስ ይላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በአሁን ሰዓት በሞዴሊንጉም በጥሩ ደረጃ ላይ ነው የምትገኘው፤ ግን ብዙ ያልተለበሱና እውቅና ያላገኙ ማራኪ የብሄር ብሄረሰብ አልባሳት ስላሉ እነሱ ትኩረቴን ስበውታል፡፡
አሁን ወደ ኢትዮጵያ የመጣሽው ለምንድነው?
ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት  በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ነው፡፡ አንደኛው የወንድሜ ሰርግ ላይ ለመገኘት ሲሆን ሁለተኛውና ዋናው ደግሞ ከሁለት ሳምንት በኋላ ወላይታ ላይ ፋሽን ሾው ለማካሄድ ነው። እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ አንዳንድ ከከተማው አስተዳደር ማግኘት ያለብኝን ፈቃድ እያሟላሁ ነው፡፡
የፋሽን ትርኢቱ ላይ የሚሳተፉ ሞዴሎች ከየት ነው የምትመርጪው?
እንግዲህ የደቡብ ልብሶች በተለይም የወላይታ ልብሶች ትርኢት የሚታይበት እንደመሆኑ ሞዴሎችን ከወላይታና ከሀዋሳ ነው የሰበሰብኩት፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ የወላይታን ልብስ በምን መልኩ ብሰራ የውጭዎቹ ይለብሱታል የሚለውንም ለመገምገም ይረዳኛል፡፡ ከሀዋሳና ከወላይታ የምወስዳቸው ፕሮፌሽናል ሞዴሎች ባይሆኑም የአገራቸውን ልብስ ማስተዋወቅ አያቅታቸውም፡፡ እኔም ፕሮፌሽናል ሳልሆን ነው የጀመርኩት፡፡ ለምሳሌ ድንጉዛን በተለያየ ዲዛይን ሰርቼ ጣሊያን የሆነ የፋሽን ሳምንት ላይ አቅርቤው ብዙ ጥያቄ ተነስቶበታል፡፡
ምን ዓይነት ጥያቄ?
ጥያቄው ምን መሰለሽ----የልብሱ ከለር ከጀርመን ባንዲራ ጋር እንዴት ሊመሳሰል ቻለ? የሚል ነው። የጀርመን ባንዲራ ጥቁር ቀይና ቢጫ ቀለም ያለው ነው። እዚያ ሾው ላይ “የጀርመን ባንዲራ” ብለው ነው አስተያየት የሰጡበት፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት የሚወጣ “ቼ” የተባለ መፅሄት ላይ የድንጉዛ አመጣጥ፣ የየትኛው ብሔር ልብስ እንደሆነ፣ አጠቃላይ ዝርዝሩ ይወጣል፤ ጥያቄውን ለመመለስ፡፡
ይህ ማለት ልብሱ ይበልጥ እየታወቀና እያነጋገረ ይሄዳል ማለት ነው፡፡ አሁን ድንጉዛው ህልውናውን ሳያጣ፣ ሳሳ አድርጌ ለበጋም ልብስ እንዲሆን እየሰራሁ ነው፡፡
ጣሊያን ውስጥ የአገር ልብሶችን መልበስ ታዘወትሪያለሽ?
በጣም! ድንጉዛ እለብሳለሁ፤ በስካርፍ መልክ… በቦርሳ… በክራባት… በቁምጣ መልክ እለብሳለሁ። ሌላ የሀበሻ ቀሚሶችን በተለያየ ዲዛይን ለራሴ ሰርቼ በብዛት እለብሳለሁ፡፡ ለምሳሌ ተመልከቺ (በባህል አልባሳት የተነሳቻቸውን ፎቶዎች ከአልበሟ እያሳየችኝ) በኩራት ነው የምለብሳቸው፡፡ ከዚህም ስሄድ ለጣሊያን ሰዎች ሻርፕ፣ የአንገት ልብስ---  በስጦታ እሰጣለሁ። በኤጀንሲም ላይ አሰቅዬ አውቃለሁ፡፡
ይሄም የማስተዋወቂያ አንዱ መንገድ ነው፡፡ ብቻ ጣሊያኖቹ ስለኢትዮጵያ የአሁን ሁኔታ እንዲያውቁ እፈልጋለሁ፡፡ ለምን መሰለሽ? አንዳንዴ ለማበሳጨት ብለው በምን መጣሽ ይሉኛል? ከዚህ ጣሊያን በእግሬ እሄድ ይመስል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአፍሪካ ሁሉ አንደኛ ነው፤ የስታር አሊያንስ አባልም ነው፤ ይሄን አያውቁትም አልልም፤ ያው ዘረኝነታቸው ነው እንጂ፡፡ ግን ሁሉም ፈረንጅ ዘረኝነት ተጠናውቶታል ለማለት አይደለም፤ ጣሊያን ውስጥ የማየው ዘረኝነት ግን ትንሽ ይበዛል ልበል?
ቀደም ሲል እንደነገርሽኝ ከካቶሊኮች ጋር ገዳማዊት ሆነሽ ነው ያደግሽው፡፡ እንዴት ወደ ዓለማዊነት ገባሽ?
ህይወቱ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ በዚያ ላይ በህጻንነቴ በቤተሰብ ግፊት ነው ወደዚያ ህይወት የገባሁት፡፡ አባቴ አክራሪ ካቶሊክ ነው፤ግማሽ ቄስ በይው፡፡ እና እያደግሁና እየበሰልኩ ስመጣ፣ከህይወቱም አስቸጋሪነት አኳያ ስለከበደኝ ተውኩት፡፡
ወደ ፋሽን ልመልስሽ፡፡ ለአገራችን ሴቶች ምን እንዲለብሱ ትመክሪያለሽ?
ሴቶች ከለርፉል ቀሚስ ቢለብሱ ደስ ይለኛል። የሴትነቴ መገለጫም፣ዲዛይን የማደርገውም ቀሚስ ስለሆነ ሴቶች ቀሚስ ቢለብሱ እመርጣለሁ፡፡ አንዳንዴ ለሥራ አይመችም ይላሉ፡፡ ለሩጫ ካልሆነ በስተቀር ለምንም ይመቻል፡፡ ይህን ስል ሱሪ የሚለብሱትንም አልቃወምም፤ምርጫቸው ነው፡፡
የቀለም (ከለር) ምርጫሽ ምንድን ነው?
ጥቁር፡፡ እኔም እንደምታይኝ ጥቁር ነኝ፤ግን ጥቁር ቀለም በጣም ነው የምወደው፡፡
በመጨረሻስ -----
በመጀመሪያ ደረጃ እንደ ባህላቸው ቆንጥጠው፣ ጥሩ ስነ-ምግባር እንድይዝ ታግለውና ለፍተው ያሳደጉኝን ቤተሰቦቼንና በአጠቃላይ ጥሩ ባህል፣ አብሮነትና የመተጋገዝ ባህል ውስጥ የሚኖረውን የኢትዮጵያ ህዝብ አመሰግናለሁ፡፡ አዲስ አድማስንም አክብሮ እንግዳ ስላደረገኝ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡


Read 11344 times