Saturday, 07 November 2015 10:31

ከእሳት ያመለጠው ትንታግ ፈላስፋ!

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(1 Vote)

‹‹ኢዩሮች እንደ ነጎድጓድ ናቸው››

ምዕራፍ አንድ
ሶረን አይቢዬ ኬየርኬጋርድ (Søren Aabye Kierkegaard) የዳኒሽ ፈላስፋ ነው፡፡ ለኤግዝስታንሻሊዝም የፍልስፍና ዘውግ መስራች አባት ተደርጎ የሚጠቀሰው ሶረን፤ የተወለደው በዴንማርክ ‹‹የወርቃማ ዘመን›› ነው፡፡ ከእርሱ ልደት በፊት በነበሩ ተከታታይ ዓመታት (ከ1790 እስከ 1813)፤ በርካታ መከራዎች የገጠማቸው ዴንማርኮች፤ ከ1813 በኋላ ያለውን ዘመን ወርቃማ ዘመን ይሉታል፡፡
በ1790 ዓ.ም፤ ዋና ከተማዋ ኮፐንሐገን ሁለት ጊዜ በእሳት ጋይታለች፡፡ በ1801 ዓ.ም፤ የባህር መርከቦችዋ ወድመውባታል፡፡ በ1807 ዓ.ም፤ እንግሊዝ ከባህር እየተነሳች በአውሮፕላን ቦምብ አደባይታታለች፡፡ በ1813 ዓ.ም፤ ብሔራዊ ገንዘቧ ለከፍተኛ ግሽበት ተዳርጎ ነበር። ይህ ሁሉ አልፎ፤ ሶረን ከተወለደ በኋላ፤ ታላቅ የኪነ ጥበብ አዝመራ ታይቷል፡፡ የእርሱን ልደት ተከትለው በመጡት ዓመታት፤ የዴንማርክ የሳይንስ፣ የሥነ ጥበብና የሥነ ጽሑፍ ማኅፀን አብቦ ነበር፡፡፡
በእርግጥ፤ ወርቃማ በሚል በሚጠቀሰው በዚያ ዘመን፤ በዴንማርክ ኃይለኛ ማህበራዊ ትግል ይካሄድ ነበር፡፡ እርሻ እያሳረሱ በሚኖሩ የመሬት ባላባቶችና በአራሽ ገበሬዎች ይተማመን የነበረው የዴንማርክ ፊውዳላዊ ሥርዓት መሠረቱ ተናጋ፡፡ ሐብታም ነጋዴዎችና የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች ጸንቶ የቆየውን ማህበራዊ ማዕረግ መገዳደር ጀመሩ፡፡ ውስብስብ ማህበራዊ ሥርዓት መፈጠር በጀመረበት በዚያ ዘመን የተለወጠው የሶረን አባት ህይወት፤ ለአዲሱ ማህበራዊ ለውጥ አብነት ሆኖ ሊቆም የሚችል ነው፡፡
የቤተሰቡ የመጨረሻ ልጅ የሆነውና ከቤተሰብ እወርሳለሁ ብሎ የሚያስበው አንዳች ነገር ያልነበረው የሶረን አባት፤ ድህነት የተንሰራፋባትን ገጠራማዋን የትውልድ ቀየውን ጁትላንድን ለቅቆ፤ ኮፐንሐገን ይኖሩ ከነበሩ አጎቱ ዘንድ በመሄድ፤ እርሳቸውን በሥራ እያገዘ የእጅ ሙያ ለመቅሰም ወሰነ፡፡ ኮፐንሐገን ከገባ በኋላ ዕድል ቀንታለት፤ በአጭር ጊዜም የእኔ የሚለው ትንሽ ጥሪት ለመቋጠር በቃ፡፡ አዲስ ማህበራዊ ሰልፍ ውስጥም ገባ፡፡
ምዕራፍ ሁለት
ስለ እርሱ ህይወት ለመናገር የጀመረ ማንኛውም ሰው፤በቸልታም ሆነ በምርጫ ሳይጠቅሳት ሊያልፋት የማይገባ አንድ የሶረን ኪየርኬጋርድ ተረት አለች፡፡ ለብዙ ሐሳቦች እንደ ‹‹ሙሴ ቅርጫት›› ስታገለግል አገኛታለሁ፡፡ ሶረን ኪየርኬጋርድ፤ ተረቷን ለገዛ ህይወቱ ሐቅ ማስገሪያ መቃጠንና ማቅረቢያ ሰሃን አድርጓታል፡፡ የኖረበትን ዘመን መፈከሪያ አድርጎ ተጠቅሞባታል፡፡ ውብ ተረት ነች፡፡
በዚህች ተረት፤ አንድ ራሱን ሳያውቅ ብዙ ዘመን የኖረ ሰው ህይወት ተተርቶበታል፡፡ ይህ ሰው፤ በህይወት ይኑር - አይኑር እንኳን አያውቅም፡፡ ታዲያ በአንድ የታደለች ዕለት ማለዳ፤ ለዘመናት ከያዘው እንቅልፍ ድንገት ነቃ። ሆኖም፤ ከዕድሜ ልክ እንቅልፍ መንቃቱ ወይም ልባዊ መሆኑ (አዋቂነቱ)፤ ነፍሱ ከሥጋው መለየቷን እንዲረዳ ከማድረግ ያለፈ ፋይዳ አልነበረውም፡፡ በኪየርኬጋርድ ገፀ - ባህርይ የደረሰበት ችግር፤ በኒዩክሊየር ወይም በአቶሚክ ቦምብ ወይም በባዮሎጂካዊ የጦር መሳሪያዎች ወዘተ የተነሳ፤ በሥጋት ተወጥሮ ለሚገኘው ምዕራባዊው ሥልጣኔ ተምሣሌት አድርጎታል፡፡ ዕውቀቱና መራቀቁ እንቅልፍ ነው፡፡ መድረሻውን አያውቀውም። አንድ ቀን ከእንቅልፉ ሲነቃ፤ ፍጻሜው እንደ ሶረን ገጸ ባህርይ ያለ ይሆናል፡፡
ምዕራፍ ሦስት
የኪየርኬጋርድ ቤተሰብ የሞራቪያን ክርስትና ተከታይ ነው፡፡ ሆኖም፤ የሶረን ኪየርኬጋርድ አባት፤ ጥልቅ እምነት ያለው ሰው ሆኖ ሳለ፤ ዘወትር በወንጀለኝነት የጸጸት ስሜት የሚጨነቅ እንደነበር ይነገራል፡፡ የኪየርኬጋርድ አባት በወንጀለኝነት የጸጸት ስሜት መገረፍ የጀመረው፤ ገና ልጅ ሆኖ፤ ዝናብ አጥቦ ባራቆታት የጁትላንድ (Jutland) ኮረብታ ሆኖ በጎች ይጠብቅባት በነበረች አንዲት በዝናብ የሾቀች ቀን፤ በእግዚአብሔር ላይ የእርግማን ቃል ከተናገረ ወዲህ ነው ይባላል፡፡ እንደ እርግማን የቆጠራትን ንግግሩን በእምነት እንድትሰረይለት ሲጣጣር፤ እምነቱ ከዓመት ወደ ዓመት እየጸና ሄደ፡፡ ባደረጋት በዚያች መተላለፍ የተነሳ፤ የእግዚአብሔርን ቅጣት እየተቀበለ እንደሆነ ያስብ ነበር፡፡ እናም፤ሁሉም ልጆቹ ከእርሱ በፊት እንደሚሞቱ ያምን ነበር። ከልጆቹ ውስጥ አንዳቸውም 34ኛ ዓመት ልደታቸውን እንደማያከብሩ እርግጠኛ ነበር።
በዴንማርክ መዲና በኮፐንሐገን በ1813 ዓ.ም (እኤአ) ሜይ 5፣ የተወለደው ሶረን አይቢዬ ኪየርኬጋርድ እንደ አባቱ ትንቢት 34ኛ ዓመቱን ሳይደፍን አልሞተም። በዚህች ምድር፤ ከ1813 እስከ 1855 ዓ.ም ድረስ ለ42 ዓመታት ተመላልሷል።  ሆኖም፤ በዚህች ውሱን የዕድሜ ዘመኑ፤ በርካታ መጻህፍትን ጽፏል፡፡ ከእነዚህ መጻህፍት አንዱ፤ ‹‹Fear and Trembling›› ሲሆን፤ ኪየርኬጋርድ በዚህ መጽሐፉ እንዲህ ይላል፤
‹‹የእጅ ጣቴን በህልውና ላይ ሰክቼ የሙጥኝ ያዝኩ። ህልውና እንደ ውሃ አንዳች ሽታ የሌለው ነው፡፡ የት ነው ያለሁት? ይኸ ዓለም የሚሉት ነገር ምንድነው? እዚህ ነገር ውስጥ ጎትቶ ካስገባኝ በኋላ እኔን እዚህ ጥሎኝ ሹልክ ያለው ማን ይሆን? ለመሆኑ እኔ ማነኝ? ወደዚህ ዓለም እንዴት መጣሁ? የእኔ ፍላጎት ያልተጠየቀው ለምንድን ነው?›› ኪየርኬጋርድ ጥሩ ጥያቄ አንስቷል፡፡ አንዳንዶች፤ ‹‹የህልውናዊነት መሥራች አባት›› የመባል ዝና እንዲያተርፍ አስተዋጽዖ ያደረገ ጥያቄ ነው ይላሉ። እንደ ምኞቱ፤ ‹‹ወደ ዓለም ለመሄድ ትፈልጋለህ?›› የሚል ጥያቄ ባይቀርብለትም፤ ኪየርኬጋርድ በዴንማርክ በሚኖር፤ ሐብት ሳይጎድለው ምቾት በተነፈገ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ የሆነ ቤተሰብ ውስጥ ተወልዶ አድጓል። የኪየርኬጋርድ አባት፤ ሚካኤል ኪየርኬጋርድ (Michael Kierkegaard) ቤተሰቡ ከገበታ በተቀመጠ ጊዜ፤ ሆደ ባሻነት በገነነበት ስሜት፤ ስለኢየሱስ መከራና ስለሰማዕታቱ ስቃይ በሰፊው ማውራት ይወዳል። ቤተሰባዊ ህይወቱ  በአብርሃም ታሪክ በተገለጸው ዓይነት ለእግዚአብሄር ተገዢ መሆንን የሚያበረታቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶች በየጊዜው የሚነገሩበት ህይወት ነው፡፡ አብርሃም ተራ በግ ሳይሆን አንድያ ልጁን እንዲሰዋ እግዚአብሄር እንዳዘዘው፤ አብርሃምም ሳያቅማማ ልጁን በመስዋዕትነት እንዳቀረበ፤ ሆኖም በመጨረሻዋ ደቂቃ መለኮታዊ ቸርነት ተደርጎለት በልጁ ፋንታ የመስዋዕቱ በግ እንደቀረበለት ዘወትር በገበታ ላይ ይነገራል፡፡
ይህ ታሪክ ከሚካኤል ኪየርኬጋርድ ቤተሰባዊ ህይወት ጋር በቀጥታ ምን ተዛምዶ እንዳለው መናገር ቢያስቸግርም፤ ዘወርዋራ ፍቺ እንዳለው መጠርጠር ይቻላል፡፡ ወደፊት የሚመጣን መጥፎ ሁኔታ ለመጠቆም የሚናገረው ሊሆን ይችላል፡፡ አብርሃም ብቸኛ ልጁን ለመስዋዕት እንዳቀረበ፤እኔም ሁሉንም ልጆቼን ለሐጢያቴ ማስተስርያ መስዋዕት አድርጌ አቀርባለሁ ማለቱ ይሆናል፡፡ የአብርሃም ልጅ ምትክ (ቤዛ) አግኝቶ ከሞት ተርፏል፡፡ የእርሱ ልጆች ግን ተቀጥፈዋል፡፡   
ምዕራፍ አራት
ውሎ አድሮ አስፈሪው ትንቢት መፈፀም ጀመረ። አንደኛዋ ልጁ በሜዳ ስትጫወት በገጠማት ድንገተኛ አደጋ በ12 ዓመቷ ሞተች፡፡ ማረን ደግሞ፤ ምንነቱ ባልታወቀ በሽታ በ25 ዓመቷ ህይወቷ አለፈ፡፡ ብዙም ሳይቆይ፤ ማረንን ተከትለው ኒኮሊን እና ፔትሪያ የተባሉ ሴቶች ልጆቹ ተከታትለው ሞቱ፡፡ ሁለቱም በ33ኛ ዓመታቸው፤በተመሳሳይ የወሊድ እክል አረፉ፡፡  ኒየልስ (Niels) የተሰኘው ወንድ ልጁ፤ በስደት ወደ አሜሪካ ሄዶ፤ እዚያው አሜሪካ በ24 ዓመቱ ሞተ፡፡ የኒየልስ ታላቅ የሆነው ፒተር ሞት ባያገኘውም፤ ሚስቱን ኤልሲን አጣ፡፡ አሁን፤ ከፒተር ሌላ ታላቅየው ሶረን ብቻ የአባትየውን ትንቢት ሽረው የ35ኛ ዓመት ልደታቸውን ማክበር ችለዋል፡፡ ታዲያ ይህን መከራ የተመለከቱ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች፤ ‹‹ሚካኤል ኪየርኬጋርድ፤ እግዚአብሔርን መራገም እንዲህ ዓይነት ክፉ ቅጣት እንደሚያስከትል እርግጠኛ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?›› እያሉ ነገር ማውጠንጠናቸው አልቀረም፡፡ በእርግጥ፤በብዙ ለጋ ወጣቶች ህይወት የሚከፈል በደል፤ ‹‹በልጅ አንደበት ከተነገረ የድፍረት ንግግር›› በእጅግ የከፋ ሌላ ኃጢያት ሊሆን ይገባል ይላሉ፡፡ እንዲህ ያለ ቅጣት የሚያመጣው፤‹‹የልጅ ርግማን›› ሳይሆን፤ ሴትን ለገንዘብ ብቻ ብሎ ማግባትና ከሁለት ዓመታት በኋላ አጣድፎ ለሞት መዳረግ፣ ከዚያም ከቤት ሠራተኛ ዲቃላ መደቀል ሳይሆን ይቀራል? ይላሉ፡፡
እንደ አንድ ጥብቅ የሉተራን አማኝ፤ ራስን ለመግዛትና ለሥርዓት ትልቅ ግምት በሚሰጥ እንደ ኬርኬጋርድ አባት ባለ ሰው ላይ እንዲህ ያለ ግምት መሰንዘር ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡  የሆነ ሆኖ፤ የሚካኤል ኪየርኬጋርድ የመጀመሪያ ሚስት የነበረችው ክሪስቲን ባለፀጋ ሴት ነበረች፡፡ ከኪየርኬጋርድ አባት ጋር ሲጋቡ ዕድሜዋ 36 ነበር፡፡ ልጅም መውለድ አልቻለችም፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ በኒሞኒያ በሽታ ሞተች፡፡ የኪየርኬጋርድ አባት በመጀመሪያ ሚስቱ በክሪስቲን መቃብር፤‹‹….ባለቤቷ ለመታሰቢያ ካኖረው ከዚህ የድንጋይ ሰሌዳ ሥር አርፋለች›› የሚል አጭር ቃል አስፍሮበታል፡፡የቤት ሠራተኛ በነበረች ጊዜ አስረግዞ፣ ሁለተኛ ሚስት ባደረጋት በአኔ (Ane) መቃብር ባኖረው የመታሰቢያ ድንጋይ ያሰፈረው ቃል ግን እንደ መጀመሪያው አጭር ሳይሆን ዘርዘር ያለ ነው፡፡ ‹‹ወደ ዘላለም ቤቷ ወደጌታ ብትሄድም፤ በህይወት ባሉ ልጆቿ፣ በጓደኞቿ፣ በተለይም በአዛውንት ባሏ ሁሌም እንደተወደደችና እንደተናፈቀች በልባቸው ትኖራለች›› የሚል ቃል መስፈሩን የተመለከቱ ሰዎች፤ሚካኤል ኪየርኬጋርድ ከፍ ያለ ፍቅር የነበረው ለወጣቷና ለሁለተኛ ሚስቱ ነው ይላሉ፡፡
ሚካኤል ኪየርኬጋርድና ልጆቹ ለሴቶች ዝቅ ያለ ግምት ያላቸው ነበሩ፡፡ ለሴት፤ከቤት አገልጋይነት በተጨማሪ ያላት የተለየ ኃላፊነት ልጅ መውለድ ብቻ ነው ብለው የሚያስቡ ነበሩ፡፡ የሚካኤል ኪየርኬጋርድ ቤተሰብ ለሴቶች የነበረው አመለካከትና የአያያዝ ደረጃው በዘመኑ ማህበረሰብ በሰፊው ይታይ ከነበረውም ዝቅ ያለና የከፋ ነበር፡፡ እንዲያውም፤ የቤተሰቡ ወዳጅ የሆኑት ቦይሰን (Boeson) የተባሉ የአካባቢ መስተዳድር ሹም፤ የኪየርኬጋርድ ቤተሰብን የሴት ልጆች አያያዝ በመቃወም መናገራቸው ይወሳል፡፡
ምዕራፍ አምስት
ሶረን ኪየርኬጋርድ፤ በመጽሐፎቹ ስለአባቱ በሰፊው ያትታል፡፡ሆኖም የእናቱንና የእህቶቹን ጉዳይ አንድም ቦታ አያነሳም፡፡ ሶረን ኪየርኬጋርድ፤ አብዝቶ ስለሞት በማሰብ ይጨነቅ ስለነበረው አባቱ የአድናቆትና የፍርሃት ስሜት በሚንጸባረቅበት አኳኋን ፅፏል፡፡ አንዳንድ ጊዜም የአባቱ ‹‹እብደት›› የቤተሰቡን ህይወት ይመርዝ እንደነበርም ጠቅሷል፡፡  ማንም ሰው ሊገምተው እንደሚችለው፤ በለጋነት የመቀጠፉ ትንቢት፤ በወጣቶቹ የኪየርኬጋርድ ልጆች ህይወት ላይ መጥፎ ጥላ አጥልቶ ነበር፡፡
ገና ህጻን ሳለ ጀምሮ ሶረን ኪየርኬጋርድ ዋዛ የሚወድ ልጅ አልነበረም፡፡ በተረፈ፤ እሱም እንደ አባቱ፤ ሙሉ ቀልቡ የእግዚአብሔርን ነገር በማውጠንጠን የተያዘ ነው፡፡ ይሁንና አባቱም ሆኑ ሶረን በወቅቱ በህብረተሰቡ ዘንድ የሚታየውን ለውጥ በእጅጉ የሚነቅፉ ነበሩ፡፡ ሁነኛ ማህበራዊ እሴቶችና ለአመኑት ነገር የመሰጠት ነገር እየተራከሰ መምጣቱን ወይም ጨርሶ መጥፋቱን የሚያምኑ ነበሩ፡፡ ሶረን ኪየርኬጋርድ፤ ‹‹የአዲሲቷ ዴንማርክ›› ግብዝ ጠባይ ግልጥ ብሎ የሚታየው በኮፐንሐገን በተቋቋመ አንድ የፈንጠዝያ ፓርክ (amusement park) ነበር፡፡ የመዝናኛ ፓርኩ በርካታ ብልጭልጭ ነገሮችና መጫወቻዎች ያሉበት ሲሆን፤ በዚያ የሚታየው ነገር ሁሉ ከንቱ፣ ግብዝና ከሐይማኖት የወጣ የህይወት ዘዬ መዘክር ነው ብሎ ያስብ ነበር፡፡
ገና የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ሆኖ የቅጽል ሥሙ ‹‹ሹካው›› የሚል ነበር፡፡ ጓደኞቹ ሹካው የሚል የቅጽል ስም ያወጡለት፤ ከክፍል ጓደኞቹ ጋር ክርክር ሲገጥም የማያፈናፍን ስለነበረና በክርክር ውስጥ የተዛነፈ ነገር ነቅሶ በማውጣት የሚረታቸው ስለነበር ነው፡፡ እያደር፤ ክርክር ከማሸነፍ ተራ ፍላጎት ተሻግሮ፤ በሥነ ጽሑፋዊው ዓለም ሚና ያለው ሰው ሆነ፡፡
በዓለም በሰፊው አድናቆት ካተረፉ ዝነኞች ክበብ ቀስበቀስ ተቀላቀለ፡፡ ዕውቅ የዳኒሽ ጸሐፌ ተውኔትና የሮያል ቲአትር ዳይሬክተር በነበረው፤ በጣም ውብ የሆነች ተዋናይት አግብቶ በሚኖረውና በኮፐንሐገን የምርጥ የሥነ ጽሑፍ ሳሎን ባለቤት በነበረው ጄ.ኤል. ሔይበገርግ ህይወት በጣም ይቀና ነበር፡፡ የሌት የቀን ህልሙና ጥረቱ በዚህ የተከበረ የሥነ ጽሑፍ ክበብ ተጋባዥ መሆን ነበር፡፡ በዚሁ ዘመን አካባቢ ነበር ሶረን ኪየርኬጋርድ ሪን ኦልሰን (Regine Olsen) ከተባለች ወጣት ጋር የተጫጨው። ከዚህች ወጣት ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቀው የ14 ዓመት ልጃገረድ ሳለች ነበር። የህይወት መንገድ እርከኖች (Stages on Life’s Way) ሲል በጻፈው አንድ መጽሐፉ፤ ‹‹የሰው ልጅ ከሚያከናውናቸው የፍለጋ ጉዞዎች እጅግ ወሳኝ የሆነው፤ እንዲም ሆኖ የሚዘልቀው ጉዳይ ጋብቻ ነው›› ሲል ገልጾ ነበር፡፡ ሶረን በጻፋቸው ሥራዎች ሪን ኦልሰንን፤ ዋና ጭብጥ አድርጓት ነበር፡፡ ሆኖም፤ አወንታዊ ገጽታ አላብሶ አልገለጻትም፡፡ ከነበሩት በርካታ የብዕር ሥሞች አንዱ በሆነው ‹‹አማላዩ ዮሐንስ›› (Johannes the Seducer) በሚል የብዕር ስሙ ባወጣው አንድ ጽሑፍ፤ “to poeticize oneself into a young girl is an art; to poeticize oneself out of her is a masterpiece” ሲል ጽፎ ነበር፡፡
ወደ ኋላ ደግሞ፤ ‹‹የአማላዩ ዮሐንስ የዕለት ማስታወሻ›› (“Diary of the Seducer”) ሲል በጻፈው አንድ መጽሐፉ እንደሚከተለው ብሎ ነበር፤ ‹‹በወጣትነት ዘመን የሚቀሰቀስ የወሲብ ፍላጎት፤ ደስታችንን ከእኛ ውጭ ባሉ ሰዎች ላይ እንዲመሠረት ያደርገዋል፡፡ የዚህ ፍላጎት እርካታም በሌላ ሰው የነጻነት ትግበራ ላይ ጥገኛ ይሆናል። ወሲባዊ ስበት በላቀ የደስታ ስሜት ይሞላናል፡፡ በዚያው ልክ፤ ኃላፊነትን በመሸከም ፍርሃት ይንጠናል፡፡ ጭንቀት፤ በፍርሃትና በሐሴት መካከል የሚመላለስ ወላዋይ ዥዋዥዌ ነው፡፡››
ስለዚህ ሪን መሄድ ነበረባት፡፡ ሆኖም ሶረን ‹‹ግንኙነታችን እዚህ ላይ ያበቃል›› ብሎ ከመለያየት ይልቅ ምርጫ ያደረገው፤ በራሷ ውሳኔ ግንኙነቱን ታቋርጣለች በሚል ተስፋ፤ ፍቅረኛውን በህዝብ ፊት ማሳፈር ነበር፡፡ እንዳሰበው ተለየችው፡፡ ከእርሱ ተለይታ ከሄደች በኋላ የሶረን ተቀናቃኝ የነበረን አንድ መምህር (በኋላ ዲፕሎማት) አገባች፡፡ ከሪን ጋር የነበረው ህይወት ያስቋጠረው ስንቅ፤ በስምንት ዓመታት ውስጥ ሃያ መጻህፍትን ለመጻፍ አበቃው፡፡
ሆኖም፤ ይህ ሁሉ ሐብት እያለው ለመቀላቀል የሚመኘው የሥነ ጽሑፍ ክበብ ሙሉ አባል መሆን ባለመቻሉ ይቆጭ የነበረው ሶረን፤ በራስ የመተማመን ችሎታው ተሸረሸረና፤ አነስተኛ ወደ ሆነ ክበብ ወርዶ ተቀላቀለ፡፡ መሸታ ቤት ማዘውተር ጀመረ፡፡ ኃይለኛ ጠጪ ከሆኑ ሰዎች ጋር ጓደኝነት መሠረተ፡፡ በዚህ ቡድን ውስጥ በጻፋቸው ድንቅ ተረቶች ዝናን ያተረፈውና በጣም ዓይን አፋርነት የሚያጠቃው፤ ሃንስ ክሪስትያን አንደርሰን (Hans Christian Andersen) ይገኝ ነበር፡፡ ሶረን በስብሰባ ላይ አንደርሰንን ማሽሟጠጥ ይወድ ነበር፡፡ ሆኖም ሁለቱ ጸሐፊዎች፤ ተቀያይመው ያደርጉት የነበረውን የደብዳቤ ልውውጥ ሳያቋርጡ ዘልቀዋል፡፡ ግን የሶረን ሕይወት በጣም እየተመሰቃቀለ ሄደ፡፡ ዕዳም ውስጥ ተዘፈቀ፡፡ ታዲያ ከከባድ ዕዳው በተደጋጋሚ የታደጉት አባቱ ነበሩ፡፡
ሶረን ከውርደት አዘቅት የወረደው፤ ‹‹The Corsair›› የተሰኘ አንድ ምጸተኛ ጋዜጣን (መጽሔት) ለመገዳደር በሞከረ ጊዜ ነበር፡፡ ጋዜጣው ምላሽ ሰጠ፡፡ ጥበብን በተላበሰ አኳኋን ሶረንን የሚያጣጥል ጽሑፍ አተመ፡፡ ‹‹ሶረን አጭር ሱሪ አድርጎ፤ በኮፐንሐገን ጎዳና ካገኘው ሰው ጋር እያወራ ከተማዋን ሲያካልል የሚውል ዘዋሪና ውል የለሽ ባህርይ ያለው ሰው ነው›› በማለት መራራ ስላቅ ጻፈበት፡፡ ሶረን በዚህ ስላቅ በጣም ተጎዳ፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር፤ ‹‹ኢዩሮች (Geniuses) እንደ ነጎድጓድ ናቸው፡፡ ነፋሱን እየሰነጠቁ በመንጎድ ሰዎችን የሚያስበረግጉና የደፈረሰውን አየር የሚገላልጡ ናቸው›› ሲል የጻፈው፡፡  ሶረን የሃያ አምስት ዓመት ወጣት ሲሆን፤ ‹‹ሊገለጽ የማይችል ሐሴት›› ሲል በጠቀሰው አንድ የህይወት ልምድ ውስጥ አለፈ፡፡ እናም ራሱን ለማስተካከል ወሰነ፡፡ መጠጥ ተወ፡፡ ከአባቱም ታረቀ። የመጀመሪያ መጣጥፉን አሳተመ፡፡ የፍልስፍና ህይወት ጉዞውን ጀመረ፡፡ አፍላጦን፤ ‹‹ፈላስፎች ምርጥ ሐሳብ ማፍለቅ የሚጀምሩት በ35ኛ ዓመት ዕድሜአቸው ነው›› ያለው እውነት መሆን አለበት።


Read 2518 times