Print this page
Saturday, 14 November 2015 09:40

ለ25 ዓመት አገልግሎት፤ የ25 ሚሊዮን ብር መኖሪያ ቤት!!!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(20 votes)

• ባለሥልጣናቱ፤የሞህ ኢብራሂምን ሽልማት ያሸነፉ መስሎኝ ነበር!
• የመንግስት ሹመኞች ወጪያቸው የሚጨምረው ጡረታ ሲወጡ ነው?

   የዛሬ ወጋችንን፣በዜጐችና በፖለቲከኞች መካከል ያለውን ጉልህ ልዩነት በምታሳይ ቁምነገር አዘል ቀልድ እንጀምረው፡፡ ቀልዷ ለአሜሪካውያን የተሰራች ብትመስልም  ለኛም አገር ትሆናለች፡፡ (ህልማችን ሁሉ አሜሪካ አይደል!) ቀልዱ ይቀጥላል፡-
አንድ ቀን አንድ አበባ ሻጭ፣ፀጉሩን ለመቆረጥ ወደ ወንዶች የውበት ሳሎን ይሄዳል፡፡ (ጸጉር ቤት ላለማለት እኮ ነው!) ከዚያም ፀጉሩን ይከረከምና ሲጨርስ፤ ሂሳብ ለመክፈል ይጠይቃል፡፡ ፀጉር ቆራጩ ግን፤“ገንዘብ አልቀበልም፤በዚህ ሳምንት የማህበረሰብ አገልግሎት እየሰጠሁኝ ነው” ይለዋል፡፡ (እኛ አገር ቢሆን “ስለት ይኖርበታል” ነበር የምንለው!)
አበባ ሻጩ ግን ደስ አለው እንጂ አልገረመውም፡፡ እናም እጆቹን ኪሱ ውስጥ ከትቶ እያፏጨ ከጸጉር ቤቱ ወጣ፡፡
 በነጋታው ማለዳ ላይ ፀጉር አስተካካዩ፣ ጸጉር ቤቱን ሊከፍት ሲል በሩ ላይ ምን ቢያገኝ ጥሩ ነው? የምስጋና ካርድና የአበባ ስጦታ! (አይገርምም! ሁለቱም ባህላችን አይደለም!) የሥራ ቀኑን በአሪፍ ሙድ ጀመረ ማለት ነው፡፡
ረፋዱ ላይ ታዲያ የአትክልት መደብር ያለው ሌላ ደንበኛ፣ ወደ ጸጉሩ ቤቱ ጎራ ይልና እሱም ፀጉሩን ይስተካከላል፡፡ ሲጨርስ ሂሳቤን ልከፍል ቢል፣“ይቅርታ  ገንዘብ አልቀበልም…እቺን ሳምንት የማህበረሰብ አገልግሎት ላይ ነኝ” አለው ፤ጸጉር ቆራጩ፡፡ ባለ አትክልት መደብሩም ደስ ብሎት ወደ ሥራው ሄደ፡፡  
በነጋታው ጠዋት ፀጉር አስተካካዩ፣ ጸጉር ቤቱን ሊከፍት ሲል በሩ ላይ ምን ቢጠብቀው ጥሩ ነው? የምስጋና ካርድና በተለያዩ ፍሬሽ አትክልቶች የተሞሉ የኪስ ወረቀቶች!
በዚህ ዕለት ደግሞ አንድ ያልተለመደ ሰው ወደ ጸጉር ቤቱ ጎራ ይላል - ፖለቲከኛ ነው! ደግነቱ ጣጣ ሳያበዛ እንደ ማንኛውም ደንበኛ ተከርክሞ ጨረሰና፣ሂሳቡን ለመክፈል ቦርሳ አወጣ፡፡ ፀጉር አስተካካዩ ግን በጄ አላለውም፡፡ “በዚህ ሳምንት የማህበረሰብ አገልግሎት እየሰጠሁ ስለሆነ፣ ገንዘብ አልቀበልም” ሲል አስረዳው፡፡  
ፖለቲከኛውም በደስታ እየፈነጠዘ፣ከፀጉር ቤቱ ወጥቶ ሄደ፡፡  
ፀጉር አስተካካዩ፣ በነጋታው ጠዋት ፀጉር ቤቱ በር ላይ ሲደርስ ምን ቢጠብቀው ጥሩ ነው? (የወረፋ ሰርፕራይዝ!) ደርዘን የሚያህሉ ፖለቲከኞች ፀጉራቸውን በነፃ ለመከርከም ሰልፍ ይዘው እየጠበቁ ነበር፡፡ (የትላንቱ ፖለቲከኛ ሥራ እኮ ነው!)
ወዳጆቼ፤ይሄ እንግዲህ በአገራችን ዜጎችና በሚመሯት ፖለቲከኞቿ መካከል ያለውን መሰረታዊ ልዩነት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ (የቀልዱ ማጠቃለያ ነው!)
በነገራችን ላይ --- ከዚህ ቀደም ስለ ፖለቲከኞች ሳወራ፣ ብዙ ጊዜ ፖለቲከኞችን በአንድ ሙቀጫ ውስጥ የመክተት አዝማሚያ ይታይብኝ ነበር፡፡ ፖለቲከኞች አንድ ናቸው ከሚል ተነስቼ እኮ ነው፡፡ (ማን አንድ አደረጋቸው!) እናላችሁ ---- ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ስለዚህ በኢህአዴግ ቋንቋ፤ “ሂሴን ውጫለሁ!” አያችሁ----ፖለቲከኞች ሲባሉ ዋሾዎች ናቸው ---- ፖለቲከኞች ሁሉ ሥልጣን ይወዳሉ----- ፖለቲከኞች ሞሳኞች ናቸው ወዘተ --- ዘልማዳዊ አባባል እንጂ እውነተኛ ወይም በመረጃ የተደገፉ አይደሉም፡፡
እኔ ግን ቢያንስ አንድ ነገር ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ የአሜሪካና የአገሬ ፖለቲከኞች ጨርሶ አይገናኙም፡፡ በምንም!! (አራምባና ቆቦ ዓይነት ናቸው!) ወዳጆቼ፤አሁን በምን መመዘኛ ነው የጦቢያ “ልማዳዊ” ፖለቲከኞችና የአሜሪካ “ስልጡን” ፖለቲከኞች አንድ የሚሆኑት? (ማሰቡ ራሱ ኢ-ፍትሃዊ ነው!)
እኔ የምላችሁ…ለአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በዲሞክራቶችና በሪፐብሊካን መካከል የሚደረገውን የሞት - ሽረት ፉክክር እየተከታተላችሁ ነው? (የእነ ኦባማ ፓርቲ ግን ተስፋ ያለው አይመስልም!) እንዴ ---- ኦባማና ፖሊሲያቸው፣ በአሜሪካና ህዝቧ ላይ ያስከተለው ጥፋት --- እየተባለ የሚዘረዘረው እኮ (የሥራ አጥ ቁጥር ማሻቀብ፣የመንግስት ዕዳ መቆለል፣የኢኮኖሚው አለማደግ፣የውጭ ፖሊሲ ኪሳራ፣የትናንሽ ቢዝነሶች መክሰም፣የማያሰሩ ህጎችና ደንቦች መብዛት ፣የመንግስት ሚና ማደግ---) ዲሞክራቶችን እንኳን ዘንድሮ፣ ከ30 ዓመት በኋላም የሚያስመርጥ አይደለም፡፡ (“በአዲስ መንገድ ፓርቲ ጀምረናል” ካላሉ በስተቀር!)
 በነገራችን ላይ የአሜሪካ ምርጫ ደስ የሚል ነገር አለው፡፡ አንደኛ፤ በዕውቀትና በጥልቀት ነው የሚያካሂዱት፡፡ ሁለተኛ ንትርክና ውዝግብ የለም፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩ ጠቧል የሚለውን አሜሪካ አታውቀውም፡፡ እናላችሁ---የቅስቀሳ ዘመቻቸው፣ የሚዲያ ክርክራቸው፣ የሎቢ ሥራቸው፣አማራጭ ፖሊሲያቸው ፣ለአገራቸው ያላቸው ቀናኢነት፣ተቆርቋሪነት ወዘተ ------ ብዙ ብዙ ነገራቸው ያስቀናኛል፡፡ (የእኛም አገር ምርጫ አሜሪካ ይደረግ እንዴ?)
እኔ የምላችሁ…ከስልጣን በጡረታ ለተገለሉ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት (ፕሬዚዳንትና ሚኒስትሮች) በአገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተንጣለለ መኖሪያ ቤት (Mansion) ሊገነባላቸው መሆኑን ሰማሁ ልበል፡፡ (ምነው ዘገየ ታዲያ?) በነገራችሁ ላይ ---- ለ25 ዓመት የመንግስት አገልግሎት የ25 ሚሊዮን ብር መኖሪያ ቤት ማለት እኮ ነው፡፡ እኔማ ---- ባለሥልጣናቱ የሞህ ኢብራሂም ፋውንዴሽን ሽልማትን ያሸነፉ መስሎኝ ነበር፡፡ በነገራችሁ ላይ ለጡረተኛ  ባለስልጣናት መኖሪያ ቤት እንዴት ይገነባል? ከሚሉ ወገኖች ጋር አልስማማም፡፡  ጦቢያ፤የወጣትነት ዕድሜያቸውን በበረሃ ትግል፣ጉልምስናቸውን ደግሞ በመንግስት ሃላፊነት ሲያገለግሉ የቆዩ ባለስልጣናትን ሜዳ ላይ የምትጥል ውለታ ቢስ አገር እንድትሆን አልመኝም፡፡ እንደ እኔማ ቢሆን ---- የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳም ከመኖሪያ ቤታቸው መፈናቀላቸው ተገቢ አይደለም፡፡  
ጥብቅናዬ ግን ለመንግስት ባለሥልጣናት ብቻ አይደለም፡፡
 አገሩን በቅጡ ላገለገለ አንጋፋ ኢትዮጵያዊ በሙሉ ነው፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዕድሜያቸውን ሙሉ ያስተማሩት ረዳት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፤ከዩኒቨርሲቲው በጡረታ እንዲወጡ በተደረጉ ማግስት ኪራይ ከፍለው ከሚኖሩበት መኖሪያ ቤት ማፈናቀል ተገቢ ነው? ፕሮፌሰሩ እንደ ባለስልጣናቱ የ25 ሚሊዮን ብር mansion ባይሰራላቸው እንኳን አማካይ መኖሪያ ቤት ግን ሊነፈጋቸው አይገባም፡፡
በተለይ እኔ የምመኛት ጦቢያ በገዢው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲ አባላት መካከል ልዩነት የምታደርግ አይደለችም፡፡ (እውነተኛዋ ጦቢያም በልጆችዋ መካከል ልዩነት ማድረግ አትፈልግም!!)
በነገራችን ላይ እኔ የምመኛት ኢትዮጵያ (የማታ ማታ ለልጆቻችን የምናስረክባት መሆኗ ነው!) እንኳንስ ለምሁራን ለተቃዋሚ ፓርቲዎችም (መቃወም እንጀራችን ነው ለሚሉትም ጭምር!) ቀናና ምቹ እንድትሆን እሻለሁ፡፡ እናላችሁ--- ምናለ የመሰብሰቢያ አዳራሽ እንዳይቸግራቸው ኢህአዴግ ቢረዳቸው (ሞልቶ ከተረፈ የቀበሌ አዳራሽ!) ምናለ ለቢሮ የሚሆን ህንፃ እንዲገነቡ ሁኔታዎች ቢመቻቹላቸው፤ (የአገር ገፅታ ግንባታም እኮ ነው!) ምናለ የኢህአዴግ ጉባኤ ላይ ቢጋበዙ (ለኢህአዴግ ከቻይናና ከኢዴፓ ማን ይቀርበዋል?) ምናለ ከስንት ቀን አንዴ በቤተመንግስት የእራት ግብዣ ቢደረግላቸው? (ሥልጣን ብዙም ሩቅ እንዳልሆነ በዚያው ያዩት ነበር!)
ወዳጆቼ----እኒህ ሁሉ ቅዠትና ህልም ሊመስሉን ይችላሉ፡፡ ግን እውን መሆን የሚችሉ ቀና ሃሳቦች ናቸው፡፡ በተለይ ኢትዮጵያን ከፓርቲ፤ ከብሔር፣ ከዘር፣ ከሁሉም ነገር በላይ የምንወዳት ከሆነ ምንም ነገር ይቻላል፡፡ እስቲ ኢትዮጵያን እንውደዳት፡፡ የአገር ፍቅራችን በአንድነት ያስተሳስረናል፤ ከጥላቻ ፖለቲካ ይፈውሰናል፤ ለሥራና ለፈጠራ ያተጋናል፤ በሃይልና በተስፋ ይሞላናል፡፡ ጦቢያችን እንደሆነ ሰፊ ናት፤የእኛ ዓመል አስቸገረ እንጂ ለሁሉም ትበቃለች፡፡ ለተቃዋሚው፣ ለኢህአዴጉ፣ ለዳያስፖራው፣ ለነፃ ፕሬሱ፣ ለኢንቨስተሩ፣ ለሁሉም በቂ ናት፡፡ (ልባችን ጠበበ እንጂ አገራችንስ ሰፊ ናት!)
እኔ የምለው ግን ---- የእኛ ባለሥልጣናት፣ ጡረታ ሲወጡ ነው እንዴ ወጪያቸው የሚጨምረው? ከምሬ እኮ ነው ----- ሚኒስትሮቻችን በስልጣን ዘመናቸው የ10 ሚሊዮን ብር ቤት ነበራቸው እንዴ? (የ25 ሚ. ብር መኖርያ ቤትማ አይታሰብም) ለምን ብትሉ---አገሪቱ የላትማ!! አንዳንድ ያልበሰሉ (ፍሬሽ ነገር!) የኢህአዴግ ካድሬዎች ወጪው አልበዛም ወይ ስል ቢሰሙ፣ ምን እንደሚሉ ታውቃላችሁ? “አሁን ወጪውን መሸከም የሚችል ኢኮኖሚ ስለፈጠርን ችግር የለም፤ እንቋቋመዋለን!” (ሸክም ሲበዛ እኮ መውደቅ ይመጣል!)

Read 6734 times