Saturday, 14 November 2015 09:52

“....መድሀኒቱ ተህዋሱን እንዲለማመደው እያደረግን ነው...”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ/ዮዲት ባይሳ ኢሶግ
Rate this item
(2 votes)

   በተለያየ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የፀረ-ተህዋሲያን መድሀኒቶች በጤና ተቋማት፣ በጤና ባለሙያዎች እና በመድሀኒት ተጠቃሚዎች ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ ይህ ጥንቃቄ የጎደለው የመድሀኒት አጠቃቀም ታካሚዎችን ለከፍተኛ የጤና መቃወስ እንዲሁም መድሀኒቱን ለተላመዱ ጀርሞች ወይም ተህዋሲያን የማጋለጥ እድሉ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡
ፀረ-ተህዋሲያን የሚባሉት በሰውም ሆነ በእንስሳት ላይ በባክቴሪያ፣ በፈንገስ፣ በቫይረስ እና በተለያዩ ጥገኛ ተህዋሲያን አማካኝነት የሚከሰቱ በሽታዎችን ለማከም የሚሰጡ የመድሀኒት አይነቶች ሲሆኑ በአግባቡ እና በትክክለኛው መንገድ አገልግሎት ላይ ካልዋሉ ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ያይላል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ ተላላፊ በሽታዎች በስፋት ተሰራጭተው ይገኙባቸዋል ከሚባሉት ሀገራት መካከል ተጠቃሽ ናት፡፡ በዚህም ሳቢያ የተለያዩ የፀረ-ተህዋሲያን መድሀኒቶች በስፋት አገልግሎት ላይ ይውላሉ፡፡ የእነዚህ መድሀኒቶች የማዳን ሀይል ከፍተኛ ቢሆንም አሁን እየተስተዋለ ያለው አግባብ ያልሆነ የመድሀኒት አጠቃቀም መድሀኒቶቹ የተፈለገውን ለውጥ እንዳያመጡ ከዛም አልፎ በሽታ አምጪ ጀርሞች ከፀረ-ተህዋሲያን መድሀኒቶቹ ጋር እንዲላመዱ ያደርጋል፡፡ ይህም ከግለሰብ አልፎ የማህበረሰብ ጤና ችግር እየሆነ መጥቷል፡፡ መድሀኒቱን የተላመደ የሳንባ በሽታ ለዚህ ተጠቃሽ ነው፡፡  
አቶ በለጠ አያልነህ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በፋርማሲ ትምህርት ቤት መምህር እና በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ክሊኒካል ፋርማሲስት ናቸው፡፡ የፀረ-ተህዋሲያን መድሀኒቶች በጀርሞች መለመድ ማለት ምን ማለት ነው? አንድ የፀረ-ተህዋስ መድሀኒት የማያድነውስ በምን ሁኔታ ነው? ስንል ያነሳንላቸውን ጥያቄ ሲመልሱ፡-
“...ተህዋሲያን ወይም ጀርሞች ፀረ-ተህዋሲያን መድሀኒትን ወይም በአጠቃላይ መድሀኒቶችን ተላመዱ ሲባል በተፈቀደው የመድሀኒት መጠን ከዚህ በፊት ያድን የነበረ አንድ መድሀኒት አሁን ላይ መፍትሄ ሳይሰጥ ሲቀር መድሀኒቱን የተላመደ ጀርም ወይም ደግሞ መድሀኒቱን የተላመደ ተህዋስ ተፈጠረ ይባላል።”  ይህም በቀጥታ የመድሀኒቶቹ የማዳን ሀይል ቀንሶ ወይም የጀርሞች ጉልበት አይሎ የሚፈጠር ሳይሆን አግባብ ባልሆነ የመድሀኒቶች አጠቃቀም ሳቢያ የሚከሰት መሆኑንም ይገልፃሉ፡-
“...አንድ መድሀኒት አንድን ጀርም ወይም ተህዋስ እንዲገል ወይም ደግሞ መራባቱን እንዲያቆም ለማድረግ መከተል ያሉብን የተለያዩ ሳይንሳዊ አካሄዶች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የመድሀኒቱ መጠን አንዱ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ መድሀኒት ለታካሚ ስንሰጥ በቀን ውስጥ በምን ያህል መጠን መወሰድ እንዳለበት እንነግራለን፡፡ ይህ ዘዴ እንድ መድሀኒት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የአንድን ባክቴሪያ ወይም ፈንገስ የመራባት አቅም እና ፍጥነትን ለመግታት ብሎም ባክቴሪያዎችን ለመግደል እንዲችል የምናደርግበት አንዱ መንገድ ነው፡፡ ሌላው አንድ መድሀኒት በቀን ውስጥ ለምን ያህል ግዜ መወሰድ እንዳለበትም እንነግራለን፡፡ ለምሳሌ አንድ መድሀኒት በቀን ሶስት ጊዜ በየስምንት ሰአት ልዩነት መወሰድ አለበት ስንል የወሰድነው መድሀኒት ባክቴሪያውን ወይም ፈንገሱን ሳይራባ ለስምንት ሰአታት ያህል ይዞልን ይቆያል ማለት ነው፡፡ ወይም የወሰድነው መድሀኒት መጠን በስምት ሰአታት ውስጥ ባክቴሪያውን ወይም ፈንገሱን ለመግደል በቂ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የመድሀኒቱ መጠን፣ የመድሀኒቱ ድግግሞሽ እና ለምን ያህል ጊዜ መወሰድ አበት? የሚሉት አንድን ተህዋስ በሳይሳዊ መንገድ ከሰውነታችን እንዲወገድ ወይም ስርጭቱ እንዲቀንስ የምናደርግባቸው መንገዶች ናቸው፡፡...”
እነዚህን ያላማከለ የመድሀኒት አወሳሰድ ወይም አጠቃቀም መድሀኒቱ ተህዋሲያኑን ከማዳን ይልቅ ቀስበቀስ እንዲላመደው እና ተህዋሱ መድሀኒቱን መቋቋም እንዲችል ያደርገዋል ይላሉ፡-
“...ለምሳሌ የታዘዘው የመድሀኒት መጠን 500 ግራም ሆኖ 250 ብንወስድ፣ በቀን ሶስት ጊዜ ተብሎ ሁለት ጊዜ ብቻ የምንወስድ ከሆነ፣ ሰባት ቀን ውሰዱት ተብለን ከሶስት ቀን በኋላ ካቆምን መድሀኒቱ የታለመለትን ግብ አይመታም፡፡ ስለዚህ መድሀኒቱ ገብቶ ተህዋሱን እንዲገል ሳይሆን እንዲለማመደው እያደረግን ነው፡፡ ከጊዜበኋላ ደግሞ መድሀኒቱ ምንም አይነት ምላሽ እንዳይሰጥ እያበረታታን ነው፡፡ ...ይሄንን ነው እንግዲህ መድሀኒቱን የተላመደ ተህዋስ ወይም ጀርም ተፈጠረ ብለን የምንለው፡፡...”
የመድሀኒቶች የጥራት ጉድለት ወይም አግባብ ያልሆነ የመድሀኒቶች አቀማመጥም መድሀኒቶች የተፈለገውን ለውጥ ማምጣት እንዳይችሉ ወይም ተህዋሲያንን ከመግደል ይልቅ እንዲለማመዱዋቸው ያደርጋል፡፡ በዚህም ሳቢያ በፊት በቀላሉ መዳን የሚችሉ ህመሞችን ለማከም አስቸጋሪ ይሆናል፡፡
“...አንዳንድ ጊዜ ከመድሀኒቱም በኩል ችግሮች ይታያሉ፡፡ ይህም ማለት መድሀኒቱ በአግባቡ ጥራቱን ጠብቆ ያልተመረተ ከሆነ፣ አቀማመጥ ላይ ችግር ካለበት ወይም በሙቀት እንዲሁም በቅዝቃዜ ተጎድቶ ከሆነ ታካሚው መድሀኒቱን ባለሙያ ባዘዘው መሰረት እየወሰደ እንኳን ቢሆን ላያድነው ወይም የተፈለገውን ለውጥ ላያመጣ ይችላል፡፡ ወይም ደግሞ መድሀኒቱን ለተላመደ ጀርም ወይም ተህዋስ ሊጋለጥ ይችላል፡፡...”
የተለያዩ ተላላፊ በሽታዎችን በማከም እረገድ የፀረ-ተህዋሲያን መድሀኒቶች ወይም የአንቲባዮቲክስ ሚና እጅግ ከፍተኛ ቢሆንም አለአግባብ ጥቅም ላይ ሲውሉ በሽታ አምጪ ጀርሞች በቀላሉ እና በቶሎ መድሀኒቶቹን እንዲላመዱ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ቀደም ሲል በቀላሉ መታከም የሚችሉ የበሽታ አይነቶችን ለማዳን አዳጋች እንዲሆን ያደርጋል አንዳንዴም ፈፅሞ በሽታውን ማከም የማይቻልበት ደረጃም ላይ ይደረሳል፡፡
ከሁሉ የከፋው ደግሞ ይላሉ አቶ በለጠ፡-
“...ከሁሉ የሚከፋው ይህ ችግር ሰዎችን ያለ ሀጢያታቸው የሚቀጣ መሆኑ ነው፡፡ ...ለምሳሌ ቲቢን ወይም የሳንባ በሽታን ብንወስድ አንድ ሰው መድሀኒቱን በአግባቡ ባለመውሰዱ ምክንያት መድሀኒቱን ለተላመደ የቲቢ በሽታ ቢጋለጥ እና ይህ ሰው በሽታውን ወደ ሌላ ሰው ቢያስተላልፍ የሚያስተላልፈው ይህንኑ መድሀኒቱን የተላመደ ባክቴሪያ ይሆናል፡፡ ...ኤችአይቪንም ብንወስድ እንደዚሁ ነው፡፡ አንድ ሰው በተለያየ አጋጣሚ መድሀኒቱን ለተላመደ የኤችአይቪ ቫይረስ ሊጋለጥ ይችላል፡፡ ቫይረሱ ወደ ሌላ ሰው ሲተላለፍ በተመሳሳይ ሁኔታ መድሀኒቱን የተላመደ ሆኖ ይገኛል፡፡ ስለዚህ ይህ ሁኔታ እየሰፋ ትልቅ ህብረተሰባዊ ችግር ይፈጥራል፡፡...”
ይህንን የማህበረሰብ ጤና ችግር ለመፍታት በጤና ባለሙያዎች፣ በመንግስት አካላት እንዲሁም በራሳቸው በታካሚዎች በኩል ያሉትን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት እና የታዩ ችግሮች ላይ ተባብሮ በመስራት ለውጥ ማምጣት እንደሚቻልም ይናገራሉ፡-
“...መድሀኒቱን የተላመደ ተህዋሲያን ወይም ፀረ-ተህዋሲያንን የተላመዱ ጀርሞች እንዳይፈጠሩ ወይም ደግሞ ከተፈጠሩም በኋላ መደረግ ያለባቸው ህብረተሰባዊ እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ ይህም የብዙ አካላትን ተሳትፎ ይጠይቃል፡፡ በዋነኛነት የባለሙያውን እና የመንግስትን ቀጥሎም የህብረተሰቡ ጥረት መኖር አለበት፡፡ የህክምና ባለሙያዎች መድሀኒት በሚያዙበት ወቅት በተቻለ መጠን በሽታውን በሚገባ መለየት፣ የፋርማሲ ባለሙያዎችም እነዚን የፀረ-ተህዋሲያን መድሀኒቶች አለሀኪም ማዘዣ ለተጠቃሚዎች አለመሸጥ በሀኪም ታዞም ከሆነ አጠቃቀሙን በሚመለከት በበቂ ሁኔታ ለታካሚዎች ማስረዳት አለባቸው፡፡ ታካሚዎችም ቢሆኑ የታዘዘላቸውን መድሀኒት በባለሙያ የሚሰጣቸውን መመሪያ ተከትለው መውሰድ  ይኖርባቸዋል፡፡ ...መንግስት ደግሞ በጤና ጥበቃ ወይም በሌሎች ተቆጣጣሪ አካላት በኩል የተለያዩ መመሪያዎችን በማውጣት፣ የመድሀኒቱን አጠቃቀም በሚመለከት ህብረተሰቡ ትምህርት ማግኘት የሚችልበትን መንገዶች በማመቻቸት፣ ባለሙያዎችን በማሰልጠን እንዲሁም የመድሀኒቶች ጥራት እና ስርጭት ላይ ቁጥጥር በማድረግ መፍትሄ ማምጣት ይቻላል፡፡...”     
ተከታዮቹን ነጥቦች ተግባራዊ በማድረግ ፀረ-ተህዋሲያንን የተላመዱ ጀርሞች እንዳይፈጠሩ ማድረግ ችግሩ ተከስቶም ከሆነ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል መቆጣጠር ይቻላል፡፡  
////////
የፀረ-ተህዋሲያን መድሀኒቶች በጀርሞች መለመድን መከላከያ መንገዶች
የግል እና የአካባቢ ንፅህናን መጠበቅ
ህመምን በአግባቡ መመርመር
ስለታመሙ ብቻ የፀረ-ተህዋሲያን መድሀኒቶችን ሳያስፈልግ አለመውሰድ
የፀረ-ተህዋሲያን መድሀኒቶችን የጤና ባለሙያ በሚያዘው መሰረት ብቻ መጠቀም
መድሀኒቶችን ከህጋዊ መድሀኒት ቤቶች እና የጤና ተቋማት ብቻ መጠቀም
የፀረ-ተህዋሲያን መድሀኒቶችን ከታዘዘው መጠን አብልጦ ወይም አሳንሶ አለመጠቀም
የፀረ-ተህዋሲያን መድሀኒቶች ታዝዘው መውሰድ ከጀመሩ በኋላ የጤና ባለሙያ ሳያማክሩ አለማቋረጥ
ለሌላ ሰው የታዘዘን የፀረ-ተህዋሲያን መድሀኒት አለመዋስ/ አለመጠቀም
የፀረ-ተህዋሲያን መድሀኒቶችን ለሌላ ጊዜ ብሎ አለማከማቸት
የፀረ-ተህዋሲያን መድሀኒቶችን ያለ ጤና ባለሙያ ምክር አለመጠቀም
አግባብ ያልሆነ የፀረ-ተህዋሲያን መድሀኒቶች አጠቃቀም ለእርስዎ፣ ለቤተሰቦዎ እና ለህብረተሰቡ ጎጂ መሆኑን መገንዘብ
የፀረ-ተህዋሲያን መድሀኒቶችን የተላመደ ጀርም ሲያጋጥም በቶሎ በመቆጣጠር    

Read 5346 times