Saturday, 14 November 2015 09:57

በማያንማር ምርጫ ተቃዋሚው ፓርቲ በሰፊ ልዩነት እየመራ ነው

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የሰላም ተምሳሌቷ አን ሳን ሱ ኪ፣ ህጉ ባይፈቅድላትም አገሯን ለመምራት ቆርጣለች

   ከአስር አመታት በላይ ወታደሩ በገነነበት አገዛዝ ስር የቆየችው ማያንማር ባለፈው እሁድ ታሪካዊና የአገሪቱን መጻይ ዕጣ ፋንታ ይወስናል የተባለለትን የፓርላማ ምርጫ አካሂዳለች፡፡ ወታደሩ አገሪቱ ወደተሟላ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንድትገባ ያለው ፈቃደኝነትን ይታይበታል ተብሎ የሚጠበቀው የዚህ ወሳኝ ምርጫ ጊዜያዊ ውጤት ባለፈው ረቡዕ ይፋ ተደርጓል፡፡
በምርጫ ውጤቱ መሠረትም፣ የኖቤል የሰላም ተሸላሚዋና የሰላማዊ ትግል ተምሳሌት የሆነችው አን ሳን ሱኪ ያሸነፈች ሲሆን የምትመራው ፓርቲ “ናሽናል ሊግ ኦፍ ዲሞክራሲም”፣ በስልጣን ላይ ያለውን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት “ቴን ሴን ፓርቲ ዩኒየን ሶሊዳሪቲ ዲቨሎፕመንት” ፓርቲን በሰፊ ልዩነት እየመራ እንደሚገኝ አረጋግጧል፡፡
ምርጫ ከተደረገባቸውና ጊዜያዊ ውጤቱ ከታወቀባቸው 40 በመቶ ያህል የፓርላማ መቀመጫዎች፣ ናሽናል ሊግ ኦፍ ዲሞክራሲ 90 በመቶ ያህሉን ማሸነፉን የዘገበው ቢቢሲ፣ እስካሁን ድረስም ምርጫ ከተካሄደባቸው 491 ያህል የሁለቱ ምክር ቤቶች መቀመጫዎች 163 ያህሉን ሲያሸንፍ፣ ገዢው ፓርቲ በበኩሉ፤ 10 ያህሉን ብቻ ማሸነፉ መረጋገጡን ጠቁሟል፡፡
ከአገሪቱ ፓርላማ 664 መቀመጫዎች መካከል ሩብ ያህሉ ለጦር ሃይሉ የተተወ እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፣ የአን ሳን ሱ ኪው ፓርቲ “ናሽናል ሊግ ኦፍ ዲሞክራሲ” አብላጫውን ድምጽ ይዞ አዲሱን የአገሪቱ ፕሬዚደንት መምረጥ የሚችለው ከቀሪዎቹ ወንበሮች ቢያንስ ሁለት ሶስተኛውን ወይም 329 ወንበሮችን መያዝ ሲችል ነው ብሏል፡፡
አን ሳን ሱኪ የምርጫው ውጤት ዘገየ እየተባለ መነገሩን ተከትሎ ባለፈው ማክሰኞ በስልጣን ላይ ላለው የአገሪቱ መንግስት በላኩት ደብዳቤ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎቹ መካከል እስከ መጪው ሳምንት ድረስ ውይይት እንዲደረግና ብሄራዊ እርቅ እንዲፈጠር የጠየቁ ሲሆን፣ የፕሬዚዳንቱ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ዛው ታይ፣ ፓርቲውን ላገኘው ውጤት “እንኳን ደስ አለህ” ብለው፣ መንግስት ለመወያየት ፈቃደኛ መሆኑንና ይህን መሰሉ ውይይት ሊደረግ የሚችለው ግን፣ የመጨረሻው የምርጫ ውጤት ከተገለጸ በኋላ እንደሆነ መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በስልጣን ላይ ያለው የአገሪቱ መንግስትና አን ሳን ሱ ኪን ለአመታት በቁም እስር እንድትማቅቅ የፈረዱባት የመንግስቱ ታማኝ የጦር አበጋዞች ያወጡት ህገ መንግስት፣ አን ሳን ሱ ኪን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ከመሆን እንደሚያግዳት የዘገበው ዘ ቴሌግራፍ በበኩሉ፣ እሷ ግን አሻንጉሊት ፕሬዚዳንት በመሾም ከበስተጀርባ ሆና አገሪቱን ለመምራት ማሰቧን አስታውቃለች፡፡
ይሄም የአገሪቱ የጦር አዛዦችን ክፉኛ አስቆጥቷል ተብሏል፡፡ የአገሪቱ ህገ መንግስት፤ ለፕሬዚዳንትነት የሚመረጠው ሰው የትዳር አጋሩ ወይም ልጆቹ የውጭ አገራት ዜግነት ያላቸው ከሆነ፣ ስልጣን መያዝ አይችልም የሚል ገደብ ማስቀመጡን ያስታወሰው ዘገባው፣ አን ሳን ሱኪ የቀድሞ ባለቤቷና ልጆቿ የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸው ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ፣ ፓርቲዋ ቢያሸንፍም እሷ ፕሬዚዳንት መሆን እንደማትችል ጠቁሟል፡፡
ቢቢሲ ከትናንት በስቲያ እንደዘገበው ደግሞ፣ የአገሪቱ የጦር ሃይል ሃላፊ ሚን ኡንግ ህሌንግ፤ የጦር ሃይሉ የምርጫው የመጨረሻ ውጤት መገለጹን ተከትሎ ከሚመሰረተው አዲሱ የአገሪቱ መንግስት ጋር ተባብሮ ለመስራት ፈቃደኛ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ለ15 አመታት ያህል በቁም እስር ላይ የቆየችውና በ2012 የፓርላማ ምርጫን ያሸነፈችው አን ሳን ሱ ኪ፣ ሰላማዊ ትግልን መርህ በማድረግ ሰብአዊ መብቶችን ለማስከበርና ዲሞክራሲን እውን ለማድረግ ባደረገችው ተምሳሌታዊ ተግባር የ1991 የአለም የኖቤል የሰላም ሽልማትን መቀበሏ ይታወሳል፡፡

Read 1636 times