Saturday, 21 November 2015 13:52

ሥልጣንን የማስጠበቂያ፤ አስርት ትዕዛዛት

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(3 votes)

  ከሰሞኑ፤ ‹‹መቃ ፕሮሞሽን›› ከኢትዮጵያ ብሮድካስንቲግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ) ጋር በመተባበር ያቀረበው ‹‹ማያ ቶክሾው›› የመሪነት ጉዳዮችን በማንሳት ውይይት አድርጎ ነበር፡፡ መሪ ማነው? የመሪነት ሰብእና ምንድን ነው? መሪ ሊሆን የሚገባው ማነው? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ድንቅ ውይይት ሲያደርግ ተመለከትኩ፡፡ በዚህ ውይይት ቆስቋሽነት፤ አንትሮፖሎጂስቶች፤ የመሪነትን (ስልጣንን) ጉዳይ እንዴት እንደሚመለከቱት የሚያሳይ ሐሳብ ለማቅረብ ፈለግኩ፡፡ በውይይቱ የተነሱት ሐሳቦች በሙሉ ከሥነ-ምግባር ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው ሐሳቦች መሰሉኝ፡፡ እኔ እዚህ የማነሳው ሐሳብ፤ ከፍሬድሪክ ኒች ሐሳብ የሚጎራበትና ሥነ ምግባርን የራቀ ነው፡፡ ምክንያቱም፤ በማህበራዊ ዐውድ መሪ መሆን የሚቻለው አሸናፊ ሆኖ (በኃይል ጭምር) በመገኘት ብቻ እንደሆነ የሚያትት ነው፡፡ በሰዎች ህብረት ውስጥ መሪ ለመሆን የሚያበቁ ህግጋት፤ በእንስሳት መንጋ መሪ ለመሆን ከሚያበቁት የተለዩ እንዳልሆኑ የሚገልጽ ሐሳብ ነው፡፡
መነሻ
አንትሮፖሎጂስቶች፤ ማህበራዊ ህይወትን፤ የትብብርና የፉክክር ዐውድ አድርገው ይመለከቱታል፡፡ የትብብር ህይወትን የግድ የሚያደርጉ ነገሮች እንዳሉ ሁሉ፤ ፉክክርንም የግድ የሚያደርጉ ጉዳዮች አሉ፡፡ የትብብሩን ያህል የመገፋፋትና የመጠላለፍ ነገር ይስተዋላል፡፡ አንዱ በአንደኛው ላይ ተንጠላጥሎ፤ ከፍ ያለ ማህበራዊ እርከንን ለመቆናጠጥ ይሞክራል፡፡ ከዚያም፤እንዲያ ተጋግጦና ተላልጦ ያገኘውን ማህበራዊ ማዕረግ ጠብቆ ለመቆየት ይታገላል፡፡ ዘወትር ጭብጦውን ለመቀማት በማሰብ አሰፍስፎ የሚጠብቅና የሚያደባ ተቀናቃኝ ይኖራል፡፡ ተፈጥሮ ራሷ፤ በሹምሽር ጣልቃ ትገባለች፡፡ ስለዚህ፤ አንድ ስልጣን የያዘ ሰው፤ ምንም ያህል ቆቅ ቢሆን፤ ማህበራዊ ማዕረጉን ወይም ስልጣኑን እስከወዲያኛው ጠብቆ ሊያቆየው አይችልም፡፡ በተፈጥሮ ህግ፤ ቀድሞ የተወለደ ቀድሞ ያረጃል፡፡ ከፍተኛውን ማህበራዊ ማዕረግ የያዙ ሰዎች (top dogs) ኖረው - ኖረው ሲያረጁ፤ ይዘውት የቆዩት የበላይነት ወይም ስልጣን ፈተና ውስጥ ይወድቃል፡፡ እነሱ ከቀደሙት ነጥቀው እንደ ወሰዱ፤ እነሱም በሂደት በዙሪያቸው ባሉ ተቀናቃኞች ተፈንግለው ይወድቃሉ፡፡
ማህበረሰብን ከዕድሜ አንፃር ስንመለከተው፤ በአንድ ጫፍ ሽማግሌዎች፤ በሌላኛው ጫፍ ወጣትና ህፃናት ይገኛሉ፡፡ ወጣትና ህፃናቱ እያደጉ ሲመጡ፤ ከከፍተኛው ማህበራዊ ማዕረግ መንበር የተቀመጡት እርጅ እየተጫናቸው፤ በሞት እጅ እየተጎተቱ ከሰልፉ ይወጣሉ፡፡ በዕድሜም ባይሆን፤ በቆየ በሽታ ወይም በድንገተኛ ህመም ምድርን ይሰናበታሉ፡፡ እነርሱ ሲሞቱ ክፍተት ይፈጠራል፡፡ ይዘውት የቆዩት ከፍተኛ ማህበራዊ መንበር፤ ከታች በሚመጡት ወጣቶች ይሞላል፡፡ በዚህ ዓይነት ጉዞው ይቀጥላል፡፡
ስለዚህ ማህበራዊ ህይወታችን፤ የተፈጥሮ ሹም - ሽር የሚካሄድበትና የተሻለ ማህበራዊ መንበር ለመያዝ ግብ ግብ የሚደረግበት ነው፡፡ ፈረንጆቹ፤ ይህን በውጥረት የተሞላ የማያቋርጥ ትግል፤ ‹‹ማዕረግ ወለድ ውጥረት‹‹ (status tension) ይሉታል፡፡ እንኳንስ በርካታ ማህበራዊ ቡድኖች በሚገኙበት በዘመናዊው ዓለም፤ በጥንታዊና ተፈጥሮአዊው ዐውድ በሚኖሩ ሰዎች ዘንድም ፉክክር ነበር፡፡ ሆኖም፤ በጥንታዊና ተፈጥሮአዊው ዐውድ በሚኖሩ ሰዎች የሚኖረው ፉክክር፤ በትብብር ይለዝባል፡፡ የማህበራዊ ቡድኖቹ ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ የተነሳ፤ ፉክክሩ የሚያስከትለው ውጥረት ብዙ አስጨናቂ አይሆንም፡፡ ነገር ግን፤ እንደ እስረኛ ጠባብ የመላወሻ ሥፍራ ባለው ሰው ሰራሽ የከተማ ማህበራዊ አውድ፤ የማህበራዊ ቡድኖቹ በቁጥርና ዓይነት በጣም በርካታ ከመሆናቸውና የመወዳደሪያ ሜዳውም ጠባብ በመሆኑ፤ ከፍ ያለ ማህበራዊ ደረጃን ለመቀዳጀት የሚደረገው ሩጫ ኃይለኛና አደገኛ ነው፡፡
አንዳንዴ ውድድሩ ተጋግሎ ከቁጥጥር ውጭ ይሆናል፡፡ አንዱ አንደኛውን ረግጦ ገኖ ለመውጣት የሚያደርገው ትግል ልጓም ያጣል፡፡ በዚህ ጊዜ የመንጋው ወይም የነገዱ አለቆች ውጥረት ውስጥ ይገባሉ፡፡ ደካማ የማህበረሰብ አባላት ነፍስ የሚያወጣ ጫና ውስጥ ይወድቃሉ፡፡ አንዱ በሌላኛው የበላይ ሆኖ ለመውጣት የሚያደርገው ውድድርና ሩጫ ሚዛን ሊያጣ ይችላል፡፡ ፉክክሩ ሚዛን ሲያጣ፤ ወደ መጥፎ ሁከት ይለወጣል፡፡ አንዳንድ ጊዜ፤ በዚህ የውድድርና የፉክክር ሂደት፤ለማህበራዊ ህይወታችን ጽኑ መሠረት የሚሆኑ እሴቶች ጭምር ቸል የሚባሉበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ በዚህ ጊዜ፤ ሌላው ቀርቶ፤ በወላጅና በልጅ መካከል የሚኖር የፍቅር ግንኙነት ጭምር ለከፍተኛ ጉዳት ይዳረጋል፡፡
ታዲያ፤አንዳንድ ትሮፖሎጂስቶች፤‹የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚካሄደው ትግል የሚመራባቸው መሠረታዊ ህጎች›› በሚል የሚያስቀምጧቸው አንዳንድ ነጥቦች አሉ፡፡ ‹‹የአንድ ቡድን ወይም ማህበረሰብ መሪ የሆነ ሰው፤ የመሪነት ሥፍራውን ጠብቆ ለመዝለቅ ሊከተላቸው የሚገቡ ‹‹ወርቃማ›› ህጎች አሉ›› ይላሉ፡፡ ‹‹እነኚህን ህጎች ሳያከብሩ፤ የበላይነቴን አስጠብቄ እዘልቃለሁ ማለትም ዘበት ነው›› የሚሉት ምሁራን፤ እነዚህ ህጎች ሁሉም መሪዎች (የእንስሳም ሆነ የሰው መሪዎች) ሊያከብሯቸው የሚገቡ ህጎች መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ መንጋ የሚመራው ዝንጀሮም ሆነ፤ የሐገር መሪ የሆነው ፕሬዘዳንት ወይም ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ለወርቃማ ህጎቹ ተገዢ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡ ምሁራኑ የሚጠቅሷቸው አስር ህግጋት አሉ፡፡ ሆኖም፤ እኔ ከህግጋቱ መካከል የተወሰኑትን ብቻ በመጥቀስ አወጋችኋለሁ፡፡
ሕግ አንድ
የበላይ መሆንህን ለማንፀባረቅ የሚረዱ አካላዊ ወይም ቁሳዊ ነገሮችን ቸል አትበል፡፡ ለዚህ ዓላማ የሚያግዙ ማናቸውም የማጥመጃ ነገሮች በግልፅ እንዲታዩ ከማድረግም አትቦዝን፡፡
ይህን ህግ ከዝንጀሮ አንፃር ካየነው፤ አንፀባራቂና የተዘናፈለ ወይም በደንብ የተነቀሰ ጋማን ይመለከታል፡፡ አንድ የነገድ መሪ የሆነ ዝንጀሮ፤ የፀብ ሁኔታ በሌለበት ሁኔታ በተረጋጋና ዘና ባለ አኳኋን ይቀመጣል፡፡ በእንቅስቃሴው ወይም በአካሄዱ ኮራ፣ ቀብረር፣ ጀነንና ጎምለል ማለትን አይዘነጋም፡፡ ይህ ለሰው ሆነ ለዝንጀሮ የሚሰራ፤ ወሳኝ የበላይነት ማረጋገጫ ህግ ነው፡፡  
ለዝንጀሮ የተጠቀሰው ነገር፤ የተወሰኑ ለውጦች ይደረግበታል እንጂ፤ እንዳለ መሪ ለሆነ ሰው ይሰራል፡፡ መሪው፤ ከበታቾቹ ጎልቶና ደምቆ ለመታየት ጥረት ያደርጋል፡፡ አንዳንድ መሪዎች (ንጉሦች) የአንበሳ ጎፈር ያደርጋሉ፡፡ ትልቅ ካባም ሊደርቡ ይችላሉ፡፡ ለመሪዎች የተደነገጉ ወይም የተለመዱ አንዳንድ የፕሮቶኮል ስርዓቶችና ወጎች ተመሳሳይ ግብ ያላቸው ናቸው፡፡  መሪው ቢወድም - ባይወድም የፕሮቶኮል ስርዓቶችን የግድ ማክበር ይኖርበታል፡፡ መሪው ለያዘው ልዩ ማህበራዊ ማዕረግ  መግለጫ የሚሆኑ ወይም የበላይነቱ የሚያረጋግጥ አካላዊ አቋም ይዞ መታየት ይኖርበታል፡፡ የተፈጥሮ ጉድለቱ በተለያዩ ቁሳቁሶች ታግዞ ጎላ ብሎ መታየት ይገባዋል፡፡
ለምሳሌ፤ እርሱ ለመሪ (ንጉስ) በተገባ ሁኔታ ወደ ኋላ ለጠጥ - ዘና ወይም ቀጥ ብሎ ሲቀመጥ፤ ሌሎች የእርሱን ትዕዛዝ ለመቀበል አቆብቁበው መቆምና ማሸርገድ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህም ሁኔታ አንድ የዝንጀሮ መንጋ መሪ ከሚያደርገው ነገር ጋር ፍፁም ተመሳሳይ ነው፡፡ የዝንጀሮ መንጋ መሪ፤ ዘና ብሎ - ራሱን ጥሎ ጋደም ሲል፤ የእርሱ ገባሮች እንዳቆበቆቡ ወትሮ ዝግጁ ሆነው በእርሱ ዙሪያ በንቃት ይቀመጣሉ፡፡ ዝንጀሮው ኃይል የተቀላቀለበት አንዳች እንቅስቃሴ ሲያደርግ ወይም የበላይነቱን በሚያሳይ ሁኔታ ሲንጎማለል፤ ጀሌው ወይም መንጋው እንደ እንዝርት ሾሮ አቀማመጡን ያስተካክላል፡፡ የሰውም ሆነ የዝንጀሮ መሪዎች፤ የበላይነታቸውን ለማሳየት ሲፈልጉ፤ የበታቾቻቸውን አሳንሶ የሚያሳይን ሥፍራ መርጠው ይቀመጣሉ፡፡ ከፍ ላለ ሥነ-ልቦናዊ ማዕረጋቸው የሚመጥን አካላዊ ሁኔታ በመያዝ፤ ከሚገኙበት አካባቢ ከፍ ያለውን ሥፍራ መርጠው መቀመጥ ወይም መቆም ይኖርባቸዋል፡፡
በእርግጥ፤ የዝንጀሮ ‹‹ንጉስ›› ከሁሉ በልጦ የመታየቱ ነገር ብዙ የሚያሳስበው ጉዳይ አይደለም፡፡ የዝንጀሮ ‹‹ንጉስ››፤ ምንጊዜም ቢሆን ከጀሌው የበለጠ አካላዊ ግዝፈት ይኖረዋል፡፡ ከእርሱ የሚጠበቀው ወገብን ቀጥ በማድረግ ለመቆም መሞከር ብቻ ነው፡፡ ሌላውን፤ በተፈጥሮ ብልጫ ያለው አካሉ ይፈፅምለታል፡፡ በተረፈ፤ እርሱ ከሌሎች በልጦና አጉልቶ እንዲታይ ለማድረግ፤ ሌሎች አጋዥ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩለት ጀሌዎቹ ናቸው፡፡ እርሱ ኮራ - ቆፍጠን ብሎ ሲቆም፤ የሚርበደበዱ ፈሪ የመንጋ አባላት፤የሚገቡበት እስኪጠፋቸው ድረስ ይልመጠመጣሉ፡፡ ይሽቆጠቆጣሉ፡፡ ይህም ሁኔታ የበላይነቱን አክርሮና አጉልቶ ያወጣለታል፡፡
ሆኖም፤ የሰዎች መሪ የሆነ አንድ ንጉስ፤ በአካላዊ አቋሙ፤ ከገባሮቹ ሊያንስ ይችላል፡፡ ስለዚህ ሰው ሰራሽ ደጋፊ ነገሮች ያስፈልጉታል፡፡ ትልቅ ካባ መደረብ ወይም ከአናት ከፍ ብሎ የወጣ ባርኔጣ ወይም ቆብ በማድረግ ጉድለቱን ማካካስ ይኖርበታል፡፡ ቁመቱ፤ ከዙፋን፣ ከመድረክ፣ ከተንቀሳቃሽ መኪና ላይ በመቆም፤ ከእንስሳት ጀርባ ወይም ከአሽከሮቹ ትከሻ ላይ በመቀመጥ ሊካካስ ይችላል፡፡     
የዝንጀሮ አሽከሮች ሽቁጥቁጥነታቸውን በተለያየ አኳኋን እንደሚገልጹ ሁሉ፤ ሰዎችም እጅ በመንሳት፣ በመንበርከክ፣ በመንበልበል ወዘተ የበታችነታቸውን ለመግለጽና ከመሪው ጎልተው እንዳይታዩ ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡ በዚህ ረገድ ከዝንጀሮ ጋር የሚያመሳስሉን በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ ጥንታዊ ገፅታቸውን ብዙ ሳይቀይሩ ዛሬ ድረስ አብረውን ዘልቀዋል፡፡ በዘመናዊው ዓለም በሚገኙ ነገስታት፣ ጄነራሎች፣ ዳኞች፣ ቄሶች ዘንድ ዛሬም ይታያሉ፡፡ እነኝህ የክብር መገለጫዎች እንደ ጥንቱ ዘመን ዘወትራዊ ድርጊቶች ሆነው ባይታዩም፤ አልፎ አልፎ በሚደረጉ የበዓለ-ሹመት (ሲመት) ዝግጅቶች፤ ጥንታዊ መልካቸውን ይዘው ይከወናሉ፡፡ ‹‹የጉረኛ›› ዘያቸውን እንደ ጠበቁ፤ ለተመሳሳይ ግብ ዛሬም ሲተገበሩ ይታያሉ፡፡ አንዳንድ ዝግጅቶችን ሰበብ በማድረግ የሚከወኑት ደማቅ ስነ ስርዓቶችና ረቀቅ ያሉ ወጎች፤ነገር የገባቸው በሚባሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ወይም ሊቃውንት ላይ ጭምር ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ናቸው፡፡
እርግጥ፤ ነገስታት በህዝብ ለተመረጡ መሪዎች (ፕሬዘዳንቶች ወይም ጠቅላይ ሚኒስትሮች) ሥፍራውን ከለቀቁ በኋላ፤ ግለሰባዊ የበላይነትን ለማሳየት የሚከናወኑት ስርዓቶች፤ እንደ ድሮው ፍጥጥ ያሉ ድራማዎች መሆናቸው ቀርቷል፡፡ ዛሬ - ዛሬ ትኩረቱ ለወግና ለስርአት መሆኑ ቀርቶ፤ ለአመራር ሚና ሆኗል፡፡ በዚህ በአዲሱ ወግ ወደ ስልጣን የሚመጣ መሪ፤ ያሻውን ለማድረግ የሚያስችል ኃይል ያለው ቢሆንም፤ የህዝብ አገልጋይ የሚባል መሪ ነው፡፡
ታዲያ ነገስታቱን በመተካት መንበረ-ሥልጣኑን የያዙት መሪዎች፤ የድሮው መቅረቱንና የተለወጠውን ሁኔታ መቀበላቸውን ለማሳየት፤ ባልተጋነነ አለባበስ ወደ አደባባይ ብቅ ይላሉ፡፡ ግን ይኼ ተራ ሽንገላ ነው፡፡ የህዝብ አገልጋይ የሚባለው መሪ፤ ራሱን ከተራው ህዝብ እንደ አንዱ የሚቆጥር እንደሆነ ለማሳየት የሚጠቀምበት ተራ አስመሳይነት ነው፡፡ ሆኖም፤ ይህን ተራ መስሎ የመታየት ‹‹ድራማ›› ከተገቢ በላይ ለጥጦ ሊወስደው አይፈልግም፡፡ ከተገቢው በላይ ለጥጦ ከወሰደው፤ውሎ አድሮ የያዛት ስልጣን ከእጁ ትሾልካለች፡፡ ስለዚህ፤ የህዝብ አገልጋይ የሚባለው መሪ፤ አግጥጦ ባልወጣ፤ ነገር ግን በማያሻማ አኳኋን የበላይነቱን ለማሳየት የሚያግዙት ድርጊቶችን ማከናወኑን መቀጠል ይኖርበታል፡፡
የሰው ልጅ የደረሰበት ስልጣኔ ይህ የበላይነት ለማሳየት የሚያግዙ በርካታ ዕድሎችን ፈጥሮለታል፡፡ በአለባበሱ ከተራው ሰው ያልተለየ የሚመስለው መሪ፤ በልዩ ሁኔታ በተሰሩ ቢሮዎች ወይም የመኖሪያ ህንጻዎች በመኖር፤ ከእኛ እንደ አንዱ አለመሆኑን ያሳየናል፡፡ በመንገድ ሲጓዝ በሚታየው ጥበቃና አጀብ፤ በመኪናዎቹ ሰልፍና በሞተረኞቹ ጋጋታ፤ እንዲሁም የእርሱ ብቻ በሆኑ የመጓጓዣ አውሮፕላኖች ታላቅነቱን ያሳያል፡፡ ዛሬም እንደ ጥንቱ፤ ልዩ ሙያ ባላቸው ፕሮፌሽናል ‹‹ገባሮች››፤ በቢሮ ፀሐፊዎች፣ በፕሮቶኮል ሠራተኞችና አጃቢዎች ወዘተ ተከቦ ይጓዛል፡፡ የተጠቀሱት ባለሙያዎች ዋና ተግባር፤ ለእርሱ ጠብ እርግፍ የሚሉ አገልጋዮች ሆኖ መታየት ነው፡፡ ይህም፤ ልክ እንደ ዝንጀሮው ማህበራዊ ግርማ ሞገሱን ከፍ ያደርግለታል፡፡ ከዚህ ሌላ፤ በአካላዊ አኳኋን፣በእንቅስቃሴና በእጅ አሰነዛዘር፤ በአጭሩ የጥንቱ ነገሥታት የበላይነታቸውን የሚያሳዩበት አድራጎት በእርሱም ዘንድ አለ፡፡ ታዲያ ሥልጣንን የሚያመለክቱት ትዕምርቶችና ምልክቶች፤ በሰው መሠረታዊ የባህርይ መዝገብ የሰፈሩ በመሆናቸው፤ ስውሩ አዕምሮአችን እንደ ትክክለኛ ነገር ይቀበላቸዋል፡፡ እንዲያውም፤ አንዳንድ ጊዜ ይህን የሚያፈርስ ባለሥልጣን ሲገጥመን ልንቆጣ እንችላለን፡፡ አድራጎቱና አኳኋኑ፤ ረጋና ዘና ያለ፤ ቁርጠኝነት የሚንጸባረቅበትና የታሰበበት ነው፡፡ ንግግር ሲያደርግ፤ ዓይኖቹን እንደ ጦር መሳሪያ ይጠቀምባቸዋል፡፡ ዓይኑን ወደ አንዱ አገልጋዩ ወርወር በማድረግ ትክ ብሎ ከተመለከተ፤ አገልጋዩ ትህትና በተላበሰ ገፅታ አንገቱን ደፋ ያደርጋል፡፡ እርሱም፤ አገልጋዮቹ ትክ ብለው በሚያዩት ጊዜ አንዳንዴ  ፊቱን ወዲያ ይመልሳል፡፡ ይህ መሪ፤ በጠቅላላ አኳኋኑ፤ ድካምን፣ መዛልን፣ መቅበጥበጥንና መርበትበትን ወዘተ ማሳየት የለበትም፡፡ አንድ መሪ እነኝህን ሁኔታዎች ካሳየ፤ አንድ የሆነ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ በዚህም፤ በሚመራው ማህበራዊ ቡድን ውስጥ ኃያል መሪ የመሆን ሚናው ይሸረሸራል፡፡
ሕግ ሁለት
‹‹ግልፅ የወጣ የባላንጣነት ድርጊት በተከሰተ ጊዜ፤ ኃይልን በተሞላ ቁጣ የበታችህን ማስፈራራት ይኖርብሐል›› ይላል ከአስርቱ ትዕዛዛት፤ ሁለተኛው፡
የመንጋ መሪ የሆነ ዝንጀሮ፤ ከመንጋው ውስጥ ተቀናቃኝ ሆኖ የሚነሳ አንድ ጥጋበኛ ዝንጀሮ፤ የሆነ የመገዳደር ምልክት ባሳየው ጊዜ፤ መሪው ወዲያውኑ የማይቀመስ መሆኑን ማሳየት ይኖርበታል፡፡ የተቀናቃኙን ልብ የሚያርድ፤ የማስፈራራት ባህርይ ማሳየት ይኖርበታል (impressive display of threatening behavior)፡፡
‹‹እኔ ያባ ቢለዋ ልጅ›› በሚል ዓይነት ተቀናቃኙን ለማስፈራራት የሚያገለግሉ፤ በርካታ ‹‹የአልቀመስ ባይነት›› ባህርይ ማሳያ መንገዶች አሉ፡፡ ማሳያዎቹ ብዙዎች ናቸው፡፡ ለምሣሌ፤ ‹‹በብዙ ቁጣ የተፈነቀለና በትንሽ ፍርሃት የተናጠ›› አትንኩኝ ባይነት አለ፡፡ ከዚህ በተቃራኒው፤ ‹‹በብዙ ፍርሃት የተፈነቀለና በትንሽ ቁጣ የተናጠ›› አትንኩኝ ባይነትም አለ፡፡ በሌላ አገላለጽ፤ ፍርሃት ወለድ ሽኩቻ አለ፡፡ ቁጣ ወለድ ሽኩቻም አለ፡፡ ፍርሃት ወለድ ሽኩቻ፤ ደካማ ሆኖ ሳለ ጠላቱን ለመጋፈጥ በተነሳ ዝንጀሮ ዘንድ የሚታይ ባህርይ ነው፡፡ ፍርሃት ወለዱ ሽኩቻ፤ የበላይነቱን ባረጋገጠ እንስሳ ዘንድ አይታይም፡፡ አንድ እንስሳ እንዲህ ያለ ባህርይ ካሳየ፤ የመንጋ - መሪነት ስልጣኑ እየተሸረሸረ መምጣቱን ያመለክታል፡፡ ሥልጣኑ አደጋ ላይ ካልወደቀ በስተቀር፤ የመንጋ - መሪ የሆነ እንስሳ፤ በአብዛኛው የሚያሳየው የቱማታ (aggression) ባህርይና ታምቆ የተያዘ የማስፈራራት ድርጊት መግለጫ የሆኑ አኳኋኖችን ነው፡፡
በሥልጣኑ መጽናት የታመነ ሲሆን፤ እርምጃ ለመውሰድ የቆረጠ መሆኑን ለማየት ብዙ ሳይጨነቅ፤ እንዲሁ ‹‹ዋ… ሰይጣኔን አታምጣው›› የሚል ዓይነት መልዕክት ማስተላለፉ ብቻ በቂ ሆኖ ይታየዋል፡፡ አንድ ጊዜ፤ ገምናና ጭንቅላቱን ጥጋበኛው እንስሳ ወዳለበት አቅጣጫ በመወርወር ፊቱን ማዞር ብቻ ይበቃዋል፡፡ ይኸ ድርጊት፤ አቅመ - ቢስ ተቀናቃኙ ልኩን አውቆ እንዲኖር ያደርገዋል፡፡ ይህን ዓይነቱን አድራጎት፤ ‹‹መሻትን ገላጭ እንቅስቃሴ›› (intention movement) ይሉታል ምሁራን፡፡ በእንስሳት ዘንድ የሚታየው የዚህ አድራጎት ትክክለኛ ግልባጭ በሰዎች ዘንድ አለ፡፡
በበታቹ አድራጎት የተቆጣ አንድ አለቃ (ሰው)፤ የተቆጣበት የበታቹ ወደሚገኝበት አቅጣጫ ፊቱን በቁጣ በመመለስና ደም በጎረሰ ዓይኑ በአንክሮ በመመልከት ብቻ የበላይነቱ ለማረጋግጥ ይችላል፡፡ ተቀናቃኙን አደብ ሊያስገዛው ይችላል፡፡ ይህ አለቃ ጮክ ብሎ በቁጣ ከተናገረ፤ ወይም ትዕዛዙን ደግሞ ለመናገር ከሞከረ፤ የበላይነቱ በመጠኑ አደጋ ላይ መውደቁን ያመለክታል፡፡ ባለው የበላይነት ላይ ጥርጣሬ ገብቶታል ማለት ነው፡፡ ይኸ ሰው የበላይነቱን አስጠብቆ መቀጠል የሚችልበት ሁኔታ ካለው፤ የያዘውን ማዕረግ (status) ማንም ሊነካበት እንደማይችል ለማረጋገጥ፤ የበታቹን መገሰፅ ወይም የሆነ ተምሳሌታዊነት ያለው አንዳች ቅጣት ሊሰጠው ይገባል፡፡ የበላይነቱን የሚጋፋ ድርጊት በገጠመው ጊዜ፤ ድርጊቱን እንደ ተመለከተ፤ እዛው - በቦታው በጩኸት ወይም በገነፈለ ቁጣ ምላሽ መስጠት፤ በአንድ መሪ ዘንድ ድክመት መኖሩን የሚጠቁም ነው፡፡ የመሪውን ደካማነት የሚያንፀባርቅ ነው፡፡
ሆኖም፤ አንዳንድ ጠንካራ መሪዎች፤ በደመ ነፍስ አድራጎት ወይም ሆነ ብለው እና አቅደው፤ በገነፈለ ቁጣ ምላሽ መስጠትን የበላይነትን አደላድሎ ለማስቀመጥ የሚያግዝ መሣሪያ አድርገው ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ መዘንጋት የለብንም፡፡ የመንጋ አለቃ የሆነ ዝንጀሮም ተመሳሳይ ነገር ያደርጋል፡፡ ድንገት በቁጣ ቱግ በማለት የበታቾቹን በማሸማቀቅ፤ የበላይነቱን እንዳይዘነጉ ለማድረግ ይሞክራል፡፡ እንዲህ በማድረግ ለበታቹ እንዲተላለፍ የሚፈልገውን አንዳንድ መልዕክት ለማስተላለፍ ይሞክራል፡፡ አንዴ በኃይል ያምባርቅና ፊቱን መለስ እንኳን ሳያደርግ መለለ- ጎምለል እያለ መንገዱን ይቀጥላል፡፡
አንዳንድ መሪዎችም እያሰለሱ ተመሳሳይ ነገር ያደርጋሉ፡፡ ለበታቾቻቸው ቆፍጠን ያለ ትዕዛዝ በማስተላለፍ (በመደንገግ)፤ ወይም ድንገተኛ የቁጥጥር ቅኝት በማድረግ ወይም ሠራተኞቻቸውን ሰብስበው የሚያርበደብድ የቁጣ ንግግር በማድረግ እንደ ዝንጀሮው የበታቾቻቸውን ታዛዥነት አረጋግጠው ለማለፍ ይፈልጋሉ፡፡
በመሪነት ኃላፊነት ላይ የቀመጠ አንድ ሰው፤ ለረጅም ጊዜ በዝምታ ከቀጠለ፣ ከዓይን ከራቀና መኖሩ ሳይታወቅ ብዙ ጊዜ የሚያሳልፍ ከሆነ አደጋን ይጋብዛል፡፡ በመሆኑም፤ የሥራው ተፈጥሮአዊ ሂደት፤  ኃይልና ሥልጣኑን ለማሳየት የሚያስችል ዕድል የሚነፍገው ከሆነ፤ ያለውን ኃይል እና ሥልጣን ለማሳየት የሚያስችል የእጅ ሥራ ሁኔታ መፍጠር ይገባዋል፡፡ ለአንድ መሪ፤ ሥልጣን የተሰጠው ወይም ባለሥልጣን መሆኑ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ መሪው፤ የሥልጣኑ ባለቤት መሆኑ በግልፅ መታየት የሚችልበት አጋጣሚ ሊኖር ይገባል፡፡
ሕግ ሦስት
አካላዊ ኃይል መገዳደርን የሚጋብዙ አጋጣሚዎች በተፈጠሩ ጊዜ፤ አንተ (ወይም ሥልጣንህን ያስተላለፍክለት እንደ ራሴህ) የበላይ መሆናችሁን እንዲያውቁት ማድረግ፤ ሥልጣንህን ልትጠቀምና ልትደቁሳቸው እንደምትችልም ማሳየት ወይም ማንበርከክ ይኖርብሃል፡፡
የማስፈራራቱ ነገር ካልተሳካ፤ የኃይል እርምጃ መውሰድ ወይም ጥቃት መሰንዘር ይከተላል፡፡ በዚህ ረገድ በሰውና በዝንጀሮ አለቃ መካከል ልዩነት ይታያል፡፡ ለባለ ሥልጣን ዝንጀሮ የኃይል እርምጃ መውሰድ እጅግ አደገኛ ነገርን ይጎትታል- በሁለት ምክንያቶች፡፡ በመጀመሪያ፤ ድብድብ ከተከሰተ፤ በድብድቡ አሸናፊ የሚሆነው ዝንጀሮ አካላዊ ጉዳት እንደሚገጥመው የታወቀ ነው፡፡ አካላዊ ጉዳቱ ከገባሩ ዝንጀሮ ይልቅ፤ ለንጉሡ ዝንጀሮ የከፋ አደጋን ይጋብዛል፡፡ አካሉ በጉዳት የቆሰለ አለቃ ዝንጀሮ፤ ሌላ አጥቂ ዳግመኛ ከተነሳበት፤ በሁለተኛው አመፀኛ ላይ የበላይነቱን ማረጋገጥ አይችልም፡፡ በሌላ በኩል፤ እርሱ አንድ ነው፡፡ የበታቹ ግን በቁጥር ብዙ ናቸው፡፡ እናም፤ አመፃ ያነሱበትን የበታቾቹን ከመኖሪያ ክልሉ አሳድዶ፤ ከእሱ አካባቢ እንዲርቁ ካደረጋቸው፤ በአድማ ተደራጅተው ሊያጠቁት ይመጡ ይሆናል፡፡ በተባበረ ጉልበትም ሊያሸንፉት ይችላሉ፡፡ በእነዚህ በሁለት ምክንያቶች፤ በማህበረ-ግመሬ ዘንድ ግብግብ ከመግጠም ይልቅ ማስፈራራት ተመራጭ ዘዴ ይሆናል -ለንጉሱ ዝንጀሮ፡፡
ሆኖም፤ በሰዋዊ ማህበረሰብ ዘንድ መሪ የሆነው ሰው፤ ‹‹አድማ በታኝ›› ወይም አደብ የሚያስይዝ ልዩ ኃይል በመጠቀም በሆነ ደረጃም ችግሩን ለማስታገስ ይቻለዋል፡፡ ወታደሮች ወይም ፖሊሶች እንዲህ ያሉ ግጭቶችን እንዴት መግታትና ማማምከን እንደሚቻል የሚያውቁ፤ በዚህ ጥበብ የተካኑ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ የሐገሩ ህዝብ በጠቅላላ ሆ ብሎ ካልተነሳባቸው በስተቀር፤ ለተራ ቡድን የሚበገሩ አይሆኑም፡፡ እንዲያውም አንዳንድ አምባገነኖች ከመደበኛው ኃይል የላቀ ብቃት ያላቸው አደብ የሚያስገዙ ልዩ ኃይሎችን (‹‹ቅልብ- ጦርን››) ያደራጃሉ፡፡ መደበኛው አማቂ ኃይል ልቡ ሸፍቶ ለአመጽ የሚነሳበት ዕድል ሲፈጠር፤ ልዩ ኃይልን አንዳንዴም ምስጢራዊ የፖሊስ ኃይልን በመጠቀም አመጽን ለማምከን ይችላሉ፡፡
እንዲያውም አንዳንድ የለየላቸው አምባገነኖች፤ በረቀቀ አደረጃጀት እና የአስተዳደር ስርዓት በመፍጠር፤ ከእነሱ በስተቀር ሌላ የአስተዳደር አካልና አባል ሊቆጣጠረው የማይችለው ኃይል አደራጅተው አገዛዛቸውን ለማፅናት ይሞክራሉ፡፡ መደበኛው ኃይል የበላይ ትዕዛዝን ካላገኘ እርምጃ ሊወስድ አይችልም፡፡ ስለዚህ ግራ መጋባት ውስጥ ይገባል፡፡ በዚህ መሐል የአምባገነኑ ኃይል ፈጣን ርምጃ በመውሰድ ተቀናቃኞቹን አስገብሮ አገዛዙን ለማጽናት ይችላል፡፡
ሕግ አራት
ግብ ግቡ ጉልበትን ሳይሆን አዕምሮን የሚጋብዝ ከሆነ፤ መሪው ተቀናቃኝን የሚያስከነዳ የማሰብ ብቃት ሊኖረው ይገባል፡፡
የዝንጀሮ አለቃ፤ ጠንካራና ኃይለኛ ከመሆን ባሻገር ‹‹ለምሳ ያሳቡትን ቁርስ›› ማድረግ የሚችል ቆቅ መሆን ይኖርበታል፡፡ ከዳተኝነት የራቀ፣ ፈጣን፣ አርቆ አሳቢ እና አላሚ መሆን ይገባዋል፡፡ በዚህ ረገድ፤ የማህበረሰብ መሪ የሆነ ሰው፤ ከዝንጀሮው የበለጠ የአዕምሮ ብቃት ሊኖረው እንደሚገባ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ሥልጣን በዘር በሚወረስበት የአገዛዝ ስርዓት፤ አንዳንዴ ከርፋፋ ሰው ስልጣን ሊይዝ ይችላል፡፡ ግን ውሎ ሳያድር፤ ከዙፋን ይፈነገላል፡፡ አለዚያ ለላንቲካ የሚቀመጥ ይሆናል፡፡ ሌላ እውነተኛ ባለስልጣን፤  ከጀርባ ሆኖ እንደ ፍላጎቱ የሚዘውረው እና የሚመራው የፈረስ ጋሪ ይሆናል፡፡
በዘመናዊው ዓለም፤ የአስተዳደር ችግሮች እጅግ ውስብስብ ሆነዋል፡፡ በመሆኑም፤ የዛሬ ዘመን መሪዎች ምሁራዊ ብቃት ባላቸው ልዩ ሙያተኞች (Intellectual specialists) ተከብበው የሚሰሩ ናቸው፡፡ ሆኖም፤ ፈጥኖ ውሳኔ የማስተላለፍ ብቃት ይዞ የመገኘትን አላስፈላጊነት ሊያስቀረው የሚችል ሁኔታ አልተፈጠረም፡፡ አማካሪው ቢርመሰመስ፤ የመጨረሻው ውሳኔ የሚተላለፈው በእሱ ነው፡፡ ስለዚህ፤ ቁርጥ፣ ግልፅና የማይልፈሰፈስ ውሳኔ የማሳለፍ ሸክሙ ከእርሱ ትከሻ አይወርድም፡፡

Read 3762 times