Saturday, 21 November 2015 14:35

የፓሪሱ ጥቃት ቀጣይ ፈተናዎች ስደተኞችና ቱሪዝም

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 አይሲስ የተባለው አሸባሪ ቡድን ባሳለፍነው ሳምንት አርብ በፓሪስ ስድስት የተለያዩ አካባቢዎች የሰነዘረው የሽብር ጥቃት፣ 136 ያህል ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት ዳርጓል፡፡ የመቁሰል አደጋ ከደረሰባቸው 352 ሰዎች መካከልም ከ100 በላይ የሚሆኑት ክፉኛ በመጎዳታቸው በአስጊ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፡፡የፈረንሳይ መንግስት፣ የአርቡን የሽብር ጥቃት ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት በሽብር ድርጊቱ የተሳተፉ ተጠርጣሪዎችን የማፈላለግ ዘመቻ ጀምሯል፡፡ እስካሁንም አራት ያህል ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር እንዳዋለ ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
ሌሎች የሽብር ጥቃቶች ሊሰነዘሩ ይችላሉ የሚል ስጋት ያደረበት የፈረንሳይ መንግስት፣ የጥቃት ኢላማ ሊሆኑ ይችላሉ ባላቸው የተለዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተጨማሪ 1 ሺህ 500 ያህል ወታደሮችን አሰማርቶ፣ ጥብቅ ጥበቃ እያደረገ ይገኛል፡፡ በድንበር አካባቢዎችም የተለየና የተጠናከረ ጥበቃ እየተደረገ ነው፡፡
የሽብር ጥቃቱ ካደረሰው ሰብአዊ ጥፋት በተጨማሪ በስደተኞችና በአገሪቱ የቱሪዝም መስክ ላይ የራሱ የሆነ ጉልህ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ እንደሆነ  ዘገባዎች ያስረዳሉ፡፡
የስደተኞች ጉዳይ
የፓሪሱ ጥቃት ከፈረንሳይ አልፎ የመላ አውሮፓ ብሎም የሌሎች አገራት ጉዳይ ሆኗል፡፡ ተጽዕኖውም ድንበር መሻገር ይዟል፡፡ ጥቃቱ የአውሮፓ አገራት የድንበር ላይ ቁጥጥርን ለማቆም ያሳለፉትን ውሳኔ ቀጣይነት ጥያቄ ውስጥ ጥሎታል፡፡ ይሄው ውሳኔ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ በብዙዎቹ የአውሮፓ አገራት ተጥሷል፡፡ የጥቃቱ ዋነኛ ሰለባ ፈረንሳይ የድንበር ላይ ቁጥጥሯን እንደገና የጀመረች ሲሆን፤ ስዊድን፣ ጀርመንና ስሎቫኒያም የድንበር ላይ ቁጥጥራቸውን ከጥቃቱ አስቀድመው ዳግም አጠናክረው ጀምረዋል፡
የአውሮፓ አገራት በመካከላቸው ያለውን ድንበር ብቻም ሳይሆን፣ የአህጉሪቱን ድንበሮች ለሶርያና ለሌሎች አገራት ስደተኞች ወደ መዝጋት ተሸጋግረዋል፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ፣አይሲስ ለሽብር የመለመላቸውን አባላቱን ከስደተኞች ጋር ወደ አውሮፓ አገራት እያስገባ ነው የሚል ነው፡፡
ኒውዮርክ ታይምስ እንዳለው፤የፓሪሱ ጥቃት አውሮፓ በስደተኞች ላይ ያላትን አቋም እንድትቀይርና ትኩረቷን ስደተኞችን ከማቋቋም ወደ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እንድትለውጥ እያስገደዳት ነው፡፡ በፓሪሱ ጥቃት ከተሳተፉት አሸባሪዎች አንዱ ወደ ፈረንሳይ የገባው በሶርያ ፓስፖርት መሆኑን የሚያሳይ መረጃ መገኘቱ በስፋት መነገሩን ተከትሎ፣ የአውሮፓ አገራት መሪዎች ድንበራቸውን አልፈው ወደ ግዛቶቻቸው የሚገቡ ስደተኞች ጉዳይ ክፉኛ እያስጨነቃቸው ነው ይላል ዘገባው፡፡
ሲቢኤስ ኒውስ በበኩሉ፤ የፓሪሱ ጥቃት በስደተኞች ላይ የፈጠረው ተጽዕኖ ከአውሮፓ አልፎ አሜሪካ መግባቱን ዘግቧል፡፡ ግማሽ ያህሉ የአሜሪካ ግዛቶች፣ የሶርያን ስደተኞች ወደ ግዛቶቻቸው ከመግባት የሚያግድ ውሳኔ ለማሳለፍ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ፖላንድ ከአውሮፓ ህብረት የደህንነት ዋስትና እስካልተሰጣት ድረስ፣ ከአሁን በኋላ ስደተኞች ወደ ግዛቷ እንዲገቡ እንደማትፈቅድ መግለጧን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ፓሪስ የቱሪስቶች መናኸሪያ ሆና ትቀጥል ይሆን?
ከአለማችን የቱሪስት መዳረሻ ከተሞች በቀዳሚነት የምትጠቀሰው ፓሪስ፣ በዚህ አመት ብቻ ሁለት አሰቃቂ የሽብር ጥቃቶችን አስተናግዳለች፡፡ ይህም የከተማዋን ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን ከመላ አለም ወደ ከተማዋ ለመጓዝ ያሰቡ በርካታ ቱሪስቶችንና የንግድ ጉዞ ለማድረግ ቀጠሮ የያዙ ኩባንያዎችን በድንጋጤ ክው አድርጓል፡፡
ፎክስ ኒውስ እንደዘገበው፤ ከአጠቃላዩ የአገር ውስጥ ምርቷ 7.4 በመቶ ያህሉን በቱሪዝም የምታገኘው ፈረንሳይ፣ በተሰነዘሩባት የሽብር ጥቃቶች ሳቢያ የቱሪዝም መስክ ገቢዋ እንደሚቀንስ እየተነገረ ነው፡፡የሰሞኑ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ወደ ፈረንሳይ ለመሄድ ተመዝግበው የነበሩ የተለያዩ አገራት ቱሪስቶች ጉዟቸውን ሰርዘዋል፤ ፓሪስ ውስጥ የነበሩ ቱሪስቶችም በድንገተኛው ጥፋት ተደናግጠው ባፋጣኝ ከተማዋን ለቅቀው ወጥተዋል፡፡ ከጥቃቱ በኋላ ታዋቂውን ኤፍል ታወር ጨምሮ በአገሪቱ የሚገኙ ዋነኛ የቱሪስት መስህቦች እስከ አራት ቀናት ያህል ለጎብኝ ዝግ እንዲደረጉ መወሰኑ በአገሪቱ ቱሪዝም ላይ የፈጠረው ተጽዕኖ እንዳለ ሆኖ፣ ፕሬዚዳንት ሆላንዴ የአገሪቱ ድንበሮች እንዲዘጉ ማዘዛቸውም፣ ፈረንሳይ ከቱሪዝም የምታገኘውን ገቢ ክፉኛ እንደሚጎዳውና ጥቃቱ በቀጣይም በአገሪቱ ቱሪዝም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ መፍጠሩ እንደማይቀር እየተነገረ ነው፡፡
ዘ ጋርዲያን ባለፈው ሰኞ ያወጣው ዘገባ ግን፣ የፓሪሱ ጥቃት የከተማዋንና የአገሪቱን ብቻ ሳይሆን የመላ አውሮፓን የጉዞና የሆቴል ዘርፍ ኢንቨስትመንት ክፉኛ እንደሚጎዳ ይገልጻል፡፡
የፓሪሱ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ በነበሩት ሶስት ቀናት ብቻ፣ ጥቃቱ በመላው የአውሮፓ አገራት ቱሪዝምና በተጠቃሚዎች ላይ  ተጽዕኖ ያሳድራል የሚል ስጋት በኢንቨስተሮች ላይ በመፈጠሩ፣ የአህጉሪቱ የጉዞና የሆቴል ዘርፍ ኢንቨስትመንት ከ2 ቢሊዮን ፓውንድ በላይ አጥቷል ይላል ዘገባው፡፡
ሌሎች የሽብር ጥቃቶች ሊሰነዘሩ ይችላሉ የሚለው ስጋት እንዲሁም በድንበር ላይ ያለው ጥብቅ ቁጥጥር የመንገደኞችንና የንግዱን ማህበረሰብ እንቅስቃሴ ሊያስተጓጉለው ይችላል ከሚለው ግምት ጋር ተዳምሮ፣ ኤር ፍራንስ - ኬኤልኤምን የመሳሰሉ አየር መንገዶች እንዲሁም ቶማስ ኩክን የመሳሰሉ ታላላቅ የጉዞ ወኪል ኩባንያዎች የአክሲዮን ድርሻ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ አድርጎታል ብሏል ዘገባው፡፡

Read 2374 times