Saturday, 21 November 2015 14:57

የቀድሞው የናይጀሪያ ባለስልጣን በ2 ቢ.ዶላር ሙስና እንዲታሰሩ ተወሰነ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

12 ሄኮፕተሮችንና 4 ተዋጊ ጀቶችን ለመግዛት የተመደበ ገንዘብ በልተዋል ተብለዋል
    የቀድሞው የናይጀሪያ ብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ሳምቦ ዳሱኪ የአገሪቱን አሸባሪ ቡድን ቦኮ ሃራም ለመታገል ለተጀመረው ብሄራዊ ወታደራዊ ዘመቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ የጦር መሳሪያዎችን ለመግዛት የተመደበውን 2 ቢሊዮን ዶላር ለግል ጥቅማቸው አውለዋል በሚል የእስር ትዕዛዝ እንደተላለፈባቸው ቢቢሲ ዘገበ፡፡ግለሰቡ 12 ሄኮፕተሮችን፣ አራት ተዋጊ ጀቶችንና ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን ለመግዛት በተደረገው ድርድር በነበራቸው ተሳትፎ ገንዘቡን ለግል ጥቅማቸው አውለዋል ቢባሉም፣ እሳቸው ግን ድርጊቱን እንዳልፈጸሙ ተናግረዋል፡፡
አዲሱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ግለሰቡ እንዲታሰሩ ትዕዛዝ የሰጡት ሰሞኑን ቢሆንም፣ ግለሰቡ ግን ህገወጥ የጦር መሳሪያ ይዘው በመገኘት ወንጀል ተከሰው በቁም እስር ላይ እንደነበሩና ጉዳያቸውን የያዘው ፍርድ ቤትም ፓስፖርታቸው ተመልሶላቸው ህክምናቸውን በእንግሊዝ እንዲከታተሉ ቢፈቅድላቸውም መንግስት ከአገር እንዳይወጡ እንደከለከላቸው ዘገባው ገልጧል፡፡
የፕሬዚዳንት ቡሃሪ ቃል አቀባይ፣ ግለሰቡ የሰሩት የሙስና ወንጀል በሺህዎች የሚቆጠሩ የአገሪቱ ዜጎች በአሸባሪው ቦኮ ሃራም ለሞት እንዲዳረጉ ምክንያት ሆኗል ማለታቸውን ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡ግለሰቡ በስልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ ሁሉ የአገራቸውን ብሄራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ ህጋዊ ስራ ሲሰሩ እንደነበር ገልጸው፣ ይሄን ያህል ገንዘብ በሙስና ለግል ጥቅማቸው አውለዋል፤የተጠቀሱት የጦር መሳሪያዎችም በአግባቡ ተገዝተው ለመንግስት አልደረሱም የሚለው ውንጀላ እንዳሳቃቸው ተናግረዋል፡፡

Read 2174 times