Saturday, 28 November 2015 14:02

አርቲስት ፍቃዱ ተ/ማርያም ከሳሽም ምስክርም ሆኖ ፍ/ቤት ቀረበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(15 votes)

    አንጋፋው ተዋናይ አርቲስት ፍቃዱ ተ/ማርያም በሽርክና የሚያሳትመውን የመረጃና የስልክ አድራሻ ማውጫ ዳይሬክተሪ፤ አመሳስለው በማዘጋጀት ለገበያ አቅርበውብኛል ባላቸው አካላት ክስ መስርቷል “እንደ ልጄ የማየውን ሥራዬን ነው የወሰዱብኝ” ብሏል - አርቲስቱ፡፡
በአቃቤ ህግ የቀረበው የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው፤ ዌብ ፕላኔት አይቲ ሶሉሽን እና ስራ አስኪያጁ አቶ ዳንኤል ታፈሰ በ1999 የንግድ ፍቃድ የተሰጠው የአርቲስት ፍቃዱ ተ/ማርያም የኪነ ጥበብና የማስታወቂያ ስራዎች ድርጅት፣ “የኢትዮጵያ የመረጃ እና ግብይት ዳይሬክቶሪ” የተሰኘ የአድራሻና የመረጃ ዳይሬክትሪን የመረጃ ቅንብር (ዳታ ቤዝ) በማመሳሰል፣ “National Info and Business Directory” በሚል ርዕስ አዘጋጅቶ በ117 ሺህ ብር የማስታወቂያ ክፍያ በመሸጥ በተበዳይ ላይ ጉዳት አድርሰዋል::
ተከሳሹ የንግድ ፍቃድ ሳይኖራቸው ዳይሬክተሪውን አሳትመው ማሰራጨታቸውም በክሱ ተጠቅሷል፡፡ አቃቤ ህግ 7 የሰው ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎችን ያቀረበ ሲሆን ባለፈው ማክሰኞ ሰባቱም ምስክሮች ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡
ከአቃቤ ህግ ምስክሮች አንዱ ሆነው የቀረቡትና በአርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም የኪነ ጥበብና ማስታወቂያ ድርጅት ውስጥ የ50 በመቶ ድርሻ ያላቸው ኢ/ር ብስራት ዳንኤል በሰጠው ቃል የዳይሬክተሪውን ሙሉ የመረጃ ቅንብር (ዳታ ቤዝ) እሳቸው እንዳዘጋጁት ጠቁመው፣ ተከሳሽ የመረጃ ቅንብራቸውን ሙሉ ለሙሉ በመገልበጥ ማሳተማቸውን ተናግረዋል፡፡ ድርጅቱ ከተመሰረተ ጀምሮ 4 ተከታታይ ህትመቶችን ማውጣቱን የገለፁት ምስክሩ፤ የተወሰደባቸው የመረጃ ቅንብር ለ2012/13 እ.ኤ.አ ያዘጋጁት ሲሆን ተከሳሹ ለ2014/15 በሚል ወቅታዊ አድርገው ማሳተማቸውን አስረድተዋል፡፡
ሐምሌ 20 ቀን 2006 ዓ.ም ህትመቱን ከቻይና ወደ ሀገር ውስጥ ያስገቡት ተከሳሹ፤ ነሐሴ 14 ቀን 2006 ዓ.ም ከጉምሩክ በማስወጣት፣ ማሰራጨት መጀመራቸውን ምስክሩ ጠቅሰው ለተለያዩ ድርጅቶች በአጠቃላይ በ117ሺ ብር አሰራጭተዋል ብለዋል፡፡ የተከሳሹ ዳይሬክተሪ በድርጅታቸው ከሚታተመው ዳይሬክተሪ ጋርም በስያሜ፣ ውስጥ ባሉ መረጃዎችና አቀማመጣቸው፣ በወረቀትና ቀለም አጠቃቀምና በማስታወቂያ አቀማመጥ እንደሚመሳሰሉ ተናግረዋል፡፡
ተከሳሹ፤ በአርቲስት ፍቃዱ ድርጅት ውስጥ የሽያጭ ሰራተኛ አስተባባሪ ሆነው ይሰሩ እንደነበር ያስታወሱት ምስክሩ፤ በ2002 ከድርጅቱ ከወጡ በኋላ ወረቀትና የወረቀት ውጤቶችን የማስገባት ፍቃድ እንጂ የማስታወቂያ ስራ ፍቃድ ሳይኖራቸው ነው ዳይሬክተሪውን ያሳተሙት ሲሉ ለፍ/ቤቱ አብራርተዋል፡፡ ተከሳሹ ጉዳዩ በፍ/ቤት ተይዞ ሳለም ሁለተኛ ህትመት ማሳተማቸውንም ምስክሩ ተናግረዋል፡፡
ሁለተኛ የአቃቤ ህግ ምስክር ሆኖ የቀረበው ራሱ አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም ሲሆን፤ “ከቲያትር ስራ ጡረታ ከወጣሁ በኋላ መጦሪያዬ ይሆነኛል ያልኩትንና እንደ ልጄ የማየውን ስራዬን ነው ተከሳሽ የወሰዱብኝ” ብሏል፡፡ “ስምንት ዓመት የለፋንበትን ነው ገልብጠው ያሳተሙብን” ያለው ምስክሩ፤ ስራችን የመንግስት አካላት ተገቢ እውቅና የሰጡበት ነው ብሏል፡፡
ፍ/ቤቱ የአቃቤ ህግ ምስክሮችን በሙሉ ካደመጠ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከሉ በማለት ምስክሮችን ለመስማት ለጥር 3 ቀን 2008 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡     

Read 7027 times