Print this page
Saturday, 11 February 2012 10:19

ጉዞ ወደ ጐንደር

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(0 votes)

ከተራ …ከጐንደሮች ጋራ

(የጉዞ ማስታወሻ - ክፍል አራት)

“…እንሻገር ጐንደር ጐንደር

እንሻገር ጐንደር

ሳርና ቅጠሉ ሰውም አገር አገር

እንሻገር ጐንደር …”

(የአገሬ ዘፋኝ)

***

ተሳስቻለሁ…!

ባለፈው ሳምንት “ጐንደር ደርሻለሁ” ብዬ ጽፌ ነበር፡፡ ከአዲስ አበባ ተነስተን፣ ሙሉቀን ተጉዘን፣ ከምሽቱ አራት ሰአት ላይ ጐንደር ደረስን፤ ብዬ ለአንባቢዎቼ ነበር፡፡ ጐንደር ደርሼ ያየሁትን ማራኪ ትዕይንት አስነብቤ ነበር፡፡ አፌን ሞልቼ “”ጐንደር ደረስኩ፣ ደርሼም ይሄን አየሁ…” ብዬ መናገሬ በድፍረት ሳይሆን በስህተት ነው፡፡ ከአዲስ አበባ 748 ኪሎ ሜትሮች ያህል ርቃ ያለችዋን፣ ሙሉ ቀን ስጓዝ ውዬ ከመሸ ያገኘኋትን የዛሬዋን ጐንደር አይቼ ነው፣ በስህተት “ጐንደር ደረስኩ” ያልኩት፡፡

ተሳስቻለሁ!

ጐንደር የዘመናት ጉዞ ናት …ቢሄዱ ቢሄዱ የማይገፏት፡፡ ደርሰው የማይጨርሷት ሩቅ ናት፡፡

አልደረስኩም፡፡

አባይን ተሻገርኩ፣ ጐጃምን አለፍኩ፣ ፎገራን ዘልቄ ሊቦ ከምከምን አቆራረጥኩ፣ አዘዞን ሰንጥቄ ከመሸ ጐንደር ደረስኩ…አልኩ እንጂ ገና ነኝ፡፡

ጐንደር አድሬ፣ ጐንደር ብውልም ገና መንገደኛ ነኝ …ወደ ጐንደር ተጓዥ፡፡

ማልጄ ተነስቼ ጉዞዬን ቀጥያለሁ፡፡ የጐንደር ጐዳናዎችን ተከትዬ ወደ ጐንደር እገሰግሳለሁ፡፡ እንዲህ ድካም ሲያዝለኝ ደግሞ ጥላ ፈልጌ አረፍ እላለሁ፡፡ ጃንተከል ዋርካውን ተጠልዬ ቁጭ እንዳልኩ፣ ወደ ሩቋ ጐንደር አዘግማለሁ፡፡

ወደ ጥንቷ ጐንደር እጓዛለሁ፡፡

በአንገረብና በቀሃ ወንዞች መካከል ከዘመናት በፊት በቅላ እያደር የሰፋች፣ እያደር የገዘፈች የጥንቷ ጐንደር የዘመናት ጉዞ ናት፡፡

አፄ ፋሲል ከደንቀዝ ቤተ መንግስታቸውን አንስተው ወዲህ ወደ እሷ በመጡበትና መናገሻቸው ባደረጓት ጊዜ እንደተመሰረተች ቢነገርም የጐንደር ጉዞ ግን ከዚያ በፊት እንደጀመረ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በአፄ አምደጽዮን ዜና መዋዕል “ጐንደር” የሚል ስም ተጠቅሶ መገኘቱ የከተማዋ ታሪክ ከዚያም በፊት ርቆ እንደጀመረ ያመለክታል የሚሉ አሉ፡፡

ከ250 አመታት በላይ የሀገሪቱ መናገሻ ከተማ ሆና ያገለገለችዋ ጐንደር እርግጥም የዘመናት ጉዞ ናት…

ረጅም ነው የእሷ መንገድ፡፡

…ሩቅ ይወስዳል፡፡ ከዘመናት በፊት የተቀየሰ፣ ባህር የሚያሻግር ብዙ ረጅም መንገድ አላት ጐንደር፡፡

ከዘመናት አስቀድሞ የተዘረጉ ሶስት መስመሮች የነበሯት የሲራራ ንግድ ማዕከል ናት፡፡

አንዱ በወገራ አድርጐ፣ ደባርቅ አሻግሮ፣ ሊማሊሞን አጠማዝዞ፣ ሽሬና አድዋን አሳልፎ ምጽዋ ያዘልቃል፡፡

ሌላው በጭልጋ በኩል መተማ አድርሶ፣ ሱዳን አሻግሮ አልፎ ግብጽ ይገባል፡፡

ወዲህ ያለው ደግሞ ወደ ጐጃም የሚወስደው፣ አባይን አሻግሮ ከእናኸሪያ ካፋ ድረስ የተዘረጋው የሲራራ ንግድ መንገድ አለ፡፡

እኔ እዚህ ነኝ…

ከአደባባይ እየሱስ ወደ ፒያሳ የሚወስደውን መንገድ ተከትዬ አዘግማለሁ፡፡

ስፍር ቁጥር ከሌለው ህዝብ መሀል ነኝ፡፡ “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ” ብለው አምረው ተውበው ከወጡ ሴቶች፣ በሆታና በጭፈራ ዙሪያ ገባውን ከሚያናውጡ ጐረምሶች፣ ይህን ድንቅ ትዕይንት ለማየት ከሩቅ አገር ከመጡ ቱሪስቶች ጋር ነኝ፡፡ ዛሬ ከተራ ነው፡፡

ወጣቶች፣ ህፃናት፣ ጐልማሶች፣ አረጋውያን፣ የቤተክርስቲያናት አገልጋዮች፣ ምዕመናን ሁሉም ወደ መስቀል አደባባይ ይጐርፋሉ፡፡

ቀሳውስትና ካህናት በካባ፣ በሸማ፣ በጥንድ ድርብና በተለያዩ አልባሳት ደምቀውና ተውበው የከተራን በአል ለማድመቅ ወጥተዋል፡፡

ህዝቡ ታቦታቱን አጅቦ ወደ ጥምቀተ ባህሩ ለመውረድ ነቅሎ ወጥቷል፡፡

መድሀኒያለም፣ ፊት ሚካኤል፣ አጣጣሚ ሚካኤል፣ እልፍኝ ጊዮርጊስ፣ አበራ ጊዮርጊስ፣ ልደታ ማርያም፣ ቅዱስ ዮሐንስ፣ ቀሃ እየሱስ…እነዚህ ታቦታት በታላቅ ድምቀት ወደ ጥምቀተ ባህሩ ጉዟቸውን ጀምረዋል፡፡

ኮረብታማ ጐንደር ከጥንታዊ ታሪክ ማህደርነቷ ጋር በተያያዘ የበርካታ ቱሪስቶች መዳረሻ ከመሆኗ ባሻገር የሃይማኖታዊ ቱሪዝም ማዕከል ናት፡፡

እርግጥም ጥምቀትን በጐንደር መታደም መባረክ ነው፡፡ ታቦታቱ በካህናት ዝማሬና ሽብሸባ፣ በባህላዊ ጭፈራ፣ በተለያዩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትዕይንቶች ታጅበው ቁልቁል ወደ ጥምቀተ ባህሩ እየተጓዙ ነው፡፡ በተለየ ሁኔታ የሚከበረው የጥምቀት በአል ሲደርስ እንዲህ ከአለም ዙሪያ የሚመጡ በርካታ ቱሪስቶች ጐንደርን ያጥለቀልቋታል፡፡

እርግጥም ጥምቀትን በጐንደር መታደም መባረክ ነው፡፡

ታቦታቱ በካህናት ዝማሬና ሽብሸባ፣ በባህላዊ ጭፈራ፣ በተለያዩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትዕይንቶች ታጅበው ቁልቁል ወደ ጥመቀተ ባህሩ እየተጓዙ ነው፡፡ ጥምቀትን በጐንደር ለመታደም ሩቅ ተጉዘው የመጡ በርካታ የውጭ አገራት ቱሪስቶች በደስታ ስሜት ተውጠው ይታያሉ፡፡

ይህንን የሚደንቅ ትዕይንት በካሜራዎቻቸው ለማስቀረት ከወዲያ ወዲህ ይሯሯጣሉ፡፡

እኔ ደግሞ ቱሪስቶቹ በሚያዩት ነገር ምን እንደተሰማቸው ለማወቅ አለፍ አለፍ እያልኩ እጠይቃቸዋለሁ፡፡

“የሁሉም ምላሽ በሚያዩት ትዕይንት ፍፁም መደነቃቸውን የሚገልጽ ነበር” ብዬ ማለፍ አልፈልግም፡፡

ፒያሳ አካባቢ ስላገኘሁት ስዊዘርላንዳዊ ቱሪስት ላውጋችሁ፡፡

የቴሌ ህንፃ በረንዳ ላይ ቆሞ ታቦታቱን እያጀበ የሚጓዘውን ህዝብ በአድናቆት ይመለከታል፡፡ በሚያየው ነገር መደሰቱን ገለፀልኝ፡፡

“ይህ እጅግ ማራኪ ትዕይንት ነው” አለኝ ቱሪስቱ ወደ ህዝቡ እየጠቆመ፡፡

ህዝቡን አየሁት፡፡

ከህዝቡ መሀል ደግሞ ፒያሳ አደባባዩ ላይ ጋሻ፣ ጦር፣ ጐራዴውን ይዞ የቆመውን የአባ ታጠቅ ካሳን ሀውልት አየሁት፡፡

“ስለዚህስ ምን ትላለህ?” አልኩት ቱሪስቱን ወደ ሀውልቱ እየጠቆምኩት፡፡

“ጥሩ ሃውልት ነው” አለኝ ጥቂት አመንትቶ፡፡

“የማን ሃውልት እንደሆነ ታውቃለህ?” መልሼ ጠየቅኩት፡፡

“አላውቅም…ብዙ ህዝብ በተሰበሰበበት ትናንት ተመርቆ ሲከፈት አይቻለሁ፡፡ ሰውዬው ማን እንደሆነ ግን አላውቅም፡፡ እንደሚመስለኝ ግን ሰውዬው ታዋቂ ጀግና ሳይሆን አይቀርም፡፡ ህዝቡ ከትናንት ጀምሮ ከሀውልቱ ጋር ፎቶግራፍ ሲነሳ አስተውያለሁ፤ ሰውዬው ጀግና መሆን አለበት” አለኝ፡፡ እርግጠኛ መሆን ያልቻለው “ሰውዬው ማን ነው?” በሚለው ነው፡፡

ለነገሩ አይፈረድበትም፡፡ በአገሩ ሳለ ስለ ሰውዬው ምንም ነገር ላያውቅ ይችላል፡፡ ወዲህ ጐንደር መጥቶ ሀውልቱን በቅርብ ርቀት እያየ “የሆነ ሰውዬ ነው” ብሎ እንደዋዛ ማለፉም የቱሪስቱ ጥፋት አይደለም፡፡

በሚሊዬን የሚቆጠር ገንዘብ ፈስሶበት ፒያሳ ላይ የቆመው የአፄ ቴዎድሮስ ሃውልት “ሰውዬው ማን ነው፤ መቼ ተወልዶ፣ ምን ሰርቶ፣ መቼ ሞተ”…የሚሉ ጥያቄዎችን የሚመልስ በውጭ አገራት ይቅርና በአገሬው ቋንቋ እንኳን የተፃፈ ቁራጭ መረጃ የለውም፡፡

“መንገዶች ሁሉ…” …ወደ ጥምቀተ ባህሩ ይወስዳሉ፡፡

ወደ አፄ ፋሲል መዋኛ… ከዳር እስከ ዳር በህዝብ ወደተጥለቀለቀው አደባባይ…

እዚህም እዚያም ክብ ተሰርቶ ይጨፈራል፣ እስክስታ ይወረዳል፡፡

ዙሪያ ገባው በሃይማኖታዊና ባህላዊ ትዕይንቶች ደምቋል፡፡

ከፋሲል መዋኛ ፊትለፊት የሚገኘው የአብነት ትምህርት ቤቶች መንደር ውስጥ እገኛለሁ፡፡

ለዘመናት በርካታ የቤተክርስቲያን ሊቃውንትንና ምሁራንን ሲያፈሩ የኖሩ መሰል የአብነት ትምህርት ቤቶች አሏት - ጐንደር፡፡

አለፍ አለፍ ብለው የተቀለሱ ሰባት ጐጆዎች ጐንደር ከአብነት ትምህርት ማዕከልነት ጋር የተያያዘ ለዘመናት የዘለቀ ቁርኝት እንዳላት የሚያሳዩ ትዕይንቶችን ያስተናግዳሉ፡፡

የፊደል ሃዋርያና ንባብ ጉባኤ፣ የቅኔ ጉባኤ፣ የድጓ/ፅዋዕተ ወዜማ ጉባኤ፣ የአቋቋም ጉባኤ፣ የትርጓሜ መፃሕፍት ጉባኤ ትምህርት በምን መልኩ እንደሚሰጥ የሚያሳዩ ናቸው ጐጆዎቹ፡፡

ተማሪዎች በየጐጇቸው ደጃፍ ተኮልኩለው በየኔታ መሪነት የየራሳቸውን ትምህርት ተያይዘውታል፡፡

ታቦታቱ ከየመንበራቸው ተነስተው በምዕመናኑ ታጅበው ረጅም ርቀት ተጉዘው ወደ ማደሪያቸው እያመሩ ነው፡፡ ጥምቀተ ባህሩ የሚገኝበት የፋሲል መዋኛ ከዳር እስከዳር በህዝብ ተጨናንቋል፡፡ እልልታና ሆታው፤ ዙሪያውን ያስተጋባል፡፡ መዘምራን በያሬዳዊ ዝማሬ፣ በሽብሸባና በከበሮ ታጅበው ማራኪ ትዕይንት ያሳያሉ፡፡

የአፄ ፋሲል መዋኛ 17ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ግቢ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ግቢው መሀል ላይ 50 ሜትር በ25 ሜትር ስፋትና 2 ሜትር ጥልቀት ያለው ገንዳ ይገኛል፡፡

በ16ኛው ክፍለዘመን የተገነባው ይህ የመዋኛ ስፍራ እጅግ የሚደንቅ የኪነጥበብ ውጤት ሲሆን፤ አሰራሩና ቅርስነቱ በዩኔስኮ መዝገብ ሊያሰፍረው ችሏል፡፡

ከአንድ ኪሎ ሜትር በላይ ርቆ ከሚገኘው የቀሃ ወንዝ የተጠለፈ ውሃ ውስጥ ለውስጥ በቦይ ፈስሶ ወደዚህ መዋኛ ገንዳ ይገባል፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም፤ ውሃው አገልግሎት ከሰጠ በኋላ በተዘጋጀለት ቦይ ወጥቶ ተመልሶ ወደ ወንዙ እንዲገባ በሚያስችለው መልኩ የተሰራ መሆኑ ጐንደር በዚያ ዘመንም ደረጃውን የጠበቀ የፍሳሽ መስመር ዝርጋታ ጥበብ ባለቤት መሆኗን ይመሰክራል፡፡

መዋኛ ገንዳው መሃል ላይ የባንዲራ መቀነት ታጥቆ አሸብርቆ የሚታየው ባለ አንድ ፎቅ ጥንታዊ ህንፃ የታቦታቱ ማደሪያ ነወ፡፡

ታቦታቱ በደማቅ ስነስርዓት ወደ ማደሪያቸው በማምራት ላይ ናቸው፡፡

እየመሸ ነው፡፡ ለአይን መያዝ እየጀመረ…

እየመሸም ግን ዙሪያ ገባው ደምቋል፡፡ የፋሲል መዋኛ ግቢ በምዕመናን ተጥለቅልቋል፡፡

ሆታና ጭፈራው አልቀዘቀዘም፡፡

ዙሪያ ገባው አሁንም እንደደመቀ ነው፡፡

የምሽቱ ውርጭ የግቢውን ሙቀት አላሸነፈውም፡፡

ዙሪያዬን በሚሞቅ ነገር ተከብቤያለሁ፡፡ ውርጭ በማያሸንፈው ሙቀት ውስጥ ከአንድ ጥንታዊ ፍርስራሸ ህንፃ አጠገብ ተቀምጫለሁ፡፡ ይህ ፍርስራሽ ህንፃ መቃብር ነው፡፡ የአፄ ፋሲል ፈረስ “ዞብል” ያረፈበት መቃብር፡፡

መቃብሩን ተደግፌ ቁጭ ብያለሁ፡፡

እዚህ የምሽት ውርጭ ቢያይልም፣ “በረደኝ” አያስብልም፡፡

“ኑሮ ካሉት…” ብሎ ነገር፣ ምን የሚሉት ተረት ነው እናንተው?

እዚህ ሲሆን መቃብርም ይሞቃል!

በዙሪያዬ ያለውን ደማቅ ትዕይንት እያየሁ የተቀመጥኩበት ድንጋይ አይቀዘቅዝም፡፡

እነሱ ‘ኑሮ ካሉት፣ መቃብር ይሞቃል’ ይላሉ፡፡

እኔ ‘ኑረው ካዩት፣ መቃብር ይሞቃል’ እላለሁ፡፡

እንዲህ እንደ እኔ እዚህ ግቢ ውስጥ ተገኝተው፣ ከህዝቡ መሀል ኑረው… ይህንን ትዕይንት እያዩ ተደግፈውት ቁሞ ያሉት መቃብር አይቀዘቅዝም፡፡

በከተራ… ከጐንደሮች ጋራ… እንኳን ሌላው መቃብርም ይሞቃል…

(ይቀጥላል)

 

 

Read 3277 times Last modified on Saturday, 11 February 2012 10:25