Saturday, 28 November 2015 14:04

የረሃብ አደጋውን፣ ‘ዱብዕዳ’ ወይም ‘ጊዜያዊ’ አናስመስለው!

Written by  ዮሐንስ ሰ.
Rate this item
(4 votes)

• ‘ግድብ-መስኖ አትስሩ’ የሚል ዘመቻ፣ እና ተመፅዋች ረሃብተኛ

1. ከሃያ የዓለማችን ድሃ አገራት አንዷ!
በየዓመቱ 10 ሚ. ችግረኞች፣ እርዳታና ድጎማ ይቀበላሉ።
ዘንድሮ ግን፣ የተረጂዎቹ ቁጥር ወደ 15 ሚሊዮን ጨምሯል።
2. አስቸኳይና የሚያዛልቁ መፍትሄዎች!
የለጋሾች እርዳታ እንዲዳረስ በጥንቃቄና በፍጥነት መስራት።
ግድብና መስኖ፣ ‘የሞት ሽረት’ ጉዳይ እንደሆኑ መገንዘብ።      
3. ቢከለክሉንስ? ዩኤን - ለኢትዮጵያ፡
በድርቅ ለተጠቁት፣ የለጋሾችን እርዳታ እየመዘገበ ያስተባብራል።
‘ግድብና መስኖ አትስሩ’ የሚለውን አለማቀፍ ዘመቻ ያስተጋባል።  
የረሃብ ጥቃት የሚቆረቁረን ሰዎች፤ የመስኖና የግድብ ‘ተቆርቋሪ’ መሆን የለብንም? የድርቅ እና የረሃብ አደጋው ካንገበገበን፣... የገደል አፋፍ የድህነት ኑሮ እንደ እሬት ከመረረን፣ ተመፅዋችነት በአካልና በመንፈስ ከቆረቆረንና ውጋት ከሆነብን፤... ሕይወትን ከማበልፀግ የበለጠ አንዳችም ቁምነገር እንደሌለ፣ ሕይወትን ከማሻሻል ውጭ ቅንጣት በጎነት እንደማይገኝ፣ ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለብንም።
ረሃብና መስኖ፣... ‘የሞት ሽረት’ ጉዳይ መሆናቸውን መገንዘብ እንደማለት’ኮ ነው።
በዚህ መሃል፣... ኢትዮጵያ፣ በግድብና በመስኖ እንዳትጠቀም፣ አለማቀፍ ዘመቻ ሲታወጅ ብንመለከት፤... በሕይወታችን ላይ አልተዘመተም እንላለን? ዘመቻው፣ ሚስጥራዊ ሴራ አይደለም። የዘመቻው ሰነድ፣ በዩኤን የእርዳታ ማስተባበሪያ ድረገፅ ላይ፣ ቦታ ተሰጥቶት፣ ፊት ለፊት ይታያል።
አስገራሚው ነገር፣ የዩኤን “የእርዳታ ማስተባበሪያ” ድርጅት፣ የዛሬ ሰላሳ ዓመት ገደማ የተቋቋመው፣ በኢትዮጵያ ሰበብ ነው - በ77 ዓ.ም ድርቅ። እስከዛሬም፣ ከድርጅቱ መደበኛ ስራዎች መካከልም፣ ‘ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ሚሊዮኖች ለረሃብ ተጋልጠዋል’ እያለ  የእርዳታ ጥሪ ማስተላለፍ ነው። (reliefweb.int/country/eth የሚለውን ድረገፅ መመልከት ይቻላል)። የእርዳታ ጥሪው፣ ከወር ወር፣ ከዓመት ዓመት አይቋረጥም።     
ከዓለማችን የመጨረሻ ድሃ አገራት አንዷ!
አለማወቃችን እንጂ፣ የዘንድሮው የረሃብ አደጋ፣ ድንገተኛ ‘ዱብዕዳ’፤... ወይም ያልተለመደ ጊዜያዊ አደጋ አይደለም። ቀድሞውንም፣ ከአደጋ የራቅንበት ዓመት የለም።
በጭፍን፣ “ሽራፊ የኢኮኖሚ እድገት አልተገመዘገበም” ለማለት ፈልጌ አይደለም። እንዲያውም፣ ሰሞኑን፣ የዓለም ባንክ ያሰራጨውን ሪፖርት መመልከት እንችላለን። እንደ አበባ፣ እንደ ርችት፣ የደመቀ የተንቆጠቆጠ ሪፖርት ነው።
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት፣ ልዩ እና አስደናቂ መሆኑን ይተነትናል - ይሄው አዲስ የዓለም ባንክ ሪፖርት። እናም፣ ከ15 ዓመት በፊት፣ “የዓለማችን ሁለተኛዋ ድሃ አገር” የነበረችው ኢትዮጵያ፣ ዛሬ በፈጣን እድገት ተሻሽላ፣ “የአለማችን፣ 11ኛዋ ድሃ አገር” ለመሆን እንደበቃች ሪፖርቱ ይገልፃል።   
ምን ለማለት ፈልጌ ነው? ድህነት ከመብዛቱ የተነሳ፣ “ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት” የሚል ሙገሳ ውስጥ እንኳ፣ የአገሪቱ ድህነት ጎልቶ ይታያል። ድንገት የተከሰተ ዱብዳ፣ አልያም ለከርሞ ብን ብሎ የሚጠፋ ‘ጊዜያዊ እንቅፋት’ አይደለም። የአገራችን የረሃብ አደጋም፣ እንደዚያው ነው።
አምናና ካቻምና፤ ዘንድሮና በሚቀጥለው አመት...
ከዘንድሮው የድርቅ አደጋ በፊትም ቢሆን፣ ከዓመት ዓመት፣ የእህል እርዳታ ወይም ድጎማ ካላገኙ፣ ኑሮን መቋቋም የማይችሉ የገጠር ነዋሪዎች፣ አስር ሚሊዮን ይሆናሉ።
“የምግብ ዋስት” ድጎማ
በአንድ ወገን፤ ‘ከጥር በኋላ፣ ጓዳቸው ይመናመናል’ ተብለው ለድጎማ የሚመዘገቡ ከ7 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አሉ። ድጎማ ካላገኙ፣ ኑሯቸው ይናጋል። እናም ከጥር እስከ ሰኔ ድረስ፣ የእህል ወይም የብር ድጎማ ይሰጣቸዋል - በየዓመቱ። “የምግብ ዋስትና ፕሮግራም” ይሉታል። ይሄ ብቻ አይደለም።
“ደራሽ እርዳታ”
ደራሽ እርዳታ፣... “ክፉኛ፣ ለረሃብ ተጋልጠዋል” ተብለው ለሚመዘገቡ ሰዎች የሚዘጋጅ እርዳታ ነው። የእነዚህ ተረጂዎች ቁጥር፣ በየዓመቱ፣ አነሰ ቢባል፣ ወደ ሦስት ሚሊዮን ገደማ ይሆናል።
በአጠቃላይ፣ በየዓመቱ፣ ቢያንስ ቢያንስ፣ 10 ሚሊዮን ሰዎች፣ ለረሃብ ይጋለጣሉ ማለት ነው። ለዚያውም፤ የዝናብ እጥረት በሌለበት ዓመት!
የዝናብ እጥረት ሲያጋጥምስ?
ድርቅ ከመጣ፣ የችግረኞችና የተረጂዎች ቁጥር እንደሚጨምር፣ የረሃብ አደጋውም እንደሚባባስ፣ ምን ጥርጥር አለው? የዝናብ እጥረትና ድርቅ ደግሞ፣ አልፎ አልፎ መከሰቱ እንደማይቀር ግልፅ ነው። እንዴት ይጠፋናል?
ያው፤ የዘንድሮ ዓይነት ድርቅ ሲከሰት፤ የዘንድሮ ዓይነት የረሃብ አደጋ መፈጠሩ፤ በጭራሽ ‘ዱብዳ’ አይደለም።
በእርግጥ፤ ከረሃብ አደጋ ርቀን የተጓዝን ይመስል፤ የዘንድሮውን አደጋ፣ ‘ጊዜያዊ እንቅፋት’ ሊያስመስል ይሞክራል - መንግስት። ነገር ግን፣ አደጋው፣ ‘ከስኬት ሆይሆይታ’ የሚያስተጓጉል፣ ‘ጊዜያዊ እንቅፋት’ አይደለም።
በተቃራኒው፣ ከአጠገባችን ርቆ የማያውቅ፣ ነባር አደጋ ነው። ‘ጊዜያዊ እንቅፋት ነው’ እያሉ መነዛነዝ ምን ዋጋ አለው? በየዓመቱ 10 ሚሊዮን ተረጂዎች ነበሩ። ዘንድሮ ወደ 15 ሚሊዮን ጨመረ። ማለትም፣... ‘ነባሩ አደጋ’ ነው ዘንድሮ የተባባሰው።
 በርካታ ተቃዋሚዎችም እንዲሁ፤ የረሃብ አደጋው፣ በኢትዮጵያ ያልነበረና፣... ድንገት መንግስት ጎትቶ ያመጣው፣ ‘ዱብዳ’ እንግዳ ያስመስሉታል።... ለነገሩ፤ በሚቀጥለው ዓመት፣ ዝናቡ ደህና ከሆነ፣ የረሃብ አደጋው፣ ትንሽ ይቃለላል። እናም፤ አደጋው ጨርሶ የጠፋ ያህል፣ መነጋገሪያ መሆኑ ይቀራል፤ ይረሱታል።
አደጋውን የምንረሳው ግን፤... የተረጂዎቹ ቁጥር፣ ከ15 ሚሊዮን ወደ አስር ሚሊዮን ስለሚቀንስ ብቻ ነው! አደጋው ካልከበደ በቀር፤ የመናቆሪያ ሰበብ ሊሆንልን ስለማይችል፤ እርግፍ አድርገን እንተወዋለን።
ለዘለቄታውስ?
በእስካሁኑ አያያዛችን የምንቀጥል ከሆነ፤ ከጥቂት ዓመታት በኋላ፣ እንደገና የዝናብ እጥረት መከሰቱና የረሃብ አደጋ መክበዱ አይቀርም። ያኔ፣ እንደገና፣ በውግዘትና በማስተባበያ፣ የመናቆር ጩኸት ይጋጋላል።... ግን አደጋው ቀለል ሲል፤ እንዘነጋዋለን፤... ያው፤ ተመልሶ እስኪባባስ ድረስ።
ማለቂያ የሌለው አዙሪት!
የዛሬውን ከባድ አደጋ ከማቃለል ጎን ለጎን፤ ለዘለቄታውም ማሰብ ካልጀመርን፣ ... ከገደሉ አፋፍ ለመራቅ ዘዴ ካላበጀን፣... እያሰለስን፣ ወደ ከባዱ አደጋ ስንመላለስበት... ይታያችሁ።
እናም፣ አደጋውን እንደ አዲስ፣ “ድንገተኛ ዱብዳ” እያስመሰልን እሪ የምንልበት፣ “ጊዜያዊ እንቅፋት” እያስመሰልን በማስተባበያ የምንነዛነዝበት አጋጣሚ ሲሆንልን አስቡት።
ለመሆኑ ከምር ይቆረቁረናል ወይ?
ከእርሻ ተሻግሮ በኢንዱስትሪ ለማደግና የስራ እድል ለመፍጠር ያልቻለ ኢኮኖሚ... የድህነት ኢኮኖሚ የመሆኑን ያህል፤በዝናብ ላይ ብቻ የሚተማመን እርሻ፣... የድህነት እርሻ ነው። የገደል አፋፍ ላይ የተንጠለጠለ ኑሮ፤ ቢበዛ ቢበዛ፣ ከእጅ ወደ አፍ ስለሆነ፤ትንሽ ዝናብ ሲዛባ፣ ወደ ከባድ የረሃብ አደጋ እንገባለን።
ጥያቄው እዚህ ላይ ነው። ‘የረሃብ አደጋ’፣ የፖለቲካ ቁማር መጫወቻ ካርድ መስሎ ካልታየን በቀር፣... ‘የሞትና የሕይወት ጉዳይ’ መሆኑን ከምር የምንገነዘብ ከሆነ፤ ተመፅዋችነት ከምር የሚቆረቁረን ከሆነ፤...  የኢንዱስትሪ፣ የግድብ፣ የመስኖ ‘ተቆርቋሪ’ መሆን የግድ አይደለም ወይ?    
ታዲያ፤ በኢትዮጵያ፣ የግድብ ግንባታ እንዳይጀመር፣ የተጀመረውም እንዲቋረጥ... ሰፊ ዘመቻ ሲካሄድ፣ ምነው አልቆረቆረን? የአለም ባንክ፣... ከዚያም የአፍሪካ ልማት ባንክ፣... ለግድብ ግንባታ አንዳችም ብድር ላለመስጠት ሲወስኑ፣ ያን ያህልም አላሳሰበንም።
ለምንድነው፣ ብድር የከለከሉት? “የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪ ነን” በሚል ነው። ‘የወንዝ ነባር ጎርፍ’፣ ‘የአካባቢውን ነባር ገፅታ’፣ ‘ነባሩ የእርሻ አሰራርና አኗኗር’፣...  
እንደ ድሮው ተጠብቆ መቀጠል አለበት። ግድብ ከተገነባ ግን፣ “ተፈጥሯዊ ያልሆነ”፣ “አርቴፊሻል ኃይቅ” ይፈጠራል በማለት ይቃወሙታል። መስኖ ከተዘረጋ፣ የድሮው እርሻና አኗኗር ይለወጣል በማለት ያወግዙታል።
በእርግጥም፣ መስኖና ግድብ፣ “ከአካባቢ ጥበቃ” እና “ከባህል ጥበቃ” ጋር ይቃረናል። ምን ጥርጥር አለው? ግድብና መስኖ የሚገነባው፤ ነባሩን አካባቢና አኗኗር ለመቀየር ነው። ... ለማሻሻል። ከሁለቱ፣ አንዱን መምረጥ የግድ ነው። አንድም፤ “የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪዎች” እንደሚነግሩን በነባሩ መንገድ፣ ረሃብተኛና ተመፅዋች ሆኖ መቀጠል ነው። አልያም፤ የረሃብ አደጋው ይቆረቁረናል የምንል ከሆነ፤ በመስኖ ከረሃብና ከተመፅዋችነት ለመውጣት ተጣጥረን ሕይወትን ለማሻሻል መምረጥ እንችላለን - የሕይወት፣ የመስኖ ተቆርቋሪነትን መምረጥ። ከየትኛው ነን?
ከጥቂት ሳምንታት በፊት፣ በኢትዮጵያ የግድብና የመስኖ ግንባታዎችን በመቃወም፣ ሂዩማን ራይትስ ዎች አለማቀፍ ዘመቻ ጀምሯል። ይሄ ይቆረቁረናል ወይ?
ወይስ፤ የዩኤን የእርዳታ ማስተባበሪያ ድረገፅ ላይ እንደምናየው፤ በአንድ በኩል የእርዳታ ጥሪ እየለፈፍን፤ ከዚሁ ጎን ለጎን፣ ረሃብተኛና ተመፅዋች ሆኖ መቀጠልን እንፈቅዳለን? ኢትዮጵያ፣ ግድብንና መስኖን እንዳትጠቀም ለመከልከል የተዘጋጀውን የዘመቻ ሰነድ ማስተጋባት ወይም በቸልታ መመልከት፣ ሌላ ትርጉምና ውጤት ሊኖረው አይችልም - ነባሩን ረሃብና ምፅዋት በፀጋ እንደመቀበል ነው።

Read 3163 times