Saturday, 28 November 2015 14:06

ብዙ ከያዘ ነገረኛ ትንሽ የያዘ ሀቀኛ ይስጥህ

Written by 
Rate this item
(22 votes)

    ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አባት፣ ወንድ ልጁን ይዞ፣ አህያውን ለመሸጥ ወደገበያ እየሄደ ነበር፡፡ መንገድ ላይ የሆኑ ኮረዶች እየሳቁ እያላገጡ፣
“እንደነዚህ አባትና ልጅ ያሉት ጅሎች በዓለም ላይ ታይተው አይታወቁም፡፡ በዚህ አቧራማ ጎዳና አህያው ላይ ወጥተው እየጋለቡ መሄድ ሲችሉ፤ በእግራቸው ይኳትናሉ!” አሉ። አባትየው ኮረዶቹ ያሉት ልክ ነው ብሎ አሰበ፡፡ ስለዚህ ልጁን አህያው ላይ አወጣውና እሱ በእግሩ መጓዝ ጀመረ፡፡ ጥቂት እንደተጓዙ የዱሮ ወዳጆቻቸው አዩዋቸው፡፡
እንዲህም አሉ፤
“ይሄን ልጅ በጣም አወማጠልከው፡፡ አንተን የሚያህል ሽማግሌ በእግሩ እየሄደ ይሄ ወጣት በአህያ መሄዱ ነውር ነገር ነው፡፡ “ኧረ በእግሩ ይሂድ፡፡ ወጣት ሮጠና አይደለም እንዴ?!”
አባት የዱሮ ወዳጆቹን ምክር ተቀበለ፡፡ ልጁን ና ውረድ ብሎ ሲያበቃ፣ በእሱ ቦታ ራሱ ፊጥ አለ፡፡ ብዙም ሳይሄድ እናቶችና ልጆቻቸው ብቅ አሉ፡፡ እነሱም፡-
“ምን ያለው ራስ - ወዳድ አባት ነው እባካችሁ! ራሱ ተዝናንቶ በምቾት እየጋለበ፣ ልጁን በእግሩ መከራ ያሳየዋል!” እያሉ ሲሳለቁ አባትየው ሰማ፡፡ ይሄንንም አመዛዘነና ትችቱን ተቀብሎ ልጁን ከጀርባው አፈናጠጠው፡፡
አሁንም ብዙም ሳይጓዙ መንገደኞች ያገኟቸዋል፡፡ እነሱም፤ “ለመሆኑ ይቺ አህያ የራስህ ንብረት ናት፤ ወይስ እንዲያው ከጫካ ያገኘሃት የዱር አውሬ ናት”
አባትየውም፤ “ኧረ የራሴ ናት! እንዲያውም እዚህ ታች ገበያ ልሸጣት አስቤ ነው የምሄደው”
“ኧረ የሰማያቱ ያለህ! እዚያ ስትደርስ‘ኮ አንደኛዋን ሞታ ነው የምትገኘው! ይልቁንም ተሸክማችሁ ብታደርሷት ነው የሚሻለው!
አባትየው - “ዕውነታችሁን ነው!” ብሎ ምክሩን ተቀብሎ ሁለቱም ወረዱና አህያዋን አሰሩዋትና በትልቅ እንጨት አንጠለጠሉ፡፡ ወደሚቀጥለው ከተማም ደረሱ፡፡
አባትና ልጅ አህያ ያንጠለጠሉበትን ትርዒት ያየ የከተማው ሰው ሁሉ፤ ግማሹ ዕብድ ናቸው አለ፡፡ ግማሹም በዱላ ይመቷቸው ጀመር፡፡ አህያውን ተሸክመው በወንዝ ላይ ወዳለው ድልድይ ሄዱ፡፡ አህያው የህዝቡ ጩኸት በእንግዳ ሆኖበት እየተንፈራገጠ፣ የታሰረበትን ገመድ በጠሰና ተስፈንጥሮ ወንዙ ላይ ወደቀ፡፡ በዚያው ሰምጦ ሞተ፡፡ ዕድለ ቢሱ አባት በመከራ ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡ ሁሉንም ሰዎች አረካለሁ ብሎ አንዱንም ሰው ሳያረካ፤ አህያውንም አጥቶ ቀረ።
*           *            *
አማካሪን ሁሉ ከየአቅጣጫው እንዲያውም ተቃራኒውን ሀሳብ ጭምር፣ መስማትና መቀበል፣ ማታ ማንም ፍሬ ሳያፈራ እንዲቀር ያደርገዋል፡፡ በየጊዜው የሚለዋወጥ አቋም አንዱንም በወግ ለመያዝ ሳንችል እንድንቀር ያደርገናል፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ አንዱን በሥነ ስርዓት ለፍፃሜ ሳናበቃ ሜዳ ላይ እንድንወድቅ እንሆናለን፡፡ ዕቅደ ብዙ መሆን ብቻውን ከግብ አያደርስም፡፡ ይልቁንም ቅደም ተከተል አስይዘን፣ የከፋውን ችግር መጀመሪያ መፍታት፣ ምንም ይሁን ምን ችግርን አለመሸሸግ፣ በግልፅ ድክመትን ማመን፣ አለቃ እንዳይቆጣ ተብሎ እቅጩን አለመናገርን ማስወገድ፣ ሀገርን ከፓርቲ፣ ከቡድን ወይም ከግለሰብ ጥቅም ማስቀደም ወዘተ መልካም አካሄድ ነው፡፡ ከሁሉም ቁልፍ ነገር በዕውቀት ማመን ነው። በዕውቀት ላይ የተመሰረተ የሀገር ግንባታ ርዕዩ ሩቅ ይሆናል፡፡ የተገነባው እንዳይፈርስ ባለቤት ሊኖረው እንደሚገባ አለመዘንጋት ነው፡፡ የተሰራው መንገድ፣ ባቡሩ፣ ግድቡ ወዘተ. በኃላፊነት የሚይዛቸው ከወራት የዘለለ ሀገር ወዳድነት ያለው አመራር ይሻሉ፡፡
ድርቁን እኛው በኛው እንመክተው ካልን ቁርጠኝነታችንን በውል መፈተሽ ደግ ነው፡፡ ምግብና ሌላ እርዳታ በአግባቡ መዳረሱን ለማየት ረዥም መንገድ ተጉዞ የደረሰው ባቡር “ላሜ ወለደች” ያሰኘን ቢሆንም፤ ቀጣዩ ተግባር ስኬታማ እንዲሆን ጠንቃቃ ትኩረት ይጠይቃል፡፡
የሀገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት ነገር ሁሌም አሳሳቢ እንደሆነ ነው፡፡ እንኳን ለአዘቦቱ ሰው፣ ለክቱ የኢኮኖሚክስ ባለሙያም አወዛጋቢና አነጋጋሪ ነው! ለኢኮኖሚው ዕድገት ችግር የሚሆነው የሰለጠነ የሰው ኃይል ማነስ ነው የሚሉ ያሉትን ያህል፣ የሰው ኃይል እጥረት አሳሳቢ አይደለም የሚሉም አሉ፡፡ መዋቅራዊ ለውጥ ያስፈልጋል የሚሉና ለጊዜው አያስፈልግም የሚሉም ይኖራሉ፡፡ ከገጠር ወደ ከተማ ፍልሰት፣ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ሥርዓተ ኢኮኖሚ ስንሸጋገር፣ አይቀሬ ክስተት ይሆናል ሲባል የህዝብ ብዛት ፍንዳታ ምን መፍትሔ ይኖረው ይሆን ብሎ መጠየቅም ያባት ነው፡፡ የአገሪቱ የቅጥር ሁኔታም አሳሳቢ ስለመሆኑና ለውጥ ስለማስፈለጉ ብዙ እየተነገረ፣ “ቄሱም ዝም፤ ዳዊቱም ዝም” እንደሆነ አለ፡፡
አሁንም ከዘርፈ ብዙ ችግሮቻችን አኳያ ቅደም  - ተከተል ማበጀት ወሳኝ ነው፡፡ ሳይታሰብ ቅድሚያ የተሰጠው፣ ግን ሊዘገይ ይችል የነበረ ጉዳይ ካለ፤ ቆም ብሎ መፈተሽ ተገቢ ነው። ባንድ ወቅት አሳሳቢ የመሰለን ችግር በሌላ ወቅት ቀላል ሆኖ ሊገኝ እንደሚችል ማስተዋል ያሻል፡፡ መሥሪያ ቤቶች “በጉዳይ - ገዳይ” እጅ ላይ እየተንሳፈፉ፣ ቀልጣፋ የሥራ አመራር አለ ለማለት ያዳግታል፡፡ አገራችን “አንዱ ያለማ አንዱ ያደለማ” አጣብቂኝ ውስጥ ናት፡፡ በዚህ ዓይነት ወደፊት ፈቀቅ እያልን ነው ብንል የዋህነት ያለብን ያስመስላል፡፡ በየቢሮው የምናየውና በአደባባይ የምንሰማው መራራቅ የለበትም፡፡ አንዱ በታታሪነት ደፋ - ቀና ሲል ሌላው በዳተኝነት “ከልኩ አያልፍም” እያለ የምንጓዘው ጉዞ እየፃፉ እንደማጥፋት ነው፡፡ የሩቅ ዕቅዳችንንና የረዥም ጊዜ ራዕያችንን እያወደስን የቅርብ - የቅርብ ፍሬዎቻችንን በወጉ ሳንሰበስብ ከቀረን፣ ከአፍ እስከገደፉ የሞላውን ወሬ ነጋሪና ጉዳይ አስፈፃሚ በጊዜ ካልገደብን፤ “እሾክ ብቻ ሆነ እግሬን ብዳብሰው እንዴት መራመጃ መሄጃ ያጣል ሰው” እንደሚባለው ነው የምንሆነው፡፡ ከልብ አገርን ማሳደግ የምንሻ ከሆነ፣ “ብዙ ከያዘ ነገረኛ፣ ትንሽ የያዘ ሀቀኛ ይስጥህ” የሚለውን ተረት ልብ እንበል!

Read 8351 times