Saturday, 28 November 2015 14:13

ባለ መንታ እራስ አበባ

Written by  ደራሲ፡- ጆን ስታንቤክ ተርጓሚ፡- አሸናፊ አሰፋ
Rate this item
(7 votes)

ክረምቱ ያመጣው ግራጫ የደመና ቡልኮ የሳሊናስ ሸለቆን ጀቡኗታል፡፡ ሳሊናስ ከሰማዩም፣ ከሌላው አለምም በደመናው ተከልላለች፡፡ በታህሳስ ወትሮም ፀሐይ የለችም፡፡
የፀጥታ ጊዜ ነው፡፡ የጥበቃ ጊዜ ነው፡፡ አየሩ ለሰስ ያለ ቀዝቃዛ ነው፡፡ ቀለል ያለ ነፋስ ከደቡብ ምዕራብ ይነፍሳል፡፡
ሄነሪ አለን እርሻው ላይ ብዙም የሚሠራ ሥራ የለውም፡፡ ለድርቆሽ የሚሆነው ሳር ታጭዶ፣ ተከምሯል። የፍራፍሬ እርሻው ለሚጠበቀው ዝናብ ዝግጁ እንዲሆን ታርሷል፡፡
ኤሊሳ አለን እንደ ተለመደው የአበባ ተክሎቿን እየተንከባከበች ነው፡፡ ባሏ ሄንሪ አለን ሱፍ ከለበሱ ሁለት ሰዎች ጋር ትራክተሩ የሚቆምበት መጠለያ ውስጥ ሆኖ እያወራ ነው፡፡ ሶስቱም አንድ፣ አንድ እግራቸውን ባለ ሁለት በሯ ፎርድ ላይ ሠቅለዋል፡፡ እያጨሱ ነው፡፡
ኤልሳ አየት አድርጋቸው ስራዋን ቀጠለች፡፡ ሰላሳ አምስት ሆኗታል፡፡ ፊቷ ቀጭንና ጠንካራ ነው፡፡ አይኖቿ የውሃ እንክብል ይመስላሉ፡፡ አበቦቹን ለመንከባከብ የለበሰችው ልብስ ውጥር አድርጓታል፡፡ ያደረገችው ኮፍያ የወንድ ነው፡፡ የተጫማችው ከስክስ ጫማ ነው፡፡ የአበቦቹን ቁርጥራጮች፣ የአፈሩን ማለስለሻ፣ የአበቦቹን ዘሮችና ሰንጢዋን እንዲይዝላት አራት ኪሶች ያሉት ሽርጥ ለብሳለች፡፡ እጅግ ወፍራም የቆዳ ጓንት አድርጋለች፡፡
አደገኛ ስለት ባለው አጭር መቀስ ባለፈው አመት የተከለቻቸውን የክሪዝአንተመም አገዳዎች እየቆረጠች ነበር፡፡ አልፎ፣ አልፎ ቀና እያለች ባሏንና ሁለቱን ሰዎች አየት ታደርጋቸዋለች፡፡ ፊቷ ውብ ነው፤ ብስለት ይነበብበታል፤ መጓጓትም አለበት፡፡ መቀስ አያያዟና አጠቃቀሟ ይህንኑ ይመሰክራል፡፡ ትኩረትና ሀይሏ የበዛ ነው፡፡ የክሪዝአንተመም ስሮች ሀይሏን መቋቋም አልቻሉም፡፡
(Chrysanthemums፡- ሁለትና ከዚያም በላይ እራስ ያለው ለጌጥና ለመድሃኒት መቀመሚያነት የሚውል አበባ ነው-ተርጓሚው፡፡)
ፊቷ ላይ የፈሰሱትን ፀጉሮች ወደ ኋላ በእጆቿ ስትመልስ፣ ጉንጯን በእርጥብ አፈር ለወሰችው፡፡
ከጀርባዋ ባለ ነጭ ቀለሙ ቤታቸው ይታያል፡፡ ፅድት ተደርጎ ተጠርጓል፡፡ መስኮቶቹ በደንብ ተወልውለዋል። መግቢያው ላይ ንጹህ ምንጣፍ አለ፡፡ ቀና ብላ ወደ እንግዶቹ አየች፡፡ እንግዶቹ ወደ መኪናቸው እየገቡ ነበር፡፡ ስራዋን ጨርሳለች፡፡ ትኩስ እየበቀሉ ያሉት ክሪዝአንተመሞች አምረው ይታያሉ፡፡ የአበቦቹን ስፍራ ለእነሱ ፀር ከሆነ ነገር ሁሉ አፅድታለች፡፡
የባሏ ድምፅ አስደነገጣት፡፡ ኮቴውን አጥፍቶ፣ ሳትሰማው አጠገቧ ደርሷል፡፡ አበቦቿን ከከብቶች፣ ከውሻና ከዶሮዎች ለመጠበቅ የሠራችውን አጥር ተደግፎ ነበር፡፡
“ዛሬም እነሱው ላይ ነሽ” አላት፡- “አዲስ የሚበቅሉልሽ አበቦች ጠንካራ እንደሚሆኑ ካሁኑ መናገር ይቻላል፡፡”
ኤልሳ ቀና አለች፡፡ ስራዋን ስትጨርስ አውልቃው የነበረውን የእጅ ጓንት መልሳ አደረገችው፡፡
“አዎ፤ በሚቀጥለው አመት የሚደርሱት አበቦች ጠንካሮች ነው የሚሆኑት፡፡” አለች፡፡ ድምጿ ውስጥ ትንሽዬ አንጀባ አለች፡፡
“ሥራ ታውቂያለሽ፤ የስራ ተሰጥኦ አለሸ፤ ይሳካልሽማል፤ የነካሽው ሁሉ ውብ ይሆናል፡፡” አለ ሄንሪ፡- “አምና ያበቀልሻቸው ቢጫዎቹ ክሪዝአንተመሞቸ ወደ ጎን ሀያ ስድስት ሴንቲ ሜትር ያህል ነበሩ፡፡ ወደ ፍራፍሬ እርሻው ጎራ ብለሽ ፍራፍሬዎቹን ነካ፣ ነካ ብታደርጊያቸው እነሱን የሚያካክሉ ፖሞች ማብቀል እንችል ነበር፡፡”
አይኖቿ ጥብብ አሉ፡- “ምናልባት የፖሙም እንደ አበቦቹ ይሳካልኝ ይሆናል፡፡ የተሰጥኦ ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡ እናቴም እንዲሁ ነበረች፡፡ ምንም ነገር አንስታ ከመሬት ጋር ታገናኘው ብቻ-ይበቅላል፡፡ የአትክልተኛ እጆች የምትለው ነገር ነበራት፡፡ የአትክልተኛ እጆች ያለው ሰው ያውቀዋል፡፡ ”
“ይኸው አንቺ በአበቦችሽ አስመስክረሻል፡፡” አላት፡፡
“ሄንሪ፣ ታወራቸው የነበሩት ሰዎች እነማን ነበሩ?”
“እ? አወራቸው የነበሩት ሰዎች? ስለ እነሱ ልነግርሽ ነው የመጣሁት እንደውም፡፡ ከዌስተርን ስጋ ኩባንያ ነው የመጡት፡፡ ሶስት አመት የሞላቸውን ሰለሳውን ወይፈኖች ሸጥኩላቸው፡፡ የጠየቅሁትን ዋጋ ነው የከፈሉኝ ማለት ይቻላል፡፡”
“ጥሩ፡፡” አለች ኤሊሳ፡- “ይሁንልህ እስኪ፡፡”
“እና ምን አሰብኩ መሰለሽ” ብሎ ቀጠለ ሄንሪ፡- “ዛሬ ቅዳሜም አይደለ እና ሳሊናስ ወስጄሽ የደስ ደስ እራት ልጋብዝሽ አስቤያለሁ፡፡ እራት ከበላን በኋላ ፊልም እናያለን፡፡ ጥሩ ሀሳብ ይመስለኛል፡፡ ”
“ጥሩ ነው፡፡” አለች፡- “ጥሩ ሃሳብ ነው፡፡”
“የቦክስ ፍልሚያም አለ ዛሬ ምሽት፡፡ እንዴት ነው ፊልሚያውን የማየት ፍላጎት አለሽ ?” አለ ሄንሪ እየቀለደ፡፡
“ኸረ በፍጹም!” አለች ትንፋሽ ባጠረው ድምፅ፡-“ እኔ ፍልሚያ አልወድም፡፡”
“እየቀለድኩ ነው ኤሊሳ፡፡ ፊልሙን እናያለን፡፡ እስኪ ቆይ፤ አሁን ስምንት ሰዓት ሆኗል፡፡ የሸጥኳቸውን ወይፈኖች ከሚግጡበት አምጥቼ ለሰዎቹ ማድረስ አለበኝ፡፡ ከስኩቲ ጋር አብረን እንሄዳለን፡፡ ግፋ ቢል ሁለት ሰዓት ቢወስድብን ነው፡፡ ከዚያ እንደተመለስኩ፣ እ…አስራ አንድ ሰዓት አካባቢ ሳልመለስ አልቀርም፤  ወደ ከተማ ሄደን ኮሚናስ ሆቴል እራት እንበላለን፡፡ መልካም ሀሳብ አይደለምን? ወደድሽው?”
“መልካም ነው፡፡ አንዳንዴ እንኳ ከቤት ወጣ ብሎ መመገብ ጥሩ ነው፡፡”
“እሺ፡፡”     
“የቀሩኝን አበቦች መልሼ እስክተክላቸው በቂ ጊዜ ይኖረኛል ብዬ አስባለሁ፡፡” አለችው፡፡
ከአፍታ ከቆይታ በኋላ ባሏ ስኩቲን ሲጣራ ሰማችው። ከሌላ አፍታ ቆይታ በኋላ በፈረሶቻቸው ከብቶቹ ወደ ሚግጡበት ሲሄዱ አየቻቸው፡፡
* *  *
ጎዳናው ላይ የሚንሴጣሴጡ የሰረገላ ጎማዎችና የሚያዘግሙ እንሰሳዎች ድምጽ ተሰማ፡፡ ኤሊሳ ቀና ብላ ተመለከተች፤ የሚገርም ሰረገላ በሚገርም ሁኔታ እየተጎተተ  ሲመጣ አየች፡፡ በክብ ሸራ የተሸፈነ ሰረገላ ነው፡፡ በከሲታ ፈረስና በነጭና በግራጫ በተዥጎረጎረች ውርንጭላ እየተጎተተ ነው፡፡ ችምችም ያለ ፂም ያለው ሰውዬ ነው ሾፌሩ፡፡ በሰረገላው የፊት ጎማዎች መሀል አንድ ከሲታና ዲቃላ ውሻ፣ እያንጎላጀ፣ ኩስ ኩስ ይላል፡፡
የሰረገላው ሸራ ላይ ሰው ቢሆኑ ኖሮ፡- ጀዝባ፣ አሿፊ፣ አጭበርባሪ እና ጨካኝ ሊባሉ በሚችሉ ፊደላት ይህ ተፅፏል፡- “ማሰሮ፣ መጥበሻ፣ ሰንጢ፣ መቀስ፣ የማጨጃ መሺን”፡፡ ከስሩ “በመደበኛ ዋጋ” የሚልም ፅሁፍ አለ፡፡
ኤልሳ በእብዶች የተሰራ የሚመስለውን ሰረገላ ሲያልፍ ልታየው ቀና አለች፡፡ አላለፈም፡፡ ተገረሚ ሲላት እሷ ወደ አለችበት ታጠፈ፡፡ ቀፋፊ ድምፁን እያሰማ ወደአለችበት መጣ፡፡ ኮስማናው ውሻ ከነበረበት ወጣ፡፡ የቤቱ ሁለት ውሾች እየሮጡ መጡበት፡፡ ሶስቱም ውሾች ጭራቸውን እየቆሉ፣ ቀጥ ብለው፣ በክብርና በኩራት እርስ በእርስ ተሻተቱ፡፡ ሰረገላው የኤሊሳ የሽቦ አጥር ጋ ሲደርስ ቆመ፡፡ የባለ ሰረገላው ውሻ የሀይል አስላለፉን አይቶ፣ በቁጥር መበልጡን ተገንዝቦ  ውሾቹን እንደማይችላቸው ገባው፡፡ ፀጉሩን አቁሞ፣ ጥርሶቹን አግጦ ወደ ነበረበት ተመለሰ፡፡
ባለ ሰረገላው፡-“ቀላል ውሻ እንዳይመስልሽ፤ ሲነሳበት እኔ ነኝ ያለ ውሻ አይችለውም፡፡” አላት፡፡
ኤልሳ ሳቀች፡፡
“አዎ ያስታውቃል፡፡ መቼ፣ መቼ ነው ግን የሚነሳበት?” አለች ሳቋን ሳታቋርጥ፡፡ ሰውየው የኤልሳ ሳቅ ተጋብቶበት ሳቀ፡፡
“ደግነቱ ብዙ ጊዜ አይነሳበትም፡፡” እያለ ከሰረገላው ወረደ፡፡ ፈረሱና ውርንጭላዋ እንደ ጠወለገ አበባ አንገታቸው ድፍት አለ፡፡
ሰውየው እጅግ ግዙፍ ነው፡፡ ፀጉሩና ፂሙ መሸበት ቢጀምሩም የሸመገለ አይመስልም፡፡ የለበሰው ጥቁር ሱፍ ነትቧል፤ በዚያም ላይ በግራሶ የተጨማለቀ ነው፡፡ ሳቁን ሲያቆም ፊቱ ላይ ምንም አይነት የፈገግታ ዱካ አልቀረም፡፡ ፊቱም አይኖቹም ከቅፅበት በፊት ይስቅ የነበረ ሰው ፊትና አይኖች አይመስሉም፡፡ አይኖቹ ጥቋቁር ሆነው፤ የከባድ መኪና ሹፌርና የመርከበኞች አይን ላይ የሚታየው ቁዘማ ይነበብባቸዋል፡፡ አጥሩ ላይ ያሳረፋቸው እጆቹ ተሰነጣጥቀዋል፤ ስንጥቆቹ ጥቋቁር ናቸው፡፡ በእርጅና የተጎሳቆለውን ኮፍያውን አወለቀ፡፡
“የተለመደው መንገዴን እየተከተልኩ አይደለም፡፡” አለ ሰውየው ፡- “ይህ ጥርጊያ መንገድ ወደ ሎስ አንጀለስ ወደ ሚወስደው ዋና ጎዳና ያወጣኝ ይሆን?”
ኤልሳ ተነስታ ቆመች፡፡ መቀሷን ሽርጧ ውስጥ ከተተችው፡- “አዎ፤ ይወስድሀል፤ በዚህ በወንዙ በኩል ከሄድክ ወደ ዋናው ጎዳና ያወጣሀል፡፡ ሰረገላህን  የሚጎትቱት ክቡራን ግን ችለው መልካውን የሚሻገሩት አይመስለኝም፡፡”
“ስንት ነገር እንደተወጡና መወጣት እንደሚችሉ ብነግርሽ አታምኚኝም፡፡” አለ ሰውየው በሀይለ ቃል፡፡
“ሲነሳባቸው ማለት ነው? መቼ ነው እነሱ ደግሞ የሚነሳባቸው፡፡” አለች ኤሊሳ፡፡
ፊቱ ላይ ትንሽዬ ፈገግታ በፍጥነት ተወልዳ በአጭሩ ተቀጨች፡- “ሲነሳባቸው ነዋ፡፡ ሲነሳባቸው ይነሳባቸዋል።”
እጆቹን ከሽቦ አጥሩ ላይ አንስቶ ጧ አድርጎ አስጮሃቸው፡- “ይኸውልሽ የኔ እመቤት አልቸኩልም። በየአመቱ ከሲአትል ሳንዲያጎ እመላለሳለሁ፡፡ ነጠላ ጉዞው ብቻ ስድስት ወር ይወስዳል፡፡ ህይወቴን የፈጀሁት እንዲያ ነው፡፡ በአሁኑ ጉዞዬ ምቹ አየር ያለውን መንገድ ለመከተል ወስኛለሁ፡፡”
ኤልሳ ጓንቶቿን አውልቃ መቀሱ ያለበት የሽርጧ ኪስ ውስጥ ወሸቀቻቸው፡፡ ሳይሸፈኑ ያመለጡ ፀጉሮች ፍለጋ ያደረገችውን የወንድ ኮፍያ ዳበስ አደረገችው፡፡
“የሚገርም ህይወት ነው፡፡ አሪፍ ሳይሆን አይቀርም።”  አለች፡፡
ምስጢር እንደሚናገር በአጥሯ ላይ ወደ ፊት ሰገግ አለ፡- “የሰረገላው  ሸራ ላይ የተፃፈውን  ያየሽ ይመስለኛል። ማሰሮዎች አድሳለሁ፤ ሰንጢና መቀሶች እስላለሁ፡፡ የሚታደሱ ወይ መሳል የሚያስፈልጋቸው እቃዎች አሉሽ?”
“ውይ! የሉኝም፡፡” አለች በፍጥነት፡- “አንድም የሚታደስ እቃ የለኝም፡፡”
“ለማደስ አስቸጋሪዎቹ መቀሶች ናቸው፡፡” አለ ሰውየው ፡- “አብዛኞቹ ጠጋኞች እናድሳለን ብለው የበለጠ ያበላሹዋቸዋል፡፡ እኔ አንድም አውቅበታለሁ፤ በዚያም ላይ ልዩ መሳሪያ አለኝ፡፡ ለመሳሪያዬ የፈጠራ ባለቤትነቴን የሚገልጽ ሰርተፊኬት ተሰጥቶኛል፡፡ ተአምረኛ መሳሪያ ናት፡፡”
“የኔ መቀሶች ሁሉም በጣም ስል ናቸው፡፡”
“እንግዲያውስ የተበሱ ወይም የተጣመሙ ማሰሮዎች ፈልጊ፡፡” አለ በቁም ነገር፡- “አዲስ አድርጌ ቁጭ አደርግልሻለሁ፤ ስለዚህ አዲስ መግዛትሽ ይቀራል። ለአዲሶቹ የምታወጪውን ወጪ ያስቀርልሻል፡፡ ቁጠባ ማለት እንዲህ ነው፡፡”
“የለኝም፡፡” አለች፡- “ምንም የሚታደስ እቃ እንደሌለኝ ነገርኩህ እኮ፡፡”
ፊቱን የተጋነነ ሀዘን አለበሰው፡፡ ድምፁን የንጭንጭ ቃና አስያዘው፡- “ዛሬ አንዳችም ነገር አልጠገንኩም። ስለዚህ እራት የሚባል ነገር ላላገኝ ነው፡፡ ችግሩ በምን መሰለሽ የተከሰተው፣ ዛሬ የወትሮውን መንገዴን ቀይሬያለሁ፡፡ እንዲያ ባይሆን ኖሮ የሚሰራ ነገር አላጣም ነበር፡፡ በማዘወትረው መንገድ ላይ፣ ከሲያትል እስከ ሳንዲያጎ ድረስ ያሉትን ነዋሪዎች በሙሉ አውቃቸዋለሁ። እቃቸውን ከእኔ ሌላ ለማንም አያስጠግኑም፡፡ በቅናሽ ነው የምጠግንላቸው፡፡”  
“አዝናለሁ፡፡” አለች ኤሊሳ ብስጭት ባለ ሁኔታ፡- “ምንም የሚጠገን ነገር የለኝም፡፡”  
አይኖቹን ከኤልሳ ላይ አነሳና ያሉበትን ቦታ መቃኘት ያዘ፡፡ አካባቢውን ሲያስሱ የነበሩት አይኖቹ ክሪዝአንተመምቹን ሲያዩ ቆሙ፡- “እነሱ ተክሎች ምንድናቸው የእኔ እመቤት?”
ኤሊሳ ጥያቄውን ስትሰማ ንዴቷና አልረታ ባይነቷ ከፊቷ ላይ በነው ጠፉ፡- “እነዚህ ክሪዝአንተመም የሚባሉ አበቦች ናቸው፤ ባለ ነጭ ቀለምም አሉ፤ ቢጫዎችም አሉ። እኔ የምተክላቸው ክሪዝአንተመሞች እዚህ አካባቢ ያሉ ከሚያበቅሏቸው ሁሉ የላቁ ናቸው፡፡ ረዣዥም ናቸው፡፡”  
“ባለረዥም አገዳ አበቦች ናቸው ልበል? ምን እንደሚመስሉ ታውቂያለሽ? የሚትጎለጎሉ ባለ ቀለም ጭሶች ነው የሚመስሉት፡፡”
“ልክ ነህ፡፡ አገላለፅህ ድንቅ ነው፡፡”
“ሽታቸው ግን መጥፎ ነው፤ ላለመዳቸው ሰው ያስጠላል፡፡” አለ፡፡
“መጥፎ ሽታ አይደለም፡፡ ጠንከር፣ ቆፍጠን፣ መረር ያለ ሽታ ነው፡፡” አለች ጠንከር፣ ቆፍጠን፣ መረር ባለ ሁኔታ፡- “እንጂ ፈፅሞ መጥፎ ሽታ አይደለም፡፡”
ንግግሩን ወዲያው አስተካከለ፡- “ነገሩን አልኩ እንጂ እኔማ ሽታቸውን ወድጄዋለሁ፡፡”
“በዚህ አመት የፈኩት አበቦች ሀያ ስድስት ሴንቲ ሜትር ስፋት ነበራቸው፡፡” አለች፡፡
ሰውየው በአጥሩ ላይ የበለጠ አስግጎ፡- “ይኼውልሽ ወዲህ ወደምሄድበት መንገድ ላይ አንዲት የሚገርም የአትክልት ቦታ ያላት ሴት አውቃለሁ፡፡ የአትክልት ቦታዋ እስከዛሬ አይተሻቸው ከምታወቂያቸው የአትክልት ቦታዎች ሁሉ ይልቃል፡፡ ከክሪዝአንተመም በቀር ሁሉም አይነት አበቦች አሉዋት፡፡ ባለፈው ጊዜ ከነሀስ የተሰራ የእጅ ማስታጠቢያ ስጠግንላት (ከባድ ስራ ነበር፣ ሰውየው እኔ ነኝ እንጂ) በመንገድህ ላይ ካሉት ቤቶች በአንዱ ምርጥ የሆኑ ክሪዝአንተመሞች ካገኘህ እባክህ  አምጣልኝ ብላኛለች፡፡ የእውነት እንዲያ ብላኛለች፡፡”
የኤልሳ አይኖች በአንዴ ንቁና ጉጉ ሆኑ፡- “ያልካት ሴትዮ ስለክሪዝአንተመሞች ብዙ የምታውቅ አይመስለኝም፡፡ ክሪዝአንተመሞቹን ከፍሬያቸውም ማብቀል ይቻላል፤ እንዲህ እንደኔ አይነት ችግኞች ብታገኝ ደግሞ ነገሮች በእጅጉ ይቀሉላት ነበር፡፡”
“ዋ!” አለ፡- “እኚህን መሳይ ችግኞች አግኝቼ ልወስድላት አልችልማ፡፡”
“እንዴታ! ትችላለችህ እንጂ!” አለች ኤሊሳ ከፍ ባለ ድምፅ፡- “በአትክልት መትከያ አድርጌ እሰጥሃለሁ፡፡ ስር ሲያበቅሉ በቀላሉ የአትክልት ቦታዋ ላይ ልትተክላቸው ትችላለች፡፡”
“በጣም ነው ደስ የሚላት፡፡ አበቦቹ ያምራሉ ብለሽኛል አይደል?”
“እጅግ ውቦች ናቸው፡፡” አይኖቿ አበሩ፡፡ ኮፍያዋን አውልቃ የሚያምር፣ ጥቁር ፀጉሯን ነሰነሰችው፡- “ና ወደ አትክልት ስፍራው ግባ፡፡”
ወደ ቤቷ ጀርባ ሮጣ ሄደች፡፡ ትልቅ ቀይ የአበባ መትከያ ይዛ ተመለሰች፡፡ መሬት ላይ ተንበርክካ አሸዋማውን አፈር በእጆቿ እያፈሰሰች የአበባ መትከያው ውስጥ አደረገች፡፡ የእጅ ጓንቷን ማድረግ ረስታለች፡፡ አሸዋማውን አፈር ሞልታ ከጨረሰች በኋላ ትንንሽዬዎቹን ችግኞች ተከለቻቸው፡፡
“ይኼውልህ አሁን እምነግርህን አስታውስህ ለሴትዮዋ እንድትነግራት ልብ አድርገህ  አድምጠኝ፡፡ እንዳትረሳ፡፡”  
“እሺ፤ ለማስታወስ እሞክራለሁ፡፡”
ክሪዝአንተመሞቹ እንዴት መተከል እንደለአባቸው፣ መቼ እንደሚፈኩ፣ መወሰድ ያለበትን ጥንቃቄ አብራራችለት፡፡ እዚህ ጋ ግራ በመጋባት አይነት ንግግሯን ቆም አደረገች፡- “በጣም ጥንቃቄ የሚጠይቀው ዘር መረጣው ነው፡፡ እንዴት እንደማስረዳህ አላውቅም። ቆይ ልሞክር፡፡ የአትክልተኛ እጆች ሲባል ሰምተህ ታውቃለህ?”
“ሰምቼ የማውቅ አይመሰለኝም እመቤቴ፡፡”
“ነገርየውን ዘርዝሮ ለማስረዳት ይከብዳል፡፡ የሚፈጥረውን ስሜት ነው ልነግርህ የምችለው፡፡ ጣቶችህ ከፍሬዎቹ ጋር፣ ከእምቡጦቹ ጋር የሚፈጥሩት ትውውቅ አለ፡፡ ቀሽሙን ፍሬ ስትመርጥ ጣቶችህ ይነግሩሀል፡፡ መረጣውን ስታካሂድ ሁለመናህ ጣቶችህ ላይ ይሆናል። ያንተ ድርሻ የሚሆነው ጣቶችህ መረጣውን ሲያደርጉ መመልከት፣ መታዘብ ብቻ ነው፡፡ ስራውን የሚሰሩት ጣቶችህ ናቸው፡፡ አንተ ስሜቱ ይደርስሃል፤ ልክ መሆን አለመሆናቸውን ስሜትህ ይነግርሃል፡፡ ምርጥ ምርጡን፣ መረጥ መረጥ ነው፡፡ አንዲትም ስህተት አይሰሩም፡፡ ከተክሉ ጋር በጣም ይናበባሉ፤ ይግባባሉ፡፡ የምነግርህ ገባህ? ጣቶችህና ተክሉ እውቂያ ይፈጥራሉ፡፡ ሁሉ ነገር ጣቶችህን አልፎ እስከ ክንዶችህ ድረስ ይሰማሃል፡፡ ጣቶችህ የጥናት ጊዜያቸውን ጨርሰው አዋቂ የሚሆኑበት ደረጃ ደርሰዋል ማለት ነው፡፡ አዋቂ ሆነዋል፤ ጥሩውን ከመጥፎው ዘር ለይተው ያውቃሉ፡፡ አዋቂ እንደሆኑ አንተም ይታወቅሀል፡፡ በዚህ ጊዜ በምንም ተአምር አትሳሳትም፡፡ አግኝተኸኛል? የምልህ ገብቶሃል?”
ይህን ስትናገር አሁንም መሬት ላይ እንደተንበረከከች ናት፡፡ ጡቶቿ በስሜት ከፍ ዝቅ ይላሉ፡፡ እሷ ሽቅብ፣ ሰውየው ቁልቁል እየተያዩ ነው፡፡
የሰውየው አይኖች እንደ መጥበብ አሉ፡፡ በሀፍረት አይኖቹን ካሉበት አንስቶ አሻግሮ ማየት ጀመረ፡- “ያልሺው ሳይገባኝ አይቀርም፡፡” አለ፡- “አልፎ አልፎ ስረገላዬ ውስጥ ማታ፣ ማታ …”
ኤልሳ አቋረጠችው፡- “አንተ እንደምትኖረው ኖሬ ባላውቅም የምትለው ግን ይገባኛል፡፡ በድቅድቅ ጨለማ፣ የሚያበሩ ከዋክብቶች ኖረው፣ ፀጥታው እጅግ ሆኖ… አንተ ግን በንቃት ሆነህ …”
እዚያው ተንበርክካ እንዳለች በግራሶ የተጨማለቀ ሱሪው ውስጥ ያለውን እግሩን ለመንካት እጇን ሰነዘረች፡፡ ለመንካት ምንም ሲቀራት እጆቿ ተመልሰው መሬቱ ላይ ወደቁ፡፡
“እንዳልሺው ነው፤ ግን እራት ሳይበሉ፣ በባዶ ሆድ ሲሆን ነገሮች ብዙም አይመስጡም፡፡”
ድንግጥ ብላ ተነስታ፣ ቀጥ ብላ ቆመች፡፡ ሀፍረት ፊቷ ላይ አለ፡- “እንካ ይኼን ጋሪህ ውስጥ ወንበሩ ላይ፣ ሊታይህ የሚችል ቦታ አስቀምጠው፡፡” ብላ ክሪዝአንተመምቹን የያዘውን ዕቃ፣ በጥንቃቄ እጆቹ ላይ አኖረቻቸው፡-  “እስኪ የሚጠገን ነገር ካለ ልፈልግልህ።” ብላ ወደ ጓሮ ሄደች፡፡ ከአሮጌ እቃዎች ክምር ውስጥ ሁለት ረዣዥም እጀታ ያላቸው ድስቶች ይዛ ተመለሰች፡- “ይኸው እነዚህን ጠግናቸው፡፡” ብላ አቀበለችው፡፡
እቃዎቹን መጠገን ሲጀምር አኳኋኑ ተለወጠ፡፡ ባለ ሙያነቱ በአንዴ ነገስበት፡፡ አፉ እርግጠኝነቱን ያሳብቃል፤ የሚሰራውን ጠንቅቆ የሚያውቅ እንደሆነ ይናገራል። ስራው ትንሽ ሲያስቸግረው የታችኛውን ከንፈሩን ይመጥጣል፡፡
“የምታድረው ሠረገላው ውስጥ ነው?”
“አዎ ስረገላዬ ውስጥ ነው የማድረው፤ ፀሀይ ብትይ ዝናብ እንዳችም ነገር አይነካኝም፡፡”
“አሪፍ ህይወት ሳይሆን አይቀርም፡፡” አለች፡- “በጣም ጥሩ ህይወት ይመስለኛል፡፡ ሴቶችም እንዲህ መኖር ቢችሉ መልካም ነበር፡፡”
“ለሴቶች የሚሆን አይነት አኗኗር አይደለም፡፡”
“እንዴት እንዲያ ልትል ቻልክ? እንዴት አወቅህ ለሴቶች የማይሆን ኑሮ እንደሆነ?” ተናድዳለች፡፡
“እንዲያው ነው ተናገርኩት እመቤቴ፡፡ ብዙም የማውቀው ነገር የለም፡፡ እነሆ እቃዎችሽ፤ አዲስ ሁነዋል፤ አዲስ መግዛት አይጠበቅብሽም፡፡” የተጠገኑትን ድሰቶች አቀበላት፡፡
“ዋጋ?”
“ሀምሳ ሳንቲም ይበቃል፡፡ በዝቅተኛ ዋጋ ምርጥ ስራ ነው የምሰራው፡፡ ለዚህም ነው ሁሉም ደንበኞቼ የሚረኩት፡፡”
ኤልሳ እቤት ገብታ ሃምሳ ሳንቲም ይዛ ተመለሰች፡፡ የሰውየው እጅ ላይ ጣል አደረገችው፡፡ “በቅርቡ ተፎካካሪ ቢመጣብህ እንዳይገርምህ፡፡ እንደ እኔ መቀሶችን መሳል የሚችል የለም፡፡ ማሰሮዎችስ ብትል !”
“የእኔ እመቤት ብቸኝነቱ ሴቶች የሚቋቋሙት አይነት አይደለም፡፡ በዚያም ላይ በጣም አስፈሪ ህይወት ነው፤ ለሊት አውሬዎች ስረገላው ስር ሲፈነጩ ነው የሚያድሩት።” አለ ሰውዬው፡- “አመሰግናለሁ የኔ እመቤት፤ ያልሽኝን መንገድ ተከትዬ እሄዳለሁ፡፡”
ኤልሳ ከአጥር ውጭ ቆማ ጋሪው ሲሄድ እያየች ነበር። ትከሻዋ ቀጥ፣ እራሷ ወደ ኋላ ዘንበል፣ አይኖቿ ገርበብ ብለዋል፡፡ በለሆሳስ፡- “ደህና ሁን፡፡ ደህና ሁን፡፡” አለች፡- “የያዝከው ቀናውን መንገድ ነው፤ በዚያ በኩል ብርሃን አለ፡፡” ድምፅ አውጥታ እንዲያ ማለቷን ስታውቅ ድንግጥ አለች፡፡ ደግነቱ ከውሾቿ ሌላ ማንም አልሰማትም፡፡
*   *   *
ቤት ገብታ በቀጥታ ወደ መታጠቢያ ቤት አመራች። አፈር በአፈር የሆኑትን ልብሶቿን እያወለቀች ወደ ጥግ ወረወረቻቸው፡፡ እግሮቿን፣ ታፋዋን፣ ሽንጧን፣ ደረቷንና እጆቿን ቀልተው እስኪላጡ ፈትጋ አጠበቻቸው። ሰውነቷን አደራርቃ መኝታ ቤቷ ባለው መስታወት ሁለመናዋን ማየት ያዘች፡፡ ሆዷን ወደ ኋላ ልጥፍ፣ ደረቷን ወደፊት ገፋ አድርጋ ሰውነቷን አየችው፡፡ ተጠማዛ ጀርባዋንም ተመለከተች፡፡
እንዲህ ተዟዙራ እራሷን ካየች በኋላ በእርጋታ መልበስ ጀመረች፡፡ አዲሶቹን የውስጥ ልብሶቿን፣ የሚያምረው ስቶኪንጓን፣ ሴትነቷን እጅግ የሚያጎላውን ቀሚሷን አደረገች፡፡ ምን ቀረ? ፀጉሯን በጥንቃቄ ማስዋብ፤ አስዋበች፡፡ ቅንድቧን ተኳለች፡፡ ከንፈሯን አቀለመች፡፡
የባሏን የእግር ኮቴ ከበረንዳው ስትሰማ ተውባ አልጨረሰችም ነበር፡፡
“ኤልሳ፣ የት ነሽ ?”
“ክፍሌ ውስጥ ነኝ፤ እየለበስኩ፡፡ ትንሽ ነው የሚቀረኝ። ለገላህ የሞቀ ውሃ አለልህ፡፡ እየመሸ ስለሆነ ፈጠን በል፡፡”
እሱ እየታጠበ ጥቁር ሱፍ፣ ካኒቴራ፣ ሸሚዝ፣ ካልሲና ከረቫት መርጣ አልጋ ላይ አስቀመጠችለት፡፡ ተወልውሎ የተቀመጠ ጫማውንም ዝግጁ አደረገች፡፡ ሁሉን ነገር ካዘጋጀችለት በኋላ ወጥታ በረንዳቸው ላይ ቁጭ አለች። ቀጥ ብላ፣ ሰውነቷን ሰብሰብ አድርጋ ለረዥም ጊዜ ተቀመጠች፡፡
ሄንሪ ከረቫቱን ወደ ሰደርያው እየከተተ ድንገት በበሩ ብቅ አለ፡፡
“እንዴ! እንዴ! ኤሊሳ! ዛሬ በጣም ውብ ሆነሻል!”
“ውብ? ውብ ናት ብለህ ታስበኛለህ? ‘ውብ’ ስትል ምን ማለትህ ነው?”
ሄንሪ ግራ ገባው፡፡ “አላውቅም፡፡ ማለት የፈለኩት ልዩ፣ ጠንካራና ፍፁም ደስተኛ ትመስያለሽ ነው፡፡”
“ጠንካራ ነኝን? አዎ፤ ጠንካራ ነኝ፡፡ ‘ጠንካራ’ ስትል ምን ማለትህ ነው?”
ሄንሪ ግራ ተጋባ፡- “ዛሬ ደግሞ የሌለ ጨዋታ ነው ያመጣሽው፡፡” አለ አንጀት በሚበላ ሁኔታ፡- “አንድ ጥጃ በአንድ ምት ገለሽ እንደ ሀብሀብ ዋጥ የምታደርጊያት ነው የምትመስይው፤ ከዚህ በላይ ጥንካሬ አለ? ከዚህ በላይ ደስተኝነት አለ?”
ለቅፅበት ግትርነቷ ጠፋ፡- “ሄንሪ! ሁለተኛ እንደዚህ እንዳታወራ፡፡ አሁን ምን እንዳልክ ባወቅከው ኖሮ!”  ሰውነቷ ተመልሶ ስብስብ አለ፡- “ጠንካራ ነኝ፡፡” አለች፡- “እስከ ዛሬ ግን ምን ያህል ጠንካራ እንደሆንኩ አላውቅም ነበር፡፡”
ሄንሪ መኪናው ወደቆመችበት ስፍራ አየት አድርጎ፣ መልሶ ኤሊሳን አያት፤ አሁን ግራ መጋባቱ ለቆት የድሮውን ሄንሪ መስሏል፡፡
“መኪናዋን እስካስነሳ ገብተሽ ኮትሽን ደርቢ፡፡” አላት።
ኤልሳ ኮቷን ለመደረብ ቤት ገባች፤ ሆን ብላ ጊዜ ፈጀች፡፡
ሄንሪ መኪናዋን በአዋራማው መንገድ አከነፋት፡፡
አሻግራ ወደ ፊታቸው ስታይ ሚጢጢዬ ጉብታ ታየቻት፡፡ ምን መሆኑን ስታውቅ ክው አለች፡፡ ወናነት ተሰማት፡፡ ደግማ ላለማየት ታገለች፡፡ አልቻለችም። አሸዋማ አፈር ከእነ ችግኞቹ ጥርጊያው መንገድ ላይ ተጥሏል፡፡ ክሪዝአንተመሞቹ የጋሪው ጎማዎች መንገዱ ላይ የሰሩት መስመር ላይ ተጥለዋል፡፡ አሸዋው ተደፍቷል። አትክልት መትከያውን ግን የለም፤  አላየችውም፡፡ እሱ ጠቃሚ ነው፡፡ ወስዶታል፡፡ መራራው እሷ ግን የምትወደው የክሪዝአንተመሞቹ ሽታ ደረሳት፡፡ ሰውነቷ ተርገፈገፈ፡፡ በጠንካራ እጆቿ አፈረች፡፡ ድንቄም የአትክልተኛ እጆች አለች ለራሷ፡፡
መኪናቸው ሲታጠፍ ደግሞ ሠረገላውን ከርቀት አየችው፡፡ ሠረገላውንም፣ ሰረገላውን የሚጎትቱን ደባሪ ጥንዶች ላለማየት ፊቷን ሙሉ ለሙሉ ወደ ባሏ መለሰች፡፡
ሰረገላውን አልፈውት ሄዱ፡፡ “ከይሲ፡፡” አለች በውስጧ፡፡ ጮክ ብላ ደግሞ ሄንሪን እንዲህ አለችው፡- “ዛሬ ምሽቱ ምርጥ ነው የሚሆነው፡፡ ምርጥ እራት እንበላለን፡፡”
“ይኸው ደግሞ የድሮ ፀባይሽ መጣ፡፡ ቅድም በጣም ደስተኛ ነበርሽ፡፡” እንደመነጫነጭ አለ  ሄንሪ፡- “ጥፋቱ የኔ ነው፤ አዘውትሬ እራት ልጋብዝሽ ይገባ ነበር። ለሁለታችንም መልካም ነው፡፡ የእርሻ ስራው ሙሉ ጊዜያችንን ወስዶታል፡፡”
“ሄንሪ”  አለች ኤልሳ፡- “እራት ላይ ወይን ታዛለህ?”
“እንዴታ! እንዲያውም አሪፍ ሀሳብ አመጣሽ፡፡”
ፀጥ ብላ ከቆየች በኋላ፡- “ሄንሪ የቦክስ ፍልሚያው ላይ ተጋጣሚዎቹ በጣም ነው የሚቧቀሱት? ጉዳት ይደርስባቸዋል?”
“አልፎ አልፎ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ አይደለም፡፡ ለምን ጠየቅሽኝ ግን ?”
“አፍንጫቸው እንደሚሰበር፣ ደረታቸው በደም እንደሚርስ፣ የቦክስ ጓንታቸው በደም እንደሚጨማለቅ አንብቤያለሁ፡፡”
ሄንሪ ሚስቱን ዞሮ አያት፡- “ኤልሳ ምንድነው ነገሩ? እንዲህ አይነት ነገሮች እንደምታነቢ አላውቅም ነበር፡፡”
“ሴቶች የቦክስ ፍልሚያ ለማየት ይገባሉ?” ብላ ጠየቀች፡፡
“አዎ ይገባሉ፡፡ ጥቂት ናቸው ግን፡፡ ዛሬ ምንድነው ነገሩ? የቦክስ ፍልሚያ ማየት ፈልገሻል? ማየት ከፈለግሽ ልውሰድሽ እችላለሁ፡፡ የምትወጂው ግን አይመስለኝም።”
ሰውነቷን ጥላ ወንበሩ ላይ ዘና አለች፡- “ፈፅሞ፡፡ ፈፅሞ፡፡ ፈፅሞ ማየት አልፈልግም፡፡ ማየት እንደማልፈልግ እርግጠኛ ሆኜ ነው የምነግርህ፡፡” ሄንሪን ላለማየት ፊቷን አዞረች፡- “ወይን ከጠጣን በቂ ነው፡፡ ብዙ ወይን እንጠጣለን፡፡”
የኮቷን ኮሌታ ወደ ላይ መለሰችው፡፡ እንባዋን ሄንሪ እንዲያይ አልፈለገችም፡፡ አለቃቀሷ የአሮጊት ነበር፡፡
(የዚህ አጭር ልብ-ወለድ የእንግሊዝኛው ርዕስ፡- The Chrysanthemums ነው፡፡)
ስለ ደራሲው፡
ጆን ስቴንቤክ እ.ኤ.አ. ከ1902 እስከ 1968 ዓ.ም. የኖረ አሜሪካዊ የረዣዥምና የአጫጭር ልብ-ወለዶች ደራሲ ነው፡፡ በ1940 ዓ.ም. Grapes of Wrath በሚለው ልብ ወለዱ የፑልፒዘር ሽልማት ተሸልሟል፤ በ1962 ዓ.ም. ደግሞ በስነ ፅሁፍ የኖቤል ተሸላሚ ነበር፡፡ ይህች The Chrysanthemums የተባለች አጭር ልብ ወለዱ በስፋት የተነበበችና እየተነበበች ያለች ሥራው ናት፡፡


Read 3588 times