Saturday, 28 November 2015 14:22

ስታቅፈኝ ያነቅከኝ፥ ስትስመኝ የነከስከኝ ያህል ነበር

Written by  ዕዝራ አብደላ
Rate this item
(8 votes)

የማንያዘዋል “እንግዳ” ተዉኔት ሲዳሰስ

  በከተማችን ለዕይታ ከቀረቡ ፊልሞችና ከተመደረኩ ተውኔቶች ወጣ ያለ፥ ስቀውና ተክዘው የሚዘነጉት ሣይሆን መንገድ ለመንገድ ከአእምሮ እየተንገዋለለ፥ እውነታና መሰለኝ የተደባለቀበት“እንግዳ” ተውኔት ነው። ተውኔቱ ምቹ በሆነው በአዲስ አበባ ትያትርና ባህል አዳራሽ እሁድ ከሰዓት በኋላ ለሁለት ጊዜ የመደረካል። ፀሀፊውና አዘጋጁ ማንያዘዋል እንደሻው ሲሆን፥ የተውኔቱነ ሶስት ገፀባህሪያትየሚወክሉት እውቅና ድንቅ ተዋንያን ናቸው። ባል (ሽመልስ አበራ) ፥ ወላጆቹ ባወረሱት ትልቅ ቤት ውስጥ የሚኖር የቀድሞ ተዋናይ ነው። ሚስት (ሀረገወይን አሰፋ) ፥ በኑሮዋ ደስታ የራቃት ዘመናዊ ሴት ናት። እንግዳ (አልአዛር ሳሙኤል) ፥ ሚስት አጥምዳው እንደ ፍቅር ጀማምሮት፥ ከባሏ ጋር የወረራቸውን ስልቹነት ለማቅለል ምስጥሩን ሳያውቅ የተጋበዘ፥ የሥነልቦና ባለሙያ፥ የኪነጥበብ አድናቂ ነው።
ይህ ተውኔት ከሃያ ሰባት አመት በፊት የተመደረከ ነበር፤ ለተመልካች ግራ የሚያጋባ፥ በጥሞና ትዕይንቱን የሚያጣጥም ተደራሲ ያፈላልግ የነበረ፥ በወቅቱ የተደመሙበት ሠርክ ያስታውሱት ነበር። አሁን እንደገና ታሽቶ፥ የ absurdity - ዘበትነት- አፃፃፉን አለሳልሶ ወደ ዕውነታ ያደላ፥ ግን በገሀድና በቅዠት መካከል ያለውን ድንበር የፋቀ፥ የሚያወያይ ተውኔት ነው። በአንድ ወቅት ማንያዘዋል ዕውቅ ግሪካዊት ፀሃፌ-ተውኔት Lowla Anagnostik በጥቂት መስመሮች ስለ አንድ ተውኔቷ የፃፈችውን አስተዋፅኦ ያነባል። ምናልባት ያነበበው ስለ The City ተውኔት ይሆናል፤ ሁለት ተባዕትና አንዲት እንስት ይተውኑበታል። የቆየ እኩይ ታሪካቸውን ለመዘንጋት በየጊዜው ከከተማ ከተማ ይሳፈራሉ - ፍቅረኛሞቹ። በደረሱበት የሚጋብዙት አንድ ሰለባ ያድናሉ፤ ውጥረታቸውን ሊያረግብ የሚችል ግለሰብ። እንደተጋበዘ አድካሚ ሥነልቦናዊ ጨዋታ ይጀምራል። እንግዳቸው ያዝ ለቀቅ የሚያደርገው ፎቶ አንሺ ነው፤ ሞትን እረታለሁ በማለት፥ ህይወታቸው እንዳለፈ የሚያስመስሉትን ግለሰቦች በካሜራው ይቀርፃቸዋል። የ Lowla ተውኔት ከ“እንግዳ” ተውኔት ፍፁም ይለያል፤ ማንያዘዋል የሶስት ገፀባህሪያትን አሳብ እንደ ሰበዝ በመውሰድ አዲስ ተውኔት ነው የፈጠረው።
ባልና ሚስት ተሰላችተዋል፤ በየሳምንቱ አንድ እንግዳ  ጋብዘው መንፈሱን በማሰቃየት ይዝናናሉ። አሰልቺ ህይወት የእለት በእለት እንቅስቃሴን ጭራሽ እንዳይፈረፍረው፥ ከራስ ውጭ የሆነየአንድ ግለሰብ ነፍስና ሰብዕና እንዲቃስት ያደባሉ፤ የጓዳቸውን ሰቀቀን ሊያረግበውም ሊያባብሰውም አቅም ሽሽጓል። ይህን የተሸሸገ፥ በዕውነታና በቅዠት መካከል የሚዋልል የመኖር ስግብግብነት እየሳቁም፥ እየቆዘሙም አያዎነቱ ሲመደረክ፥ ተመልካች የሚዘነጋው ትያትር አይደለም። እንዴት ያበቃ ይሆን ቢያሰኝም፥ ለፍቅርም ለትዳርም ጉዳይ እንደ ተመልካቹ የግሉ ትዝታ ሆነ ቁስል እየተቀሰቀሰበት በተውኔትና በዕውነታ መካከል ይዋዥቃል። ዘመነኛ ሰው ማኅበረሰቡ መጠለያ ሳይሆነው፥ ሃይማኖት ሳይታወሰው፥ እግዜርን እንደ ምርኩዝ ሳያፈላልግ፥ ማምሸት ማንጋት ሥነልቦናዊ ስቃይ አክሎ፥ ጣዕም አልቦ ፍቅራዊና ኢ-ፍቅራዊ ትርምስ ውስጥ ምን ዶለው? “እንግዳ” ትያትር የማይዳሰስ ውስብስብ ቃለ ተውኔት ሳይሆን፥ ባልና ሚስት ሲገለማመጡ፥ አንድ አንሶላ መጋፈፍ የሲሲፈስ አለት ሽቅብ መግፋት የመሰለ ስልቹነት ሲመዘምዛቸው፥ እውነትና ሀሰት ይቀላቀላሉ። በዚህም ምክንያት ተመልካች የግሉ ጉዳይ ይመስል በተመስጦ እንደጓጓ መድረኩን ተቀላቅሎ እኩል ይቅበዘበዛል። እንግዳው -አዲስ ሰለባ- ፍቅርን ተከትሎ ነው የሚስት ግብዣ የተቀበለው።
ሚስት ፤ ለመሆኑ ለምን እስከዛሬ ሳታገባ ቀረህ ?
እንግዳ ፤ እጮኛ ነበረችኝ፥ የሚገርምሽ ነገር ቴያትር ቤት ውስጥ ገና ከሩቅ ሳይሽ ነበር ልቤ ስንጥቅ ያለው!
ሚስት ፤ አልገባኝም
እንግዳ፤ ሁለመናሽ የበፊቷ እጮኛዬን ነው የሚመስለው። ለማንኛውም መጨረሻ ላይ ተለያየን
ሚስት ፤ ምን ሆናችሁ ?
እንግዳ ፤ ከሌላ ሰው ጋር ... መውጣቷን ደረስኩበት
ሚስት ፤ ትወድህ ነበር?
እንግዳ ፤ ይመስለኝ ነበር፥ ግን ምን ዋጋ አለው?
ሚስት ፤ ለምን የለውም?
እንግዳ ፤ ምን ማለትሽ ነው?
ሚስት ፤ ከሌላም ጋር ብትወጣ አንተን አልተወችህም አይደል?
እንግዳ፤ እና
ሚስት፤ ገና ለገና ከሌላው ሰው ጋር ወጥታለች ብለህ እንዴት የምትወዳትን ሴት ትተዋታለህ?
እንግዳ፤ የምትይው አልገባኝም
ሚስት፤ ጊዜ ልትሰጣት ይገባ ነበር። ምናልባት ሌላውን ካየች በኋላ ልትመለስ ትችል ነበር።
/በስሜት/ የምትወዳት ከልብህ ቢሆን ኖሮ።
እንግዳ፤ ከመውደድም በላይ እወዳት ነበር። ከማን ጋር እንደወጣች አውቀሻል? እንደ ወንድሜ ከምወደው ጓደኛዬ ጋር እኮ ነው! ተይው
           ሊገባሽ አይችልም።    
ሚስት፤ /ለስለስ ብላ/ ይገባኛል
እንግዳ፤  አየሽ፥ ለኔ ፍቅር ፍጹም ነው፤ እንደሃይማኖት .......
ሚስት፤ /በዝግታ ትነሳና እስሩ ትንበረከካለች፥ ፊቱን እያየች ትቆይና/ ይቅር በለኝ
እንግዳ ፤ /ዝም ብሎ ያያታል/ ለምኑ?
ሚስት፤ ለተሰበረው ልብህ፥ ላሳለፍካቸው እንቅልፍ የለሽ ሌሊቶች፥ በጥላቻ ለተነደፈው ስሜትህ፥ ለተሰቃየህባቸው ጊዜያት በሙሉ!
እንግዳ፤ አንቺ ምን አረግሽኝ?
ሚስት፤ በሷ ስም እኔን ይቅር በለኝ
/ያነሳታል፥ ፊት ለፊት ይቆማል፤ ግንባሯን ይስማታል፤ አቅፋው ትንሽ ያቆያሉ/
ሚስት፤ ይዘኸኝ ልትሄድ ፈቃደኛ ነህ?
እንግዳ፤ አዎ
/ወደ በሩ ሲሄድ ባል ይገባል፤ ሁለቱም ይደነግጣሉ/
ይህን በመሰለ ምልልስ፥ የሥነልቦና ባለሙያ የሆነው እንግዳ፤ እንኳን ሊጠረጥር በማይችል ጥበብ ነው ባልና ሚስት ሰለባውን እንግዳ ለግል ህይወታቸው ስልቹነት መጫወቻ የሚያደርጉት። ቋንቋ ሌላውን የማሰቃየት አቅሙ ይደንቃል። የጠበቅነው፥ በአእምሯችን የቀረፅነው የሚገጥመን መቃረኑ ከጡዘት ወደ ጡዘት ያስዘልለናል። የመጀመሪያው ሰፊ ትዕይንት እንግዳም፥ ተደራሲም የባልና ሚስት ድርጊትና  ንግግር እንደ እውነት እንቀበለዋለን። ሁለት ጊዜ ከዚህ መረብ ወድቀናል። ትያትሩ በጓዳ ህይወት ላይ ያጠንጥን እንጂ፥ ጓዳ ሲያፍንህ [መሰልቸት] እንደ ምስጥ ሲቦረቡርህ አደባባይ ሰው -ሰለባ- ፍለጋ ትሸሻለህ። ይህን እንግዳ ከቤትህ ጋብዘህ (በተቃራኒ ፆታ ፍትወት አጥምደህ) ለሥነልቦናዊና ፍቅራዊ ጣጣህ ማስረሻ ስታደርገው በግልብጡ ያንተም ህይወት ይታመሳል። ይህን ተከትሎ ነው ተውኔቱ የተመደረከው፤ የሚናገሩት እውነት ውሽት ይሁን ግራ እስኪገባን ድረስ።
የፍቅር መንጠፍ፥ እየተሰላቹ እንደልማድ ሆኖ አብሮ መኖር፥ የወንድ የሴት ግንኙነት ውስብስብነት ... ይህን አጭር እድሜ ሲበክለው ጥያቄ  ይቀሰቅሳል። በሌላ ነገር አለመጠመድ፥ ለኑሮ የእለት ተእለት ሩጫ አለመቀማት፥ የኅላዌ ባዶነት -existential vacuum- ሲኖሩ፥ በሀገራዊ ጉዳይ አለመጠለፍ ሰው በልቡ፥ በማጀቱ ጣጣ መታቀፉ ለምን ያሰኛል?
የ“እንግዳ” ተውኔት ሤራ በመተርተር የተደራሲን ጉጉት መሻማት አልሻም። ማንም በዚህ ተውኔት ሲደመም ከግሉ ህይወት እይቆረሰ ተማልካች ብቻ ሳይሆን በስሜቱም ተሳታፊ ነው። እንግሊዛዊ ባለቅኔ Byron በአንድ ስንኙ እንደቋጠረው “boredom ... that awful yawn which sleep can not abate” ብሏል። የተውኔቱ አንድ ጭብጥ ባልና ሚስት ትዳርም ኑሮም ስለስለቻቸው የመደናገራቸውን አባዜ ሰበዙን መዞ ተመደረከ። ባይረን እንደ ተቀኘው ስልቹነት እንቅልፍ የማያደክመው ረጅም አሰቃቂ ማዛጋት ነው።
ፍቅርም፥ ቅናትም፥ ክህደትም፥ መሰልቸትም፥ መስገብገብም እስከ እውነትና ውሸት መቀላቀል ድረስ፥ ሰው የተጋለጠበት ተውኔት ነው። በትርኪ ምርኪ ከመንሳፈፍ ለረባ ትውኔት መቆጨት ይበጃል።

Read 3992 times