Saturday, 28 November 2015 14:32

ሲንጋፖር በአመት 37 ሺህ 600 አዳዲስ ሚሊየነሮችን ታፈራለች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከ5 አመታት በኋላ ከ30 ዜጎቿ አንዱ ሚሊየነር ይሆናል
   ዌልዝ ኢንሳይት የተባለው አለማቀፍ የኢኮኖሚ መረጃ ተንታኝ ተቋም፣ ሲንጋፖር በመጪዎቹ አምስት አመታት በየአመቱ በአማካይ 37 ሺህ 600 ያህል ተጨማሪ አዳዲስ ሚሊየነሮችን ታፈራለች ተብሎ እንደሚገመትና በ2020 የፈረንጆች አመት ከ30 ሲንጋፖራውያን አንዱ ሚሊየነር ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ መግለጹን ሲኤንኤን ዘገበ፡፡
ይህ የአዳዲስ ሚሊየነሮች ቁጥር በአገር ውስጥ የሚፈጠሩ ሚሊየነሮችን ብቻ ሳይሆን፣ ከውጭ አገራት ወደ ሲንጋፖር የሚገቡትንም ይጨምራል ያለው ዘገባው፣ ሲንጋፖር በአሁኑ ወቅት በድምሩ 806 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ የተጣራ ሃብት ያካበቱ 154 ሺህ ያህል ባለ ከፍተኛ ገቢ ዜጎች እንዳሏትና እነዚህ ሚሊየነሮች ከአጠቃላዩ የአገሪቱ የህዝብ ቁጥር 3 በመቶ ያህሉን እንደሚይዙም ጠቁሟል፡፡
ወደ አገሪቱ የሚጎርፉና በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የሚሰማሩ ህንዳውያንና ቻይናውያን ሚሊየነሮች ቁጥር እየጨመረ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፣ በሲንጋፖር የቀጠለው የፋይናንስ ገበያ መሟሟቅ፣የግል ባንኮች መስፋፋታቸውና የላቀ ጥራት ያለው የአኗኗር ዘዬዋ፣ ከፍተኛ ሃብት ያላቸውን በርካታ የተለያዩ አገራት ዜጎች ወደ አገሪቱ መሳባቸውን ይቀጥላሉ መባሉንም አስታውቋል፡፡

Read 3431 times