Saturday, 28 November 2015 14:38

“...ጥረቴ ..ሴቷን ወደ ሙሉ ሰውነቷ መመለስ ነው”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ /ዮዲት ባይሳ/ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

“...የማልረሳው አንድ ነገር አለኝ፡፡ አንድ ቀን በሚኒባስ ታክሲ ወደስራዬ እሄዳለሁኝ፡፡ ከለገሀር ሲነሳ  ሙሉ የነበረው ታክሲ ቀስ በቀስ ሰው እየወረደ ገና ሜክሲኮ ሳንደርስ እኔ እና ሁለት ሰዎች ብቻ ቀረን፡፡ ከዚያም ፊሊፕስ ፊት ለፊት ስንደርስ፡-
የእኔ እመቤት እባክሽ ውረጂልን? ሳንቲምሽን እንመልሳለን... አለኝ ሾፌሩ ወደእኔ ዞር ብሎ... ረዳቱ እስከጭርሱም ከወገቡ በላይ በመኪናው መስኮት ወደ ውጭ ወጥቶ ከውስጥ የምንባባለውን ነገር አይሰማም፡፡
እኔም...ለምን ግን አልኩት፡፡
እንዴ... አንቺ ብቻ ነሽ እኮ የቀረሽው... አንድ ሰው ይዤ ጦር ኃይሎች ድረስ አልሄድም፡፡     እነሱም ይወርዳሉ... አንቺ ውረጂልን፡፡ አለኝ፡፡
ለምንድነው ግን? አልኩት፡፡
እንዴ... አይሰማሽም እንዴ... ሽታው? ...ሰው ሁሉ እኮ የወረደው በዚህ ምክንያት ነው... አለኝ፡፡
ከዚያም መለስ ብዬ ወደሁዋላ ስመለከት... አንዲት ታዳጊ ልጅ እና አንድ አባት ተቀምጠዋል፡፡
እነሱን ...ወደየት ነው የምትሄዱት? አልኩዋቸው፡፡
ወደ ጦር ኃይሎች ግድም ሐኪም አለ ብለውን ወደዚያ ነው የምንሄድ... ሐኪም ቤቱንም ...ገና ጠይቄ ነው እንጂ ወዴት ብዬ አውቀዋለሁ...ልጄ... አሉኝ ...አባትየው። በሁዋላም እኔ ወደምሰራበት ፊስቱላ ሐኪም ቤት እንደሚሄዱ ገባኝ... እና በጣም አዘንኩ፡፡
የታክሲ ሾፌሩን ረጋ ብዬ አስረዳሁት፡፡ እነዚህ ሰዎች የመጡት ከገጠር ነው፡፡ ልጅቱዋ ታማባቸው ሊያሳክሙ ነው የመጡት፡፡ አንተ ካልረዳሀቸው ማን ይረዳቸዋል? ሆስፒታሉ እሩቅ ነው፡፡ እንዴት ብለው ይደርሳሉ? ስለው... ዝም ብሎ አዳመጠኝና...
...እሺ በቃ አደርሳቸዋለሁ... ብሎ እንዲያውም ገንዘብ ሳያስከፍል ...ፊስቱላ ሆስፒታል ድረስ አደረሰን፡፡
ይህ ሰው ምንጊዜም የማይረሳኝ በጎ ስራ የሰራ ሰው ነው፡፡ እኔ በስራው ላይ ብዙ ጊዜ ስላሳለፍኩኝ እና በሐዘኔታ ቅርብ ሆኜ ችግሩን ችግሬ ጉዳዩን የእራሴ ጉዳይ አድርጌ ሴቶቹን ስለምረዳ በሽንት ምክንያት የሚፈጠረውን ሽታ ለምጄዋለሁ፡፡ ምንም አይሰማኝም፡፡ እንዲያውም ሰዎች ለጉብኝት ወይንም ለአንዳንድ ስራዎች ወደ ሆስፒታሉ ሲመጡ እና ...በጣም ይሸታል ...የሚል አስተያየት ሲሰጡ አ.አ.ይ ...አረ ምንም አይሸትም የሚል ነው የእኔ መልስ፡፡
    ዶ/ር አምባዬ ወልደሚካኤል
    የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት
ከላይ ያነበባችሁት ዶ/ር አምባዬ ወልደሚካኤል በስራቸው አጋጣሚ የታዘቡት ነው፡፡ ዶ/ር አምባዬ በሕክምና ሙያ ከተመረቁ በሁዋላ እና የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትነት ከገኙ በሁዋላ በአዲስ አበባ ሐምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል ከ14 አስራ አራት አመት ላላነሰ ጊዜ አገልግለዋል፡፡ ዶ/ር አምባዬ በአሁኑ ወቅት Women and Health Alliance International Ethiopia (WAHA) በተባለው በእናቶች ጤና ዙሪያ በሚሰራው በጎ አድራጎት ድርጅት ይሰራሉ፡፡ ዋሀ/ በአለም ላይ የተሙዋላ የጤና አገልግሎት በማያገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ውስጥ የሚኖሩ እናቶች ጤና እንዲሻሻል አትኩሮ የሚሰራ ድርጅት ነው፡፡ ዋሀ ኢንተርናሽናል በ2009 የተመሰረተ ሲሆን በ23 አገራት ውስጥ ኢትዮጵያን ጨምሮ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ዶ/ር አምባዬ ወ/ሚካኤል በሙያቸው በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እየተዙዋዙዋሩ የህክምና ባለሙያዎችን ያስተምራሉ፡፡ ትምህርቱን የሚሰጡት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የአፍሪካ አገራት እና ሩቅ ምስራቅ እንዲሁም በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ነው፡፡
ዶ/ር አምባዬ እንደሚሉት “...የፊስቱላ ታካሚ ማለት በማህጸን አካባቢ የተፈጠረውን ቀዳዳ በመዝጋት ብቻ የሚያበቃ ሕክምና አይደለም፡፡ ሴቶቹ የጤና ችግር ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታሉ ሲመጡ ሌሎች የተለያዩ የጤና ችግሮች እና የስነልቡና ጉዳትም ደርሶባቸው ነው የምናገኛቸው፡፡ ስለዚህም ተመልሰው ሙሉ ጤናማ ሰው እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን እርዳታ ለማድረግ የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ፡፡ ጊዜዬን አቅሜን ሁሉ አሰባስቤ እነሱን ሙሉ ሰው ለማድረግ እጥራለሁ፡፡ በዚህ መልክ ስራዬን ሰርቼ ስጨርስም ድነው ...የተሟላ ጤንነት ይዘው ወደ ቤተሰባቸው ሲመለሱ መመልከት በጣም ያስደስተኛል፡፡ ጥረቴ የጎደለውን ጤንነት አሟልቶ ሴቷን ወደ ሙሉ ሰውነቷ መመለስ ነው፡፡
ገጠመኝ 2/
“...አንዲት እድሜዋ 15 ወይንም 16 አመት የሆናት ልጅ ፊስቱላ ታማሚ ሆና ወደ ስፒታል መጣች፡፡ እኔ ነበርኩ ሕክምናውን ያደረግሁላት፡፡ ሕመሙ ከፍተኛ ነበር፡፡  ከብዙ ትግል በሁዋላ ሙሉ ጤንነትዋ ተመልሶ ከሆስፒታል እንድትወጣ ሲነገራት ...በቀጥታ ወደ እኔ ቢሮ ነበር የመጣችው፡፡
ምነው? ምን ልታዘዝ? ...አልኩዋት
አ.አ.ይ ገንዘብ እንድትሰጪኝ ነው... አለችኝ
የምን ገንዘብ? ...የእኔ ጥያቄ ነበር፡፡ ምክንያቱም ሌሎችም ቢሆኑ ሕክምናውን ጨርሰው ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ መጉዋጉዋዣ... እና ለአንዳንድ ነገር የሚሆን ገንዘብ ስለሚሰጣቸው ነው፡፡
እሱዋም “...እኔ ስታመም ...ወደ ሐኪም ቤት እሄዳለሁ እና ገንዘብ ስጠኝ ስለው ባለቤቴ የምን ገንዘብ ነው? ...አሁን እውነት ታክመሽ ልትድኚ ነው? ...እኔ በገንዘብ አልጫወትም አለኝ፡፡ እኔም እልህ ይዞኝ... አንዲትዋን ፍየል ሰርቄ ...ሸጬ ነው ልታከም የመጣሁት፡፡ አሁን ከአገሬ ስገባ ሌባ ብሎ ይይዘኛል፡፡ ስለዚህ የፍየሊቱን ዋጋ ካልሰጠሁት በአገር አያኖረኝም፡፡” አለች፡፡
እኔም በጣም አዝኜ... የጠየቀችኝን ገንዘብ ሰጠሁዋት። የሚገርመው ነገር በሄደች በሁለት አመትዋ እርጉዝ ሆና ተመልሳ መጣች፡፡ ሁኔታውን ስጠይቃት...
“...ያው ከባለቤቴም ታርቄ ገባሁ... እኔም ይኼው ልጅ አርግዤ መጣሁ፡፡ እንደነገራችሁኝ ...ባለፈውም እንደዚያ የሆንኩት ብዙ ቀን አምጬ ስለሆነ ደግሞ     እንደዚያ እንዳልሆን ብዬ በሰጣችሁኝ ትምህርት መሰረት ቀድሜ መጣሁ አለችኝ፡፡ አዋልደናት... ተመልሳ ሄደች፡፡ በሚቀጥለው ሁለት አመትም እንደገና አርግዛ ስትመጣ ከባለቤትዋ ጋር ነበረች፡፡ እሱም በጣም አመስግኖ ሁለተኛዋን ልጃቸውን ይዘው ወደ አገራቸው ሄዱ፡፡”
ዶ/ር አምባዬ ወ/ሚካኤል በሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ በሚሰሩበት ጊዜ ካደረጉት የእለት ተእለት ተግባር በተጨማሪ የሚከተለውን አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡
“...የፊስቱል ታማሚዎች በአብዛኛው ወደ ሕክምናው አይመጡም፡፡ ምክንያቱም የአቅም ወይንም ደግሞ ችግራቸውን የሚረዳቸው ስለማይኖር እና... እንደ ሀጢአት ወይንም እርኩስ መንፈስ እንደቀረባቸው ተደርጎ ስለሚታሰብ ነው፡፡ ሕክምና መኖሩንም የማያውቁ ብዙ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ... ምናልባት መረጃው ኖሮአቸው እንሞክር ብለው ከየመስተዳድሩ ራቅ ካለ አካባቢ የሚመጡ ሲሆን እነእሱም በአብዛኛው ኑሮአቸው ዝቅተኛ እና ደሀ የሚባሉ ናቸው፡፡ በችግር ያላቸውን ከብትም ይሁን እህል ሸጠው ...በጣም ትንሽ ገንዘብ ይዘው... ለስንቅና ማደሪያ የሚሆናቸው በቂ አቅም ሳይኖራቸው እንደምንም ታግለው አዲስ አበባ መኪና ተራ ይደርሳሉ፡፡ ከዚያው ከመኪና ተራው ከደጅ ያድሩና... እንደገና በእግራቸው ተጉዘው ከብዙ ስቃይ በሁዋላ ከፊስቱላ ሆስፒታል ይደርሳሉ፡፡
ይህንን ስመለከት ሁልጊዜ ነበር የማዝነው፡፡ ከዚያም አንድ ሀሳብ አቅረብኩ፡፡ ለምንድነው ሕክምናውን ይዘን እኛ ወደታማሚዎቹ የማንደርሰው? የሚል ነበር። ሁኔታው ይታይ ተብሎ ከውሳኔ ሲደረስ... በየአካባቢው ካሉ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ጋር እየተመካከርን ሁሉን የህክምና መገልገያ መሳሪያ እና ሕክምናውን ለመስጠት የሚችሉ የህክምና ባለሙያዎችን እያሳተፍን በቀጠሮ ወደየመስተዳድሩ እየሄድን እናክም ነበር፡፡ ይህ ስራ እጅግ በጣም አድካሚ የነበረ ቢሆንም እኔ ግን ሴቶቹን ለማዳን በመሆኑ እጅግ ደስተኛ ነበርኩ፡፡ በሁዋላም ዶ/ር ካትሪን ሐምሊን ሁኔታውን አይተው ...ለምን ቦታዎች ተመርጠው ...ሕመምተኞች የሚረዱባቸው የህክምና ተቋማት አይመሰረቱም የሚል ሀሳብ አምጥተው ከውሳኔ በመደረሱ በአምስት መስተዳድሮች ሐምሊን ፊስቱላ ሐኪም ቤቶች ተመሰረቱ ብለዋል፡፡”
ዶ/ር አምባዬ ከሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ወደ ዋሀ በመሄድ ስራ ሲጀምሩም በበጎ አድራጎት ድርጅቱ አማካኝነት በሶስት መስተዳድሮች ካሉ ሆስፒታሎች እና ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የፊስቱላ ሐኪም ቤቶችን አቋቁመዋል፡፡ በጅማ... በአሰላ እና በጎንደር ሆስፒታሎች የተመሰረቱት ተቋማት ሕመምተኞችን ከማከም ባሻገር በዩኒቨርሲቲዎቹ የህክምና ተማሪዎችንም ስለፊስቱላ ሕክምና ትምህርት ይሰጣሉ፡፡
ዶ/ር አምባዬ ወ/ሚካኤል በዘንድሮው የአለም የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር FIGO  አመታዊ ጉባኤ ከኢትዮጵያ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
ይቀጥላል

Read 2385 times