Saturday, 28 November 2015 14:40

ስፖርት በቅብብሎሽ የሚካሄድ ነው ልምድና እውቀት ካላቸው ጋር መስራት ያስፈልጋል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ


በኢትዮጵያ እግር ኳስ በክለብ እና በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ በግንባር ቀደምነት ከሚጠቀሱ ባለሙያዎች አንዱ አንጋፋው አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ ነው፡፡ በአሰልጣኝነት ከ25 ዓመታት በላይ በክለብ፤ በተስፋ ቡድኖች እና በዋና ብሄራዊቡድንውስጥ ሰፊ የስራ ልምድ ያለው አስራት፤  በርካታ  የዋንጫ ድሎችንም ማስመዝገብ ችሏል፡፡ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ከአገር ውጭ አሸንፎ ዋንጫውን በማግኘት ፈርቀዳጅ ታሪክ የሰራው አሰልጣኝ አስራት፤ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት የተካሄደ ሴካፋን በማሸነፍ ለሁለት ጊዜያት የሴካፋ የዋንጫ ድሎችን የተቀዳጀ ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ 3ኛ ደረጃን ያገኘበትን ድል በዞኑ እግር ኳስ አስመዝግቧል።  አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ በክለብ ደረጃም ሲያገለግል በ4 ክለቦች አሰልጣኝነት በፕሪሚዬር ሊጉ ከፍተኛ ውጤታማነት እና ልምድ ካላቸው አሰልጣኞችም ዋናው ተጠቃሽ ይሆናል። በተለይ ለሰባት የውድድር ዘመናት በቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝነት ሲያገለግል  6 የፕሪሚዬር ሊግ የሻምፒዮናነት ክብሮችን አግኝቷል፡፡ በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር  ሊግ ከሰባት ጊዜ  በላይ የኮከብ አሰልጣኝነት ሽልማቶችን በመሰብሰብም የተሳካለት ነው፡፡
አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ በፕሪሚዬር ሊግ እጅግ ስኬታማ የሆነበትን የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ከለቀቀ በኋላ መከላከያ፤ መብራት ኃይልና የመድን ሌሎቹ ያሰለጠናቸው ክለቦች  ናቸው፡፡ ከመከላከያ ክለብ ጋር  የጥሎ ማለፍዋንጫን፤  ከመብራት ኃይል ክለብ ጋር የሲቲ ካፕ ዋንጫን እንዲሁም በክለብ ደረጃ የነበረው የመጨረሻ ቆይታው ባለፈው የውድድር ዘመን የመድን ክለብ አሰልጣኝ ሆኖ ከመስራቱ በፊት ክለቡን የብሄራዊ ሊግ ሻምፒዮን አድርጎ ወደ ሊግ ውድድር ለመመለስ የበቃ ነው። ስፖርት አድማስ ከ38ኛው የዲኤስቲቪ ሴካፋ ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ ጋር በተያያዘ ከአሰልጣኝ አስራት ኃይሌ ጋር የሚከተለውን ሰፊ ቃለምልልስ አድርጓል፡፡


የዘንድሮን ሴካፋ በአጠቃላይ እንዴት አገኘሀው? የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የተሳታፊ አገራትን ብቃት  ስትገመግመውስ
የሻምፒዮና አጀማመር ከሞላ ጐደል ጥሩ ነው፡፡ በተለይ በተሳታፊ ብሔራዊ ቡድኖች ላይ ለውጥ አለ ማለት ይቻላል፡፡ ሁሉም ቡድኖች ለሻምፒዮናው በቂ ዝግጅት አድርገው መምጣታቸውን ተረድቻለሁ። በርግጥ የመክፈቻ ጨዋታዎችን የተከታተልኩት ስታድዬም ገብቼ አይደለም፡፡ በቴሌቪዥን ነው፡፡ ምክንያቱም  የስታድዬም መግቢያ ፈቃድ ከመዘግየቱ ጋ ጋር በተያያዘ ነው፡፡
አሰልጣኝ አስራት ላቋርጥህ፤ በርግጥ ኢትዮጵያ ሻምፒዮናውን ማዘጋጀቷ ብቻ ውጤት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ግን ስኬታማ መስተንግዶ በማድረግ በኩል አንዳንድ ክፍተቶች መኖራቸውን ታዝበናል፡፡ የፕሮግራም መቀያየሮች፣ ውድድሩን የማሟሟቅ እና የማስተዋወቁ ተግባር፤ በቂ ስፖንሰር ያለማግኘት ሁኔታዎች ይስተዋላሉ፡፡ አሁን  ያነሳሀው የስታድዬም መግቢያ ፈቃድ ጉዳይም የፌደሬሽኑን አካሄድ ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ ይህን ሻምፒዮና የማዘጋጀት ፈቃድ ሲያገኝ በተሻለ አቅም፤ በሴካፋ በቂ ልምድ ካላቸው ሁሉም ባለሙያዎች ጋር መምከር ነበረበት፡፡ እንደዚያ የተሠራ ነገር የለም?
እንግዲህ ይሄ የአመለካከት እና የአስተሳሰብ ጉዳይ ነው፡፡ እኛ በዚያ ውስጥ ያለፍነውን ሰዎች ውድድሩ በአገራችን የሚካሄድ እንደመሆኑ መጠን ሃሳብ በመስጠት፣ ብሔራዊ ቡድንን በማማከር ልንሰራ የምንችልበትን መንገድ የፌደሬሽኑ ሃላፊዎች መፍጠር ነበረባቸው፡፡ ነገር ግን በዚህ ስራ ላይ ድሮ ያለፉበት ሰዎች ፌዴሬሽኑ አካባቢ ብዙም የሚፈለጉበትን ሁኔታ ብዙ እያስተዋልን አይደለም፡፡ እንደትልቅ ችግር ነው የምመለከተው። ምናልባትም ወደ ብሔራዊ ቡድን እንዳንቀርብ የሆነው የአሰልጣኞችም ፍላጐት ባለመኖሩ ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙ እኛን የመፈለግ ባህርይ ያላቸው አይመስለኝም። ይህን የምመለከተው እንደ መጥፎ ባህል  ነው። ስፖርት በቅብብሎሽ የሚካሄድ ነው፡፡ ስፖርት ልምድ ይፈልጋል፡፡ ስፖርት ዕውቀት ይፈልጋል። በተለይ በስራው ያለፍን ሰዎች ካለን ዕውቀትና ልምድ ብዙ ልንጠቀምባቸው የምንችልባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ የበለጠ አስተዋጽኦም ሊኖረን ይችላል፡፡ በሴካፋ መስተንግዶ፤ በብሄራዊ ቡድን አዘገጃጀት እና ተሳትፎ ዙርያ ምን ልምድ የሌላቸውን ሰዎች ከመጠየቅ በሙያው ያለፍነውን ሰዎች ቢያቀርቡና ቢያነጋግሩ የበለጠ ሊጠቀሙ በቻለ ነበር፡፡
ምክንያቱም እኛ አሁንም ስፖርት ውስጥ አለንበት፡፡ ስፖርት ዓለም አቀፋዊ ነው፡፡ አዳዲስና ተለዋዋጭ ነገሮች የሚመጡበት ነው፡፡ እኛ እዚህ ሙያ ውስጥ እስካለን ድረስ፣ ዘመኑን የተከታተለ ስራ እየሰራን መሄድ መቻል ነበረብን፡፡
በውድድሩ መስተንግዶ ዙርያም በኮሚቴ ደረጃም ለመስራት በዚያም ፍላጐት ላይኖር ይችላል። ቢያንስ ግን ለብሔራዊ ቡድኑ የቴክኒክ ድጋፍ ልንሰጥበት  የምንችልበት መንገድ መፈጠር ነበረበት፡፡ የሴካፋ ዋና ፀሐፊ የሆኑትን ኬንያዊው ኒኮላስ ሙንሰኜ ረጅም ጊዜ አውቃቸዋለሁ። ከብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞችም ለምሳሌ ከእነሚቾ ባሻገር፤ ከሱዳኑ አሰልጣኝ በደንብ ነው የምንተዋወቀው ሁለታችንም በየብሔራዊ ቡድኖቻችን ሃላፊነት ተገናኝተናል፡፡ በአፍሪካ ይኸም ደረጃም በጋራ የወሰድነው የአሰልጣኝነት ኮርስ አለ፡፡
እስቲ ወደ ሴካፋ የዘንድሮ ሻምፒዮናው እንመለስ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አቋምን በተመለከተ የታዘብካቸው ሁኔታዎች ምንድናቸው?
ብሔራዊ ቡድናችን እንደጠበቅኩት አይደለም። እንደተዘጋጀው አይነት አይደለም እንቅስቃሴው። ገና ወጣቶች ናቸው፡፡ ብዙ ልምድ የላቸውም። ይጐድላቸዋል፡፡ ይህ አይነቱን ስብስብ በዋና ብሔራዊ ቡድን ሳይሆን በወጣት ቡድን ደረጃ መያዝ የተሻለ ነበር፡፡
ብዙ መስተካከል የሚቀራቸው ነገሮች አሉ፡፡ ዞሮ ዞሮ አሁን ያሉት ልጆች በሂደት እየተሻሉ ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ግን በከፍተኛ ሁኔታ ሊሰራባቸው ያስፈልጋል፡፡ በብሔራዊ ቡድን ግንባታ ላይ በአንድ ጊዜ ስርነቀል ለውጥ አድርጎ መስራት የሚያዋጣ አካሄድ አይደለም፡፡ በዋና ብሔራዊ ቡድን ስብስብ በቂ ልምድ ያላቸው ተጨዋቾች መኖር ነበረባቸው፡፡
በእኔ ዋና አሰልጣኝነት ስለሠራሁበት መንገድ ምሳሌ አድርጌ ላስረዳህ፤ በ2000 በሴካፋ ሩዋንዳ ላይ ስወዳደር 3ኛ ደረጃ በማግኘት የነሐስ ሜዳሊያ ይዤ መጥቻለሁ፡፡ በ2001 እ.ኤ.አ ላይ በድጋሚ በሴካፋ ለመወዳደር ነሐስ ሜዳልያ ካገኘው ስብስብ የተወሰኑ ተጨዋቾችን ይዤ ነበር፡፡
ልምድ ያላቸውን ከአዳዲስ ልጆች ጋር ደባልቄ በሰራሁት የቡድን ስብስብ ጥሩ ውጤት ማምጣት ቻልኩ፡፡ ተጨዋቾችን መቀላቀል አስፈላጊ የሚሆነው ያለውን ልምድ ለመጠቀም ነው፡፡ ረጅም ጊዜ ለብሔራዊ ቡድን የተጫወተና አዲስ ተጨዋች ብዙ ልዩነት አላቸው፡፡ አዲሱ ተጨዋች ብዙ ግር ይለዋል። ዓለም አቀፍ ጨዋታ ነው፤ ክለቡ ውስጥ ያለውና በብሔራዊ ቡድን ያለው ጫና የተለያየ ነው፡፡ ልምድ ያላቸው ተጨዋቾች በቡድን ስብስቡ የሚገኙ ከሆነ ግን አዲሱ ተጨዋች ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ አይዞህ የሚለው የሚያበረታታው ያገኛል። አዲስ ተጨዋች ሜዳው ውስጥ የሚያበረታታው ካገኘ ተነሳሽነት ውስጥ ይገባል፡፡
እና እግር ኳስ ተጨዋች በነበርንበት ዘመንም ይሄ አይነቱን የቡድን አወቃቀር ነው ያለፍንበት፡፡ ከክለብ ደረጃ ተነስተን ብሔራዊ ቡድን የደረስነው በእንዲህ ዓይነት መንገድ ነው፡፡ ከእኛ ጋር ልምድ ያላቸው ልጆች አሉ፡፡ እነሱ ያበረታታቱናል ይመክሩናል። እና ደግሞ የእነሱን ፈለግ ተከትለን እንሄዳለን፡፡ አሰልጣኛችን ከሚሰጠን ስልጠና በተጨማሪ ልምድ ያላቸው ተጨዋቾች አስተዋፅኦ በግድ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡
አሰልጣኝ ከሆንኩ በኋላም የሰራሁበት መንገድ ነው፡፡ ከ2000 ብሔራዊ ቡድን 5 እና 6 ልጆች ይዤ ነበር የ2001 ብሔራዊ ቡድን ያሠራሁት፡፡ በ2000 የነሐስ ሜዳልያ ያገኘሁት ልጆች ወጣት ቢሆኑም ልምድ ነበራቸው፡፡ በ2001 ደግሞ ምንም ልምድ የሌላቸውና ወጣቶች ነበሩ፡፡ ሁለቱን ስብስብ በማዋሃድ ዋናው ብሔራዊ ቡድን ተሠርቷል፡፡
በዚህ ስብስብም ወደ ሩዋንዳ ተጉዞና ውጤት ይዘን መጣን፡፡ ሩዋንዳ ላይ ሴካፋን ያሸነፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ እጅግ በጣም ጠንካራና ውጤታማ ነበር፡፡ እንደዚህ ዓይነት ጥንካሬ ያለው ቡድን ያለም አይመስለኝም፡፡ ይሁንና በቀጣይ የሴካፋ ውድድር ከዚያ ምርጥ ቡድን የሚቀነሰውን ቀንሼ ዋና ዋናዎችን በመያዝ በአዲስ አበባ በተዘጋጀው የሴካፋ ውድድር ገባን፡፡ ዋንጫው ተገኘ፡፡ ዋንጫውን ሁሉንም ጨዋታዎችን አሸንፈን ነው የወሰድነው፡፡
በአጠቃላይ ብሔራዊ ቡድንን በአንድ ጊዜ በስር ነቀል ለውጥ ውጤታማ ማድረግ አይቻልም፡፡ በሂደት መሠራት ያለበት ነው፡፡
የሚገርምህ ተጨዋቾቹ ብቻ አይደለም፡፡ አሰልጣኞቹም ልምድ ያላቸው መሆን አለባቸው። ሃቁን ለመናገር አሁን በሃላፊነት ላይ የሚገኙት አሰልጣኞች ምን ውጤት አምጥተው ነው በብሔራዊ ቡድኑ ላይ የተሾሙት፡፡ የአንድ አገር ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝነት ዝም ብሎ ከመሬት ተነስቶ መሰጠት የበለትም፡፡ ለእኔ የብሔራዊ ቡድኑ ኃላፊነት የተሰጠኝ በሂደት ነው፡፡
መጀመሪያ የተስፋ ቡድን አሰልጣኝ ነበርኩ በተስፋ ቡድን ያደረግኩትን አስተዋኦ እና በክለቦች ዋና አሰልጣኝነት በአገር ውስጥ በዓለም አቀፍ ውድድሮች የነበረኝን ልምድ በመንተራስ የተረከበኩት ሃላፊነት ነው፡፡ መጀመርያ የያዝኩት የተስፋ ቡድን ከ22 ዓመታት በፊት በተዘጋጀ ውድድር ላይ የተሳተፈ ነው፡፡ ዋናው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመንግስቱ ወርቁ የሚሰለጥን ነበር፡፡ በወቅቱ የተስፋ ቡድኑ የተሳተፈበት ውድድር የናይጀሪያዎቹ ትልልቅ ተጨዋቾች እነ አሞካቺ፤ ያኪኒ ሁሉ የነበሩት ቡድነና እነሱዳንም ተጋባዦች ሆነው የተሳተፉበት ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያ በውድድሩ ላይ የተሳተፈችው በወጣት ቡድኑ እና በዋና ብሔራዊ ቡድኑ ነው፡፡
እንግዲህ በዚህ ሂደት ነው የተስፋ ቡድኑን የገነባሁት፡፡ ከፍተኛ ልምድ ያገኘሁበት ነበር፡፡ በወቅቱ ዋናው ቡድን አንደኛ ደረጃ ሲያገኝ የእኔ ተስፋ ቡድን ሁለተኛ ነበር፡፡
በተስፋ ቡድኑ እና በክለብ ደረጃ ካከበትኩትት ልምድ በኋላ ነው ወደ ዋናው ብሄራዊ ቡድን ሹመት የመጣሁት፡፡ የዋና ብሔራዊ ቡድን ኃላፊነት ከልምድ ጋር ተያይዞ መስጠት አለበት፡፡ ልምድ ያለው አሰልጣኝ በማናቸውም ሁኔታዎች ውስጥ ተፅእኖ ውስጥ አይገባም፤ የተቃራኒ ቡድኖችንም አቋም ስለሚያውቅ ጫና አይፈጠርበትም፡፡….
 ይቀጥላል   


Read 3301 times