Saturday, 05 December 2015 09:04

የምንጃሯ “ተራማጅ” ወይዘሮ!

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(5 votes)

• “በባዶ እግር የሚያስኬድ ባህል ለምን ጥንቅር አይልም”
• “ሸክም በአህያ እንጂ በሴት ጀርባ ማጓጓዝ መቆም አለበት”
• “ከአባይ ማዶ ጀምሮ የሴቶች ስቃይና እንግልት የበረታ ነው”

    ባለፈው ሰሞን ለሥራ ጉዳይ ወደ ሰሜን ሸዋ በተጓዝኩበት ወቅት ከአንዲት የ56 ዓመት ቆፍጣና የሴቶች መብት ተሟጋች ሴት ወይዘሮ ጋር የመገናኘት ግሩም ዕድል ገጠመኝ፡፡ ባለትዳርና ስምንት ልጆቻቸውን ለወግ ለማዕረግ ያበቁት እናት ወ/ሮ ትበልጪ ኃይሌ ይባላሉ፡፡ የአረርቲና አካባቢዋ የሸማቾች ማህበር ሥራ አስኪያጅ በመሆን ትርጉም ያለው ሥራ እየሰሩ መሆናቸውንም በልበሙሉነት ይናገራሉ፡፡
በአዳማ ገላውዲዮስ ት/ቤት እስከ 10ኛ ክፍል ትምህርታቸውን የተከታተሉት እኚህ ወ/ሮ፤  በሃላፊነት በሚመሩት የሸማቾች ማህበር ስጋ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ፣ ሥጋ መብላት እየፈለገ በአቅም ማጣት ሲቸገር ለኖረው ህብረተሰብ የዋጋ ንረትን እያረጋጉ እንደሆነ ገልፀውልኛል፡፡
በአካባቢያቸው ዝነኛና ተወዳጅ የሆኑት ወይዘሮዋ፤ በሁለመናቸው ሥልጡንና ዘመናዊ አስተሳሰብ አቀንቃኝ መሆናቸው በእጅጉ አስደንቆኛል፡፡ በቅርቡ ለሥራ ጉዳይ ወደ ባህርዳር ሄደው በነበረ ጊዜ ከአባይ ማዶ ጀምሮ የሴቶችን ስቃይና እንግልት ተመልክተው፣ በንዴት እንቅልፍ ማጣታቸውን ነግረውኛል፡፡ ሴቶች ከአቅማቸው በላይ ከባድ ሥራዎችን መስራታቸው፣ ያለ ጫማ ባዶ እግራቸውን መሄዳቸውና ባል በትሩን ይዞ ሲንጐማለል ሴቷ መሸከሟ በእጅጉ አንገብግቧቸዋል። የመንግስት አካል ወይም የአካባቢው የሴቶች ጉዳይ ቢሮ፣ የሴቶቹን ጉዳት እስካሁን አለመመልከቱንም ወይዘሮዋ ይተቻሉ፡፡
“በዚህ የሰለጠነ ዘመን ይሄ ሁሉ የሴቶች ስቃይ መኖሩ አሳዝኖኛል” ያሉት ወ/ሮ ትበልጪ፤ ይሄን ችግር ለመፍታት ይጠቅማሉ ያሏቸውን ጠንካራ የመፍትሔ ሃሳቦች ሰንዝረዋል፡፡ የሌሎች አካባቢ ሴቶች ስቃይና የኑሮ ጫና እንዲህ ያስደነገጣቸው ወይዘሮዋ፤ እሳቸው የሚኖሩበት የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ሴቶች የተሻለ ህይወት እንደሚመሩ ይገልፃሉ፡፡ ስለሴቶች ስለ ሴቶች መብት ተሟጋችነታቸው፣ የስጋ ዋና ስለማረጋጋት፣ እንዲሁም የግል ህይወታቸውን በተመለከተ ጠይቄአቸዋለሁ፡፡ በድፍረትና በልበሙሉነት ያወጉኝን እንደወረደ በሚጣፍጥ አንደበታቸው እነሆ፡-
ጨዋታችንን ከግል ህይወትዎ ብንጀምርስ...?
ያው ትውልድና እድገቴ ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ኩምቢ ቀበሌ ወልአብ ጎጥ ይባላል፡፡ ከዚህ ከአረርቲ ከተማ የግማሽ ሰዓት መንገድ ያስኬዳል፡፡ ከአንድ እስከ ስድስተኛ ክፍል በትውልድ አካባቢዬ ተምሬ፣ ከሰባት እስከ 10ኛ ክፍል ናዝሬት ገላውዲዮስ ት/ቤት ነው የተማርኩት፡፡
ከ10ኛ ክፍል በኋላስ…?
በወቅቱ የስርዓት ለውጥ ሊመጣ ነበር መሰለኝ… ረብሻ ሲፈጠርና በቅርብ ጓደኞቻችን ላይ አንዳንድ ችግር ሲደርስ፣ እኔና ባለቤቴ ትምህርቱን ትተን ወደ ወላጆቻችን ተመለስን፡፡
ባለቤቴ? አንድ ላይ ነበር የምትማሩት?
ኧረ የአንድ አካባቢ ልጆች ነን፡፡ አብረን ነው ያደግነው፡፡ ትምህርታችንን አቋርጠን ከተመለስን በኋላ ወላጆቻችን ጥሩ ወዳጆች ስለነበሩ፣ የእሱ ቤተሰቦች ልጃችሁን ለልጃችን ብለው ሽማግሌ ላኩ፡፡ የእኔ ቤተሰቦች ፈቃደኛ ሆነው ተጋባን፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በሰላምና በፍቅር አብረን አለን፡፡ 12 ልጆች ወልጄ አራቱ ሲሞቱብኝ፣ ሌሎቹ ሁሉም ቁምነገር ላይ ደርሰዋል። ከባለቤቴ ንጋቱ ውቤ ጋር ስንኖር ክፉ ነገር ደርሶብኝ አያውቅም፤ ወንድምም አባትም  ጓደኛም ማለት ነው። ልጆቻችን ሁሉ መሃንዲሶች ናቸው፡፡ ሀኪም ልጅም አለችን፡፡ ከውጭ መጥታ አዲስ አበባ የምትኖርና ኢትዮጵያ አየር መንገድ ይሰራ የነበረ፣ አሁን በግል ሥራ የሚተዳደር ልጅም አለን፡፡ የሚማሩ ልጆችም አሉን፡፡ ፈጣሪ የተመሰገነ ይሁን እኔ ለልጆቼ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢዬ ሰው ሁሉ እናት ነኝ፡፡ ህብረተሰቡ ለኔም ለባለቤቴም ፍቅር ሰጥቶናል፤ ተከብረን ነው የምንኖረው፡፡
በአካባቢዎ ለሴቶች እኩልነትና መብት በመሟገት ይታወቃሉ፤ ስለሱ ይንገሩኝ…
እርግጥ እኔ በምኖርበት ወረዳ የሴቶች ህይወት የተሻለ ነው፡፡ ትንሽ የመሰልጠን ነገር ይታያል፡፡ በትዳር ግንኙነት ባል ሚስቱን ማዳመጥና መብቷን ማክበር ተለምዷል፡፡ ከአለባበስ ከንፅህና አጠባበቅ ጀምሮ ሁኔታዎች ጥሩ ናቸው፡፡ እንደዛም ሆኖ ችግሮችን ስመለከት ከመናገር ወደ ኋላ አልልም፡፡ አሁን በቅርቡ ለስራ ጉዳይ ባህርዳር ሄጄ ነበር፤ ያን ጊዜ ከአባይ ማዶ ጀምሮ ወደዛ አካባቢ ያሉ ሴቶችን ስቃይና እንግልት ስመለከት ተናድጄም አላባራሁ፡፡ በጣም በጣም ነው ያዘንኩት፡፡ ለመሆኑ እንዲህ በሰለጠነ ጊዜ ይህ ሁሉ ስቃይ እንዴት ሊኖር ይችላል ብዬ እንቅልፍ አጥቼ ነው የከረምኩት፡፡
ምን ዓይነት ስቃይ ነው የተመለከቱት?
ሀይለኛ ሥራ ይሰራሉ፣ ከአቅማቸው በላይ እንደ አህያ ሸክም ይሸከማሉ፡፡ ይሄ ብቻ አይደለም፤ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፣ ያን ሁሉ ተሸክመው ደግሞ ባዶ እግራቸውን ነው የሚሄዱት፡፡ ያንን የሚያክል የጤፍ ሸክም በቅርጫት ሞልተው ተሸክመው በባዶ እግራቸው ሲኳትኑ ሳይ ውስጤ ክፉኛ አዝኗል፡፡ በዚያ አካባቢ በየደረጃው ያለው የመንግሥት አካል የሴቶቹን ጉዳት አልተመለከተም፡፡ ወይም የአካባቢው የሴቶች ጉዳይ ቢሮ ለእነዚህ ሴቶች እየሰራ አይደለም፤ አሊያም ደሞ እያየ እንዳላየ ሆኗል፡፡
እርስዎ የዚህን ወረዳ ማለትም የምንጃር ሸንኮራን የገጠር አካባቢ ሴቶች ዞረው ተመልክተዋል? አባይን ሲሻገሩ ካዩአቸው ጎስቋላ ሴቶች በምን ይለያሉ?
በእኛ ወረዳ በሴቶች የሚጓጓዝ ሸክምም በባዶ እግር መሄድም የለም፤ ድሮ የቀረ ታሪክ ነው፡፡ በአሁን ሰዓት የሴቱ ልብስ፣ ጫማው ጌጡ በአይነት ነው፡፡ እዚህ አካባቢ ወዟ የደረቀ ጎስቋላ ሴት ካየሽ እኔ እቀጣለሁ፡፡ እዚህ እኛ ከምንኖረው ህይወት የገጠሮቹ ሴቶች የበለጠ እየኖሩ ነው፡፡ እጃቸው አምስቱንም ጣታቸውን ብታይ በጌጥ የተንቆጠቆጠ ነው፡፡ እኛ አካባቢ አህያና ግመል ነው እቃ የሚጫነው፡፡ እዛ አካባቢ ደግሞ የሴትና የበቅሎ ስቃይ በጣም የበረታ ነው፡፡
እዚህ አካባቢ በቅሎ ለጭነት አያገለግልም?
በፍፁም! እዚህ አካባቢ በቅሎ የተከበረ ነው። ምርጥ መኪና ማለት ነው፡፡ እንደውም አሁን አሁን እየቀረ ነው እንጂ በድሮ ጊዜ ጥሩ በቅሎ ያለውና ጨዋ ሚስት የያዘ ሰው እጅግ ይከበራል፡፡ እዛ አባይን ስሻገር ያየሁት የሴቶችና የበቅሎ ስቃይ ግን እስካሁን እንቅልፍ ነስቶኛል፡፡ ምንድነው እንዲህ ዓይነት ግፍ በሰለጠነ ዘመን! በጣም በጣም ነው ያዘንኩት፤  አንጀት ይበላሉ፡፡
ለምን በባዶ እግራቸው እንደሚሄዱ አልጠየቋቸውም?
ኧረ አሳምሬ ጠይቄ ነበር፡፡ በባዶ እግር መሄድ ባህል ነው፤ ወግ ነው ብለውኝ አረፉ! እንዴት እንዴት ያለ ባህል ነው፡፡ ደሞ እኮ ወንዱ ምንም አይሸከምም! ዱላ ብቻ ይዞ እሷ እንደዛ ተሸክማ እያቃሰተች ዳገት ትወጣለች፤ ቁልቁለት ትወርዳለች፤ እሱ ዱላውን ትከሻው ላይ አድርጎ እየተጀነነ ከኋላ ከኋላ ይከተላታል፡፡ ይሄ የሚሆነው በምን የተነሳ ነው? በዚያ ላይ መውለድ አለ፡፡ እንደው የቤቱ እንግልት አንሷት ነው ይሄ ሁሉ መከራ? በርካታ ተማሪዎችን አይቻለሁ፤ አነጋግሬያለሁ፤ ዩኒፎርም ለብሰዋል ግን ባዶ እግራቸውን ናቸው፡፡ ለምን ስል… ባህል ነው፤ እንደ ውሻ በባዶ እግር የሚያስኬድ ባህል ለምን ጥንቅር አይልም! መጥፎ ባህል እኮ መጥፋት እንጂ መቀጠል የለበትም፡፡ እንደው አማራ ክልል ተብለን ተደበላለቅን እንጂ የእኛ የሰሜን ሸዋ ዞን ሴቶች እንዲህ አይነት ስቃይ የለባቸውም፡፡
እንደው ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
በተለይ በባህርዳር መንገድ ላይ ያሉት አካባቢዎች የሴቶች ስቃይ በአስቸኳይ መቆም አለበት! በባዶ እግር መሄድ እንደ ጎጂ ልማድ ታይቶ መወገድና ሴቶችና ህፃናት በጫማ መሄድ አለባቸው፡፡ ሸክም በአህያ እንጂ በሴት ጀርባ ማጓጓዝ በፍጥነት መቆም አለበት። የክልሉና የዞኑ  መንግሥታት ተመካክረው ሳይውሉ ሳያድሩ መፍትሄ መፈለግ አለባቸው፤ እውነቴን ነው፡፡ መንግሥት ለሴቶች እኩልነት እሰራለሁ ካለ፣ እነዚያን ምስኪን ሴቶች ይመልከታቸው ባይ ነኝ፡፡
በአረርቲና አካባቢዋ የሸማቾች ማህበርን በስራ አስኪያጅነት መምራት የጀመሩት መቼ ነው?
የሸማቾች ማህበሩ የተቋቋመው በ2000 ዓ.ም ነው። እኔ በኃላፊነት ማህበሩን መምራት ከጀመርኩኝ ሁለት ዓመት ከ7 ወር ሆኖኛል፡፡ እስካሁን ጥሩ እያስኬድነው ነው፡፡
እርስዎ ማህበሩን ሲረከቡት በምን ሁኔታ ላይ ነበር? አሁንስ ምን ለውጥ ታየ?
እኔ ስረከበው ካፒታሉ 200ሺ 974 ብር ከ30 ሣንቲም ነበር፡፡ የሚሰራውም በኪራይ ቤት ውስጥ ነበር፡፡ ወደዚህ ማህበር በህብረተሰቡ ተመርጬ ከገባሁ በኋላ ከወረዳው የተለያዩ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ለምሳሌ ከንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ፣ ከኮሙኒኬሽን ቢሮ፣ ከከተማው አስተዳደርና ከማዘጋጃ ቤቱ ጋር በመነጋገርና በማሳመን፣ ማህበሩ ከኪራይ ቤት ወጥቶ የራሱ ቢሮና የመሸጫ ቦታ አግኝቶ፣ ህብረተሰቡ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያለው ነዋሪ ስጋ መብላት እየፈለገ በአቅም ማጣት ሲቸገር ኖሯልና በስጋ በኩል ያለውን የዋጋ ንረት እያረጋጋን እንገኛለን፡፡ ከእኔ ጋር ያሉ አመራሮችም ጠንካራ በመሆናቸው፣ በስጋ በኩል ከፍተኛ ምስጋና ከህብረተሰቡ እየቀረበልን ነው፡፡
ከተማዋ ላይ ስጋ በኪሎ ስንት ብር ይሸጣል? የእናንተስ ዋጋ ምን ያህል ነው?
እንግዲህ በከተማዋ ለወጥ ተብሎ የሚሸጠው ስጋ 140 ብር ሲሆን ለቁርጥ ደግሞ 180 ብር ነው። እኛ ህብረተሰቡ እንዳቅሙ እንዲመገብ ለወጥ 90 ብር፣ ለቁርጥ 120 ብር ነው የምንሸጠው፡፡ አስቢው በእያንዳንዱ ላይ ያለውን የዋጋ ልዩነት፡፡ በዚህ ህብረተሰቡ ደስተኛ ነው፤ እኛም ደስተኞች ነን፡፡
ለህብረተሰቡ የምታቀርቡት ስጋ ብቻ ነው?
በዋናነት በስጋ ላይ ነው የምንሰራው፤ ነገር ግን በሳሙና፣ በኦሞ፣ በአጠቃላይ የፅዳት እቃዎች ላይም እንሰራለን፡፡ በአሁኑ ሰዓት አንድ ሳሙና በትንሹ ከ8 ብር በታች አይሸጥም፤ ተራ ሳሙና እንኳን፡፡ እኛ የጉለሌ 555 ሳሙና ምርቶችን ከ3 ብር ከ50 ጀምሮ ህብረተሰቡ እንደየአቅሙ ገዝቶ ንፅህናውን እንዲጠብቅ እየሰራን ነው፡፡
በዚህ አጋጣሚ “የባላገሩ አስጎብኚ” ድርጅት ባለቤት አቶ ተሾመ አየለን ላመሰግን እወዳለሁ። እሱ የጉለሌ ምርቶችን በሁሉም የሰሜን ሸዋ ዞኖች አከፋፋይና ወኪል ነው፤ ለእኛም ያለምንም መያዣ በእምነት ብቻ የዘጠና ሺ ብር እቃ ሰጥቶን ከሸጥን በኋላ እንድንከፍል ተባብሮናል፡፡
በአሁን ሰዓት የስጋ ዋጋ በእጅጉ ከመወደዱ የተነሳ ብዙኃኑ ስጋ የመብላት አቅም እንደሌለው ይታወቃል። እንደውም “5 በመቶው ብቻ ቁርጥ ሲበላ፣ 95 በመቶው ቁርጡን አውቆ ተቀምጧል” የሚል ቀልድ ሁሉ መጥቷል፡፡ መፍትሔው ምን ይመስልዎታል?
ይሄ ምኑ ነው ቀልድ? ጥርት ያለ እውነት እኮ ነው፡፡ ወደ ናዝሬትና አዲስ አበባ አካባቢ የቁርጥ ስጋ 280 እና 300 ብር መግባቱን ሰምቻለሁ፡፡ አንዳንዶች እኮ ወሩን ሙሉ በ300 ብር ደሞዝ የሚኖሩ አሉ። እንዴት ነው ስጋ የሚበሉት? ስለዚህ እኛ አካባቢ የወረዳችን መንግስት ትብብር አድርጎልን ይህን የሸማች ማህበር እንዳቋቋመ ሁሉ በመላው ኢትዮጵያ ተቋቁሞ ህብረተሰቡ እንዳቅሙ ስጋ እንዲበላ መደረግ አለበት። ደሀው የበይ ተመልካች ሆኖ እንዳማረው መቅረት የለበትም፡፡ ሸማቾች መስፋፋት አለበት፡፡ እኛ ደሀው ስጋ እንዲበላ ስለጣርን ያኮረፉን የገላመጡን አሉ፡፡ ግን ሁሉም ከልኩ አላለፈም፡፡ እኛ እርካታችን ደሀው ሲደሰት ማየት ነው። በቀጣይ በርበሬም በቅናሽ ልናቀርብ ተዘጋጅተናል፡፡ እያስፋፋን እያስፋፋን በሁሉም ነገር ህዝቡን እናገለግላለን፡፡ “እልል ስጋ በላን፤ እሰይ ተባረኩ፤ እንዳታቆሙ ቀጥሉ” እየተባልን እየተመረቅን ነው፡፡ ለእኛ ይሄ እርካታ ነው፡፡ በዚሁ እንቀጥላለን፡፡

Read 3580 times