Saturday, 11 February 2012 10:45

የመንገድ ዳር ፍልስፍናዎች

Written by  ቢኒያም ሐብታሙ
Rate this item
(0 votes)

ስለ አንድ ነገር ለመፃፍ ስነሳ ሁልጊዜ እራስ ምታት የሚሆንብኝ ፅሁፌን ምን ብዬ መጀመር እንዳለብኝ ማሰብ ነው፡፡ የሆነ፣ አይን ያዝ የሚያረግ አጀማመር፤ የፅሁፍ አይን አባት ይምጣልህ ወይ እንደማትሉኝ ነው፡፡ለማንኛውም ለዛሬው አይነ-ገባዊ አገባቤን ትቼ በቀላሉ ፅሁፌን ብጀምርስ? እንዲህ ብዬ … “ፍልስፍና ምንድን ነው?” ከላይ ያቀረብኩት ጥያቄ እራሱ ፍልስፍና መሆኑ ትዝ አለኝ፤ እንዲያውም የመጀመሪያ ደረጃ የፍልስፍና ጥያቄ /first level philosophy question/ ይሉታል፤ ማወቅ ስለምንፈልገው ነገር በቀጥታ መጠየቅ “እንትን ምንድን ነው?” በተለመደው የላቲን የቃላት ትርጉም አሰጣጥ ስንጀምር፣ የላቲኑ ቃል ፊሎሶፊያ ብሎ ይጠራዋል፣ ትርጉሙም አቅፍሮተ-ጥበብ /የጥበብ ፍቅር/ እንደማለት ነው፡፡ ጥበብ ስለ አንድ ነገር ያለንን ጥልቅ የሆነ አረዳድ እና አተረጓጎምን የሚጠይቅ ነው፡፡ ጥበብ እንደ ዕውቀት ተምረን የምናገኘው ነገር አይደለም፡፡ በጣም የበሰሉ ወይም የተማሩ ሰዎች የምንላቸው ጠቢባን ላይሆኑ ይችላሉ፤ በተገላቢጦሹ ግን ያልተማሩ ጠቢባንን እናገኛለን፡፡

ማወቅ ጥበብ አይደለም፤ ጥበብ ከማወቅ በዘለለ ጥልቅ መረዳትና የዕውቀት ትግበራን ይጠይቃል፡፡ አንድ ቀላል ማነፃፀሪያ እንደ አብነት ብንወስድ ሲጋራ የሚያጨስ ዶክተር ሲጋራ ለጤና ጠንቅ እንደሆነ ያውቃል፤ ነገር ግን ዕውቀቱን ባለመተግበሩ ጠቢብ አይሆንም፡፡ ለዚህም ነው ጥበብ እንጂ እውቀት የማያድነው፡፡

ፍልስፍናን ከአፍቅሮተ-ጥበብነት ትርጉሙ ባሻገር ከባህሪው በመነሳት “የመጠየቅ ሳይንስ” ብለው የሚጠሩትም አለ፡፡ ይህም ፍልስፍና የማይጠይቀው ነገር ባለመኖሩ ነው፡፡ ስለ ህይወት ይጠይቃል፣ ስለ ዕውቀት፣ ስለ አፈጣጠር፣ ስለ አምላክ፣ ስለ ምክንያታዊነት፣ ስለ አዕምሮ፣ ስለ ባህል፣ ስለ እምነት … የሚገርመው ነገር ስለ መጠየቅ እራሱ መጠየቁ ፍልስፍናን ከሌሎች የሳይንስ አይነቶች ለየት ያደርገዋል፡፡

ፍልስፍና የመጠየቅ ሳይንስ በመሆኑ every one is a philosopher /ሁሉም ሰው ፈላስፋ ነው/ ይላሉ የመስኩ ምሁራን፡፡ ምክንያቱም ይብዛም ይነስም፣ ይቅለልም ይወሳሰብም፣ ይጠርም ይርዘምም፣ የተማረ ይሁን ያልተማረ፣ ቪላ ውስጥ ይሁን ጎጆ ቤት ሁሉም ሰው ይጠይቃልና ነው፡፡

***

ሰሞኑን ለአንድ ጉዳይ ሲ ኤም ሲ ወደሚባል ሰፈር ሄጄ ያጋጠመኝን ነገር ላውጋችሁ፡፡ ሲኤምሲ ሚካኤል እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ቁጭ ብዬ ጫማዬን እያስጠረግሁ ነው፡፡ ጫማ ጠራጊዋ /ሊስትሮዋ/ በአካላዊ ግምት የ15 ወይም የ16 አመት ልጅ ትሆናለች፤ የለበሰችው ልብስ እላይዋ ላይ ነትቧል፤ ፊቷ ጉስቁልና ይታይበታል፤ ጭብርር ያለው ፀጉሯ እንደነገሩ በእራፊ ጨርቅ ሸብ ተደርጓል፡፡ ያው እኛ አገር ሴት ሊስትሮዎች ብዙም ስላልተለመዱ የሆነ ነገር እንድጠይቃት መጠይቀ-መንፈሴ ጠየቀኝ፡፡

ጥያቄዬን ሰነዘርኩ /እንዳልጎዳት እየተጠነቀቅሁ፣ ስሰነዝር ማለቴ ነው፣ እጄን የሰነዘርኩ አስመሰልኩት አይደል? ለነገሩ አንዳንዴ ምላስ ከእጅ ይልቅ ያሳምም የለ/

“የአዲስ አበባ ልጅ ነሽ?” አልኳት /የከተማ ልጅ ስራ ይንቃል በሚል ጭፍን አመለካከት/ ጭንቅላቷን ላይና ታች በማነቃነቅ መልስ ሰጠችኝ /አዎን መሆኑ ነው፡፡/ ዝም ብዬ ለተወሰኑ ሰኮንዶች ተመለከትኳት፤ ስለ ሆነ ነገር በጥልቅ የምታስብ ትመስላለች ወይም በምሽት አማርኛ በሃሳብ ሰክራለች፡፡ መጠይቀ-መንፈሴ እንደገና ሌላ ጥያቄ እንድጠይቃት ገፋፋኝ … “የት ነው የምትኖሪው?” አንገቱዋን ዙር ሊሞላው ትንሽ በቀረው አኳኋን ወደ ጎን በማዞር ከኋላዋ ወደምትገኝ ትንሽዬ የላስቲክ ድንኳን መሳይ ቤት ጠቆመችኝ፡፡ የሃዘን ስሜት ተሰማኝ፤ “ወጣት፣ ሴት፣ ጎዳና ተዳዳሪ፣ ሊስትሮ …” አልኩኝ በሃሳቤ፣ ወዲያውም አሳዘነችኝ፤ ነገር ግን ማዘኔ ፊቴ ላይ እንዳይታይ ለማድረግ በግድ ጣርኩ፤ አንድም ሆድ እንዳላስብላት ሌላም ጥንካሬና ሞራሏን እንዳልጎዳው በማሰብ ለጥቂት ሰኮንዶች ዝም አልኩኝ … ጫማዬን ጠርጋ ጨርሳለች፤ ስልክ እጠብቅ ስለነበር እዛው ቁጭ ብያለሁ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለሁ ግን ልጅቷ ያለማቋረጥ ሆዷን በሃይል ስትጨምቅ በተደጋጋሚ እያስተዋልኳት ነበር፡፡ “ሰላም አይደለሽም? ሆድሽን ለምንድነው እንደሱ የምታደርጊው?” አልኳት፤ ትንሽ እንደማቅማማት ካለች በኋላ “ሳላረግዝ አልቀርም” አለችኝ በቀዘቀዘና ቸልተኝነት በተሞላው ቅላፄ፡፡ “እንዴት!? ቦይ ፍሬንድ አለሽ? እንዳረገዝሽ በምን አወቅሽ?” ድንጋጤዬን ለመሸፈን የጥያቄ ውርጅብኝ አወረድኩባት /ምን አስደነገጠኝ ግን?/ ካንተ ነው ያረገዝኩት አላለችኝ፤ ሆ! ቢሆንም ካለችበት ሁኔታ አንፃር ያስደነግጣል/፡፡ የጥያቄዎቹ ውርጅብኝ ግድ የሰጣት አትመስልም፣ የለበጣ ሳቅ እየሳቀች መለሰችልኝ “እንደምታየው ጎዳና ላይ ነው የምኖረው፤ ስለዚህ የጎዳና ወንዶች እየመጡ ወሲብ እንድንፈፅም ይጠይቁኛል እኔም አማራጭ ስለሌለኝ አደርገዋለሁ” “አማራጭ ስለሌለኝ ስትይ?” አልኳት የጀመረችውን ወሬ እንኳን እስክትጨርስ ፋታ ሳልሰጣት “ያው እምቢ ብላቸው እንኳን በግድ ይገናኙኛል” ይሄኔ ፊቷ ላይ ደረቅ ምሬት ታየኝ፤ ንግግሯን ቀጠለች “አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እራሴ ወንዶች ጋር ሄጄ የምተኛበት ጊዜ አለ” “እንዴት ማለት?” አልኳት ንግግሯ ግልፅ ስላልሆነልኝ “በቃ! እራሴን ለማሞቅ እንዲሁም ብርዱንና ብቸኝነቱን ለማጥፋት” አለችኝ በግድየለሻዊ አነጋገር፡፡

የጭንቀት ይሁን፣ የግርምት ባላውቀውም እሩብ አውሎ ንፋስ ያህል ከተነፈስኩ በኋላ ሌላ ጥያቄ ሰነዘርኩ፣ “… እና … እርጉዝ ከሆንሽ ምን ልታደርጊ ነው?” “አላረግዝም!” አለችኝ ፍጥነትና እርግጠኝነት በተሞላበት አኳኋን፣ የተለመደውን የጥያቄዎች ናዳ አወረድኩባት “እንዴት? መድሃኒት ትወስጃለሽ? መሃን ነሽ?” ሰዓቴን ወስጄ በቁም ነገር ላዋራት መፈለጌ ምናልባትም ታሪኳን ለማወቅ ያለኝን ጉጉቴን ያሳያት መሰለኝ አልያም የቅድሙ ድብርቷ ማውራት ስትጀምር ለቀቃት መሰለኝ አሁን ቶሎ ቶሎ መመለስ ጀምራለች፡፡ “ብዙ ጊዜ ያጋጥምኛል፣ ማለቴ እርግዝና፣ ግን ሁሌም ሆዴ ውስጥ እያለ ሽሉን በእጄ እያሸሁ ስለማፈጥረው አርግዤ አላውቅም …” “ስ-ለ-ማ-ፈ-ር-ጠ-ው!...” ከሚለው ቃል/ቃር በኋላ ምን እንዳወራች አልሰማሁም፤ አመዴ ቡን ማለቱን ልጅቷ እራስዋ ከሁኔታዬ ተረድታለች፡፡

ረጅም ጊዜያትን የወሰደ ዝምታ በመሃላችን ሰፈነ .. እንደምንም እራሴን አረጋግቼ “አሁን የምታረጊውን ነገር/ወሲብን ማለቴ ነው/ ማድረግ ግዴታ ከሆነ ለምን የወሊድ መቆጣጠሪያ መድሃኒት አትወስጂም ወይም ኮንዶም አትጠቀሚም” አልኳት በምክር አዘል አነጋገር “ለምን ብዬ?” አለችኝ፤ አሁንም ግዴለሻዊነቷ ፊቷ ላይ ይነበባል፡፡ “እእእ … በመጀመሪያ ደረጃ እራስሽን ከእርግዝና ትከላከያለሽ፤ ሲቀጥል ደግም በወሲብ ከሚተላለፉ በሽታዎች በተወሰነ መልኩም ቢሆን ትጠበቂያለሽ፡፡” ይህን አረፍተ ነገር ከተናገርኩ በኋላ በመጣለት አማርኛ ማስታወቂያ የሰራ የጤና ባለሙያ የሆንኩ መሰለኝ፡፡ ንግግሬንም በመቀጠል “ጥንቃቄ በጎደለው የወሲብ ግንኙነት ኤች አይ ቪ እንደሚተላለፍ አታውቂም? ብዬ ጠየኳት፡፡” ሌላ ቆሌዬን የገፈፈ መልስ መለሰችልኝ “ኤች አይ ቪ ቢይዘኝስ፣ ምን ይመጣል?” መሞት ነው ቢበዛ” አለችች ቀለል ባለ አነጋገር፡፡

ወጋችን አስደንጋጭነቱን እና ግርምት አጫሪነቱን ቀጥሏል፤ የልጅቷ ከመጠን ያለፈ ግድየለሽነትና ድፍረት እያስገረመኝ “እርግጥ ነው በዚህም ሆነ በዛ ሁላችንም ሟች ነን፤ ጥያቄው ግን የመሞትና ያለመሞት ጉዳይ ሳይሆን አሁን ባለሽበት ሁኔታ በቂ ሕክምና ማግኘት አትችይም፤ ስለዚህ ቫይረሱ በደምሽ ውስጥ መኖሩ ደግሞ ያለሽበትን ሁኔታ ይብሱኑ ያከብደዋል፤ ስቃይሽን ያበዛዋል!” አልኳት መረር ባለ አነጋገር፣ ምናልባት አካሄዷን ወደ ኋላ መለስ ብላ እንድትመረምርና ከድርጊቷ እንድትቆጠብ ያደርጋታል ብዬ በማሰብ፡፡ በተቃራኒው ግን በግዴለሽነት እና በለበጣ ፈገግታ በመታገዝ “አሁን ኑሮ ቀሎልኝ ነው እንዴ የምኖረው? ኑሮዬ እራሱ የስቃይ አይደል እንዴ! ታዲያ የስቃይ ሞት ለኔ አዲስ ሊሆን ነው? እየተሰቃየሁ ኖሬያለሁ፣ እየተሰቃየሁ መሞት ነው ምን አዲስ ነገር አለው! ህይወት እንዲህ ናት፤ እየተሰቃየህ ትኖራለህ እንደተሰቃየህ ትሞታለህ”

ሌላ ረጅም ዝምታ፣ ጫማዬን አፅድታ ከጨረሰች ቆይታለች፣ የምጠብቀውም ስልክ ስለተደወለልኝ ተነስቼ መሄድ ነበረብኝ፤ ነገር ግን የልጅቷ ንግግርና አመለካከት በአንድ በኩል የሚያስደነግጥ በሌላ በኩል የሚያስገርም በመሆኑ መሄድ አልፈለኩም ነበር፤ ዳሩ ምን እንደምጠይቃት ወይም ምን ማለት እንዳለብኝ ግን አላውቅም፤ ባውቅም አንደበቴ ተቆልፏል፤ ደግሞስ ምን ልላት እችላለሁ? ለምን እንዲህ አይነት አስተሳሰብ ኖረሽ? ይህን ለማለትስ ምን ስልጣን አለኝ? በሰው አስተሳሰብና የግል ፍልስፍና ላይስ ለመፍረድ እንዴት እደፍራለሁ … እነዚህና ሌሎች ጥያቄዎች ጭንቅላቴ ላይ አቃጨሉብኝ፤ ሰዓቴን አየሁና ተነሳሁ፣ ዳጎስ ያለ ቲፕ ሰጥቻት ተሰናበትኩ /“ዳጎስ ያለ ስንት ነው እንዳትሉኝ?”/ ጉዳዬን ጨርሼ ወደ ቤቴ እያቀናሁ ከልጅቷ ጋር ያደረግናቸው ቃለ ምልልሶች በጭንቅላቴ ያለማቋረጥ ያቃጭላሉ፤ “ምን አይነት ፍልስፍና ነው!?” ለራሴ አጉረመረምኩ፡፡ ኢትዮጵያዊው የዙምራ ማህበረሰብ መሪ ዙምራ ኑሩ የተናገሩት ነገር ትዝ አለኝ “ፍልስፍና በመማር የሚመጣ አልያም ባለመማር የሚጠፋ አይደለም! እውነት ነው፤ ፍልስፍና አለም አቀፋዊ ጥበብ ነው፤ ፍልስፍና ህይወታችንን ትርጉም ለመስጠት የምንጠቀመው የህይወት ቅመም ነው፤ የተመጠነ ሲሆን ጣፋጭ ትርጉምን የሚሰጥ፣ የበዛ እንደው ደግሞ ህይወታችንን ምስቅልቅልና ትርጉም አልባ የሚያደርግ …

እውነትም “ሁሉም ሰው ፈላስፋ ነው!” ፍልስፍና በየትኛውም ቦታ ትገኛለች፤ በየጓዳው፣ በየጓሮው፣ በየቪላው፣ በየት/ቤቱ … በይበልጥ ግን በመንገድ ዳር፡፡ ሰላም!

Read 4286 times Last modified on Tuesday, 14 February 2012 08:38