Saturday, 05 December 2015 09:36

“...ጥሩ መስራት ጥሩ ነው...”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

 ኢትዮጵያ በታሪክና በባህል በጣም ሀብታም ከሚባሉት ተርታ ብትሆንም በሌላ በኩል ደግሞ ድሀ ከሚባሉት መካከል እንደሆነች ፊስቱላ ፋውንዴሽን የተባለ ድረገጽ ይናገራል፡፡ ይህ ድህነት ደግሞ ይበልጡኑ በሴቶች በተለይም ደግሞ እርጉዝ በሆኑት ላይ ጎጂ ተጽእኖ አለው፡፡ ኢትዮጵያ በመውለድ መጠን ከፍተኛ አሀዝ ከተመዘገበባቸው አገራት አንዱዋ ስትሆን የእናቶች ሞትም እንዲሁ ቀላል ቁጥር አይደለም፡፡ በእርግጥ በአሁኑ ወቅት የኢኮኖሚው መሻሻል እየታየ እና እናቶችን ከሞት የማዳን ተግባር ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገበት ውጤትም እየታየበት ነው፡፡
ሴቶች በረዥም ጊዜ ምጥ የተነሳ የሚከሰትባቸው የፊስቱላ ሕመም ከአካላዊ ጤና እጦት ባሻገር ማህበራዊ ሕይወትን የሚያውክ እና ቤተሰባዊ ግንኙነትንም የሚያበላሽ የስነልቡና ጉዳት የሚያደርስ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ በተደረገ ጥናት መሰረት በ36.000 እና 39.000 መካከል የሚገመቱ ሴቶች በመላ አገሪቱ የፌስቱላ ተጠቂዎች ናቸው፡፡ በየአመቱም በግምት እስከ 3000 /ሶስት ሺህ/ የሚደርሱ ሴቶች የህመሙ ተጋላጭ ይሆናሉ፡፡ በእርግጥ ይህንን በሚመለከት ምናልባት በሆስፒታሎች የተመዘገበው ቁጥር ይህንን ባያሳይ ሕመምተኞች ግን የሉም ማለት እንዳልሆነ መረጃው ይጠቁማል፡፡ ምክንያቱም ወደ ሆስፒታል ለመሄድ መጀመሪያ የቤተሰቡ ፈቃደኝነት የኢኮኖሚው ጉዳይ የመጉዋጉዋዣው እና የመንገዱ ሁኔታ እንዲሁም የህክምና ተቋም በአቅራቢያ ያለመኖር ተዳምሮ ብዙዎች ወደ ሕክምናው ሳይደርሱ በችግር በየመንደራቸው ይቀራሉ፡፡ ለዚህም እንደማሳያ የሚሆነው በአገሪቱ ባሉ የፊስቱላ ሆስፒታሎች ከፊስቱላ ጋር ከሀያ አመት በላይ የኖሩ በእድሜያቸውም ትልቅ የሆኑ ሴቶች ታካሚ እየሆኑ መምጣታቸው ነው፡፡
ዶ/ር አምባዬ ወ/ሚካኤል በፊስቱላ ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ሆስፒታል በሚሰሩበት ጊዜ የነበራቸው ገጠመኝ የሚከተለው ነበር፡፡
“...አንድ ቀን አንዲት ሴት ወደ ፊስቱላ ሆስፒታል በልጆቻቸውና በባልተቤታቸው ታጅበው መጡ፡፡ በመጀመሪያ ለሕክምናው የቀረቡት ዶ/ር ካትሪን ሐምሊን ጋ ነበር፡፡ ዶ/ር ምርመራ ልታደርግላቸው ስትጀምር ሴትየዋ እምቢ ነበር ያሉት፡፡ ለምን ስትላቸውም... እኔ ምንም ሕመም የለብኝም፡፡ ቤተሰቦቼ ዝም ብለው ነው ያመጡኝ... የሚል ነበር መልሳቸው። ይህ በተደጋጋሚ ከሌሎች ሴቶችም የሚያጋጥም በመሆኑ ለጊዜው ወደ አልጋቸው እንዲመለሱ ተደረገና ቤተሰቦቻቸውም ወደቤታቸው እንዲሄዱ ተደረገ፡፡ ወደ አልጋቸው እንዲመለሱ የተደረገውም አንድ ሁለት ቀን ሁኔታውን እንዲያዩና እንዲረጋጉ ነበር፡፡ ከሶስት ቀን በሁዋላ ሕክምናው ወደ እኔ ተመርቶ ስመለከተው ሴትየዋ በእድሜያቸው ከ55 /ሀምሳ አምስት/ አመት በላይ ናቸው፡፡ አስቀድሜም ልጃቸውን ማነጋገር መረጥኩና ሁኔታውን እንድታስረዳኝ ጋበዝኩዋት፡፡ ልጅትዋ በእርግጥ የተመረቀች እና ስራ ያላት ብትሆንም ስለእናትዋ ግን ማስረዳት አልቻለችም፡፡ ለቅሶ ብቻ ሆነ፡፡ አረጋግቸቼ... ስትነግረኝ ...ታሪኩ የሚከተለው ነበር፡፡”
“...እናታችን የስድስት ልጆች እናት ናት፡፡ ስድስታችንም ተምረን አሁን በስራ ላይ እንገኛለን፡፡ ታዲያ ...ልጆቹ ተነጋገርንና የጋብቻ በአላቸውን ልናከብር ስንዘጋጅ... አባታችን     ከበአሉ በፊት ግን አንድ የምነግራችሁ ነገር አለ... አለን፡፡ እኛም ምንድነው ብለን... ስናደምጠው... እስከአሁን ድረስ ዝም ብለን ምስጢራችንን ደብቀን ኖረናል፡፡ ከዚህ በሁዋላ ግን ልጅነት ስለሌለ እና ዘመኑም ስለሰለጠነ እናንተም ስለደረሳችሁ አንድ ነገር ብታደርጉ ብዬ ነው... አለ፡፡ ምንድነው? ስንል ጠየቅነው። እናታችሁ ከሰላሳ አመት በላይ ሽንት መቆጣጠር አትችልም... ይፈሳታል... ሲለን... ሁላችንም አንድ ላይ ነበር የጮህንበት... እናታችን ታድያ... እኔ እግዚሀር ነው የፈረደብኝ፡፡ እሱ ምን ያርገኝ... ሽንት ሽንት አልሽኝ ብሎ አልጣለኝ... እንደ ህጻን ልጅ ዲያፐር እየገዛ አስተናግዶኛል፡፡ ገና በመጀመሪያ ልጄ ነው ልክፍቱ የመጣብኝ፡፡ ግን ከዚያ በሁዋላ አምስት ልጅ     ወልጃለሁ... በድምሩ እንግዲህ የስድስት ልጆች እናት ስሆን ባለቤቴ ተንከባክቦ እዚህ አድርሶኛል፡፡እኔ አሁንም ሕመም የለብኝም በቃ... ነበር ያለችን፡፡ አሁን ወደ ሆስፒታሉ ያመጣናት ለምነን በትግል ነው፡፡” አለችኝ፡፡
ዶ/ር ካትሪን ሕመምተኛዋን ወደእኔ ስትመራ ማደንዘዣ ተሰጥቶአቸው ምርመራው እንዲደረግላቸው ነበር፡፡ በሁዋላ ግን በሆስፒታሉ ግቢ እንዲሁም በመኝታ ክፍሎቹ ያሉትን ሰቶች ሲመለከቱ እና ሲጠይቁ ሁሉም የሽንት ችግር ገጥሞአቸው መምጣታቸውን ሲነግሩአቸው... አሀ... ለካንስ ችግሩ የእኔ ብቻ አይደለም... የሁሉም ሴቶች ነው ብለው አመኑ፡፡ እኔም ሳነጋግራቸው ...አረ አኔ ማደንዘዣም አልፈልግ... ችግሩ የመላ የሴቱ ችግር አይደለም እንዴ... አረ እንዲያው ወይኔ... አለማወቄ ጎድቶኝ ኖሯል... አሁንማ እመረመራለሁ... ብለው ሕክምና ተደርጎላቸው ድነው ሄደዋል፡፡
ዶ/ር አምባዬ ወ/ሚካኤል የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ሲሆኑ ለረዥም አመታት በሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ በአዲስ አበባው ሆስፒታል ሰርተዋል፡፡ ለትውስታ ያህል ስለሐምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል በመጠኑ እናስነብባችሁ፡፡
ሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1974 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን ያቋቋሙትም ባልና ሚስቶቹ ዶ/ር ካትሪንና እና ሬግ ሐምሊን ናቸው፡፡ ባልና ሚስቶቹ ይህንን ሆስፒታል ያቋቋሙት በኢትዮጵያ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚመጡ የፊስቱላ ታማሚዎችን በማየታቸውና ስቃያቸውም ከፍተኛ በመሆኑ ያንን ለመቀነስ አስበው ነበር፡፡ ዶ/ር ካትሪን ሐምሊን ባለቤታቸው ካረፉም በሁዋላ አንድም ቀን ከስራው ሳይለዩ ከግማሽ ምእተ አመት በላይ የፊስቱላ ታማሚዎችን እየረዱ ነው፡፡ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ጊዜ የህክምና ዲግሪያቸውን የተማሩት ዶ/ር ካትሪን ሐምሊን ዛሬ የ91 /ዘጠና     አንድ/ አመት ሴት ናቸው፡፡ ሐምሊን የሚያስተዳድሩት የአዲስ አበባው ሐምሊን  ፊስቱላ ኢትዮጵያ አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የህክምና ማእከልና ዶክተሮችን የማሰልጠኛ ቦታም ነው። ሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ በስሩ የሚተዳደሩ 5 /አምስት/ ሆስፒታሎች በየመስተዳድሩ የሚገኙ ሲሆን በአዲስ አበባም አዋላጅ ነርሶች የሚማሩበት ኮሌጅ እንዲሁም ከሕክምና ብዙም መራቅ ለሌለባቸው ታካሚዎች ማረፊያ የሚሆን ደስታ መንደር ተመስርቶ በስራ ላይ ነው፡፡
ዶ/ር አምባዬ ወ/ሚካኤል ፊስቱላ የደሀ በሽታ ነው ይላሉ፡፡ ምክንያቱም፡- “....ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ ሕመሙ የሚታየው በገጠራማው የኢትዮጵያ ክፍል ሲሆን ከገጠርነቱም ለመታከም ብዙ አቅም የሌላቸው ሲሆኑ ከሕመሙ ጋር አብረው ለመኖር ይገደዳሉ፡፡ ስለዚህ እኛ ማድረግ ያለብን ህብረተሰቡ ወይንም አገሪቷ በሙሉ ሐብታም እስክትሆን ድረስ መጠበቅ አይደለም። አቅማችን በፈቀደው መንገድ እጃችን ላይ ባለው ነገር ህብረተሰቡን በእውቀት ማስታጠቅና የህክምና ባለሙያዎችን ማሰልጠን     እንዲሁም አገልግሎቱን በተቻለ መጠን ለማዳረስ ጥረት ማድረግ ነው፡፡ ያም በመሆኑ ዛሬ በሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ከተመሰረቱት የህክምና ተቋማት በተጨማሪ Women And Health Alliance International Ethiopia በዋሀ አጋዥነት በሶስት መስተዳድሮች በሚገኙ ሆስፒታሎች ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በተያያዘ የፊስቱላ  ሕክምና ማእከልን መስርተናል፡፡ እነርሱም በጎንደር፣ በአሰላና በጅማ ናቸው፡፡”
የጎንደር ፊስቱላ ሐኪም ቤት አመሰራረትን በሚመለከት በስፍራው ተገኝተን ያነጋገርናቸው ዶ/ር ኪሮስ ተረፈ እንደገለጹት...
“...የጎንደር ፊስቱላ ሆስፒታል የተሰራው በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2011 ዓ.ም ነው፡፡ የተሰራውም በWomen And Health Alliance International Ethiopia ትብብር ሲሆን የፊስቱላ ሕመም በአካባቢው ከፍተኛ ችግር የነበረ ስለሆነ በጅምር ቆሞ የነበረ ቤት አስጨርሰው ስራቸውን እንዲቀጥሉ በሆስፒታሉ ኃላፊ ተፈቅዶ የተሰራ ነው፡፡ በእርግጥም ጠቃሚ በመሆኑ እነሆ እስከአሁን ድረስ ወደ አንድሺህ የሚጠጋ ታካሚን አስተናግደናለን፡፡ ሕክምናው የሚካሄደውም የፊስቱላ ታካሚዎች በሆስፒታሉ ከደረሱ በሁዋላ አልጋ ይዘው ዶ/ር ሙሉን ወይንም ዶ/ር አምባዬን ይጠብቃሉ፡፡ እነርሱም በፕሮግራሙ መሰረት መጥተው ቀዶ ሕክምናውን አድርገው የሚመለሱ ሲሆን ቀሪውን ሕክምና ሆስፒታሉ ያደርግላቸዋል። በተያያዘም የህክምና ተማሪዎች የሚያስፈልጋቸውን የተለየ ስልጠና ያገኛሉ፡፡”
ዶ/ር አምባዬ ወ/ሚካኤል የአለም አቀፉ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ፌዴሬሽን በዘንድሮው አመታዊ ጉባኤ ተሸላሚ አድርጎአቸዋል፡፡ ለሽልማቱ ከኢትዮጵያ የተላኩትም በኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር አማካኝነት ነወ፡፡ የማህበሩ ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሰላማዊት ክፍሌ የሚከተለውን ገልጸዋል፡፡
“...የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ለውድድሩ ዶ/ር አምባዬን ያቀረበው በተመሳሳይ የስራ መስክ ከተሰማሩ ሴት የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች አወዳድሮ ነው። በውድድሩም ዶ/ር አምባዬ ወ/ሚካኤል ሲመረጡ የተለያዩ መስፈርቶችን በማለፋቸው ነው፡፡ የሽልማቱም አላማ እውቅና መስጠት ሲሆን መስፈርቱም... በጽንስና ማህጸን ሕክምና ውስጥ ሳይንሳዊ ምርምርን በተመለከተ ምን አስተዋጽኦ አድርገዋል? የእናቶችና ሕጻናት ጤና ላይ አስተዋጽኦዋቸው ጎልቶ መውጣት አለበት... የሚሉ መስፈርቶች የተቀመጡ ሲሆን በአገልግሎት ዘመንም እንዲሁም ለሌሎች ሰዎች እውቀትን በማካፈል ረገድም የተሰሩ ስራዎችን በመመርመር አሳልፈናቸዋል። በአለም አቀፉም መድረክ ከተለያዩ አገራት ተወዳድረው ከመጡ ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር ተፎካክረው በማሸነፋቸውም የዘንድሮው ተሸላሚ ዶ/ር አምባዬ ወ/ሚካኤል ሆነዋል፡፡ ከአሁን በፊትም ዶ/ር ካትሪን ሐምሊን... ዶ/ር ዙፋን ላቀው... ዶ/ር ሙሉ ሙለታ... አሸናፊ ሆነው መሸለማቸው አይዘነጋም፡፡
ዶ/ር አምባዬ በስተመጨረሻው የተናገሩት የሚከተለውን ነው፡
“...ሰው መቼም ሲሸለም ደስ ይለዋል፡፡ ደስ ብሎኛል፡፡  ነገር ግን እኔ ስሰራ እሸለማለሁ     ብዬ ሳይሆን ስራዬን ነበር የምሰራው፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው ስራው በሌላ ወገን ተገምቶ ደረጃ ሲሰጠው እና እውቅና ሲያገኝ ደግሞ ያስደንቃል። ይህ እውቅና ማግኘት     እንግዲህ ከኔ  በሁዋላ ላሉ ገና በመማር ላይ ለሚገኙ ሁሉ ሞራልን የሚገነባ ነው፡፡ ለካስ ጥሩ መስራት ጥሩ ነው የሚል ግንዛቤ እንዲፈጥርላቸው ያስችላል፡፡ እኔ እናቶችን  ለማዳን የምቆጥበው ጊዜ የለኝም፡፡ በሙሉ አቅሜ አብሬአቸው ነኝ፡፡”

Read 2071 times