Saturday, 12 December 2015 11:29

ባል ሲሞት መደሰት

Written by  ደራሲ፡- ኬት ሾፒን ተርጓሚ፡- አሸናፊ አሰፋ
Rate this item
(12 votes)

     ወይዘሮ ማላርድ የልብ ድካም በሽታ አለባት። እህቷና የባሏ ጓደኛ፣ የባሏን ድንገተኛ ሞት ለማርዳት ጭንቅ ጥብብ አላቸው፡፡
እህቷ ጆሴፍን እንድታረዳት ሆነ፡፡ ጆሴፊን በተቆራረጡ አረፍተ ነገሮች፣ በተድበሰበሰ ጥቆማ፣ ነገረቻት፡፡ መርዶው ለወይዘሮ ማላርድ ሲነገር የሟች የአቶ ማላርድ ጓደኛ ሪቻርድስ በቦታው ነበር። ሲጀመር ገና የአቶ ማላርድን መሞት ያወቀው ሪቻርድስ ነበር፡፡ በሆነ ጉዳይ ጋዜጣ አታሚዎቹ ቢሮ ተገኝቷል፡፡ እናም ለጋዜጣ አታሚዎቹ በእለቱ ስለደረሰው የባቡር አደጋ ቴሌግራም ይላካል። የጓደኛው ብረንትነረ ማላርድ ስም “የተገደሉ” ከሚለው ዝርዝር ውስጥ የመጀመሪያ ሆኖ አነበበ። ጉዳዩ እርግጥ መሆኑን በቴሌግራም አረጋገጠ። ጊዜ አላጠፋም፡፡ ግድ የለሽ የሆነ ወይም ወጉን የማያውቅ አንዱ ጓደኛቸውዘ መርዶውን ለወይዘሮ ማላርድ ቀድሞ እንዳይነግር ተጣደፈ፡፡ ሴትየዋ ለራሷ የልብ ህመምተኛ ናት፡፡
ወይዘሮ ማላርድ መርዶውን ስትሰማ ሌሎች ሴቶች እንደሚሆኑት አልሆነችም፡፡ አልፈዘዘችም። አልደነገዘችም፡፡ አልተልፈሰፈሰችም፡፡ “እኔ አላምንም ይሄን!” ምናምን አላለችም፡፡ አለቀሰች። እዚያው አነባች፡፡ እራሷን የእህቷ እቅፍ ላይ ጥላ ተንሰቀሰቀች፡፡ በአንዴ ያጥለቀለቃት የሀዘን ማዕበል ሲያባራ፣ ሲሰክን ወደ ክፍሏ ሄደች፡፡ አንድም ሰው ስንኳ እንዲከተላት አልፈለገችም፡፡ ክፍሏ ውስጥ ከመስኮቱ አንፃር ምቹ ወንበር አለ፡፡ ትልቅ ነው። ዘፍ አለችበት፡፡ ሰውነቷ በማታውቀው ድካም ዝልፍልፍ ብሎባታል፡፡ ሰውነቷን የያዘው ድካም ወደ ነፍሱዋ እየተንፏቀቀ ሄደ፡፡ ነፍሱዋም በድካም ተያዘች፡፡ ነፍስ - ወ - ስጋዋ ድቅቅ አለ፡፡
በክፍሏ መስኮት የዛፎቹ አናት ይታያል፡፡ ዛፎቹ ለአዲሱ የፀደይ ህይወት ጅማሬ እያሸበሸቡ ነው፡፡ ዝናብ ሊመጣ ሲል ያለው ጣፋጭ ሽታ አየሩን አውዶታል፡፡ ሱቅ በደረቴ የእቃዎቹን ስም እየጠራ ሲጮህ ይሰማል፡፡ የሆነ ሰው ከሩቅ የሚያንጐራጉረው ዘፈን በስሱ ይሰማል፡፡ ወፎች ዝማሬያቸውን ለቀውታል፡፡ በመስኮቱ በምእራብ በኩል ደመናዎቹ ከትቅቅፋቸው ሲላቀቁ ሰማያዊው ሰማይ እዚህም እዚያም ብቅ ይላል፡፡
ጭንቅላቷን የወንበሩ መደገፊያ ላይ አሳርፋለች። አትንቀሳቀስም፡፡ እያለቀሰ እንቅልፍ የወሰደው ልጅ ተኝቶም እንደሚያለቅሰው፣ አልፎ አልፎ ሳግ እየመጣ ይንጣታል፡፡
ወጣት ናት፡፡ ቆንጅየው ፊቷ እርጋታ አለበት። ብዙ ነገር አምቃ እንደያዘች ፊቷን አይቶ ማወቅ ይቻላል፡፡ ጥንካሬ ቢጤም የፊቶቿ መስመሮች ላይ አለ፡፡ አሁን ግን ትክትና ፍዝዝ ብላ በመስኮቱ አሻግራ ሰማዩን እያየች ነው፡፡ አስተያየቷ የቁዘማ አይደለም፡፡ አኳኋኗ ሊነቃ ያለን አደገኛ ሃሳብ እንዲተኛ የሚያባብል አይነት ነው፡፡   
የሆነ ነገር ሊመጣ እንደሆነ ታውቋታል። በፍርሃት እየጠበቀችው ነው፡፡ ምንድነው ነገርየው? አላወቀችውም፡፡ እጅግ ረቀቅ ያለ ነው። ሊይዙት ሲል ያመልጣል፡፡ ስም ሊያወጡለት ይከብዳል፡፡ ይህ ነው የሚባል አይደለም። ከሰማዩ ውስጥ ወደ እሷ እየተንሸራተተ ብቅ አለ። የአካባቢውን ድምፅ፣ ጠረንና ቀለም ለብሶ፣ ቀስ እያለ፣ እያዘገመ ተጠጋት። ሆዷ ከፍ ዝቅ፣ ከፍ ዝቅ ይላል፡፡ ሁለንተናዋን ሊቆጣጠር ያለው ነገር ምን እንደሆነ ሊታወቃት ጀምሯል፡፡ ገፍታ ወደመጣበት ልትመልሰው ሞከረች፤ አልቻለችም። ነጫጭ፣ ረጃጅም እጆቿ አቅመ ቢስ ሆኑባት፡፡ ፍስስ አሉባት፡፡
ከራሷ ጋር መታገሉን ስትተው ገርበብ ካሉት ከንፈሮቿ አንድ ቃል በሹክሹክታ አመለጠ፡፡ ደጋግማ አለችው፡፡
“ነፃ!”
“ነፃ!”
“ነፃ!”
መፍዘዟን ተወች፡፡ ድንጋጤዋ ብን ብሎ ጠፋ። አይኖቿ መርማሪና ብሩህ ሆኑ፡፡ ልቧ ምቱን አፈጠነ። መጋለብ የጀመረው ደሟ የሰውነቷን ቅንጣቶች በሙሉ አሞቃቸው፤ አነቃቸው፡፡ ዘና፣ ፈታ አደረጋቸው፡፡
ምን አይነት ደስታ ነው የሰፈረብኝ? ብላ ራሱን ጠየቀች፡፡ ይህ ክፉ መንፈስ አይደለምን? ይህ ከሰይጣን ሳይሆን ይቀራልን? የሚል ሃሳብ መጣባት። ግን አይደለም፡፡
እንባ እንደማይቸግራት ታወቃት፡፡ እኛን ተንከባካቢና ስስ እጆቹን በሞት ታቅፈው ስታይ አለምንም ጥርጥር ታለቅሳለች፡፡ ፊቱስ ቢሆን? ያንን አንድም ቀን ጥላቻ አንብባበት የማታውቀውን ፊቱን፣ ሁሌም እሷን ሲያይ በፍቅር የሚጥለቀለቀውን ፊቱን ስታይስ? ያን መሳይ ፊቱን ሞት አገርጥቶት፣ አድርቆት፣ በድን ሆኖ ስታይ እንባ አይገዳትም። ታለቅሳለች፡፡ ከዚህ ቶሎ ከሚያባራ መሪር ሀዘን በኋላ ግን የማያባራ ደስታን የተሸከሙ ብዙ አመታት እየተከታተሉ ታዩዋት፡፡ እንኳን ደህና መጣችሁልኝ ልትል እጆቿን ዘረጋች፡፡
እንዴት ያለ እፎይታ ነው!! በሚመጡት አመታት ለሷ ብሎ የሚኖር፣ ወይም ላንቺ ብዬ እኮ ነው የምኖረው የሚል አንድም እንከፍ አይኖርም። እሷ ናት ለራሷ የምትኖረው፡፡ ለአንቺ ብዬ ነው እኮ ብሎ በማያቋርጥ ንዝነዛ የገዛ ፈቃዷን ገፍቶ የግል ፈቃዱን ወይም ፍላጐቱን የሚጭንባት አንድም ሰው፤ ወይም ሰው ነኝ ባይ አይኖርም፡፡ አላማው በጐም ይሁን ክፉ የራስን ፈቃድ ሌላው ላይ መጫን ወንጀል ነው፡፡
ባሏን ታፈቅረው ነበር፡፡ አልፎ አልፎ ነው ግን። ብዙውን ጊዜ አታፈቅረውም ነበር፡፡ አሁን ይኼ ምን ለውጥ ያመጣል? ምንም፡፡ ፍቅር ይሉት ነገር፣ ምስጢሩ የማይታወቅ ነገር፣ አሁን በሁለንተናዋ እየተሰማት ካለው ምሉእ የመሆን ስሜት ጋር ይወዳደራል?! ጨርሶ፡፡ እኔነት በእያንዳንዱ የህልውናዋ ቅንጣት ተሰማት፡፡
“ነፃ”
“ሰውነቴ ነፃ ወጥቷል፡፡”
“መንፈሴ ነፃ ወጥቷል”
ደጋግማ አለች፡፡
ጆሴፊን ተንበርክካ በበሩ የቁልፍ ቀዳዳ በኩል እህቷን እየተለማመጠች ነበር፡፡ “ሉዚ፣ በሩን ክፈቺው! እባክሽ ተለመኚኝ በሩን ክፈቺው! እራስሽን ነው የምታሳምሚው፡፡ ሉዚ፣ ምን እያደረግሽ ነው? ስለ አምላክ ብለሽ በሩን ክፈቺው።”
“ሂጂልኝ፡፡ እራሴን እያሳመምኩ አይደለም፡፡” ማየ-ህይወት (Elixir of Life) እየጠጣች ነበር፡፡
ምናቧ ከፊት ወደሚጠብቋት የሀሴት ቀናት በብርሃን ፍጥነት ተጓዘ፡፡ ከአሁን ወዲያ የፀደይ ቀናት የእሷ ናቸው፡፡ ከአሁን ወዲያ የበጋ ቀናት የእሷ ናቸው፡፡ ሁሉም ቀናት የእሷ ናቸው፡፡ እድሜዋ ረዥም እንዲሆን ፈጣን ፀሎት አደረሰች። ትናንት ግን እድሜዋ አጠረ ረዘመ ደንታ አልነበራትም። ትናንትና ስለ ህይወት መርዘምና ማጠር አስባ በግድየለሽነት ትከሻዋን ሰብቃ ነበር፡፡
የእህቷ ንዝንዝ አስጠልቷት ቀስ ብላ ተነሳችና በሩን ከፈተች፡፡ የድል አድራጊነት ስሜት አይኖቿ ውስጥ ይንቦጎቦጋል፡፡ ስትራመድ ከአማልክቶቹ እንደ አንዷ ነበር፡፡ ለዚያውም የድል አድራጊነት አምላክ ትመስል ነበር፡፡ የእህቷን ወገብ እቅፍ አድርጋ፣ ደረጃውን ይወርዱ ጀመር፡፡  ሪቻርድስ ታች፣ ደረጃው ስር ቆሞ እየጠበቃቸው ነበር፡፡
የሆነ ሰው የቤቱን ዋና በር በቁልፍ ሲከፍት ተሰማ፡፡ መንገድ ፊቱን ያጠየመው፣ የመንገድ ቦርሳና ዣንጥላ የያዘ፣ ቆፍጠን ያለ ሰው ገባ። ብረንትሊ ማላርድ ነው፡፡ እንኳን አደጋ ሊደርስበት፣ አደጋ ከደረሰበት ቦታ እጅግ ርቆ ነበር የከረመው፡፡ አደጋ መከሰቱንም አልሰማም እሱ፡፡
ጆሴፊን እሪታዋን ስታቀልጠው፣ ሪቻርድስ በፍጥነት ሊከልለው ሲሞክር ብረንትሊ በአግራሞት እያያቸው ነበር፡፡ ወይዘሮ ማላርድ ባለቤቷን እንዳታየው ነበር የጣረው፡፡
ሪቻርድስ በጣም ዘግይቷል፡፡
ዶክተሮቹ በልብ ድካም ነው የሞተችው አሉ። በደስታ ብዛት፡፡
እ.ኤ.አ 1984 ዓ.ም
(የእንግሊዝኛው ርዕስ፡- The Story of an Hour)
ስለ ደራሲዋ፡-
ኬት ሾፒን እ.ኤ.አ በ1850 ተወልዳ በ1904 ዓ.ም የሞተች አሜሪካዊት የአጫጭርና የረዣዥም ልብ-ወለዶች ደራሲ ናት፡፡ በደራሲነቷ ብቻ ሳይሆን በሴቶች መብት ተቆርቋሪነቷም ትታወቃለች። አንዳንዶች እንዲያውም የሴቶች መብት ተቆርቋሪነቷን በብዕሯ አደባባይ ይዛ በመውጣት ቀዳሚዋ ናት ይሏታል፡፡

Read 4525 times