Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 11 February 2012 10:53

የግጥም ጥግ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

መታሰቢያ

ገብረክርስቶስ ደስታ (1947)

በእጅ ላይ የሚውል የጣት ቀለበት

ባንገት የሚደረግ ወይም በደረቅ፣

በወርቅ የሰከረ ባልማዝ ልቡ ጠፍቶ

የተደከመበት ብዙ ገንዘብ ወጥቶ፣

ስም የተጻፈበት ሰጪን ለማስታወስ

እጅ የሚዳብሰው የሚቀመጥ በኪስ፣

የሚሰሰትለት የሚሆን ለጌጥ

መንፈስ የሚወደው ሞገስ የሚሰጥ

በጣም የሚደነቅ ሥራው የረቀቀ

ይኽ መታሰቢያ ነው ጠፍቶ ካልወደቀ፡፡

ሲቀመጥ የሚያምር በጠረንጴዛ ላይ

ክቡር ድንቅ የሆነ ጧት ማታ የሚታይ፣

ያበባ ማኖሪያ ገጸበረከት

የሚያማምር ሐረግ የተጣለበት፣

የወዳጅ ስጦታ ወይ ፎቶግራፍ

ለልጅ ልጅ የሚሆን የሚተላለፍ፣

ቤት ካልተቃጠለ፣ ሌባ ካልሰረቀው

ወይ ካልተቀደደ ሕጻን ካልሰበረው

የሩቁን ያቀርባል ይኸ መታሰቢያ ነው፡፡

በደንብ የታሠረ ቀይ ክር ያለበት

በሳጥን የሚኖር የፍቅር ወረቀት፣

“አትርሱኝ” የሆነ የፀጉር ጉንጉን

አስታዋሽ ፈላጊ ጥንት የቀረውን፡፡

ቁልፍ የሚጠብቀው ባመት የሚወጣ

ልብስና መሀረም የሚኖር በሻንጣ፣

ጫማም የውስጥ ልብስ ትንኒሽ ስጦታ

ለጊዜው ያጠግባል ሲታይ በደስታ፣

ነጋሪ ይናል ብል ካላነተበው

ያለፈውን ጊዜ መልሶ ሲያመጣው፡፡

ቁልፍ የማይደብቀው መታሰቢያ ሞልቷል

በግልጽ እየታየ ሊሰወር ይችላል፣

ሳጥን መክፈት የለም ወረቀት ማንበብ

ቦታው፣ ማከማቻው፣ ማደሪያው ነው ልብ፣

ብርሃን አያሻውም ጨለማ አይጋርደው

ጊዜ አይለውጠውም ዓይን እንኳን ባያየው፤

ልስልስ ጣፋጭ ጥፊ ጉንጭ ላይ የሚያርፍ

“እወድሀለሁኝ” ብሎ ሲጋረፍ

የሚያማምረው ጣት ፍጹም አይረሳም፡፡

ወረቀት በመጻፍ ዝብዝብ አያሻም፡፡

ወይም አለ ቁጣ ውስጡ የውሸት

ፈገግታን የሚሰጥ ሲያሰላስሉት፣

ወዲያው ተለውጦ ደግሞም በመሳቅ

አፍን ከፈት አርጎ ከንፈርን ለቀቅ፣

ጥርስን አሳይቶ ፈዞ በማስተዋል

ከንፈርን ከከንፈር አምጥቶ በማዋል፤

ሙዚቃው ሲዘፍን ቀዩ ብርሃን በርቶ

ዳንሱን ሲራመዱት በጣም ተጠጋግቶ፤

ጆሮን ሲማርከው ቀስ ያለው ንግግር

መታሰቢያ ይኽ ነው የማይበላው አፈር፡፡

ሁኔታው ጊዜውም ቦታው ተጨምሮ

አስታዋሽ በመሆን የሚኖር ነው አብሮ፣

በፍጹም አይዝግም አያረጅ ቢቀመጥ

እያሸበረቀ ጊዜው ሲለዋወጥ፤

ካንጎል አይፋቅም በአእምሮ ተጽፎ

ሲታወስ ይመጣል ብዙ ዘመን አልፎ፡፡

መታሰቢያ ይኽ ነው፤ የተሰራ ባጥንት

ሥጋ ያለበሰው ያጣበቀው ጅማት፤

ቆዳ ያለበሰው በደም የተቀባ

ነፍስና አካል ሁኖ በሰው የሚገባ፡፡

 

 

Read 4913 times Last modified on Saturday, 11 February 2012 10:55

Latest from