Saturday, 12 December 2015 12:00

“...የጨቅላ ሕጻናት ሕክምና...”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(2 votes)


    የአለም የጤና ድርጅት እንደሚጠቁመው በአፍሪካ በ2013 ወደ 6.3 ሚሊዮን ሕጻናት የአምስት አመት ልደት በአላቸውን ሳያከብሩ ለሕልፈት ተዳርገዋል፡፡ ይህም ሲሰላ በየደቂቃው አምስት ልጆች ከአምስት አመት በታች ባላቸው እድሜ እንደሚያልፉ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ደግሞ 3ቱ ሞተዋል ተብሎ የሚታሰበው ገና በጨቅላነት እድሜያቸው ማለትም በተወለዱ በቀናት ውስጥ ማለት ነው፡፡  
ጨቅላ ሕጻናቱ የሚሞቱባቸው ምክንያቶች በርካቶች ቢሆኑም አንዱ በትክክለኛው መንገድ የእናቶቻቸውን ጡት ባለመጥባታቸው መሆኑን እማኞች ይመሰክራሉ። ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ከክብደት በታች ሆነው የሚወለዱ ሕጻናት ከ7-42 በመቶ የሚደርሱ ናቸው፡፡ በተያየዘም የአለም የጤና ድርጅት ሪፖርት እንደሚጠቁመው ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት በትክክለኛው መንገድ እስከ ስድስት ወር ድረስ ጡት በመጥባት የሚያድጉ ልጆች 37 ከመቶ ብቻ ናቸው። ከስድስት ወር በሁዋላም ለሕጻናቱ የሚሰጡዋቸው ተጨማሪ ምግብ በሚፈለገውና በተሟላ መንገድ አለመሆኑ ሕጻናቱን ለሕልፈት ይዳርጋል፡፡
በጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል እና በባህር ዳር ፈለገ ሕይወት ሆስፒታል በመገኘት እንደተወለዱ ችግር የሚገጥማቸውን ሕጻናት የሕክምና አገልግሎት የዚህ አምድ አዘጋጅ ለመመልት ሞክራለች፡፡ በዚህ እትም ለንባብ የሚቀርበው የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የጨቅላ ሕጻናት ሕክምና ክፍል የስራ እንቅስቃሴ ሲሆን አዘጋጅዋ ከሆስፒታሉ እንደደረሰች በክፍሉ አንድ ሁኔታ ተመልክታለች፡፡ እንደሚከተለው ትገልጸዋለች፡፡
“...ሐኪሞቹ በአንድ የህጻናት መተኛ ቦታ ተሰብስበዋል፡፡ እንደምንም በሰዎች መካከል ለመመልከት ስሞክር አንድ የሚያሳዝን ህጻን ገና በተወለደ በሶስተኛ ቀኑ ወደ ሆስፒታሉ እንደመጣ ነበር የተረዳሁት፡፡  ሐኪምዋ ከነርሶችና ከከበቡዋቸው የህክምና ባለሙያዎች ጋር በፍጥነት ይነጋገራሉ፡፡ ይህን ስጡኝ... ይህን አድርጉ... አቀብዪኝ... ተቀበለኝ... የሚሉና የመሳሰሉ ቃላትን ይለዋወጣሉ፡፡ አንድ ረዘም ያለ ነርስ ከመዳፉ ብዙም ተርፎ     የማይታየውን ሕጻን አየር ለመስጠት ደረቱን እየተጫነ ይታገላል፡፡ ደረቱን ከመጫን     ባለፈም አፉ ላይ ኦክስጂን መስጫው ተደቅኖአል፡፡ መድሀኒት ቢሰጡ... አየር ቢሰጡ... ደረቱን እየተጫኑ ሳንባው እንዲሰራ ቢታገሉ አልተሳካም፡፡ ...ወዲያው አንዲት ግድግዳ ጥግ ቆማ ትመለከት የነበረች ሴት... ወይኔ ልጄ ብላ ጩኸትዋን አቀለጠችው፡፡ የክፍሉ ጽጥታ ድፍርስ ሲል ከደጅ ደግሞ አንድ ወንድ... ወይኔ.. አንቺ ነሽ ልጄን ያስነጠቅሺኝ... ስነግርሽ አልሰማም ብለሽ... እያለ ወደ ውስጥ ገባ፡፡ ወዲያውም ክፍሉ ስለተረበሸ ከውጭ እንዲቆዩ ተደረጉ፡፡ የዚህ አምድ አዘጋጅም ሁኔታውን ለማጣራት ከተል ብላ አባትየውን አነጋገረች፡፡
ጥ/ እናትየው ምን አድርጋ ነው አንቺ ነሽ ያጠፋሽው የምትላት?
መ/ ልጁ ገና እንደተወለደ ጀምሮ ጡት መሳብ ሲያቅተው... እኔ ወደ ሐኪም ቤት እንውሰደው ስል ምንም አይሆንም ብላ እምቢ አለችኝ፡፡
ጥ/  የት ነው ልጁ የተወለደው?
መ/ ድንገት ምጥ ስለአፋፋማት ከቤት ነው የተወለደው
ጥ/ ሐኪም አላየውም
መ/ አላየውም፡፡ ሐኪምማ ገና አሁን ማምጣታችን ነው፡፡ ይኼው በቃ አልተሳካልንም፡፡
የሚል ነበር መልሱ፡፡ በጨቅላ ሕጻናት ሕክምና ክፍል የነበሩት ሐኪም ዶ/ር አስራት ደምጸ ይባላሉ፡፡ ዶ/ር አስራት የህጻናት ሀኪም ሲሆኑ ኒኦናታሎጂስት ናቸው፡፡ ዶ/ር ወደ ጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል የጨቅላ ሕጻናት ሕክምና ክፍል የሚመጡትን ታካሚዎች በሚመለከት የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
“...ወደ ሕክምናው የሚመጡት ጨቅላዎች ተወልደው እስከ ሰባት ቀን እድሜያቸው ድረስ ችግር የገጠማቸው ሲሆኑ አስተኝተን የሚያስፈልጋቸውን ሕክምና እናደርግላቸዋለን፡፡
የሚታከሙት ልጆች ምክንያታቸውም...”
ጊዜያቸው ሳይደርስ የሚወለዱ ልጆች፣
ክብደታቸው በጣም ዝቅተኛ የሆነ ልጆች፣
የመተንፈሻ አካል ችግር ያላቸው፣
ታፍነው የተወለዱ ልጆች፣
በተለያየ የሰውነት ክፍላቸው ላይ የአፈጣጠር ችግር ያላቸው ልጆች፣
ኢንፌክሽን ያላቸው ልጆች፣
ጁዋንዲስ ወይንም ሰውነትን ቢጫ የሚያደርገው ችግር ያለባቸው ልጆች ፣
የእናትየውና የልጆቹ ደም ያለመስማማት (አር.ኤች) በሚፈጥረው ችግር የሚመጡ ልጆች፣
ለመሳሰሉት አስፈላጊው ሕክምና እንደሚሰጥ ገልጸዋል።  
በጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል ያለው የጨቅላ ሕጻናት ሕክምና መስጫ ሰፋ ያለ ክፍል ሲሆን በውስጡም የሙቀት መስጫ (ኢንኪዩቤተር) የመሳሰሉ የተለያዩ መሳሪያዎች ይገኛሉ፡፡ የአምድ አዘጋጅዋ ወደ ክፍሉ በገባች ጊዜ ክፍሉ ሰው የሌለበት እስኪመስል ድረስ በጸጥታ ተውጦአል፡፡ ወደ 35 የሚደርሱ የሙቀት መስጫ አልጋዎች እና ሰውነታቸው ቢጫ ለሆኑ ጨቅላዎች የጨረር ሕክምና በሚሰጥባቸው አልጋዎች ላይ ከተወለዱ የቀናት እድሜ ያለቸው ጨቅላዎች ተኝተዋል፡፡ ነገር ግን አንዳቸውም ድምጽ አያሰሙም፡፡ ምክንያቱም ክብደታቸው ትንንሽ እና በሌላም ምክንያት አቅም ስለሌላቸው ወይንም ሙቀቱ ተመችቶአቸው ነው፡፡
አንዲት እናት ታለቅሳለች፡፡ ምን ሆና እንደሆነ እንደሚከተለው ትገልጻለች፡፡
“...እኔ ከወለድኩ ገና አራት ቀኔ ነው፡፡ የመጣሁት ከክብረመንግስት ነው፡፡ ለምርመራ እንደሄድኩ በድንገት  አዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል እንደወለድኩኝ ሽንት መሽናት እምቢ     ስላለው ወደ አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ይዘሽ ሂጂ አሉኝ፡፡ አሁን እዚህ ስመጣ ደግሞ ኦፕራሲዮን ይደረጋል አሉኝ፡፡ አሁን እግዚአብሔር አኔን ሲቀጣኝ እንጂ የአራት ቀን ልጅ እንዴት ተደርጎ ነው ኦፕራሲዮን የሚደረገው?”
ሀዘኔታዋ ነበር የሚያስለቅሳት፡፡ በእርግጥም ለብዙዎች ግራ የሚያጋባ ሊሆን ይችላል፡፡ በቀናት መካከል ያሉ ሐጻናት በምን መንገድ ኦፕራሲዮን ማድረግ ይቻላል? የዚህን ህጻን ታሪክ ጨምሮ ስለሁኔታው ዶ/ር አስራት የሚከተለውን ገልጸዋል፡፡
“...ሕጻኑ ኩላሊቱ ቁስለት ይታይበታል፡፡ በሽንት መሽኛው ላይም የሚታየው ችግር መጥበቡ ነው፡፡ ስለዚህ ያ የጠበበው ቦታ በኦፕራሲዮን ካልተከፈተ በስተቀር ሽንት መሽናት አይችልም፡፡ ሽንቱን ካልሸና ደግሞ ሽንቱ ኩላሊቱ ውስጥ ተጠራቅሞ ኩላሊቱን     ከጥቅም ውጭ ያደርገዋል፡፡ ኩላሊቱ ካልሰራ ደግሞ ለሕይወቱም የሚያሰጋው ነገር ይከሰታል ማለት ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ልጅ ከተወለደ በሁዋላ ሽንቱ ወደ ውጭ እንዲወጣ     ወደ ፊኛው ቱቦ ገብቶለት ሽንቱ እንዲወጣ እየተደረገ ነው፡፡ ነገር ግን ለዘለቄታው የሚሆነው ኦፕራሲዮን መደረግ ብቻ ነው፡፡ ጨቅላዎቹ ምንም እንኩዋን የቀናት እድሜ     ያላቸው ቢሆኑም በአቅማቸው ማደንዘዣ ተሰጥቶ የቀዶ ሕክምናው በተገቢው መንገድ እንደማንኛውም ሰው ይደረግላቸዋል፡፡ ይህ እንዲያውም በጣም ቀላል ስራ ነው፡፡ ለምሳሌ የጉሮሮ ቱቦአቸው የተቋረጥ እና ከአየር ቧንቧ ጋር የተገናኘ ልጆች የኦፕራሲዮኑ ስራ ከበድ ያለ ነው፡፡ እነዚህ ልጆች የጉሮሮአቸው ቱቦ ከሆድ እቃቸው ጋር የተገናኘ ስላልሆነ እና ስለተቋረጠ መብላት መጠጣት አይችሉም፡፡ የእነዚህ ጨቅላዎች ኦፕራሲዮን ከሳንባቸው አካባቢ ጀምሮ ደረታቸው ተከፍቶ ስለሚሰራ በጣም ከባድ ነው፡፡ እንደዚህ ያለ ችግር ያለባቸው ጨቅላዎች ከኦፕራሲዮኑም በሁዋላ በቀጥታ ምግብ በሆዳቸው መብላት ስለማይችሉ ምግቡ የሚሰጠው በደምስር ይሆናል፡፡ ያ በደም ስር የሚሰጠው ምግብ ደግሞ በአገር ውስጥ አለመኖሩ ሁኔታውን የበለጠ ውስብስብ ያደርገዋል፡፡ ስለዚህ አንዳንድ ቤተሰቦች ከውጭ አገር እያስመጡ ስለሚጠቀሙ የተረፈ ካለ ለሌሎች ተመሳሳይ ችግር ለገጠማቸው ጨቅላዎች እንዲሆን እየተደረገ ሕይወታቸው እንዲተርፍ ይደረጋል፡፡”
ሕጻናቱ አስፈላጊው እርዳታ ከተደረገላቸው በሁዋላ ጡት በደንብ መጥባት ሲጀምሩ ክብደታቸው ከሚፈለገው ደረጃ ሲደርስ በእናቶቻቸው እቅፍ እንዲቆዩ ይደረጋል፡፡ ካንጋሩ የምትባለው እንስሳ ልጁዋን በምታቅፍበት መንገድ የጨቅላዎቹ ክብደት 1500 ኪሎ ግራም እስኪደርስ ድረስ በዚያው በሆስፒታል ውስጥ እናቶቻቸው አልጋ በመያዝ አቅፈው ሙቀት እንዲለግሱዋቸው ይደረጋል፡፡ ዶ/ር አስራት እንደሚሉት፡-
“...ኢንኪዩቤተር ውስጥ የሚገቡት ገና እንደተወለዱ ነው፡፡ ከዛ በሁዋላ ግን ግሉከስ የማይፈልጉ፣ ኦክስጂን የማይፈልጉ ሲሆን ወደ ካንጋሩ የእናቶች እንክብካቤ እንዲገቡ ይደረጋል፡፡ ያም... ልክ ኢንኪዩቤተር ውስጥ ያገኝ የነበረውን ሙቀት እንዲያገኝ የሚያስችለው ነው፡፡ በካንጋሩ አያያዝ ከእናቱ ጋር ቅርበት እንዲኖረው፣ ሙቀትዋን እንዲጋራ፣ ድምጹዋን እንዲያዳምጥ ያስችለዋል፡፡”
ይቀጥላል

Read 3383 times