Saturday, 19 December 2015 10:30

በቪያግራ ስም የሚመረቱ መድሃኒቶች የጤና ጉዳት ያስከትላሉ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(32 votes)

በህገወጥ መንገድ የሚመረት ቪያግራ ገበያውን ተቆጣጥሮታል


“የቪያግራ ተጠቃሚ መሆን ከጀመርኩ ብዙ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ገና በወጣትነት እድሜዬ በገጠመኝ የወሲብ ችግር መፍትሄ ፍለጋ ብዙ ጥረት አድርጌአለሁ፡፡ ጉዳዩ እንዲህ እንደልብ ካገኙት ሰው ጋር ሁሉ ተወያይቶ መፍትሄ የሚበጅለት ባለመሆኑ ችግሬን ለብቻዬ ይዤ ለአመታት ተሰቃይቼአለሁ። በዚህ ችግሬ ምክንያትም ብዙ አጋጣሚዎችና ዕድሎች አምልጠውኛል፡፡ በአንድ አጋጣሚ ስለዚህ መድሃኒት ሰማሁና እስቲ ልሞክረው ብዬ ተጠቀምኩበት፡፡ ውጤቱ እጅግ አስገራሚ ነበር፡፡ እንደገና የተፈጠርኩ ያህል ነበር የተሰማኝ፡፡ ችግሬ ሙሉ በሙሉ በዚህ መድሃኒት መፍትሄ በማግኘቱ መድሃኒቱን የሙጢኝ አልኩኝ፡፡ “ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን መድሃኒቱ እንደቀድሞው ፈጣን ውጤት ሊያስገኝልኝ አልቻለም፡፡ አንዳንዴ እንደውም በቀን ሁለት ጊዜ የምወስድበት አጋጣሚ አለ፡፡ ይህ ሁኔታ ምናልባት ሰውነቴ ከመድሃኒቱ ጋር ተለማምዶ ይሆን ብዬ እንዳስብ አድርጐኛል፡፡ ከሰው ጋር ግን ስለዚህ ጉዳይ አንስቼ የተነጋገርኩበት አጋጣሚ የለም፡፡ እንዴት ብዬ? ለማንስ ነው የማወራው? ግን መድሃኒቱ ምን ሆኖ ነው እንዲህ የሆነው? እውነት መድሃኒቱ ከሰውነት ጋር ይለማመዳል?” ከላይ የቀረበው ችግርና ጥያቄ አንድ ወጣት በኢሜይል አድራሻዬ የላከልኝ ሲሆን፤ የህክምና ባለሙያዎችን አነጋግሬ በጉዳዩ ዙሪያ የሰጡኝን ማብራሪያ እንደሚከተለው አጠናቅሬዋለሁ፡፡
በአገራችን በተለይም በከተማችን አዲስ አበባ በርካታ ወንዶች የቪያግራ ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን የገለፁልኝ አንድ የፋርማሲ ባለሙያ፤ ሁሉም ለማለት በሚያስደፍር ደረጃ መድሃኒቱን የሚጠቀሙት በሃኪም ታዞላቸው ወይም ደግሞ ተገቢውን ምርመራ አድርገውና ችግሩ እንዳለባቸው አረጋግጠው ሳይሆን በዘፈቀደና በፍላጐታቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ ችግሩን ከማስወገድ ይልቅ ጤናቸው ላይ ከፍተኛ ችግር ሊያስከትልባቸው ይችላል የሚሉት ባለሙያው፤ ችግሩ ከቋሚ የአካል ጉዳት ጀምሮ እስከ ሞት ሊያደርስ እንደሚችል ይገልፃሉ፡፡
በአዲስ አበባ የቪያግራ ተጠቃሚው ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን የሚናገሩት የፋርማሲ ባለሙያው፤ በተለይ በሳምንቱ መጨረሻና በበአል ቀናት መድሃኒቱ በብዛት እንደሚቸበቸብ ይገልፃሉ፡፡ ቪያግራ አሜሪካ ሰራሽ ለሆነው (ሲልዲናፊል ሲትሬት) ዋንኛ መጠሪያ በመሆን ገበያ ላይ በስፋት ቢታወቅም በደንበኞቻችንም ሆነ በእኛ ዘንድ “ኩፒድ” ወይም “ቬጋ” በሚል ስያሜው ነው የሚጠራው፡፡ እነዚህ መጠሪያዎች ቪያግራን መሰል አገልግሎት ለሚሰጡ መድሃኒቶች ሁሉ መጠሪያ ሆነው ይታወቃሉ ብለዋል - ባለሙያው፡፡ እውነተኛ ብራንድ ያለው አሜሪካ ሰራሹ ቪያግራ በአሁኑ ወቅት በአገራችን ገበያ ውስጥ አለመኖሩን የሚናገሩት ባለሙያው፤ ምርቱ በተለያዩ አገራት እየተመረተና የተለያዩ ስያሜዎች እየተሰጡት ወደ ገበያ እንደሚመጣና በተለይም ለታዳጊ አገራት እየተባሉ የሚመረቱት የቪያግራ ምርቶች የጥራት ደረጃቸውን ያልጠበቁና የጐንዮሽ ጉዳታቸው እጅግ የከፋ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ መድሃኒቶቹ በተለያዩ አገራት ፎርጅድ እየተሰሩ በህገወጥ መንገድ ገብተው ለገበያ እንደሚቀርቡም ይገልፃሉ፡፡ በዚህ መንገድ ገብተው ለገበያ የሚቀርቡት መድሃኒቶች የታለመላቸውን ዓላማ ለመምታት እንደማይችሉና በዚህም ሳቢያ ብዙ የመድሃኒቱ ተጠቃሚዎች ቅሬታ ሲያሰሙ እንደሚደመጡ ይናገራሉ፡፡ “የሸጥክልኝ ቪያግራ ነው ፓራሴታሞል እያሉ ይጠይቁኛል፡፡ አብዛኛዎቹም መድሃኒቱ በትክክልም የስንፈተ ወሲብ መድሃኒት ስለመሆኑ ይጠራጠራሉ” ብለዋል፡፡
የቪያግራ ውጤታማነት እንደ ምርት ጥራቱ የሚለያይ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ የተሻለ የተባለውም ምርት ውጤት አልባ ሲሆን ይታያል ያሉት ባለሙያው፤ ከቪያግራ ተጠቃሚ ወንዶች 40% ያህሉ መድሃኒቱ ምንም አይነት መፍትሄ እንዳላስገኘላቸው መናገራቸውን የሚገልፅ አንድ ጥናት ማየታቸውንም ይገልፃሉ፡፡
በአብዛኛው የስንፈተ ወሲብ ችግር ባለባቸው ወንዶች ጥቅም ላይ የሚውለው ቪያግራ፤ ስራውን የሚያከናውነው በብልት ውስጥ ያሉ ቀጫጭን የደምስሮች እንዲለጠጡ እንዲሁም በውስጣቸው በቂ የሆነ ደም እንዲንሸራሸርና የወንዱ ብልት በሚገባ እንዲወጠር በማድረግ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም መድሃኒቱ ስነ ልቦናዊ በራስ መተማመንን በመፍጠር ስኬታማ ወሲብ ለመፈፀም እንደሚያስችል የፋርማሲ ባለሙያው ይናገራሉ፡፡ አንድ የቪያግራ ተጠቃሚ ወንድ፤ በሂደት በራስ መተማመኑን አዳብሮ ብቃቱን በራሱ ማምጣት ይኖርበታል፡፡ ይህንን ካላደረገ በስተቀር እስከወዲያኛው የመድሃኒቱ ጥገኛ ሆኖ ይቀራል፡፡  
የሥነልቦና አማካሪው ዶ/ር አንድነት አባተ እንደሚናገሩት፤ በአገራችን ስለቪያግራ ተጠቃሚዎች የተደረጉ ጥናቶች እምብዛም ባይኖሩም በሆስፒታሎችና በተለያዩ የምርምር ሥራዎች ላይ የተደረጉ አነስተኛ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ በርካታ ወንዶች የቪያግራ ተጠቃሚዎች እየሆኑ የመጡ ሲሆን አብዛኛዎቹም የስንፈተ ወሲብ ችግር ያልገጠማቸውና መድሃኒቱን ወሲብ ላይ ተጨማሪ ብርታትን ለማግኘትና በየፖርኖግራፊው የሚያዩትን አይነት ወሲብ ለመተግበር አስበው የሚጠቀሙበት ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ተጠቃሚዎቹ የኋለኛ እድሜያቸው ላይ ሲደርሱ ለከፋ ጉዳትና አደጋ እንዲጋለጡ ያደርጋቸዋል ብለዋል፡፡
የስንፈተ ወሲብ ችግር ስነልቦናዊ አሊያም አካላዊ ሊሆን እንደሚችል የሚናገሩት ባለሙያው፤ ችግሩ እንኳንስ ለህክምና ባለሙያ ለትዳር ጓደኛም መናገር ስለሚያሳቅቅ ብዙዎቹ የመድሃኒቱ ተጠቃሚ የሚሆኑት ማንንም ሳያማክሩና ያለባቸውንም ችግር በውኑ ሳያውቁ እንደሚሆንና ይህም በተጠቃሚዎቹ ላይ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ገልፀዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በገበያ ላይ በስፋት የሚገኙት የቪያግራ አይነቶች ውጤት አልባ ሆነዋል የሚለውን ጉዳይ አስመልክቶም ሲናገሩ፤ መድሃኒቱ እንዲህ እንደ ራስምታትና ሆድ ቁርጠት መድሃኒት በየገበያው በስፋት እየተሸጠ ውጤታማ ቢሆን ነበር የሚገርመኝ፡፡ ጥናት አድርጌ ያረጋገጥኩት ነገር ባይኖረኝም አብዛኛዎቹ በየልብስ ሱቆች፣ የኮስሞቲክስ ቤቶችና የመድሃኒት መሸጫ መደብሮች ውስጥ የሚሸጡት የስንፈተ ወሲብ መድሃኒቶች ውጤት አልባና ተጠቃሚውንም ለከፋ የጤና ችግር ሊዳርጉ የሚችሉ ናቸው ብለዋል። ትክክለኛው መድሃኒት አሁን እየተሸጠበት ባለው ዝቅተኛ ዋጋ ለገበያ ሊቀርብ ይችላል የሚል እምነት እንደሌላቸውም ተናግረዋል፡፡
የአሜሪካ የመድሃኒት አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን ለቪያግራ ተጠቃሚዎች ያስተላለፈውን ማስጠንቀቂያ አስመልክቶ በቅርቡ ሮይተርስ እንደዘገበው፤ በቪያግራ ስያሜና ብራንድ እየተመረቱ ለገበያ የሚቀርቡ በርካታ መሰል መድሃኒቶች በተጠቃሚዎች ላይ እያደረሱ ያሉት ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ጠቁሞ፣ መድሃኒቶቹ ውጤት አልባ ከመሆናቸውም በላይ እይታን በማደብዘዝና የመስማት ብቃትን በማሳጣት ለከፋ የጤና ችግር እንደሚዳርጉና ጉዳቱም ሞትን ሊያስከትል እንደሚችል አመልክቷል፡፡
“አርካይቭስ ኦፍ ኦቶላሪኖሎጂ” የተሰኘና እዚያው አሜሪካ ለህትመት የሚበቃ አንድ የምርምር መፅሄት “How a little blue pill changed the world” በሚል ርእስ ባወጣው የጥናት ውጤት፤ እድሜያቸው ከ40 አመት በላይ ከሆናቸው ወንዶች መካከል ከ5-7 በመቶ የሚሆኑት የብልት አለመቆም ችግር አለባቸው፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ እድሜ እየጨመረ ሲሄድ የበለጠ እየከፋ ይሄዳል፡፡ ቪያግራ ምንም እንኳን ከባድ ሊባል የሚችል የጐንዮሽ ጉዳቶች ቢኖሩትም የወሲብ ህይወታቸው ችግር ላይ ለወደቀ ወንዶች ፍቱን መድሃኒት በመሆን እያገለገለ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የሚጠቀሙት መድሃኒት በትክክልም እውነተኛውን ቪያግራ መሆኑን ማረጋገጥ ግድ ይላል፤ አሊያ ግን ከጥቅሙ ጉዳቱ ማመዘኑ አይቀሬ ነው ብሏል። በአሁኑ ወቅት ቪያግራ በሚል ስያሜ በስፋት በገበያ ውስጥ የሚገኙት መድሃኒቶችም እውነተኛና ትክክለኛ አለመሆናቸውን ጥናቱ ጠቁሟል፡፡
ቪያግራን ከተለያዩ አነቃቂ እፆችና መድሃኒቶች ጋር መጠቀም እጅግ አደገኛ መሆኑን የሚገልፁት የስነልቦና ባለሙያው፤ በመድሃኒቱ ሳቢያ ሊከሰቱ የሚችሉትን እንደ የመስማት ብቃትን ማሳጣት፣ የኩላሊት መድከም፣ የልብ ሥራ ማቆምና የአይን ነርቮች መጐዳትን ይጠቅሳሉ፡፡
አንድ ሰው መድሃኒቱን በቀን ውስጥ (በ24 ሰዓት ጊዜ ውስጥ) ከአንድ ጊዜ በላይ እንዲወስድ አይመከርም ያሉት ባለሙያው፤ የልብ ድካም፣ የደም ግፊት፣ ኩላሊት፣ ስኳር፣ የጨጓራ ቁስለትና የአይን ህመም ያለባቸው ሰዎች መድሃኒቱን ከመጠቀም መቆጠብ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡ አልኮል መጠጥ ጠጥቶና ቅባት የበዛባቸውን ምግቦች ተመግቦ ቪያግራን መጠቀም በውጤታማነቱ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ አለው ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ያልተስተካከለ ቅርፅ ያለው ብልት ያላቸው ወንዶችና የደም ካንሰር ያለባቸው ወንዶች፤ መድሃኒቱን ፈፅሞ ሊጠቀሙ እንደማይገባም አሳስበዋል፡፡
ቪያግራ በተለያየ ስያሜና ብራንድ እየተመረተ በመላው አለም ጥቅም ላይ ቢውልም ከጥራቱ አንፃር ከፍተኛ ችግር እየታየበት መሆኑን የተገነዘበውና European Society for Sexual Medicine (ESSM) የተሰኘው ተቋም በመጪው የካቲት ወር በስፔን ማድሪድ አለም አቀፍ ጉባኤ የሚያደርግ ሲሆን በዚህ ጉባኤ ላይ ችግሩ ለምክክር ይቀርባል ይበጅለታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን ከወሲብ የሚገኝ ደስታን ፍለጋ ስንማስን ህይወታችንን እንዳናጣ እንጠንቀቅ፡፡

Read 30103 times