Saturday, 19 December 2015 10:32

ቁጣ ማለስለስ

Written by 
Rate this item
(10 votes)

አጨሳለሁ!...ማለቴ የሠርጌ እለት ማጨስ እፈልጋለሁ፡፡
አንሙት ጓደኛዬ ሰሞኑን ከመካኒክነት ስራው ጋር ተያያዥነት ያለው ቁጣ ማለስለስ የሚል ስልጠና ወስዷል፡፡ በዚህ ስልጠና መሰረት ቁጣዬ እንዳይነድ ልተገብር ስለሚገባኝ የተለያዩ የቁጣ ማለስለሻ ዘዴዎች ነግሮኛል፡፡ ከዘዴዎቹ መሃከል ማጨስ ይገኝበታል፡፡
የሠርጌ እለት ለትዳር ጠይቄያቸው “እምቢ” ያሉኝ አስራ አንድ ሴቶች ድንገት በአይኔ ላይ ድቅን ቢሉ ቁጣዬ መንደዱ አይቀርም፤ በጣም ነው ያረዘሙብኝ ይሄን ጐዳና፡፡ ንግስት እልፍኝ እስኪደርስ የሚደረደሩ አሳላፊዎች መሆናቸው በገባኝና “እለፍ!” ከማለታቸው በፊት አሳልፉኝ ብዬ በጠየቅኩ፡፡
ብቻ እነርሱ ድንገት ትውስ ካሉኝ ቁጣዬ ሊነድ ስለሚችል ለስለስ ለማድረግ የአንሙቴን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብኛል፡፡ በክብር ከሚጠራው ታዳሚ ፊት ቁጣዬን ለማለስለስ ብዬ ማስቲካ አላኝክም፡፡ ረዘም ያለ የእግር ጉዞ ማድረግ በጭራሽ አይታሰብም፤ ያለኝ አማራጭ ማጨስ ነው፡፡ ምን? ሲጃራ…አላደርገውም! እሺ ሊነድ የሚችለው ቁጣዬን እንዴት ላለስልሰው?
ምን አስጨነቀኝ ከዚህ ሁሉ ሙሽራይቱን ባጨሳትስ!? ቁጣ የእሳት አመድ ስለሆነ ታምቆ ይቆያል፡፡ ጠንካራ ሲሆን ሃይለኛ ችግር ይፈጥራል፡፡ በስራ፣ በፍቅርና በእለተ ተእለት ግንኙነት መሃከል ጣልቃ እየገባ ይበጠብጣል፡፡ በተጨማሪም ቁጣ የእሳት ፍም ስለሆነ አልፎ ወደ ትዳሬ ከዘለለ ጥሩ አይመጣም፡፡ ለትዳር ጠይቄያቸው እንቢ ባሉኝ አስራ አንዱ ሴቶች የተፋፋመው ቁጣዬ፣ ወደ ትዳሬ ተላልፎ ቤቴ ሲነድ ማየት አልሻም፡፡
***
“ዢያኛ…ኩኛ” ቁጣ ምንድነው? ቁጣ ምን ያመጣል?
ቁጣ ውስጣችሁ ሲኖር፤ እንዲሁ ይታወቃችኋል፡፡ ምቾት አይሰማችሁም፤ በሆነ ባልሆነው ትረበሻላችሁ። ደረታችሁ ጥብቅ፣ ልባችሁ ምትት…ምትት፣ ጡንቻዎቻችሁ ውጥርጥር፣ እግሮቻችሁ ድክም፣ ላብና ራስ ምታት ይፈራረቅባችኋል፡፡ ጩሁ ጩሁ፣ እቃ ስበሩ ስበሩ፣ ሰው ተማቱ ተማቱ፣ ተሳደቡ ተሳደቡ፣ አልቅሱ አልቅሱ፣ ተጋፉ ተጋፉ ይላችኋል፡፡ ለራስ በቂ የሆነ ጊዜ አለመስጠት ለቁጣችሁ መንደድ መነሻ ይሆናል፡፡ መዳረሻው ደግሞ ይከብዳል፡፡ ሃይለኛ ቁጣ ሲነድ “ምን ይሻለኛል…ልፈንዳ ይሆን? ልብረር ይሆን?” ያሰኛል፡፡
በተለይ እናትና አባት ሲጣሉ ተወርውሮ ከግድግዳ እየተጋጨ የሚሰባበረውን የቤት እቃ ሲለቃቅም ያደገ ልጅ ቁጣን መቆጣጠር ይከብደዋል፡፡ ንዴት ሁኔታዎችን ሲያባብስ እንጂ የማንንም ችግር ሲፈታ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም፡፡ “ማሂቲያ” ይሄን መረዳታችሁን ቁጣን ለማለስለስ ያግዛችኋል፡፡
“ምን አይነት ቆሻሻው ነህ?”
“ልታሞኘኝ ትፈልጋለህ እንዴ?”
“ግድ የለሽ!”
“እረፊ!...ልጐዳሽ እችላለሁ”
“ይሄ አካባቢ በጣም አስጠልቶኛል”
ተቃራኒ የሆኑ አስተሳሰቦችን እንድንከተል ጫና ስለሚያሳድሩብን እንዲህ አይነት ንግግሮችን ልናስወግድ ይገባናል፡፡ “የሚወራው መጥፎ ነገር ሁሉ እኔን በማስመልከት ነው” ብለን ልናስብ አይገባም፡፡ አለበለዚያ በተወራው ሁሉ መታመማችን ነው፡፡ ስለ እኛ በጐ በጐውን ከሚናገሩ ሰዎች ልንርቅ አይገባም፡፡
“ሚፊቺሚ” “እኔ ፍፁም ነኝ!” ይሄ አስተሳሰብ ፍፁም ቁጠኛ እንድትሆኑ በአያሌው ይተባበራችኋል፡፡ የሰው ፍፁም የለውም! ወይ ማግኘት አልያም መሞት የሚባል ነገር አይሰራም፡፡ ማግኘት ካላገኙም እንደገና ለማግኘት መኖር፡፡ ለምን ትቸኩላላችሁ? ሞት እንደው ሳትጠሩትም ቢሆን መምጣቱ አይቀርም፡፡
“ዩኒ ሚት” ቁጣን ለማንደድ መንገድ ጠራጊ የሆኑትን ተቃራኒ አስተሳሰቦች እንዴት ማስወገድ እንደምትችሉ ላሳያችሁ…
የሆነ ሰው አፍጥጦ ሲመለከታችሁ “ለምን እንዲህ አፍጥጦ ያየኛል? ይሄኔ በሆዱ ሲያስጠላ እያለኝ ነው” እያላችሁ ከማሰብ “አፍጥጦ እያየኝ ነው፤ነገር ግን ምን እያሰበ እንደሆነ አላውቅም” ማለት ይሻላችኋል፡፡ “ለምንድነው ጣል ጣል የሚያደርጉኝ?” ከማለት “አንድ ቀን ውድድድ…ያደርጉኛል” ብሎ ማሰብ፡፡ “ስለ እኔ ምንም ግድ አይሰጣትም፤ የሆነች ግድ የለሽ!” ከምትይ “በራሷ ጉዳይ በጣም ስለተወጣጠረች ረስታኛለች” ማለቱ አይበጅሽም ወይ?
“እኔ ቁጣ የለብኝም፤ ቁጣዬ የሚነደው ሰዎች ተልካሻ የሆነ ነገር ሲያደርጉ ሳይ ነው” የምትል ከሆነ፡፡ ከውጪ መጥቶ ይስፈርብህም ከውስጥህ ይንደድብህም ንዳድ እንደው ንዳድ፤ ቁጣም እንደው ቁጣ ነው፡፡
“ሺን ሹአ” ቁጣ ሲነድ ከማይሆን ቦታ ይጥላችኋልና ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ አለባችሁ፡፡ ቁጣዬ ሲነድ መቆጣጠር ይከብደኛል ከምትሉ ቀድሞ መንገድ ጠራጊ የሆኑትን ጉዳዮች መቀናነስ ይጠቅማል፡፡ ለራሳችሁ በቂ ጊዜ ከመስጠት አትቦዝኑ፡፡ አቅሙ ካላችሁ “ዮጋ” ብትማሩ መልካም ነው፡፡ ካልሆነም ስሜቱ ሲሰማችሁ ሙዚቃ ማዳመጥ፣ ቴሌቪዥን ማየት (ከዜና በስተቀር)፣ ማስቲካ ማኘክ፣ ማሽላ ማፈንዳት (ፈንዲሻ) ወይም የፈነዳውን መብላት፣ ፎቶ መነሳት (እየሳቃችሁ ቢሆን ይመረጣል) እና እየደጋገማችሁ ምስር ክክ! ምስር ክክ! ማለት ወዘተ…፡፡
“ሁጂን ቹኣ?!” ሚስቴ በጩኸት…”ከስራ የምትወጣው ስንት ሰአት ላይ ነው?!” ስትለኝ “ቲሞቻሚሽ” “ቆይ መጣሁ ማሬ” እላትና ከነደደው ቁጣዬ ለመለስለስ ሽንት ቤት ገብቼ ለሁለት ሰአታት ያህል በረዥሙ አየር አስባለሁኝ፡፡ ለስልሼ ስጨርስ ተመልሼ እሄድና “ሁሻቺ” “ለምን እንዲህ ብለሽ ጠየቅሽኝ? እስቲ ቁጭ በይና ባነሳሽው ሃሳብ ዙሪያ እንወያይበት” ብዬ እርሷንም አለሰልሳታለሁኝ፡፡
ቁጠኛ ብሆን ገና ጥያቄውን ከማንሳቷ “ሺን ሲሺ ፒካ ሲኦ!” “ለምን አስፈለገሽ? በመሃከላችን መተማመን ጠፋ ማለት ነው?” እያልኩ አፍ አፏን እላታለሁኝ፡፡ እሷም እየጮኸች መልስ ትሰጠኛለች፤ቤታችን በአንድ እግሩ ቆመ ማለት አይደለም? “ላሼ ላሼ” የራስን ብቻ ማዳመጥ ሳይሆን መደማመጥም ያስፈልጋል፡፡
በፈጠራችሁ “እኔ መቼም ቢሆን ተወዳጅ ሰው ልሆን አልችልም!” አትበሉ፡፡ “ሁዋል ሲኛ” ሰው አንደኛ የሚወድላችሁ ነገር ቢኖር እራሳችሁን መውደዳችሁን ነው! የማትወዱት ማንነታችሁን ማንም አይወድላችሁም!
“ሲሞ ሺሞ ሺኝ” በትውልዳችሁ እርግማን እንዳይመጣ ሌሎችንም መውደድና መንከባከብ ተማሩ፡፡ የጥቁር ህዝቦች እናት ምድር ኢትዮጲስ፤ የበኩር ልጆቿ ሌሎችን ልክ እንደራሳቸው መውደድና መንከባከብ ሊማሩ አልቻሉም፡፡ በእነርሱ ምክንያት አምላክ ተቆጥቶ ረግሟት እስከ አሁን ድረስ ክፉኛ ተጐሳቁላለች፡፡ በቀደመው ዘመን ምድሪቱን ከገነት የሚፈሱ ወንዞች ያጠጧታል፤ከእርሷ ዘንድ የሚወለዱት ሁሉ በክርታዝ ጥቅል ነው፡፡ ከሽሉ ውስጥ የደም ጠብታ አይገኝም፤ ንፁህ ውሃ ብቻ! በአምላክ አብዝታ የተወደደች የሰው ዘር መገኛ፡፡
“ላይሙ ዣቲዬ” ታዲያ እንዲህ ሆነ፡፡ በየሜዳው ታርደው የሚጣሉት እንስሳት ደም ነፍስ ወደ ሰባተኛው ሰማይ አብዝቶ ጮኸ፡፡ በተለይ የአንዲት ላምና የበግ ግልገል ደመ-ነፍስ፡፡ አምላክም…
“ከጠይሟ መሬት ዘንድ እሪታ በረከተ፤ የአንዲት ላምና የበግ ግልገል ከደመ ነፍሳቸው “የበደል ወናፋችን ሞላ፤ ፍረድልን!” የሚል እሪታ ከሁሉም አይሎ ይሰማኛል፡፡ እስቲ ወርደህ የጠይሚቱ ልጆች የሆኑት ሀበሻትና ሙካሪብን ጠርተህልኝ ተመለስ!” አለው ለመልዐኩ፡፡
በመልዐኩ መልእክት አድራሽነት ሀበሻትና ሙካሪብ አብረው እንዲመጡ ቢጠሩም፣ ሙካሪብ አዲስ ለሚሰራው ጐጆ ማጣበቂያ እንዲሆነው በማሰብ የሰጐን እንቁላሎችን እየሰባበረ ስለነበር ሳይሄድ ቀረ፡፡ ሀበሻት ብቻውን መጥቶ ከአምላክ ፊት ቆመ…
“የኢትዮጲስ ልጆች፤ ስለምንድን ነው የላሚቱንና የበግ ግልገሉን ቆዳ ደመ - ነፍሳቸው ሳይወጣ በፊት ከላያቸው የላጣችሁት?” አምላክ ሀበሻትን ጠየቀው፡፡
“ወደ ፑንት ወረድንና ግብር አድርሰን ስናበቃ፣ በቅባት የራሱት መዳፎቻችንን ለማፅጃ የሚሆነን እንስሳ በዙሪያችን አላገኘንም፡፡ እናም ከሙካሪብ ተማክረን ከአምባው ላይ ሳር ስትግጥ ያገኘናትን ላም ቆዳዋን ላጥንላት፡፡ ከማረዳችን ቀድመን ቆዳዋን ስናነሳባት፤ ስታጠባው የነበረ እንቦሳዋ ሲጮህ በአንድ ጥፊ ፀጥ አሰኘሁት፡፡ እሜዳው ላይ ተንፈራፈረ፤ ድፍት ሳይል አልቀረም፡፡ እርሱን እርሳው፡፡ አሀሀሀሀ! ይገርምል አምላክ፤ ላሚቱን ልጠን ስናበቃ ግልጥ አላለልን መሰለህ። ለካንስ የላሚቱ ቆዳ ልስላሴው መዳፍ ለመጥረግ አይበጅም ኖሯል፤ አሀሀሀ…” እያስካካ መለሰለት፡፡
ሀበሻት ቀጠለ….”ለጥቆ ካለው ቀዬ እልፍ እንዳልን ማለፊያ ጠጉር ያለውን ግልገል በግ ስናገኝ ቆዳውን ገፈፍንለትና መዳፎቻችንን አፀዳን፡፡ ጨዋታ ይዞን ስለነበር ከነ ነፍሱ፤ በህይወት እያለ ቆዳውን መግፈፋችን ትዝም አላለን፡፡ በኋላ ላይ እንደ ላሚቱና እንደ እንቦሳዋ እርሱም ተደፋ” አለው፡፡
አምላክ “ስለምን ቆዳቸውን መላጥ አስፈለገ? እንደ ከዚህ ቀደሙ እጆቻችሁን እንስሶቹ በህይወት ሳሉ በላያቸው አትጠርጉም ነበር ወይ?” ሲል ጠየቀው፡፡
ሀበሻት “ኤዲያ፤ ኖሩ አልኖሩ ምን አባታቸው ይሰራሉ?! ሲል መለሰለት፡፡
“ሺን ሲሺ ፒካ ሲሜ ቱዪ ሾማ ኦኦ!!! ኦ!!! ኦ!! ኦ!...”
በሙካሪብና ሃበሻት ግድ የለሽነት የአምላክ ቁጣው ነደደ…
“ሳይሞቱ፤ በህይወት እያሉ ቆዳቸው ይላጥ፡፡ ሁለቱም ከጉልበታቸው የሚወጣ፤ ዘራቸው በሙላ ቆዳ ቢስ ይሁን!” ሲልም ተራገመ፡፡
ከዛን ጊዜ ጀምሮ አትችሉም፡፡ ምንም እንኳን ከገነት እየወጡ ምድሪቱን የሚያረሰርሱት ወንዞች እስከ አሁን ቢኖሯችሁም፤ የምትዋለዱት የመንፈሳችሁ ቆዳ እንደተላጠ ነውና ስትነካኩ ክፉኛ ያማችኋል፡፡ ለቻይና ሊትረፈረፍ የሚችል የተፈጥሮ ገፀ በረከት ለእናንተ ግን አልበቃችሁም! እስቲ ተዋደዱ? አትችሉም፡፡ ከተዋደዳችሁ መተቃቀፍ አይቀርም፤ መተቃቀፍ ደግሞ የመንፈሳችሁ ቆዳ ስለተነሳ ለእናንተ በሽታ ነው፤ ደዌ፡፡ ስትነካኩ ክፉኛ ያማችኋል!
“ሙኣ ሙኣ!...ሙኣ” “ሲካ ማቼ??...ሲካ…ማቼ??”
እንዴ…ለምን? ለምን?...ለምን አትሉም? አይበቃም! አይበቃም! አይበቃችሁም ወይ? ይህ ብሶት የሚወልደው የአፍሪካውያን ጩኸት መቼ ነው የሚሰማው? በዚህች ምድር ላይ የወንድማማቾች ጥላቻ እስከ መቼ እድሜውን እያራዘመ ይኖራል?
እረኡኡኡኡ…ኡኡኡኡ “እባክህን እባክህን ስለ ፍቅር እረደን??? እረረ!! ደ!!ደ!! ንንን!!” “እረደን” በሉት። “ማኦቲኛ” …ምህረቱን አውርዶላችሁ አሳርዱትና፤ ሳትላጡ ከነመንፈሳችሁ ቆዳ ለመተቃቀፍ ምቹ እየሆናችሁ…ደጋግማችሁ ተወለዱ፤ ዳግም በፍቅር መንፈስ ተወለዱ እንጂ?!
*   *   *
ቁጣ ማለስለስ ከተባለው ትምህርት ላይ ቀንጨብ አድርጐ ይሄን ገራሚ ታሪክ ያወጋኝ አንሙቴ ሲሆን፣ ያስተማራቸው ደግሞ የባቡር ሃዲድ ዝርጋታ የከፍተኛ ትምህርቱን ያጠናቀቀ ቻይናዊ ነው፡፡
ኤዲያ፤ ቻይና ተናገረ አልተናገረ ምን አባቱ ይሰራልኛል?!
ሲጀመር የቻይናዊና የኢትዮጵያዊ ቁጣ መሃል ሰፊ ልዩነት አለ፡፡ የቻይኖቹ ቁጣ ቀሰስተኛ፤ የሚነደውም ቀስ በቀስ ነው፡፡ ድህነታቸው ላይ ቁጣቸው ነዶ ሰላሳ አመት ሙሉ ሲጐተት ከርሞ ነው ትቷቸው የሄደው፡፡ የእነርሱን አይነት ቁጣ ኑሮዬን እቆጣዋለሁ፡፡
እንደነርሱ ቁጣው ድህነት ላይ አልነደደም እንጂ ኢትዮጵያዊ ድህነቱን ቢቆጣ በአምስት አመት ችግር ድራሹ ይጠፋ ነበር፡፡ አመሉ መሬት ነው! ኮሶ ኮሶ እስከሚለው ድረስ እጅግ ካላስመረሩት፤ የአበሻ ቁጣው አይነድም፡፡
ይቅርበት ኮሶ እንዳታቀምሰው! ኢትዮጵያዊን ነካክተህ መሬት የሆነ ሸጋ አመሉን ካስጣልከው፤ እምር ብሎ ይነሳብሃል! እምር ብሎ ከተነሳ በኋላ ምኑን ልንገርህ? ከቁጣው ንዳድ ብዛት…ከቁጣው ንዳድ ብዛት፤ አህያ ብትሆን እንኳን ክንፍ አውጥተህ ትበራለህ!
ጣልያንን ያበረርነው በቁጣችን፣ ከሰው ሀገር ገብተን የኮሪያን “ኮሚውኒስት” ያበረርነው በቁጣችን፤ መንግስቱ ሃይለማርያምን ያበረርነው በቁጣችን፣ ኤርትራንም ያበረርናት በቁጣችን፡፡ የኢትዮጵያዊ ቁጣው የነደደ እለት ፈጣሪ በኮባ ቅጠል ሸብልሎ ይሰውረኝ፡፡
አወይ እዳ፤ እንግዲህ የሠርጌ እለት ቁጣዬ የሚነድ ከሆነ ሠርገኛውን ከነድንኳኑ ማብረሬ ነው፡፡ እሺ ቁጣዬ በምን ይለስልስ? “ሙሽራይቱን በጥፊ ማጨስ” የሚለው ሃሳብ አልተዋጠልኝም፤ በስንት ዳዴ አግኝቻትማ አላጨሳትም፡፡
እምምም…ወ-ተ-ት …አሹ…ወተት!
ከሙሽሪትና ከእኔ ፊት የሚደረደረው ጠላና ጠጅ አጠገብ በብርሌ ተደርጐ ወተት ቢቀመጥልኝስ? ወተት እንኳንስ ቁጣ መርዝ ያረክስ የለ፡፡ የምን ቁጣ ማለስለስ፤ ስለ ቁጣ ማለስለስ በተማረው መሰረት አንሙቴ የራሱን ቁጣ ማለስለስ ይችላል፡፡ እኔ ግን የሠርጌ እለት ልክ እንደ አያት ቅድመ አያቶቼ፤ ከወተቱ እየተጐነጨሁ ቁጣዬን አረክሰዋለሁ!
ምርጥ ሃሳብ…አሹ ዳይሊጋዳ!
(“ክብሪት” ከተሰኘው የይግረም አሸናፊ
የልብወለድና ወጎች
ስብስብ መጽሐፍ የተወሰደ ከገጽ 40-47 - 2007)


Read 4429 times