ሁለቱ ክለቦች ከወር በፊት በኤፍ ኤካፕ 4ኛ ዙር ጨዋታ ላይ በተገናኙበት ወቅት ሊቨርፑል 2ለ1 ማን ዩናይትድን ማሸነፉ የሚታወስ ነው፡፡ ፈርጉሰን በዛሬው ጨዋታ ሊቨርፑልን በማሸነፍ የሊጉን መሪነት ለአንድ ቀን እንኳን ለመያዝ ሲያተኩሩ ዳግሊቭ በበኩላቸው የቀጣይ ዓመት የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎአቸውን ለማጠናከር ያቅዳሉ፡፡ በኦልድትራፎርድ የሚገኝ ድልን በማን ሲቲ ላይ ጫና ይፈጥራል ብለው እንደሚያምኑ የሚናገሩት ፈርጉሠን ሊቨርፑል ከዋንጫ ፉክክር ውጭ ነው ብለዋል፡፡ ሉዊስ ስዋሬዝ በኤፍኤካፕ የአራተኛ ዙር ጨዋታ በአንፊልድ ከኤቭራ ጋር በፈጠረው ግጭትና ተሳድቧል ተብሎ ጥፋተኛ በመደረጉ የ8 ጨዋታ ቅጣት ተጥሎበት መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በፕሪሚዬር ሊጉና በሌሎች ውድድሮች በተደረጉ ያለፉት 15 ጨዋታዎች ማንዩናይትድ 2 ሲሸነፍ ሊቨርፑል ደግሞ ሶስቴ ሽንፈት ገጥሞታል፡፡ ሁለቱ ክለቦችበመጀመሪያ ዙር የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታ ኦንፊልድ ላይ ሲገናኙ 1ለ1 አቻ ወጥተዋል፡፡