Saturday, 19 December 2015 11:09

የ2015 የፊፋ የወርቅ ኳስና ሌሎች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(3 votes)

ሜሲ እንዲሸለም አስተያየቶች በዝተዋል
                 ሮናልዶ ገና 7 የውድድር ዘመናት እጫወታለሁ ይላል
                 ኔይማር እጩ መሆኑ አርክቶታል
                 ያያ ቱሬ ለ5ኛ ጊዜ የአፍሪካ ኮከብ ሊሆን ይችላል
                        
      በ2015 የፊፋ የወርቅ ኳስና ሌሎች የሽልማት ዘርፎች የሚፎካከሩት የመጨረሻዎቹ እጩዎች  ከ2 ሳምንታት በፊት የተገለፁ ሲሆን አሸናፊዎቹ ከወር በኋላ ይታወቃሉ፡፡ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ የሽልማት ስነስርዓቱን በዙሪክ ከተማ በሚገኘው ‹‹ኮንግረስሃውስ› አዳራሽ እንደሚያካሂድ ቢጠበቅም ዘንድሮ በታመሰበት  የሙስና እና የአስተዳደር ቀውስ ሳቢያ  እንዳይቀዛቀዝ ተሰግቷል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ  የፊፋ ፕሬዝዳንት ሴፕ ብላተር በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ በመገኘት አሸናፊዎችን ለመሸለም ተስፋ ማድረጋቸውን እየተናገሩ ናቸው፡፡ ሰሞኑን ለሙንዶ ዲፖርቲቮ ለተባለ ሚዲያ አስተያየት የሰጡት ሴፕ ብላተር የወርቅ ኳሱን ሜሲ ለአምስተኛ ጊዜ ቢያሸንፈው እና ብሸልምው እደሰታለሁ ብለዋል፡፡ ለሙንዶ ዲፖርቲቮ እንደዘገበው ሴፕ ብላተር ለ90 ቀናት የተጣለባቸው እግድ ከሽልማት ስነስርዓቱ ቀናት ቀደም ብሎ የሚያበቃ ሲሆን በሚቀጥለው ሳምንት ለፊፋ የስነምግባር ኮሚቴ ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ የወርቅ ኳሱን የመሸለም ፍላጎታቸው ሊሆንላቸው እንደሚችል ገምቷል፡፡የስዊዘርላንድ ፍትህ ሚኒስትር እስከ 100 ሚሊዮን ዶላር የሚተመን የፊፋን ገንዘብ በ10 የስዊዝ ባንኮች የሚገኙ 55 አካውንቶች እንዳይንቀሳቀሱ ማገዱ በዓለም አቀፉ ተቋም እየተደረገ ያለው ምርመራ ከፍተኛ ደረጃ መድረሱን ያመለክታል፡፡  የፊፋ  ስነምግባር ኮሚቴ የ79 ዓመቱን ብላተርን ቃል ከሰማ በኋላ በሚቀጥለው ሳምንት ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በሽልማት ስነስርዓቱ በተለይ ከፍተኛ ትኩረት በሚስበው የፊፋ የወርቅ ኳስ ሽልማት አሸናፊነት ሲሆን፤ከ209 የፊፋ አባል አገራት  207 ያህሉ ተሳትፈዋል፡፡ በወርቅ ኳሱ ለቀረቡት እጩዎች 165 አገራት ድምፅ መስጠታቸውንና የብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኞች እና አምበሎች 79.71 በመቶ እንዲሁም የሚዲያ ተወካዮች 88.6 በመቶ እንደሆኑ ታውቋል፡፡
ለ2015 የወርቅ ኳስ የመጨረሻ እጩዎች ሆነው የቀረቡት ሶስቱ ተጨዋቾች ፖርቱጋላዊው ክርስትያኖ ሮናልዶ ከሪያል ማድሪድ እንዲሁም አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ እና ብራዚላዊው ኔይማር ዳሲልቫ ከባርሴሎና ናቸው፡፡ ሊዮኔል ሜሲ በ2009, 2010, 2011 እና በ2012 እኤአ ለአራት ጊዜያት የወርቅ ኳሶችን የወሰደ ሲሆን ዘንድሮ እጩ ሆኖ የቀረበው ለአምስተኛ ጊዜ ለመሸለም ነው፡፡ የቅርብ ተቀናቃኙ  ክርስትያኖ ሮናልዶ ደግሞ በ2008፤ በ2013 እና በ2014 እኤአ ላይ ለሶስት ጊዜያት የወርቅ ኳሶቹን መሰብሰቡ ሲታወቅ ዘንድሮ  ለአራተኛ ጊዜ ክብሩን በማግኘት ከሜሲ ጋር የሚጋራው ክብረወሰን  ይመዘገብለታል፡፡ በሶስተኛ እጩነት የገባው ብራዚላዊው ኔይማር ሁለቱን የወርቅ ኳስ ቀበኞችን በመብለጥ የዘንድሮውን ክብር ሊነጥቅ መቻሉ የማይጠበቅ ቢሆንም በተጨዋችነት ዘመኑ ለመጀመርያ ጊዜ ለዓለም ኮከብ ተጨዋችነት ማእረግ መቃረቡ እንደስኬት ተቆጥሮለታል፡፡
ማን እንደሚገባው የተሰጡ አስተያየቶች
ፊፋ ለ2015 የወርቅ ኳስ ክብር የሚፎካከሩትን የመጨረሻ ሶስት እጩዎች ካሳወቀ በኋላ ባለፉት 4 ሳምንታ ማን ማሸነፍ እንደሚገባው በርካታ አስተያየቶች ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡  ኔይማር ዳሲልቫ  ለመጨረሻ ፉክክር ከቀረቡት  አንዱ በመሆኑ ብቻ መረካቱን ለግሎቦ ስፖርቴ ሲገልፅ፤ ሊዮኔል ሜሲ በበኩሉ ሶስቱም የመጨረሻ እጩዎች ከባርሴሎና መሆን እንደነበረባቸው በተናገረበት አስተያየቱ ከሮናልዶ ይልቅ ለስዋሬዝ ቅድሚያ ግምት አለመሰጠቱ እንዳልተመቸው አሳውቋል፡፡ በሌላ በኩል በ2014 ያገኘውን የወርቅ ኳስ ክብር ለማስጠበቅ ተፎካካሪ ሆኖ የቀረበው ክርስትያኖ  ሮናልዶ በሰጠው አስተያየት የማሸነፍ እድሉ ለሜሲ ሊያጋድል እንደሚችል መረዳቱን ገልፆ፤ በሊግ  እና ሻምፒዮንስ ሊግን ዋንጫዎችን በማሸነፉ ብዙ ድምፅ እንደሚያስገኝለት ስለምገምት ነው ብሏል፡፡ የ30 ዓመቱ ሮናልዶ ገና ሰባት የውድድር ዘመናትን በከፍተኛ የክለብ እግር ኳስ ደረጃ በመጫወት እንደሚቀጥል በተጨማሪ ተናግሮ የኮከብ ተጨዋችነት ሽልማቶች ወደፊትም ማግኘቴ ስለማይቀር ዘንድሮ ቢያመልጠኝ ብዙም አልከፋበትም ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ የ2015 የወርቅ ኳስን ማን ሊያሸንፍ እንደሚችል በርካታ አስተያየቶች ሲሰጡ የሰነበቱ ሲሆን በተለይ በሁለቱ የስፔን ክለቦች ዙርያ ያሉ እግር ኳሰኞች ንቁ ተሳትፎ ነበራቸው፡፡ የባርሴሎናው ዳኒ አልቬዝ የወርቅ ኳሱን በሰፊ የድምፅ ልዩነት ሜሲ ማሸነፍ እንዳለበት ሲናገር፤ ሮናልዶ ሶስቱ ውስጥ መግባትም እንዳልነበረበት በማስረዳት ሲሆን፤ ግለኛ ለሆነ ተጨዋች የወርቅ ኳስ መሸለም አይገባም በማለት  ቲቪአይ የብሮድካት ተቋም ተናግሯል፡፡ የቀድሞው የባርሴሎና  ምርጥ ተጨዋችና አሰልጣኝ ዮሃን ክሮፍም የአልቬዝን ሃሳብ በሚያጠናክርበት አስተያየቱ የወርቅ ኳሱ ያለጥርጥር የሚገባ ለቡድን ተጨዋች እንደሆነ አመልክቶ ሁኔታ የሜሲን አሸናፊት የሚያረጋግጥ ነው ብሏል፡፡  የቀድሞው የፖርቱጋል፤ የባርሴሎና ተጨዋች ሊውስ ፊጎ በበኩሉ ምርጫው በጎሎች ላይ የተንተራሰ ከሆነ ማሸነፍ የሚገባው ሮናልዶ ይሆናል ካለ በኋላ፤ ዋንጫዎችን በማሸነፍ መስፈርት ከተሄደ ግን ሚያሸንፈው ሜሲ ሊሆን ይችላል ሲል አስተያየት ሰጥቷል። የብራዚሉ አሰልጣኝ ዱንጋ  በአንፃሩ ሮናልዶና ሜሲን ከአሸናፊነት ውጭ በማረግ ለብራዚል ብሄራዊ ቡድን ወጣት አምበል ኔይማር ዳሲልቫ ሽልማቱ ይገባል በማለት ለግሎቦ ስፖርቴ አስረድቷል፡፡ የአርሰናል ክለብ አሰልጣኝ አርሴን ቬንገር በበኩላቸው  በእግር ኳስ የሚሰጥ ማንኛውም ሽልማት ለቡድን ስራ አስተዋፅኦ ላላቸው መሆን እንዳለበት አስገንዝበው  ይህም አሸናፊው ሜሲ መሆኑን ያመለክታል በማለት ለሌፓሬስያን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ንፅፅር በ2015 ውጤታማነት
በ2015 እኤአ የውድድር ዘመን ሶስቱ ተጨዋቾች ከነበሯቸው አጠቃላይ ውጤቶች አንፃር  ለወርቅ ኳሱ  የሚፎካከሩት ሜሲና ሮናልዶ ናቸው፡፡ በዚሁ የውድድር ዘመን ክርስትያኖ ሮናልዶ በሁሉም ውድድሮች  55 ጨዋታዎችን ሲያደርግ 53 ጎሎችን ማግባቱና 16 ለጎል የበቁ ኳሶችን ማቀበሉ ሲመዘገብለት፤ ሊዮኔል ሜሲ ደግሞ 59 ጨዋታዎችን አድርጎ፤ 50 ጎሎችን ማግባቱና 26 ለጎል የበቁ ኳሶችን ማቀበሉ ተመዝግቦላቸዋል፡፡ በ2015 እኤአ በ52 ጨዋታዎች 4555 ደቂቃዎች ለሪያል ማድሪድ የተሰለፈው ሮናልዶ እና በ56 ጨዋታዎች 4793 ደቂቃዎች ለባርሴሎና የተሰለፈው ሜሲ እያንዳንዳቸው 48 ጎሎች ሲያመዘግቡ በ59 ጨዋታዎች 4946 ደቂቃዎች ለባርሴሎና የተሰለፈው ኔይማር 45 ጎሎች አሉት፡፡ በየክለቦቻቸው ደግሞ በ52 ጨዋታዎች 4555 ደቂቃዎች ለሪያል ማድሪድ የተሰለፈው ሮናልዶ እና በ56 ጨዋታዎች 4793 ደቂቃዎች ለባርሴሎና የተሰለፈው ሜሲ እያንዳንዳቸው 48 ጎሎች ሲያመዘግቡ በ59 ጨዋታዎች 4946 ደቂቃዎች ለባርሴሎና የተሰለፈው ኔይማር 45 ጎሎች አሉት። ፖርቱጋልን ለ2016 የአውሮፓ ዋንጫ ማለፏን ያረጋገጠው ሮናልዶ በክለቡ ሪያል ማድሪድ   በአውሮፓ ደረጃ የተለያዩ አዳዲስ የጎል ሪከርዶችን በማስመዝገቡ ከሁለቱ የባርሴሎና ፊትአውራሪዎች ብልጫ ሲያገኝበት፤  በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ከሩብ ፍፃሜው በፊት ባስመዘገባቸው 11 ጎሎች የላቀ ስኬቱ ጎልቶ ይወጣል፡፡ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የተሳትፎ ታሪኩ  ሮናልዶ ያገባቸውን ጎሎች ብዛት  89 በማድረስ በምንግዜም ከፍተኛ ግብ አግቢነት መሪነቱን እንደያዘ መቀጠሉም የሚጠቀስ ሲሆን ሜሲ በ80 ጎሎች ርቆ ይከተለዋል፡፡  ክርስትያኖ ሮናልዶ በ2014/ 15 የውድድር ዘመን በሁሉም ውድድሮች 61 ጎሎች አስመዝግቦ እያለ ከክለቡ ሪያል ማድሪድ ጋር አንድም ዋንጫ አለማግኘቱ ግን በምርጫው ተፅእኖ ሊፈጥርበት የሚችል ሲሆን በአንፃሩ  ባርሴሎናን የወከሉት ሁለቱ እጩዎች ክለባቸውን ለሶስትዮሽ የዋንጫ ድል ማብቃታቸው ብዙ ድምፅ ያስገኝላቸዋል፡፡ በ2014/ 15  የውድድር ዘመን ሜሲ በኮፓ አሜሪካ አገሩን ለዋንጫ አለማብቃቱና በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የዘንድሮ እና የምንግዜም ሪከርዱ ከሮናልዶ ወደኋላ በመቅረቱ ብቻ የሚያገኘውን ድምፅ ብዛት ሊያቀዘቅዝበት ይችላል፡፡ ባለፉት 10 የውድድር ዘመናት በኮከብ ተጨዋች ምርጫው ሊዮኔል ሜሲ እና ክርስትያኖ ሮናልዶ ቢፈራረቁም ብራዚላዊው ኔይማር ዘንድሮ የእነሱን የበላይነት ለመፎካከር እየተቃረበ መምጣቱ በራሱ ትልቁ ውጤት ይሆንለታል፡፡ ምናልባትም በርካታ ትንታኔዎች እንደሚገልፁት በሚቀጥለው ዓመት ያለጥርጥር ተሸላሚው ኔይማር ሊሆን ይችላል፡፡
የሽልማቱ ቀደምት ታሪኮች
 ከ2010 እ.ኤ.አ ወዲህ ግን ከፊፋ የዓመቱ ኮከብ ተጨዋች ምርጫ ጋር በመዋሃድ ለአሸናፊዎቹ እየተሸለመ በሚገኘው የወርቅ ኳስ ሽልማትን ለ4 ጊዜያት በማሸነፍ  ክብረወሰኑን የያዘው የአርጀንቲናው ሊዮኔል ሜሲ ነው፡፡ ሁለቱን የወርቅ ኳሶች የወሰደው ሽልማቱ በፍራንስ ፉትቦል መፅሄት  ሲዘጋጅ ሲሆን  ሌሎቹን ሁለት ሽልማቶች ደግሞ በፊፋ እና ፍራንስ ፉትቦል ጥምረት መካሄድ ከጀመረ በኋላ አግኝቷቸዋል።  በሌላ በኩል ክርስትያኖ ሮናልዶ የመጀመርያ የወርቅ ኳስ ሽልማቱን ከፍራንስ ፉትቦል መፅሄት በ2008 እኤአ ከወሰደ በኋላ ሽልማቱ በፊፋ የዓለም ኮከብ ተጨዋች ስር ከገባ ደግሞ በ2013 እና በ2014 እኤአ አከታትሎ ለሁለት ጊዜያት በመሸለም ተሳክቶለታል፡፡ በሌላ በኩል የወርቅ ኳስ ወይንም የፊፋ የዓመቱ ኮከብ ተጨዋች ሽልማትን ከአንድ ጊዜ በላይ አከታትሎ በማሸነፍ የተሳካላቸው አራት ተጨዋቾች ብቻ ናቸው፡፡ የፊፋ የዓለም ኮከብ ተጨዋች ክብርን ሁለት ጊዜ አከታትሎ በማሸነፍ የመጀመርያው ተጨዋች የነበረው ብራዚላዊው ሮናልዶ ሊውስ ናዛሪዮ ዴሊማ ሲሆን በ1996 እና በ1997 እኤአ በማሸነፉ ነው። ከእሱ በኋላ በ2004 እና በ2005 እኤአ ሌላው ብራዚላዊ ሮናልዲንሆ ጎቾ አሳክቶታል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ከ2009 እሰከ 2012 ያሉትን ሶስት የፊፋ የዓመቱ ኮከብ ተጨዋች እና የወርቅ ኳስ ሽልማቶች በመሰብሰብ ሜሲ የበላይነት ነበረው፡፡ ክርስትያኖ ሮናልዶ ደግሞ በ2013 እና በ2014 እኤአ ላይ የወርቅ ኳሱን በመሸለም ከስኬታማዎቹ ኮከብ ተጨዋቾች ተርታ ለመሰለፍ በቅቷል፡፡
የወርቅ ኳሱ በፍራንስ ፉትቦል መፅሄት እና ፊፋ ጥምረት በ2007 እኤአ ለመጀመርያ ጊዜ ሲካሄድ  የመጀመርያው አሸናፊ ብራዚላዊው ሪካርዶ ካካ ነበረ፡፡ ባለፉት 7 የውድድር ዘመናት ግን የወርቅ ኳስ ሽልማቱን ሜሲ እና ሮናልዶ ተፈራርቀውበታል። ዘንድሮ ከመጨረሻዎቹ ሶስት እጩዎች አዲስ ሆኖ የገባው ኔይማር ሲሆን ባለፉት ሽልማቶች በመጨረሻ እጩነት ከ1 እስከ 3 በነበረው ደረጃ መሰረት የሚከተሉት የምርጫ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ በ2007 ካካ፣ ሮናልዶ፣ሜሲ፤ በ2008 ሮናልዶ፤ ሜሲ፤ ቶሬስ፤ በ2009 ሜሲ፣ ሮናልዶ፣ ዣቪ፤ በ2010 ሜሲ፣ ኢንዬስታ፣ ዣቪ፤ በ2011 ሜሲ፣ሮናልዶ፣ ዣቪ፤ በ2012 ሜሲ፣ ሮናልዶ፣ ኢንዬስታ፤ በ2013 ሮናልዶ፣ ሜሲ፣ ሪበሪ እንዲሁም በ2014 ሮናልዶ፣ ሜሲ ፣ኑዌር ነበሩ፡፡ ባለፈው ዓመት የ2014 የዓለም ኮከብ ተጨዋች ሆኖ ሮናልዶ የወርቅ ኳሱን ለመሸለም የበቃው 37.66 በመቶ ድምፅ በማግኘት ሲሆን ሜሲ በ15.76 እንዲሁም ግብ ጠባቂው ማኑዌል ኔዌር በ15.72 በመቶ ድምፅ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ አግኝተው ነበር፡፡
 ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር “ፊፋ” ከፍራንስ ፉትቦል ጋ ለወርቅ ኳስ ሽልማት ከመዋሃዱ በፊት የሽልማት ስነስርዓቱን የዓለም ኮከብ ተጨዋች በሚል ስያሜ ከ1991 እ.ኤ.አ እስከ 2009 እ.ኤ.አ ለ18 ጊዜያት አካሂዶታል፡፡ ይህንኑ ሽልማት 3 ጊዜ ለመሸለም የበቁት የፈረንሳዩ ዚነዲን ዚዳንና የብራዚሉ ሮናልዶ ለውስናሃሪዮ ዴልማ ናቸው፣ ሮናልዲንሆ ለ2 ጊዜያት ለመሸለም ሲበቃ ሊዮኔል ሜሲና ክርስትያኖ ሮናልዶ እያንዳንዳቸው አንድ ጊዜ ደርሷቸዋል፡፡ የወርቅ ኳስ ሽልማት በታዋቂው የፈረንሳይ የእግር ኳስ መጽሔት “ፍራንስ ፉትቦል” አዘጋጅነት ከ1956-2009 እ.ኤ.አ ለ53 ጊዜያት ሲሸለም ፍራንስ ፉትቦል ከፊፋ ጋር ከመዋሃዱ በፊት የአውሮፓ ኮከብ ተጨዋች በሚል ማእረግ ነበር፡፡ በእነዚህ ጊዜያት እያንዳንዳቸው ሶስቴ ለመሸለም የበቁት ደግሞ ጆሃን ክሩፍ፤ ሚሸል ፕላቲኒ እና ማርኮ ቫንባስተን ሲሆኑ ሚሸል ፕላቲኒ ለሶስት ተከታታይ የውድድር ዘመናት የአውሮፓ ኮከብ ሆኖ በመሸለም ብቸኛው ነው፡፡ ሽልማቱ ከአውሮፓዊ ውጭ የሌላን ዓለም ተጨዋች በማካተት ሲካሄድ ለማሸነፍ የበቃው ብራዚላዊው ሊውስ ናዛሪዮ ዴሊማ በ1997 እኤአ ላይ ሲሆን በ1998 ተሸልሞ ደግሞታል፡፡እንደሮናልዶ ሁሉ የወርቅ ኳስ ሽልማቱን የአውሮፓ ኮከብ ተጨዋች ተብለው ሁለት ጊዜ እያንዳንዳቸው የተሸለሙ ሌሎች ተጨዋቾች አልፍሬዶ ዴስቲፋኖ፤ ፍራንዝ ቤከንባወር፤ ኬቨን ኪጋንና ሩሚነገ ናቸው።
ከወርቅ ኳሱ ባሻገር
ከዓመቱ ኮከብ ተጨዋች የወርቅ ኳስ ሽልማት ባሻገር ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር በሌሎች  የሽልማት ዘርፎች አሸናፊዎቹን በመምረጥ እንደሚሸልምም ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ ሽልማቶች የመጀመርያ ግምት የሚያገኘው የፊፋ 2015 ምርጥ ቡድን  ተብሎ የ11 ምርጥ ተጨዋቾች ስብስብ የሚታወቁበት ነው፡፡  በዚህ ምርጥ ቡድን ምርጫ ላይ  የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጨዋቾች ማህበር አባል የሆኑና በ70 አገራት የሚወከሉ 25ሺ ተጨዋቾች ድምፅ ይሰጣሉ፡፡ ለፕሮፌሽናል ተጨዋቾቹ ምርጥ 11ን ለመለየት የቀረቡት 55 እጩዎች ሲሆኑ 5 ግብ ጠባቂዎች፤ 20 ተከላካዮች፤ 15 አማካዮች እንዲሁም 15 አጥቂዎች ናቸው፡፡ የዓለም እግር ኳስ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ማህበር አባላት በሚቀጥለው 1 ወር ውስጥ አንድ ግብ ጠባቂ፤ 4 ተከላካዮች፤ 3 አማካዮች እና 3 አጥቂዎችን የሚገኙበትን ምርጥ ቡድን በመምረጥ ያስታቃሉ፡፡ በ2015 ኮከብ ቡድን ምርጫው በየጨዋታው ስፍራ ከቀረቡት 55 እጩዎች ስፔን 11 ተጨዋቾችን በማስመዝገብ ግንባር ቀደም ስትሆን ጀርመንና እና ብራዚል እያንዳንዳቸው 6 ተጨዋቾችን በእጩነት አስመልምለው ይከተላሉ፡፡ በሊግ ደረጃ ላሊጋው 23 ተጨዋቾችን በማካተት ግንባርቀደም ሲሆን ቦንደስሊጋው በ12 እጩዎች  እንዲሁም የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ  በ11 እጩዎቻቸው ተከታታይ ደረጃ ይሰጣቸዋል፡፡ ባለፈው የ2014 ምርጥ ቡድን ዝርዝር ላይ ግብ ጠባቂ ማኑዌል ኑዌር ፤ ተከላካዮች ፍሊፕ ላሃም፣ ሰርጂዮ ራሞስ፣  ቲያጎ ሲልቫና ዴቪድ ሊውዝ ፤ አማካዮች አንድሬስ ኢንዬስታ፣ ቶኒ ክሮስና አንጄል ዲማርያ አርጀንቲና እንዲሁም አጥቂዎች ክርስትያኖ ሮናልዶ፣ አርያን ሩበን እና  ሊዮኔል ሜሲ ነበሩ፡፡ በሌሎች የሽልማት ዘርፎች ይፋ በሆኑት የመጨረሻዎቹ እጩዎች ዝርዝር መሰረት በ2015 የዓመቱ ምርጥ ጎል ምርጫ ለሚበረከተው የፑሽካሽ አዋርድ ላይ የቀረቡት ሶስት የመጨረሻ እጩዎች ለወርቅ ኳስም በእጩነት የቀረበው ሜሲ ፤ ጣሊያናዊው የሮማ ተጨዋች አሌሳንድሮ ፍሎሬንዚ እና ብራዚላዊው አጥቂ ዌንደል ሊራ ፤ በኮከብ ተጨዋችነት በሴቶች ምድብ የአሜሪካዋ ካርሊ ሉሎይድ ፤ የጃፓኗ አያ ሚያማ እና የጀርመኗ ሴሊያ ሳሲክ ፤ በኮከብ አሰልጣኝ በወንዶች የመጨረሻ እጩ ሆነው የቀረቡት የባየር ሙኒኩ ፔፕ ጋርዲዮላ፤ የባርሴሎናው ሊውስ ኢነርኬ እና ቺሊን ለኮፓ አሜሪካ ድል ያበቁት ጆርጌ ሳምፖሊ እንዲሁም በሴቶች ደግሞ የአሜሪካዋ ጂል ኢሊስ፤ የእንግሊዙ ማርክ ሳምፕሰንና የጃፓን ኖርዮ ሳሳክ ናቸው፡፡
በአፍሪካ ደረጃስ…
ከዓመቱ ኮከብ ተጨዋች ምርጫ ጋር በተያያዘ ሌላው የሚነሳው ወቅታዊ ነገር የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን በ2015 የግሎ ካፍ አዋርዶች ስነስርዓት በተለያዩ 12 ዘርፎች የመጨረሻ እጩ ሆነው የቀረቡትን ዝርዝር ሰሞኑን ማስታወቁ ነው፡፡ የአሸናፊዎች ምርጫውን የሚያካሂዱት  የካፍ የሚዲያ ኮሚቴ አባላት ሲሆኑ የሽልማት ስነስርዓቱ ከሶስት ሳምንታት በኋላ በናይጄርያ ዋና ከተማ አቡጃ ውስጥ ይካሄዳል፡፡ ከሁሉም ሽልማቶች በዋናነት መጠቀስ ያለበት የዓመቱ የአፍሪካ ኮከብ ተጨዋች ምርጫ ሲሆን 3 የመጨረሻ እጩዎች የቀረቡት ጋናዊው የስዋንሴ ክለብ ተጨዋች አንድሬ አየው፤ ጋቦናዊው የቦርስያ ዶርትመንድ ተጨዋች ፒዬር ኤምሪክ አቡሚያንግ እንዲሁም ኮትዲቯራዊው የማንችስትር ሲቲ ተጨዋች ያያ ቱሬ ናቸው፡፡ የ32 ዓመቱ ያያ ቱሬ የ2015 የአፍሪካ ኮከብ ተጨዋች ተብሎ የቢቢሲን ሽልማት ያገኘ ሲሆን  በካፍ የዓመቱ ኮከብ ተጨዋች ምርጫም በማሸነፍ ሽልማቱን ለአምስት ጊዜያት ያሸነፈ የመጀመርያ ተጨዋች ሊሆን እንደሚችል ተጠብቋል። አምና ቱሬ የአፍሪካ ኮከብ ተጨዋች ተብሎ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ሲመረጥ ለአራተኛ ጊዜ ስለነበር ተመሳሳይ ክብር ከነበረው የካሜሮኑ ሳሙኤል ኤቶ ክብረወሰን ተጋርቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡በካፍ ግሎ ሽልማት በ2015 ሌሎቹ ዘርፎች ለሽልማት ከቀረቡ እጩዎች በዓመቱ ምርጥ ክለብ ዩሲኤምአልጀርስ ከአልጄርያ፤ ቲፒ ማዜምቤ ከዲ.ሪ ኮንጎ፤ ኦርላንዶ ፓይሬትስ ከደቡብ አፍሪካ፤ ኤትዋል ደሳህል ከቱኒዚያ እንዲሁም በዓመቱ ምርጥ ብሄራዊ ቡድን  ኮትዲቯር፤ ጋና፤ ሀ17  ጋና እንዲሁም የናይጄርያ ሀ17 እና ሀ23 ቡድኖች መፎካከራቸው ይጠቀሳል፡፡

              ሊዮኔል ሜሲ
28 ዓመቱ፤ 1.69 ሜትር ቁመቱ ፤ 10 የማልያ ቁጥሩ
120 ሚሊዮን ዩሮ በዝውውር  የዋጋ ግምቱ
300 ሚሊዮን ዶላር ጥሪት ሃብቱ
71 ሚሊዮን ዶላር የዘንድሮ ገቢው
22 ሚሊዮን ዶላር በየዓመቱ ከማስታወቂያ እና የስፖንሰርሺፕ
አዲዳስ ፤ ቱርኪሽ ኤርላይንስ፤ ፔፕሲ፤ ሀርባ ላይፍ፤ ኢኤ ስፖርትስ፤ ዶልቼ ጋባና እና      
ጂሌት ስፖንሰሮቹ ናቸው፡፡
ከአዲዳስ ጋር ለሰባት ዓመት በዓመት 20 ሚሊዮን በ7 ዓመት 140 ሚሊዮን ዶላር ትልቁ ገቢው
ከ26 በላይ ዋንጫዎቹ ከባርሴሎና ጋር 7 የላሊጋ፤ 3 የኮፓ ዴላ ሬይ፤ 4 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ፤2 የዓለም ክለቦች ዋንጫዎች
ከ2004 ጀምሮ በባርሴሎና 603 ጨዋታዎች 472 ጎሎች
ክርስትያኖ ሮናልዶ
30 ዓመቱ፤ 1.85 ሜትር ቁመቱ፤ 7 የማልያ ቁጥሩ
110 ሚሊዮን ዩሮ የዝውውር ዋጋ ግምቱ
325     ሚሊዮን ዶላር ጥሪት ሃብቱ
80 ሚሊዮን ዶላር የዘንድሮ ገቢው
28 ሚሊዮን ዶላር በየዓመቱ ከማስታወቂያ እና የስፖንሰርሺፕ
ናይኪ ፤ ኮካ ኮላ፤ ካትሮል፤ ኮናሚ፤ ሞተሮላ፤ ሀርባላይፍ፤ ኤምሬትስ እና እረማኒ    
 ከሌሎች ስፖንሰሮቹ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ናይኪ ጋር እስከ 2019 እኤአ በዓመት 21.7 ሚሊዮን ዶላር በ5 ዓመት 105 ሚሊዮን ዶላር ትልቁ ገቢው
ከ16 በላይ ዋንጫዎች በማንችስተር ዩናይትድና በሪያል ማድሪድ
ከ2002 ጀምሮ በ3 የተለያዩ ክለቦች 644 ጨዋታዎች 457 ጎሎች በስፖርቲንግ ሊዝበን፤ በማንችስተር ዩናይትድ እና በሪያል ማድሪድ
ኔይማር ዳሲልቫ
23 ዓመቱ፤ 1.74 ሜትር ቁመቱ 10 / 11 የማልያ ቁጥሩ
100 ሚሊዮን ዩሮ በዝውውር የዋጋ ግምቱ
80 ሚሊዮን ዶላር ጥሪት ሃብቱ
33.6 ሚሊዮን ዶላር የዘንድሮ ገቢው
16 ሚሊዮን ዶላር በየዓመቱ ከማስታወቂያ እና የስፖንሰርሺፕ
ካስትሮል፤ ፓናሶኒክ፤ ኤልኦሪል፤ ቮልክስዋገን ስፖንሰሮቹ ናቸው፡፡
ናይኪ ጋር ከ2012 እስከ 2022 እኤአ በዓመት 9.5 ሚሊዮን ዶላር በ11 ዓመት 105 ሚሊዮን ዶላር ትልቁ ገቢው
ከ6 በላይ ዋንጫዎቹ ከባርሴሎናና ከሳንቶስ ጋር
ከ2009 ጀምሮ በብራዚሉ ሳንቶስ እና በስፔኑ ባርሴሎና ክለቦች 174 ጨዋታዎች 99 ጎሎች

Read 4216 times