Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 11 February 2012 11:10

የካፔሎ ስንብት “ሶስቱን አናብስት” አቃውሷል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የእንግሊዝ እግር ኳስ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ሁለት አስገራሚ የውዝግብ ድራማዎች አስተናገደ፡፡ የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ፋብዮ ካፔሎ ከ4 ዓመታት በኋላ ከሃላፊነታቸው ራሳቸውን በማንሳት መልቀቂያ ሲያስገቡ፤ምትካቸው ለመሆን በዋና እጩነት የቀረቡት    የቶትንሃም ሆትስፐርሱ አሰልጣኝ ሃሪ ሬድናፕ ከ8 ሰዓታት በፊት በለንደን ፍርድ ቤት ከተከሰሱበት የታክስ ማጭበርበር በነፃ መሰናበታቸውን  አረጋግጠዋል፡፡ከካፔሎ ስንብት በኋላ ከብሄራዊ ቡድኑ ተጨዋቾች መካከል  ጃክ ዊልሸር ዩሮ 2012 ተቃርቧል ማናጀር ግን የለንም በሚል ስጋቱን ሲገልፅ ዋይኒ ሩኒ በበኩሉ ሃሪ ሬድናፕን መተካት ያወጣል በሚል በትዊተር መልእክቱ አስተያየቱን ገልጿል፡፡ የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን ከ18 ቀናት በኋላ ከሆላንድ አቻው ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ያለው ሲሆን በዚህ ወቅት አዲስ የአሰልጣኝ ቅጥር ካልተከናወነ ሃላፊነቱን በሞግዚት አሰልጣኝ ለማሰራት እቅድ መያዙን የቀድሞው የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን አምበልና አሁን የእግር ኳስ ማህበሩ ሃላፊ ሆኖ የሚሰራው ጋሬዝ ሳውዝጌት ተናግሯል፡፡

እንግሊዝ የዩሮ 2012 ተሳትፏዋን ከመጀመሯ በፊት ባሉት አራት ወራት ግን የካፔሎን ምትክ ለማግኘት አስቸጋሪ እንደሚሆንባት እየተገለፀ ነው፡፡ ጋሬዝ ሳውዝ ጌት ካፔሎን ለመተካት ዋናው እጩ የቶትንሃሙ ሃሪ ሬድናፕ ናቸው ብሏል፡፡ ይህን ሃሳቡንም በርካታ የብሄራዊ ቡድኑ ተጨዋቾች እየደገፉት ነው፡፡ ከሊጉ አሰልጣኞች የሊቨርፑሉ ኬኒ ዳግሊሽና የማን ዩናይትዱ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ሃሪ ሬድናፕ ለእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ብቁ እጩ መሆናቸውን መስክረዋል፡፡ሃሪ ሬድናፕ ሶስቱ አናብስትን እንዲያሰለጥኑ ያለውን ግፊት ተከትሎ በሰጡት አስተያየት ስለ ሃላፊነቱ አስበው እንደማያውቁ ገልፀው ዋና ትኩረታቸው በቶትንሃም ክለብ ባላቸው ስራ ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ሃሪ ሬድናፕ በቶትንሃም ክለብ ሃላፊነታቸው የ15 ወራት ኮንትራት የሚቀራቸው ሲሆን ከዘንድሮው የውድድር ዘመን መገባደድ በኋላ በእግር ኳስ ማህበሩ የቅጥር ጥያቄ ብቻ ከቀረበላቸው ብቻ ሃላፊነቱን ለመረከብ ያጤናሉ የሚሉ መረጃዎች ወጥተዋል፡፡ካስትሮል በሰራው የብቃት መለኪያ በእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት በገዛ ፈቃዳቸው የለቀቁትን ፋብዮ ካፔሎ ለመተካት ከፍተኛውን የአሸናፊነት ስኬት አስመዝግበዋል በሚል በመጀመርያ እጩነት ያስቀመጣቸው ሃሪ ሬድናፕን ነው፡፡ ካፔሎን ለመተካት ከሃሪ ሬድናፕ ሌላ ጆሴ ሞውሪንሆ፤ ጉስ ሂድኒክ እና ሮይ ሁጅሰን በእንግሊዝ እግር ኳስ ማህበር የአሰልጣኞች አደን ኢላማ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ሃሪ ሬድናፕ ከ3 ዓመታት ጀምሮ በዋና አሰልጣኝነት በሰሩባቸው ሁለት ክለቦች ፖርትስማዝ እና ቶትንሃም 49 በመቶ ድል አድራጊነታቸው ተለክቷል፡፡ ሬድናፕ ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት በሰሜን ለንደኑ ክለብ ቶትንሃም እየሰሩ በፕሪሚዬር ሊግና በአውሮፓ ውድድሮች በታሪክ ከፍተኛውን የውጤታማነት ጉዞ አሳክተዋል፡፡

ሃሪ ሬድናፕ ከኤፍኤው በይፋ ሃላፊነቱን እንዲረከቡ ጥሪ ከቀረበላቸው ላለመቀበል ያዳግታቸዋል፡፡ ከትናንት በስቲያ በሰጡት አስተያየት እስቲ ካናገሩኝ እድሉን ለመጠቀም ደስተኛ ነኝ ሲሉ እንኳን ብሄራዊ ቡድንን ከባዱን የክለብ አሰልጣኝነት እየሰራሁ ነኝ ብለዋል፡፡ ቶትንሃም ሆትስፐርስ በሊጉ ተፎካካሪነት የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነቱን ለማረጋገጥና በኤፍ ኤካፕ ለዋንጫው ያለውን እድል በትኩረት ልሰራበት እፈልጋለሁ ያሉት ሃሪ ሬድናፕ 64 ዓመታቸው ነው፡፡ የእግር ኳስ ማህበሩ በሬድናፕ ቅጥር ያለውን ፍላጎት ያተኮረበት ሲሆን ቶትንሃም እኝህን ውጤታማ አሰልጣኝ ካጣ በ12 ወራት ውስጥ አራተኛውን አሰልጣኝ ማጣቱ ይሆናል፡፡ የእንግሊዝ እግር ኳስ ማህበር የሃሪ ሬድናፕን ቅጥር እውን ለማድረግ ቢያንስ 10 ሚሊዮን ፓውንድ ወጪ ማድረግ ይኖርበታል እየተባለ ሲሆን ቶትንሃም አሰልጣኙን ለመልቀቅ 5 ሚሊዮን ፓውንድ እንደሚጠይቅና የቀጣይ 15 ወራት ደሞዛቸውን 3.5 ሚሊዮን ፓውንድ መክፈል እንደሚጠበቅበት አውስቷል፡፡

በፋብዮ ካፔሎ እና በስልጠና ቡድናቸው ድንገተኛ ስንብት የእንግሊዝ እግር ኳስ ማህበርና ብሄራዊ ቡድኑ መቃወሳቸውን ያመለከቱ መረጃዎች በሁኔታው ሳቢያ 2.5 ሚሊዮን ፓውንድ ክፍያ በኪሳራ ወጭ መደረጉን ገልፀዋል፡፡ ካፔሎ በዓመት 6 ሚሊዮን ፓውንድ ደሞዝ ይታሰብላቸው የነበረ ሲሆን ሃላፊነታቸውን ሲለቁ በካሳ 1.5 ሚሊዮን ፓውንድ ያገኛሉ፡፡ ካፔሎ በብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝነት በቆዩባቸው 4 ዓመታት 20 ሚሊዮን ፓውንድ የደሞዝ ገቢ ነበራቸው፡፡ ከፋብዮ ካፔሎ ጋር አብረው የለቀቁት ሌሎቹ ጣሊያናውያን ምክትላቸው ማሲሞ ኔሪ እና የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ የነበሩት ፍራንኮ ታኬናርዲ ሲሆኑ ለእነሱም በቀሪ የኮንትራት ውል እስከ 1 ሚሊዮን ዶላር ይታሰብላቸዋል፡፡ በጣልያኖቹ ድንገተኛ ስንብት የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን የአውሮፓ ዋንጫ ዝግጅት ከገንዘብ ኪሳራው ባልተናነሰ በከፍተኛ የሰው ሃይል  እጥረት እንዲቃወስ አድርጎታል፡፡

የብሄራዊ ቡድኑን አምበል ጆን ቴሪ በዲስፕሊን ጉድለት ሃለፊነቱን በተነጠቀ ሰሞን  ዋና አሰልጣኙ ካፔሎ ደግሞ በገዛ ፈቃዳቸው ስራቸውን መልቀቃቸው በአገሪቱ እግር ኳስ ላይ ግራ መጋባት የፈጠረ ሲሆን በፖላንድና ዩክሬን የሚዘጋጀው ዩሮ 2012 አራት ወራት ሲቀሩ ሁኔታዎቹ መከሰታቸው የእንግሊዝ እግር ኳስ ማህበር ምትክ የአሰልጣኝ ቡድኑን ለማዋቀር ችግር ውስጥ ይከተዋል፡፡

ፋብዮ ካፔሎ በእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ሲሰሩ 42 ጨዋታዎች አድርገው 28 አሸንፈው፤ በስምንት አቻ ተለያይተውና በ6 ጨዋታ በመሸነፍ 67 በመቶ ድል አድራጊነት በማስመዝገብ ከ46 ዓመታት በፊት የዓለም ዋንጫ ድልን ካስመዘገቡት ራምሴይ 61 በመቶ ድል አድራጊነት የተሻለ ውጤት አስመዝግበዋል፡፡

 

 

Read 2021 times Last modified on Saturday, 11 February 2012 11:15

Latest from