Tuesday, 29 December 2015 07:20

“…ቡና ከሆነ እባካችሁ ሻይ አምጡልኝ፣ ሻይም ከሆነ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(14 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
በደጉ ጊዜ ‘ስጦታ’ ብለው የ‘ዮሐንስ አራምዴ’ ጠርሙስ እንኳን ቢያቅታቸው ካርድ ቢጤ የሚልኩ ነበሩ፡፡ ዘንድሮ  ልጄ…ዝምታው በዛ፤ እና እንትና…የሌብል ነገር ከሆነ ብላኩ ይሁንልኝ፡፡
ስሙኝማ…የምር ግን “ይሄ ችጋራም አንድ ሀብል እንኳን ይዝጋኝ!…”  “የፈለገው ቢሆን እንዴት ካርድ እንኳን አልላከችልኝም!” ምናምን እየተባባሉ ወዳጅነታቸውን የሚያፈርሱ ሰዎች አሉ ይባላል፡፡
ስጦታ መስጠት አስቸጋሪ ሲሆንስ! ልጄ በቀዳዳ ካልሲ የሁለት ሺህ ብር ጫማ እንደምናደርገው …ያላቅማችን መንጠራራት እንኳን ሲያቅተንስ! በፊት እኮ…አለ አይደል… አርቲፊሻል ጉትቻ እንኳን የገዛ እንትና፤ “የሐዋርያነት ማዕረግ ይሰጠው ተብሎ ወደ ቫቲካን ወይም ወደ ሌላ የሚመለከተው አካል ‘ፔቲሽን’ (ቂ…ቂ…ቂ…) ሊላክ ምንም አይቀረው፡፡
እናላችሁ… ዘንድሮ ይቺ ስሟ በ‘ቪ’ የሚጀምር መኪና መጣችና…ስጦታ መግዛት አይደለም  ማሰቡም አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… እንትናዎቹ እንትናዬዎቻቸው ዘንድ ሲሄዱ በ‘ቪ’ የሚጀምሩ ነገሮች ብቻ መያዛቸው…(‘ቪያግራና ቪትዝ’ ማለትም ይቻላል…) ‘በጥናት ተደግፎ’ ነው እንዴ!
ስለ ስጦታ ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…
ሰውዬው የእኔ ቢጤ ለቴሌቪዥን መስኮትና ለአደባባይ የማይሆን አይነት ነው፡፡ (ፎቶ እንኳን ቢሆን ‘ዕድሜ ለፎቶሾፕ’ ይባል ነበር!” ወደን ‘ከመድረክ የጠፋን’ እንዳይመስላችሁ…) እናላችሁ… የገና በዓል ይደርስና ለእንትናዬው ስጦታ ሊገዛ ሱቅ ይሄዳል፡፡
“ለጓደኛዬ የገና ስጦታ ልገዛላት ፈልጌ ነው፡፡ ምን የምትወድ ይመስለሻል?” ሲል ሻጯን ይጠይቃታል፡፡
እሷዬዋም ሰውዬውን ከፍ ዝቅ አድርጋ ‘አበጥራ’ ታየውና፤ “አንተን ትወድሀለች?” ስትል ትጠይቀዋለች፡፡
“አዎ፣ ትወደኛለች፡፡”
“አንተን ከወደደች ምንም ነገር ቢሆን ትወዳለች፣” ብላው እርፍ፡፡
ማን ጠይቅ አለው! ዝም ብሎ የሚገዛውን ገዝቶ አይሄድም፡፡ እሱን አይነት ሰው ከወደደች “እንዴት ይህን ታመጣለህ” ምናምን ብላ አታኮርፍማ!
የማኩረፍ ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን እዩልኝማ። በሆነ ምክንያት የሰውየው ሚስትና እህት ተኳርፈዋል። እናላችሁ…እሱዬው “ያቺም ሥጋዬ፣ ይቺም ሥጋዬ…” ይልና ለማስታረቅ ይሞክራል። ቢል፣ ቢል ግን አይሳካለትም፡፡ ሁሉም ነገር ሲከሽፍበት ምን ቢል ጥሩ ነው…
“ዓለም በሴቶች ብትመራ ኖሮ ጦርነቶች አይኖሩም፡፡ ግን አገሮች በሙሉ ተኮራርፈው አይነጋገሩም ነበር፡፡”  
አሪፍ አይደል!
ስሙኝማ…የሚገርመው ነገር ለገና ስጦታ መሰጣጠት ብሎ ነገር እኮ የእኛ አልነበረም፡፡ አሁን፣ አሁን ግን ኮረጅን፣ ኮረጅንና በግድ የእኛ ልናደርገው ምንም አልቀረን፡፡ ይኸው የገና ዛፍ የሚባለው ነገር በየቤታችን እየገባ አይደል! በቀደም እለት አንድ የምናውቀው ሰው ‘አዲስ ካገኛት’ እንትናዬው ጋር ‘ታንክስ ጊቪንግ’ ለማክበር ወደ አዋሳ፣ ላንጋኖ እንደሚሄድ ሲያወራ ነበር፡፡ ‘ታንክስ ጊቪንግ!’ እሱዬው እኮ አይደለም አሜሪካ መሄድ፣ በአሜሪካ ኤምባሲ ግንብ አጠገብ ያለፈበት ጊዜም ራሱ እንኳን ትዝ አይለውም፡፡ ‘ቫለንታይንስ ዴይ’ ሹክክ ብሎ ገብቶ ተንሰራፍቶ የለ! አሁን ደግሞ ‘ታንክስ ጊቪንግ’ ይከተልና…ምን አለፋችሁ…ቀጥ­ሎ ‘ጁላይ 4’ “ብሔራዊ በዓል ይሁንልን…” ሳንል አንቀርም፡፡
ስሙኝማ… ከዚህ በፊት ደጋግመን እንዳወራነው በኤምባሲዎች ግብዣ ላይ የተጠቀለለ እንጀራ በሹካ እያነሱ ‘ወጥ የሚያጠቅሱ’ የ‘አማርኛ መናገርና ድንጋይ መወርወር’ ከልካዮች ሲበዙ ገና የበዓላት ‘ኢምፖርት’ ባይጧጧፍ ምን አለ በሉኝ፡፡
መልእክት አለን… ልትመስሏቸው የምትሞክሯቸው ‘ፈረንጆቹ’ ያጨበጭቡባችኋል እንጂ አያጨበጭቡላችሁም፡፡ ‘መሰልጠናችንን ልናሳምናቸው’ መከራችንን ስናይ “በእናንተ መጀን…” አይነት ውዳሴ የምናዘንብላቸው ‘ፈረንጆች’… ይሄኔ “አይ የሀበሻ ነገር!” ሊሉ እንደሚችሉ ማወቁ አሪፍ ነው፡፡
የምር ግን…አለ አይደል…አሁን፣ አሁን ምኑም ከምኑ የማይለይ ነገር እየበዛብን ነው፡፡ ለምንይዘውም ነገር፣ ለምንጥለውም ነገር ምክንያት አይደለም ሊኖረን…ምክንያት የሚያስፈልገንም አይመስልም፡፡
ይቺን ስሙኝማ…አንደኛው የ‘አማሪካን’ ፕሬዝዳንት የሆነ ቦታ ላይ ትኩስ ነገር በስኒ ይቀርብላቸዋል፡፡ የቀረበላቸውንም አየት አደረጉና ምን አሉ መሰላችሁ…
“ይሄ ቡና ከሆነ እባካችሁ ሻይ አምጡልኝ፣ ሻይም ከሆነ እባካችሁ ቡና አምጡልኝ…” አሉ ይባላል፡፡
ዘንድሮም እንዲሁ ብዙ ነገር ግራ እየገባን ነው፡፡
ቡናና ሻይ መለየት እየቃተን ነው፡፡
እኔ የምለው ግን…እግረ መንገዴን…አንዳንድ ቤቶች ሻይ ቅጠሉን ስንት ጊዜ ነው ደጋግማችሁ የምታፈሉት! አሀ… ‘ሪሳይክሊንግ’ ታዲያ በእኛ ሻይ ላይ ነው እንዴ! ነው…ወይንስ ብትን ሻይ ቅጠል ላይ የመጠቀሚያ ቀን ምናምን ‘ይጻፍበት!’
እንደ ጭምጭምታ ከሆነማ…አንዳንድ ምግብ ቤቶች ‘ሪሳይክልድ ፉድ’ ምናምን ይቀርባል አሉ፡፡ ለምሳሌ ከእንትናም፣ ከእነእንትናም የተራረፈችውን እንጀራ ምናምን ሰብሰብ ተደርጋ ‘ፍርፍር’ ትሆናለች የሚባል ነገር አለ፡፡ የሚባለውን ነዋ! መአት ነገር ነው ‘ሪሳይክል’ ይደረጋል የሚባለው፡፡ (ቢላዋ የማይደፍረው ‘አኞ’ ሥጋ ‘ጭቅና’ እንዲሆን ፓፓያ ውስጥ ተዘፍዝፎ ያድራል የሚባለው ‘ሪሳይክሊንግ’ ነው ‘ፕላስቲክ ሰርጀሪ!’)
እኔ የምለው… “ግብዣውን የሚያሳምረው የሥጋው ብዛት ሳይሆን የእንግዶቹ ፈገግታ ነው…” የሚል ነገር ‘አፕዴት’ ይደረግልን እንጂ! ልክ ነዋ… መጀመሪያ ነገር ዘንድሮ ‘ሥጋው’ ከሌለ ፈገግታ ከየት መጥቶ! ቂ…ቂ...ቂ… ደግሞ በየግብዣው “አየኸው ምን የሚያካክለውን እንደሚጎርስ…” በምንባባልበት ዘመን የሁሉ አፍ በሥራ ተጠምዶ ፈገግታ ብሎ ነገር የለም፡፡
አንዳንድ ቦታ ሌላው ሰው ሲጎርስና ሲያላምጥ ፍጥጥ ብለው የሚያዩ ሰዎች አይገጥሟችሁም! እኔ የምለው… ለፊልም መሪ ገጻ ባህሪይነት እያጠኑን ነው!... ‘ኢቭል አይ’ ነገር መሆኑ ነው! “አበላሉን አይተህ ሪፖርት አድርግ…” ተብለው ታዘው ነው! ሀሳበ አለን… ‘ሰው ሲመገብ አፍጥጦ ማየት ነውር ነው፣’ ምናምን የሚል ማስታወቂያ ‘ደረሰኝ ሳይቀበሉ ሂሳብ አይክፈሉ’ የሚለው ማስታወቂያ ጎን ይለጠፍልንማ፡፡
ቡናና ሻይ መለየት እያቃተን ስለሆነ ለዩልንማ።
ስሙኝማ…እግረ መንገዴን…እዚህ አገር ይሄ ሥራው ከተጋመሰና ካለቀ በኋላ የመንገድ፣ የኮንዶሚኒየም ምናምን ‘ዲዛይን የሚለወጠው’ ግራ ግብት አይላችሁም! መንገድና ቤት ግንባታም በ‘ትራያል ኤንድ ኤረር’ ነገር ሆነ እንዴ! ደግሞስ…ፈራንካው እንዲህ እንደ ልብ ነው ማለት ነው! ወይስ ጽሁፎች ‘እስኪጠሩ’ ድረስ ተደጋግመው የ‘ዲዛይን ለውጥ’ እንደሚደረግባቸው በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ትምህርቱ እንደዛው ‘ተደጋግሞ እየፈረሰ ካለተሠራ አይጠራም’ የሚል የምናምን ክሬዲት አወር ኮርስ ተጨመረበት!
ቡናና ሻይ መለየት እየቃተን ስለሆነ ለዩልንማ፡፡
ከዚህ በፊት ያወራናትን እንድገማትማ፡፡ ሁለቱ ጓደኛሞቹ ስለ ዕድሜ እያወሩ ነው፡፡
“ዕድሜሽ ስንት ነው?”
“ሀያ ሁለት፡፡”
“ሀያ ሁለት!”
“አዎ፣ ሀያ ሁለት፡፡ አንቺስ ዕድሜሽ ስንት ነው?”
“እንዳንቺ ዕድሜ ከሆነ ገና አልተወለድኩም፡፡”
አሪፍ አይደል!
የምር ግን ሀያ ሁለትና አርባ ሁለት የሚለዩባቸው ነገሮች ይነገረንማ፡፡ አለበለዛ እኮ… አለ አይደል… ከላይ እንደተጠቀሱት የአሜሪካ ፕሬዝደንት  “ይሄ ቡና ከሆነ እባካችሁ ሻይ አምጡልኝ፣ ሻይም ከሆነ እባካችሁ ቡና አምጡልኝ…” እያልን ልንከርም ነው።
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4614 times