Saturday, 11 February 2012 11:16

የገቢ ሊጉን የስፔን ክለቦች ይመሩታል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

በዓለም እግር ኳስ የገቢ ሊግ ሁለቱ የስፔን ሃያላን ክለቦች ሪያል ማድሪድ እና ባርሴሎና ዘንድሮም በመሪነት መቀጠላቸውን ዴሊዮቴ ቢዝነስ ግሩፕ ሰሞኑን  ይፋ ባደረገው ሪፖርት አስታወቀ፡፡ ሪያል ማድሪድ ለ7ኛ ዓመት በተከታታይ የገቢ ሊጉን በአንደኛነት ሊመራ ችሏል፡፡ የገቢ ሊጉን ሪያልማድሪድ የሚመራው በ2011 የውድድር ዘመን 479.5 ሚሊዮን ዩሮ በማስመዝገቡ ነው፡፡ የቅርብ ተቀናቃኙ ባርሴሎና ደግሞ በ450.7 ሚሊዮን ዩሮ ገቢው ሁለተኛ ደረጃን ወስዷል፡፡ ከሁለቱ የስፔን ክለቦች የገቢ የበላይነት በፊት ለ8 ዓመታት የገቢ ሊጉን ይመራ የነበረው የእንግሊዙ ክለብ ማንችስተር ዩናይትድ ደግሞ ባለፈው የውድድር ዘመን 367 ሚሊዮን ዩሮ በማስገባት 3ኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡ የጀርመኑ ታላቅ ክለብ ባየር ሙኒክ በ324.4 ሚሊዮን ዩሮ ገቢው አራተኛ ደረጃ መያዙን የሚገልፀው የዴሊዮቴ ቢዝነስ ግሩፕ ሪፖርት በገቢ ሊጉ እሰከ አረተኛ ደረጃ የሰፈሩት ክለቦች በተመሳሳይ ላለፉት 4 ዓመታት ደረጃቸውን ጠብቀው እንደቆዩና በሜዳ ገቢ፤ በብሮድካስቲንግና በንግድ እንቅስቃሴያቸው መጠናከር ደረጃቸውን እንደጠበቁ አረጋግጧል፡፡

የእንግሊዟ ለንደን ከተማ ሁለት ክለቦች አርሰናል በ251.1 እንዲሁም ቼልሲ 249.8 ሚሊዮን ዩሮ ገቢያቸው 5ኛና 6ኛ ደረጃን አከታትለው እንደያዙ ያመለከተው ዴሊዮቴ የእንግሊዝ ክለቦች የገቢ ሊጉ ላይ እስከ 20 በተሰጠው ደረጃ 6 ክለቦች በማሳተፍ ከየትኛውም የአውሮፓ ሊግ በተሻለ ውክልና መገኘታቸውን ጨምሮ አስታውቋል፡፡ የጀርመኑ ክለብ ሻልካ  6 ደረጃዎችን አሻሽሎ ከመጀመርያዎቹ 10 ቡድኖች ተርታ በመግባት ከፍተኛውን የገቢ መሻሻል ያሳየ ክለብ ሲሆን 202.4 ሚሊዮን ዩሮ በማግኘት 6ኛ ደረጃን ይዟል፡፡ በገቢ ሊጉ ቶትንሃም ሆትስፐርስ  በ181 እንዲሁም ማን ሲቲ 169.6 ሚሊዮን ዩሮ ዓመታዊ ገቢያቸው 11ኛና 12ኛ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡ ሁለቱ የጣሊያን ክለቦች ኤሲ ሚላንና ኢንተር ሚላን 235.1 እና 211.4 ሚሊዮን ዩሮ ዓመታዊ ገቢ በማስመዝገብ እንደቅደምተከተላቸው 7ኛና 8ኛ ደረጃን አከታትለው ወስደዋል፡፡

የአውሮፓ ክለቦች ገቢ በ2011 አስቀድሞ ከነበረው ዓመት በ3 በመቶ ብቻ እድገት በማሳየት እስከ 20ኛው ደረጃ ባሉ ክለቦች በድምሩ 4.4 ቢሊዮን ዩሮ አስገብተዋል፡፡  የዴሊዮቴ ቢዝነስ ግሩፕ ሪፖርት  እንዳስታወቀው በገቢ ሊጉ 20 ደረጃዎች ለመጀመርያ ጊዜ በመግባት የጀርመኑ ዶርትመንድ፤ የስፔኑ ቫለንሲያ እና የጣሊያኑ ናፖሊ ሲጠቀሱ በዚሁ የደረጃ ዝርዝር የገቡ 20ዎቹም ክለቦች በ5ቱ ታላላቅ የአውሮፓ ሊጎች ተወዳዳሪ ናቸው፡፡ 14 ክለቦች በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሲወዳደሩ ሲሆን 5 ደግሞ በዩሮፓ ሊግ መሳተፋቸውን የሚገልፀው ሪፖርቱ የጀርመኑ ክለብ ሃምበርግ ብቻ በአውሮፓ ደረጃ ያለፈውን ውድድር ዘመን ሳያሳልፍ የገቢ ሊጉን ተቀላቅሏል ብሏል፡፡

ሪያል ማድሪድና ባርሴሎና በቴሌቭዥን የስርጭት መብት ከላሊጋ ክለቦች በተናጠል መደራደራቸው ገቢያቸውን አሟሙቆታል፡፡ በገቢ ሊጉ የሪያል ማድሪድ የ1ኛነት ስፍራ በቅርቡ የማይነጠቅ መሆኑን የሚያመለክተው ሪፖርቱ ባርሴሎና በኳታር ፋውንዴሽን በማልያ ስፖንሰርሺፕ በየዓመቱ የሚያገኘው 30 ሚሊዮን ዩሮ እና በሻምፒዮንስ ሊግ ያለው ውጤታማነት በቅርብ ርቀት ሁለተኛ ደረጃውን ጠብቆ ለመከተል እንደሚያስችለውም አመልክቷል፡፡ ማንችስተር ዩናይትድ ባለፈው የውድድር ዘመን የሻምፒዮንስሊጉን ዋንጫ በባርሴሎና መነጠቁና ዘንድሮ ከጥሎ ማለፉ በመሰናበቱ በገቢ ሊጉ ከስፔኖቹ ክለቦች ጋር ያለውን ልዩነት የማጥበብ እድሉን አሰናክሎበታል፡፡ የአውሮፓ ክለቦች ካለባቸው የብድርና እዳ ጫና በተገናኘ ገቢያቸው መቀዝቀዙን የሚገልፁ መረጃዎች ባለፈው የውድድር ዘመን በዚህ ሳቢያ  እስከ 1ቢሊዮን ዩሮ መክፈላቸውን አስታውቀዋል፡፡ በአውሮፓ እግር ኳስ የሚወዳደሩ 665 ክለቦች በአጠቃላይ 8.4 ቢሊዮን ዩሮ እዳና ብድር ተመዝግቦባቸዋል፡፡

 

 

Read 2315 times Last modified on Saturday, 11 February 2012 11:20