Print this page
Tuesday, 29 December 2015 07:45

ዋልያዎቹ ለቻን 2016 ዝግጅት ጀምረዋል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

    4ኛው የአፍሪካ አገራት የእግር ኳስ ሻምፒዮንሺፕ ‹‹ቻን 2016›› ከጥር 7 እስከ 29 በሩዋንዳ አዘጋጅነት የሚካሄድ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ የቡድናቸውን 30 ተጨዋቾች ለዝግጅት ጠርተዋል፡፡  
በ‹‹ቻን 2016›› የሚካፈሉ ብሄራዊ ቡድኖች መካከል አንዳንዶቹ የተጨዋቾች ዝርዝራቸውን ሲያሳውቁ ሌሎች ደግሞ ሙሉ ዝግጅት ከጀመሩ  ሳምንት አልፏቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሚገኝበት ምድብ 2  የተደለደሉ አገራት ከቻን መጀመር በፊት ቢያንስ 2 የአቋም መፈተሻ ግጥሚያዎች ለማድረግ ማቀዳቸውን አስታውቀዋል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ዋልያዎቹ ለዝግጅት ቢጠሩም ምንም አይነት የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ስለመዘጋጀቱ የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡  
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የመጀመርያውን ጨዋታ ጥር 8 ከዲ.ሪ.ኮንጎ ፤ ሁለተኛውን ጨዋታ ጥር 11 ከካሜሮን  እንዲሁም የምድቡን የመጨረሻ ጨዋታ ጥር 15 ከአንጎላ የሚያደርግ ይሆናል፡፡  ዋልያዎቹ ከምድብ ጨዋታዎቹ ሁለቱን በቡታሬ ከተማ በሚገኘው ሁዬ ስታድዬም፤ እንዲሁም የመጨረሻውን ጨዋታ በዋና ከተማ ኪጋሊ በሚገኘው አማሃሮ ስታድዬም እንደሚጫወቱ ታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን  ከምድብ ተጋጣሚዎቹ በተለያዩ ውድድሮች በመገናኘት ያን ያህል የሰፋ ልምድ አለመኖሩን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን  ከካሜሮን ጋር  በ1970 እኤአ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ተገናኝቶ 3ለ2 እንዲሁም ከዲ.ሪ ኮንጎ ጋር ደግሞ በ2000 እኤአ በኢንተርናሽናል ጨዋታ ተገናኝቶ 1ለ0 በሆኑ ውጤቶች ተሸንፏል፡፡  ከአንጎላ ጋር ግን በብሄራዊ በድን ደረጃ ተገናኝቶ አያውቅም፡፡
ከ‹‹ቻን 2016›› በፊት በደቡብ አፍሪካ ዝግጅታቸውን እያካሄዱ ካሉ አገራት ናይጄርያ፤ አንጎላና አይቬሪኮስት ይገኙበታል፡፡ ከዝግጅት ባሻገር የአቋም መፈተሻ ግጥሚያዎቻቸውንም የሚያደርጉ ይሆናል፡፡ ከምድብ 2 ቡድኖች ዲ .ሪ. ኮንጎ ባለፈው ማክሰኞ  የቡድን ስብስብ  ያስታወቀች ሲሆን  ከኤኤስ ቪታ ክለብ 11 ከስኬታማው ቲፒ ማዜምቤ ደግሞ 4 ተጨዋቾች እንደተመረጡ ተገልጿል፡፡ ዲ .ሪ. ኮንጎ ከአዘጋጇ ሩዋንዳ ጋር ታህሳስ 27 ላይ የወዳጅነት ጨዋታ እንደምታደርግም ታውቋል፡፡ በደቡብ አፍሪካ የቻን ዝግጅቷን  ከጀመረች ሳምንት ያለፋት አንጎላ  ከውድድሩ በፊት ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎች ለማካሄድ እቅድ ይዛለች፡፡ የመጀመርያው ለዝግጅት እዚያ ደቡብ አፍሪካ ከሚገኘው የናይጄርያ ቡድን ጋር የሚደረግ ሲሆን በተጨማሪ ሁለተኛ የአቋም መፈተሻ ግጥሚያ  ምናልባትም ከአይቬሪኮስት ወይም ደቡብ አፍሪካ አንዳቸውን ልትገጥም እንደምትችል ተዘግቧል፡፡  በምድብ 2 ከፍተኛ ግምት የተሰጠው የካሜሮን ቡድንም ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎችን  ከኒጀር እና ጋቦን  እንደሚያደርግም ተገልጿል፡፡
ሩዋንዳ ‹‹ቻን 2016›› በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ እስከ 1.1 ቢሊዮን ዶላር ማውጣቷን ያመለከቱ ዘገባዎች ፤ 571 ሚሊዮን ዶላር በአጠቃላይ ለውድድሩ ማካሄጃ የተመደበው በጀት እንደሆነ በሆቴሎች፤ በስታድዬም ግንባታ እና እድሳቶች እንዲሁም ሌሎች መሰረተልማቶች ተጨማሪ 570 ሚሊዮን ዶላር ወጭ መደረጉን አትተዋል፡፡  በሶስት የተለያዩ ከተሞች በሚገኙ 4 ስታድዬሞች ውድድሩን እንደሚስተናግዱ ሲጠበቅ፤ አሰትናጋጆቹ ከተሞች ዋና ከተማዋ ኪጋሊ ፤ ምእራባዊዋ የሩባቩ ከተማ እንዲሁም ሌላው ደግሞ ደቡባዊቷ ቡታሬ ከተማ ናቸው፡፡ በኪጋሊ ከተማ ያሉት ሁለቱ ስታድዬሞች 30ሺ የሚያስተናግደው አማሃሮ እና 22ሺ የሚያስተናግደው ኒያሚራምቦ ሲሆኑ በቡታሬ ከተማ 20ሺ የሚያስተናገደው ሁዬ እና 5ሺ የሚያስተናግደው ኡሙጋንዳ ስታድዬሞች ናቸው፡፡
በቻን ውድድር ላይ በመሳተፍ ከሽልማት ገንዘብ ባሻገር ብዙ ጠቀሜታዎች ይኖሩታል፡፡ በሻምፒዮናው የሚመዘገብ ውጤት በፊፋ ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃ ነጥብ ማስገኘቱ፤ ዋና ብሄራዊ ቡድንን ማጠናከሩ፤ ለታዳጊ ተጨዋቾች የውድድር እድል መፍጠሩ እንዲሁም የየአገሩ ሊጎች ተጨዋቾችን በማሳተፍ የሚኖረው አስተዋፅኦ ዋና ዋና ጠቀሜታዎቹ ናቸው፡፡ የሻምፒዮናው ሁሉም ጨዋታዎች በዲኤስቲቪ የቀጥታ ስርጭት ማግኘታቸውም ሌላው ጥቅም ሲሆን በተለይ በአፍሪካ ትልልቅ ሊግ ውድድሮች ተሳታፊ ለሆኑ ክለቦች የሚሰሩ በርካታ የተጨዋች መልማዮች በቻን ውድድር በብዛት መኖራቸውም ለወጣት ተጨዋቾች ማደግ ከፍተኛ እድሎችን ይፈጥራል፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ለሻምፒዮናው 3.2 ሚሊዮን ዶላር የሽልማት ገንዘብ ያቀረበ ሲሆንት ሻምፒዮን ቡድን 700 ሺ ዶላር፤ ለሁለተኛ ደረጃ 400ሺ ዶላር፤ ለደረጃ የሚጫወቱ ሁለት ቡድኖች እያንዳንዳቸው 250ሺ ዶላር፤ በሩብ ፍፃሜ የወደቁ አራት ቡድኖች እያንዳንዳቸው 175ሺ ዶላር፤ በምድባቸው 3ኛ ደረጃ ያገኙ 125ሺ ዶላር እንዲሁም በየምድባቸው አራተኛ ደረጃ ይዘው የጨረሱ ቡድኖች እያንዳንዳቸው 100ሺ ዶላር እንደሚከፈላቸው ታውቋል፡፡
በ2014 እኤአ ላይ በደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅነት በተካሄደው 3ኛው የቻን ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ ስትሳተፍ በምድብ 3 ከጋና፤ ከሊቢያ እና ከኮንጎ ጋር ተደልድላ ነበር፡፡ በወቅቱ ዋልያዎቹ በዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እየተመሩ በምድባቸው ያደረጓቸውን 3 ጨዋታዎች በሙሉ ተሸንፈው በ4 የግብ እዳ ያለምንም ነጥብ ከውድድሩ ሲሰናበቱ በአንድ ምድብ የነበሩት ጋና እና ሊቢያ ለዋንጫ መድረሳቸውና በቻን 2016 የማትሳተፈው ሊቢያ ሻምፒዮን ለመሆን መብቃቷ ይታወሳል፡፡
በሩዋንዳ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የ2016 የቻን አፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን  30 ተጫዋቾች ጥሪ ተደርጓል አዲስ  የሚካተቱ እና የሚቀነሱም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ይፋ ባደረገው ዝርዝር መሰረት
ግብ ጠባቂዎች ታሪክ ጌትነት (ደደቢት)፤ አቤል ማሞ (ሙገር)፤ ይድነቃቸው ኪዳኔ(መከላከያ)  ፤ ለአለም ብርሃኑ(ሲዳማ ቡና)
ተከላካዮች ስዩም ተስፋዬ (ደደቢት)፤ አሉላ ግርማ (ቅ/ጊዮርጊስ)፤ ተካልኝ ደጀኔ (ደደቢት)፤ ዘካሪያስ ቱጂ (ቅ/ጊዮርጊስ)፤ ሱለይማን መሀመድ (አዳማ)፤ አስቻለው ታመነ (ቅ/ጊዮርጊስ)፤ አንተነህ ተስፋዬ (ሲዳማ ቡና)፤ ያሬድ ባዬህ (ዳሽን)፤ ሞገስ ታደሰ (አዳማ)፤ ወንድይፍራው ጌታሁን (ኢ/ቡና)
አማካዮች ጋቶች ፓኖም (ኢ/ቡና)፤ አስራት መገርሳ (ዳሽን)፤ ተስፋዬ አለባቸው (ቅ/ጊዮርጊስ)፤ ቢኒያም በላይ (ኢ/ን/ባንክ)፤ ፍሬው ሰለሞን (መከላከያ)፤ ታደለ መንገሻ (አ/ምንጭ)፤ በሀይሉ አሰፋ (ቅ/ጊዮርጊስ)፤ ራምኬል ሎክ (ቅ/ጊዮርጊስ)፤ ታፈሰ ሰለሞን (ሀዋሳ)
አጥቂዎች ሳምሶን ጥላሁን (ደደቢት)፤ ኤሊያስ ማሞ (ኢ/ቡና)፤ ዳዊት ፍቃዱ (ደደቢት)፤ ታፈሰ ተስፋዬ (አዳማ)፤ ሙሉአለም ጥላሁን (መከላከያ)፤ ሚካኤል ጆርጅ (አዳማ)፤ ቡልቻ ሹራ (አዳማ)
ስለ ምድብ 2 ተጨማሪ መረጃዎች
ኢትዮጵያ
በቻን ውድድር የምትሳተፈው ለ2ኛ ጊዜ ነው፡፡  
ዋና አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ
የፊፋ የእግር ኳስ ደረጃ 114ኛ  ከዓለም
የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ 10 ጊዜ 1 ጊዜ አሸናፊ በ1962 እኤአ
ዲ.ሪ. ኮንጎ
በቻን ውድድር የምትሳተፈው ለ4ኛ ጊዜ ነው፡፡ በ2009 ሻምፒዮን
ቅፅል ስማቸው ዘ ሊዮፓርድስ
ዋና አሰልጣኝ ፍሎረንት ኢባንጌ
የፊፋ የእግር ኳስ ደረጃ 55ኛ ከዓለም
የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ 1 ጊዜ በ1974 እኤአ
የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ 15 ጊዜ 2 ጊዜ አሸናፊ በ1968 እና በ1974 እኤአ
አንጎላ
በቻን ውድድር የምትሳተፈው ለ2ኛ ጊዜ ነው፡፡ በ2011 2ኛ ደረጃ
ቅፅል ስማቸው ሳቢሌ አንቲሎፕስ
ዋና አሰልጣኝ ሮሚዮ ፍሌሞን
የፊፋ የእግር ኳስ ደረጃ 98ኛ ከዓለም
የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ 1 ጊዜ በ2006 እኤአ
የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ 7
ካሜሮን
በቻን ውድድር የምትሳተፈው ለ2ኛ ጊዜ ነው፡፡ በ2011 ሩብ ፍፃሜ
ቅፅል ስማቸው የማይበገሩት አንበሶች
ዋና አሰልጣኝ አሌክሳንደር ቤሊንጋ ጊዜያዊ
የፊፋ የእግር ኳስ ደረጃ 51ኛ ከዓለም
የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ 7 ጊዜ
የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ 16 አሸናፊ 4 ጊዜ 1984፤ 1988፤ 2000 እና 2002 እኤአ

Read 3295 times