Tuesday, 29 December 2015 07:52

የድረ-ገጽ ቴክኖሎጂ ከተፈጠረ 25 አመት ሞላው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የአለማችን የመጀመሪያው ድረ-ገጽ አሁንም በስራ ላይ ነው


የድረ-ገጽ ቴክኖሎጂ ከተጀመረ ተግባራዊ ከሆነና “ቲም በርነርስ ሊስ ወርልድ ዋይድ ዌብ” የተባለው የአለማችን የመጀመሪያው ድረ-ገጽ ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ በዚህ ሳምንት 25 አመት እንደሞላው ዘ ቴሌግራፍ ከትናንት በስቲያ ዘገበ፡፡
ቲም በርነርስ ሊ የተባሉት እንግሊዛዊ የኮምፒዩተር ሳይንቲስት እ.ኤ.አ ታህሳስ 20 ቀን 1990 የአለማችንን የመጀመሪያ ድረ-ገጽ እንደፈጠሩ ያስታወሰው ዘገባው፣ በዚያው አመት ነሃሴ ወር ላይ ስራ የጀመረው ድረ-ገጹ አሁንም ድረስ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጧል፡፡
በወቅቱ የአውሮፓ የኒውክሌር ምርምር ተቋም (CERN) ተመራማሪ የነበሩት ሳይንቲስቱ፤ የፈጠሩት “ቲም በርነርስ ሊስ ወርልድ ዋይድ ዌብ” የተባለው ድረ-ገጽ info.cern.ch የሚል አድራሻ ያለው ሲሆን፣ ለተጠቃሚዎች ከድረ-ገጽ ጋር በተያያዘ መሰረታዊ መረጃዎችን የሚሰጥ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
የድረ-ገጽ ቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለፉት 25 አመታት እጅግ እየተሻሻለና አሰራሩንም ሆነ አቅሙን እያሳደገ መቀጠሉን ዘገባው አስታውሶ፣ ሳይንቲስቱ አሁንም በዘርፉ እየሰሩ እንደሚገኙና የወርልድ ዋይድ ዌብ ማህበርን እየመሩ እንደሆነ ገልጿል፡፡

Read 1526 times