Tuesday, 29 December 2015 07:50

በዚህ አመት ብቻ ከ1 ሚ. በላይ ስደተኞች አውሮፓ ገብተዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከ3 ሺህ በላይ ስደተኞች ባህር ሲያቋርጡ ሞተዋል


    ሊጠናቀቅ የቀናት ዕድሜ በቀሩት የፈረንጆች 2015 ዓ.ም ብቻ ከ1 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ አገራት ስደተኞች ወደ አውሮፓ መግባታቸውንና 3 ሺህ 700 የሚሆኑትም ሜዲትራኒያን ባህርን ለማቋረጥ ሲሞክሩ ለሞት መዳረጋቸውን አለማቀፉ የስደተኞች ድርጅት ማስታወቁን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
እስካለፈው ሰኞ ድረስ በአመቱ ወደ አውሮፓ የገቡ ስደተኞች ቁጥር 1 ሚሊዮን 5ሺህ 54 መድረሱን የጠቆመው ዘገባው፣ ይህም ቁጥር ባለፈው አመት ከተመዘገበው ከአራት ዕጥፍ በላይ ማደጉን ያመለክታል ብሏል፡፡
በአመቱ ከ455 ሺህ በላይ ሶርያውያንና ከ186 ሺህ የሚልቁ አፍጋኒስታናውያንን ጨምሮ ከ800 ሺህ በላይ ስደተኞች ከቱርክ ወደ ግሪክ መግባታቸውን ያስታወቀው የአለማቀፉ የስደተኞች ድርጅት፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ስደተኞችም ወደ አውሮፓ ለመግባት እየተቃረቡ ነው ብሏል፡፡
በጦርነት ሳቢያ አገራቸውን ጥለው የሚሰደዱና ከመኖሪያቸው የሚፈናቀሉ ሰዎች ቁጥርም በዘንድሮው አመት ከ60 ሚሊዮን በላይ መድረሱን ያስታወቀው ድርጅቱ፣ በመጀመሪያዎቹ የአመቱ ወራት ብቻ 839 ሺህ ሰዎች አለማቀፍ ድንበሮችን አቋርጠው ወደ ሌሎች አገራት መሰደዳቸውንና አንድ ሶስተኛ ያህሉም ሶርያውያን መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡
በዘንድሮው አመት በአለማችን ከ122 ሰዎች አንዱ በጦርነት ሳቢያ ከመኖሪያ አካባቢው እንደሚፈናቀል ወይም ወደ ሌሎች አገራት እንደሚሰደድ ድርጅቱ አክሎ ገልጧል፡፡

Read 1567 times