Saturday, 02 January 2016 12:06

የገና ስጦታ

Written by  ደራሲ፡- ኦ. ሄንሪ ተርጓሚ፡- አሸናፊ አሰፋ
Rate this item
(8 votes)

        አንድ ዶላር ከሰማንያ ሰባት ሳንቲም፡፡ በቃ፡፡ ስድሳ ሳንቲሙ፣ በአንድ፣ በአንድ ሳንቲም ነው፡፡ አንድ፣ ሁለት፣ … እየተባሉ የተቆጠቡ ስድሳ ሳንቲሞች፡፡ በእንዴት ያለ ስቃይና መከራ እንደተቆጠቡ ዝም ይሻል ነበር፡፡ ይሉኝታ ባጣ ሁኔታ፣ ድርቅ ብላ ከባለ ግሮሰሪው፣ ከአትክልት ነጋዴው፣ ከስጋ ሻጩ ጋር ለጉድ እየተከራከረች ያዳነቻቸው ናቸው፡፡ የዋጋ ድርድር አይባልም፡፡ ንጥቂያ ነው፡፡ ከእጃቸው ፈልቅቆ የመውሰድ አይነት ነበር፡፡ በፀጥታ ቆንቋናነቷን ሲጸየፉ አስተውላለች፡፡ ትዝብታቸውን ስታይ ፊቷ ፍም ይመስል ነበር፡፡ ፊቷ ይቃጠል ነበር። ዴላ ገንዘቡን ቆጠረች፡፡ አንድ ዶላር ከሰማንያ ሰባት ሳንቲም። ዳግም ቆጠረች፡፡ አንድ ዶላር ከሰማንያ ሰባት ሳንቲም፡፡ ሶስተኛ ቆጠረች፡፡ አንድ ዶላር ከሰማንያ ሰባት ሳንቲም፡፡ ነገ የገና በዓል ነው፡፡
ምን ማድረግ ይቻላል? ግልፅ ነው ምንም፡፡ እንዲያው ምንም? አዎ፡፡ በቃ ምንም! አሮጌው ፍራሽ ላይ ዥው ብሎ፣ በደረት ተደፍቶ፣ ተንሰቅስቆ ማልቀስ ይቻላል። እሱ አያቅትም፡፡ እሱን ማንም አይከለክልም፡፡ ዴላ አሮጌው ፍራሽ ላይ ተደፍታ አነባች፡፡ እንባዋ ብቻውን አልመጣም፤ የምርምር ሀሳብ ይዞ ነው የመጣው፡፡ ህይወት ምንድናት? ህይወት ስሪቷ ከምንድነው? በጣም ቀላል ጥያቄ ነው፡፡ ህይወት የተሰራችው ከሶስት ነገሮች ነው፡፡ ለቅሶ- አንድ፡፡ ሳግ- ሁለት፡፡ ሳቅ- ሶስት፡፡ ማስታወሻ፡- ሳግ እጅጉን ድርሻ ይይዛል፡፡
እመቤቲቱ ከአንደኛው ወደ ሁለተኛው እስክትሸጋገር ያለችበትን ቤት እንቃኘው፡፡ ቤቱ፣ ከእነ ሙሉ እቃው፣ በሳምንት ስምንት ዶላር ኪራይ ይከፈልበታል፡፡ አንዳንድ ነገሮች ገለፃ አያስፈልጋቸውም፡፡ እንዲሁ ያስታውቃሉ። የመናጢ ደሀ ጎጆም ገለፃ አያስፈልገውም፡፡ እራሱ ጮሆ ይናገራል፡፡ ስታዩት የኔቢጤ ምናምን የሚል ቃል ይመጣባችኋል፡፡
ታች መተላለፊያው ላይ ዘመኑን ሙሉ ደብዳቤ ሲናፍቀው የሚኖር የፖስታ ሳጥን አለ፡፡ ሁሌም ደብዳቤ እንደተራበ ነው፡፡ በኤሌክትሪክ የሚሰራ የመጥሪያ ደውልም አለ፡፡ ችግሩ ግን አይደለም ማንም ተራ ሰው እኔ ነኝ ያለ አስማተኛ ቢመጣ ድምፅ እንዲወጣው ማድረግ አይችልም፡፡ ሌላም ወግ አለ፡፡ እዚያው ግድም፡- “አቶ ጀምስ ዲሊንግሀም ያንግ” የሚል ስም የተፃፈበት ካርድ ተንጠልጥሏል፡፡ “ዲሊንግሀም” የሚለው ስም ንፋስ ላይ የተሰጣው በደጉ ዘመን ነበር፡፡ ያኔ የባለጠግነት ጊዜ ነበር። ያኔ ተከራዩ ገቢው ወፈር ያለ ነበር፡፡ ያኔ የስሙ ባለቤት፣ በሳምንት ሰላሳ ዶላር ገቢ ነበረው፡፡ አሁን ገቢው ከስታ ሀያ ዶላር ሆናለች፡፡ ፊደላቱ ነቄ ነገር ናቸው፡፡ ወቅታዊ ሁኔታውን ያገናዘበ እርምጃ ወሰዱ፡፡ ደበዘዙ፡፡ ቁጠባ ያስፈልጋል፡፡ ዲሊንግሀም ረዥም ስም ነው፡፡ ይህ ሁሉ ፊደል ምንም አያደርግም፡፡ ብክነት ነው፡፡ “ዲ” ይበቃል፡፡ እንደድሮው ‘የማይጮህ’፣ ዝም ያለ፣ ትሁት “ዲ”፡፡ ደግነቱ ሁሌም አቶ ጀምስ ዲሊንግሀም ያንግ ደረጃዎቹን ወጥቶ፣ ክፍሉ ሲደርስ “ጂም” በሚል ቁልምጫ፣ በጥዑም ድምፅ፣ ወይዘሮ ጀምስ ዲሊንግሀም ያንግ ትቀበለዋለች፡፡ ይህ ብቻ መሰላችሁ? በፍቅር ትጠመጠምበታለች፡፡ ዴላ ስንል የነበረው እሷን ነው፡፡
ዴላ አልቅሳ አበቃች፡፡ ጉንጮቿን ፓውደር ባለው የፊት ማበሺያ አባበሰቻቸው፡፡ መስኮቱ ጋ ፍዝዝ ብላ ቆማለች፡፡ ግራጫ ድመት፣ ግራጫ ጓሮ ውስጥ፣ ግራጫ አጥር ላይ ሲሄድ ተመለከተች፡፡ ነገ የገና በዓል ነው። ለጂም ስጦታ መግዛት አለባት፡፡ ያላት አንድ ዶላር ከሰማንያ ሰባት ሳንቲም ብቻ ነው፡፡ ለአያሌ ወራት አንጀቷን አስራ ስትቆጥብ ከርማለች፡፡ ያስመዘገበችው ስኬት ይህቺው ናት፡፡ በሳምንት የሀያ ዶላር ገቢ የትም አያደርስም፡፡ ሰቀቀን ነው፡፡ ወጪዋ ከጠበቀችው በላይ ነው የሆነው፡፡ ድሮውንስ ወጪ የተጠበቀውን ያህል ወይም ከተጠበቀው በታች መች ሆኖ ያውቃል። ወጪ ሁሌም ከተጠበቀው በላይ ነው የሚሆነው። ለጂም፣ ለእሷ ጂም ምን አይነት እፁብ ድንቅ ስጦታ እንደምትገዛለት ስታወጣ፣ ስታወርድ፣ እቅድ ስትነድፍ ጣፋጭ የሀሴት ጊዜያት አሳልፋለች፡፡ የምትገዛለት ስጦታ አሪፍ፣ ብርቅና ምርጥ መሆን አለበት፡፡ ጂምን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል፡፡
በክፍሉ መስኮቶች መሀል ያለው ቦታ ቀጭን፣ ረዥም የመስታወት ግድግዳ ነው፡፡ አንዳንዴ በሳምንት ስምንት ዶላር የሚከፈልባቸው፣ ግድግዳቸው መስታወት የሆኑ ቤቶች አሉ፡፡ አጋጥሟችሁ አያውቅም? ከስንት አንድ አሉላችሁ፡፡ መስታወቱ እኮ ዝም ብሎ ጠርሙስ ነው። ቀጭንና ቀልጣፋ ሰው፣ በእንዲህ አይነት መስታወት፣ ፊቱን በፍጥነት ወዝወዝ፣ ሸርተት እያደረገ በአግድሙ የመስታወቱ ሰንበሮች ውስጥ ለመልኩ የቀረበ ምስል ሊያይ ይችላል፡፡ ዴላ ለግላጋ ስለሆነች ጥበቡን ተክናበታለች፡፡
ድንገት ከመስኮቱ ጋ ሽርር ብላ መስታወቱ ፊት ቆመች፡፡ አይኖቿ አሁንም ብሩህና አንፀባራቂ ናቸው፡፡ ፊቷ ግን በሀያ ሰከንዶች ቀለሙ ከድቶታል፡፡ እየተቻኮለች ፀጉሯን ፈትታ ቁልቁል ለቀቀችው፡፡
ጥንዶቹ ጀምስ ዲሊንግሀም ያንጎች እኩያ የሌለው ክብር እንዲሰማቸው የሚያደርጓቸው ሁለት ንብረቶች አሏቸው፡፡ አንደኛው ጂም ከአባቱ የወረሰው የወርቅ ሰዓት ነው፡፡ የጂም አባትም ከአባቱ የወረሰው ነበር። ሌላኛው የዴላ ጸጉር ነው፡፡ ንግስት ሳባ የምትኖረው አፓርታማቸው ውስጥ ለአየር ማንሸራሸሪያ የተተወው ቦታ ጋ ቢሆን ኖሮ፣ ዴላ ሆን ብላ ጸጉሯን አጥባ እንደዋዛ መስኮታቸው ላይ ታሰጣውና የንግስቲቱ ማጌጫዎችና ውድ ስጦታዎች ሁሉ ምን ያህል ተራና ርካሽ እንደሆኑ ለአለም ሁሉ ታሳይ ነበር፡፡ ከንቱነታቸውን ታሳብቅባቸው ነበር፡፡ ንጉስ ሰለሞን የፅዳት ሰራተኛቸው ቢሆንና በምድር ያለው ሀብቱ ሁሉ ምድር ቤታቸው ቢቆለል፣ ጂም ሲወጣ ሲገባ የኪስ ሰዓቱን ወጣ እያደረገ በቄንጥ ያያል፡፡ ምስኪኑ የፅዳት ሰራተኛ በቅናት ይንጨረጨራል። ጺሙን በንዴት ይነጫል፡፡ ሲያሳዝን፡፡
ነገሩ እንዲያ ነበር፡፡ ምን ያደርጋል ታዲያ?
የዴላ ውብ ፀጉር፣ እየተዘናፈለ፣ አንፀባራቂ ቡኒ ፏፏቴ መስሎ ከአናቷ ቁልቁል ፈሰሰ፡፡ ረዥም ነው፡፡ ከጉልበቶቿ በታች ዋለ፡፡ ካባ ሆናት፡፡ ስታውርደውም በችኮላ ነበር። እየተርበተበተች በችኮላ ጠቀለለችው፡፡ ለአንድ ደቂቃ ውዝግብግብ አለችና ቀጥ ብላ ቆመች፡፡ የእንባ ዘለላዎች ያረጀው ቀይ ምንጣፍ ላይ ተፈጠፈጡ፡፡
ከዚያ ምን አደረገች? አሮጌ ቡኒ ጃኬቷን ለበሰች። አሮጌ ቡኒ ኮፍያዋን አደረገች፡፡ አይኖቿ እያበሩ ጉርድ ቀሚሷ ውስጥ ገባች፡፡ ሽው ብላ በበሩ ወጣች፡፡ እየበረረች ደረጃዎቹን ወረደች፡፡ ይኸው መንገድ፡፡ ሄደች፡፡
ቆመች፡፡
የቆመችበት ቦታ እንዲህ የሚል ፅሁፍ ይነበባል፡- “ወይዘሮ ስፍሆኒ፡፡ ፀጉር፡፡ ሁሉንም አይነት ነገሮች፡፡” በሩጫ ወደ አንደኛ ፎቅ ወጣች፡፡ ትንፋሽ ለመሰብሰብ ቆመች፡፡ እያለከለከች ነበር፡፡ ወይዘሮዋ ግብዳ ናት። ንጣቷ አይነገርም፡፡ የሞት ያህል ቀዝቃዛ ናት፡፡ ስሟ እንደሚጠቁመው የውጪ ሀገር ዜጋ አትመስልም፡፡
“ፀጉሬን ትገዢኛለሽ?” ዴላ ናት፡፡
“ፀጉር እገዛለሁ፡፡” አለች ሴትዮዋ “በመጀመሪያ ኮፍያሽን አውልቂና ምን እንደሚመስል እንየው፡፡”
ሚጢጢ፣ ቡኒ ፏፏቴ ቁልቁል ፈሰሰ፡፡ ፏ አለ፡፡
“ሀያ ዶላር፡፡” ሴትዮዪቱ በሰለጠኑ እጆቿ ክምሩን አፈሰችው፡፡
“ወዲህ በይ ቶሎ፡፡”
ቀጣዮቹን ሁለት ሰዓታት በአበባ ክንፎቿ በረረቻቸው። ተላምጦ ለዛውን ያጣ አባባል ነው አይደል? እርሱት። ለጂም የሚሆን ስጦታ ፍለጋ መደብሮቹን ሁሉ ምስቅልቅላቸውን አወጣችው፡፡ አገኘች፡፡
ይገርማል፡፡ ሆን ተብሎ ለጂም የተሰራ ነው የሚመስለው፡፡ የትኛውም መደብር ውስጥ ይህን መሳይ ዕቃ አላየችም፡፡ ከፕላቲኒየም የተሰራ የኪስ ሰዓት ማሰሪያ ጌጥ ነው፡፡ ዲዛይኑ ቀላልና ፀዳ  ያለ ነው። ግርግር የለውም፡፡ ለማሳመር በሚደረግ ቀሽም ጥረት፣ በጌጣጌጦች ኮተትና ጋጋታ አልተጨናነቀም፡፡ ምርጥ ዕቃ መሆኑን እራሱ እንዲናገር ነው የተተወው፡፡ አሪፍ እቃዎች ሁሌም እንዲያ ናቸው፡፡ ወላ የጂምን ሰዓት ይመጥናል። እንዳየችው የጂም መሆን እንዳለበት ወሰነች፡፡ ጂምና ይኼ የሰዓት ማሰሪያ ይመሳሰላሉ፡፡ ስክነትና እርባና ያለው የሚሉት ቃላት ሁለቱንም ይገልጻሉ፡፡ ሀያ አንድ ዶላር አስከፈሏት፡፡ ሰማንያ ሰባት ሳንቲሟን ቆንጥጣ ወደ ቤቷ ሮጠች፡፡ ይህ ሰንሰለት የጂም ሰዓት ላይ ከታሰረ በኋላ ጂም በየቅፅበቱ ሰዓት ስንት እንደሆነ እያሳሰበው መጨነቁ አይቀርም፡፡ ግልፅ ነው፡፡ አይፈረድበትም፡፡ ታዲያ ምን ችግር አለው? በእየአንዳንዷ የሰከንድ ክፍልፋይ፣ ሰዓቱን ከኪሱ መዥረጥ እያደረገ ማፍጠጥ ነዋ፡፡ ‘በፊት’፣ ‘ድሮ ድሮ’፣ በአሮጌውና ጎማዳ የሰዓቱ፣ የጠፍር ማሰሪያ እያፈረ ያን መሳይ ሞገስ ያለው ሰዓት፣ ሰው ፊት አውጥቶ ማየት ይሸማቀቅ ነበር፡፡ በሾርኒ ነበር ሰዓት የሚያየው፡፡
ዴላ ቤቷ ስትደርስ፣ ደስታዋ ያመጣው እልል ያለ ስካር ለቀቅ አደረጋት፡፡ ከጡዘቷ ሰከን አለች፡፡ ቀልብ ገዛች፡፡ ጥንቁቅና የምክንያት ሰው ሆነች፡፡ ከርል መስሪያ ብረቷን አወጣች፡፡ ጋዙን ለኮሰች፡፡ ፍቅርና ቸርነት ተባብረው ያመሳቀሉትን ቤት ማስተካከል ያዘች፡፡ ወዳጆቼ ቀላል ስራ እንዳይመስላችሁ፡፡ እጅግ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው፡፡
በአርባ ደቂቃዎች ውስጥ እራሷ በጣም በተጠጋጉ ከርሎች ተሸፈነ፡፡ አሪፍ ፍንዳታ ተማሪ መሰለች፡፡ ምስሏን በመስታወት ተመለከተች፡፡ ዘለግ ላለ ጊዜ፣ በጥንቃቄ አጠናችው፡፡
“ጂም አይቶኝ ካልገደልኩሽ ካላለና ካልሞትኩኝ ‘የፌዝ ደሴት ላይ የሚኖሩ ፎጋሪና አሿፊ የመዝሙር ጓድ አባል ትመሲያለሽ’ ሲል መስማቴ አይቀርም፡፡ ምን ማድረግ እችል ነበር ታዲያ ? በአንድ ዶላር ከሰማኒያ ሰባት ሳንቲም ምን አባቴ ማድረግ እችል ነበር?”
አንድ ሰዓት ላይ ቡናቸውን አፍልታ አሰናድታለች፡፡ መጥበሻው ግሎ የተከተፈውን ስጋ እየጠበቀ ነው፡፡
ጂም አርፍዶ አያውቅም፡፡ ዴላ የሰዓት ማሰሪያውን አጥፋ በጭብጧ ያዘችና ጂም በሚገባበት በኩል፣ የጠረጼዛው ጫፍ ጋ ቁጭ፣ ድብቅ አለች፡፡ ታች የመጀመሪያውን ደረጃ ሲረግጥ ኮቴው ተሰማት፡፡ ለአፍታ ነጭ ሆነች፡፡ ሁልጊዜ ለሚረባውም ለማይረባውም ጥቃቅን ጉዳይ ፀሎት የማድረግ ልምድ አላት፡፡ አሁንም ፀለየች፡- “አምላክ ሆይ አደራህን፣ አሁንም ቆንጂዬ ናት ብሎ እንዲያስብ አድርገው፡፡”
ጂም ገባና በሩን ዘጋው፡፡ ክስት ነገር ብሏል፡፡ ተኮሳትሯል፡፡ ምስኪን ልጅ፤ ገና ሀያ አመቱ ነው፡፡ በዚህ ባልጠና ትከሻው ላይ የቤተሰብ ሀላፊነት የሚባል ነገር ተሸክሟል፡፡ አዲስ ካፖርት መግዛት አለበት፡፡ የእጅ ጓንት ደሞ የለውም፡፡
ጂም ጅግራ እንዳሸተተ ውሻ የማይበገር ሆኖ ቆመ። አይኖቹ ዴላ ላይ ተሰክተዋል፡፡ አይኖቹ  አንዳች ነገር እያሉ ነው፡፡ ምን እንደሚሉ ግን ዴላ ማወቅ አልቻለችም። ተሸበረች፡፡ አይኖቹ ውስጥ ያለው ንዴት አይደለም፡፡ መደነቅ አይደለም፡፡ ማንኳሰስ አይደለም፡፡ ድንጋጤም አይደለም፡፡ ይከሰታሉ ብላ ላሰበቻቸው ስሜቶች ሁሉ ተዘጋጅታ ነበር፡፡ አሁን ጂም ላይ የሚታየውን ስሜት አታውቀውም፡፡ እንግዳ ነው፡፡ እንዲሁ ብቻ፣ እንደዋዛ፣ ባእድ ስሜት ፊቱ ላይ ሰፍቶ፣ ለአፍታም አይኖቹን ሳይነቅል አያት፡፡
ጠረጴዛውን ወዲያ ገለል አድርጋ ወደ ጂም ሄደች፡፡
“ጂም የኔ ወድ፣ ስሞትልህ እንደሱ አትየኝ፡፡ ስጦታ ሳላበረክትልህ ገና እንዲያልፍ አልፈለግሁም፡፡ ጸጉሬን ሸጥኩት፡፡ ቆርጠው ወሰዱት፡፡ ቅር አለህ እንዴ? ይህቺን ታህል ቅር እንዳይልህ፡፡ ተመልሶ ያድጋል፡፡ ጸጉሬ ደሞ ሞኝ ነው፤ ቶሎ ያድጋል፡፡ ‘መልካም ገና’ በለኝ ጂም፡፡ ደስ ይበልህ፡፡ ደስ ይበለኝ፡፡ እንደሰት፡፡ ምን አይነት ምርጥ ስጦታ እንደገዛሁልህ ባወቅህ ኖሮ፡፡ እንዴት እንደሚያምር አላየህም፡፡”
“ጸጉርሽን አስቆረጥሽ?” አለ በስንት ትግል፡፡ ቃላቶቹን እያማጠ ነው የወለዳቸው፡፡ እስካሁን ተክዞ፣ ይህን ሁሉ መንገድ በሃሳብ ተጉዞ፣ እልም ያለ ቀዝቃዛና ደረቅ ሀቁ ላይ መድረስ አቅቶታል፡፡
“ምን መቁረጥ ብቻ፤ ሸጥኩትም እንጂ፡፡ ልክ እንደ ድሮው አትወደኝም አሁን? ጸጉሬ ኖረ አልኖረ፣ ፊትም ዴላ አሁንም ዴላ ነኝ፡፡ አይደለሁም  እንዴ?”
ጂም ቤቱን በጉጉት ቃኘው፡፡
“ጸጉርሽ በቃ፣ ሄዶዋል ነው ያልሽኝ?” አሁን አንድያውን ተጃጅሏል፡፡ አጠያየቁ ውስጥ ቂልነት አለ፡፡
“አትፈልገው፤ የለም፤ ሄዶዋል፡፡ ተሸጧል፡፡ አንተ ልጅ፣ የገና ዋዜማ እኮ ነው፡፡ አሁን አሪፍ ልጅ ሁንልኝ፡፡ ላንተ ተብሎ ነው የተሸጠው እሺ፡፡ በእራሴ ላይ የነበሩት ጸጉሮች ሊቆጠሩ ይችል ይሆናል…” አለች ድንገት፣ በሚያምር ሁኔታ ኩስትር ብላ፡- “ላንተ ያለኝ ፍቅር ግን አይቆጠርም፡፡ ጂም ስጋውን መጥበሻው ላይ ላድርገው?”
ጂም ነቃ፡፡ ከሄደበት ውሉ የማይታወቅ የመንፈስ አለም ድንገት ተመለሰ፡፡ ዴላን እቅፍ አደረጋት፡፡
እንዴት ነው ለአንድ ለአስር ሰከንድ ተወት እናድርጋቸው አይደል? የጨዋ ደንብ ነው፡፡ አይናችን ማረፊያ አጣ ልበል? በሌላኛው ወገን ያሉትን የቤቱን እቃዎች እንቃኝ፡፡ ለቤት ኪራይ በሳምንት ስምንት ዶላር ከፈልክ፣ ወይም በአመት አንድ ሚሊዮን ዶላር ከፈልክ ምንድነው ለውጡ? የትኛውንም የሂሳብ ሊቅ ጠይቅ፣ አለ የተባለውን የጥበብ አዋቂ አማክር፡፡ የተሳሳተ መልስ ነው የሚነግሩህ፡፡ ተሸውደው ይሸውዱሀል፡፡ ሰብአ ሰገሎች አቻ የሌለው ስጦታ ይሰጣሉ፡፡ ለዚህች ጥያቄ የሚሆን መልስ ግን የላቸውም፡፡ ጨለምተኛ ድምዳሜ መሰለ እንዴ? በኋላ እናብራራዋለን፡፡
ጂም ከካፖርት ኪሱ የታሸገ ነገር አወጣና ጠረጼዛው ላይ ወረወረው፡፡
“ዴል ስለ እኔ ፈፅሞ እንዳትሳሳቺ፡፡ ጸጉር መቆረጥ በይ፣ መላጨት በይ፣ ሻምፖ በይ፣ ምናምን በይ ለምወዳት ልጅ ያለኝን ፍቅር ይህቺን ታህል፣ ይህቺን ታህል አይቀንሰውም፡፡ የገዛሁልሽን ስጦታ ፈተሸ ተመልከቺው። ለምን ውዝግብግቤን እንዳወጣሽው ይገባሻል፡፡”
በነጫጭ ጣቶችና በንክሻ ገመዱም ተፈታ፣ ካርቶኑም ተረታ፡፡ በመጀመሪያ ጮኸች፡፡ ከዚያ ፈነደቀች፡፡ ከዚያስ? ከዚያማ… አይወራም፡፡ እግዚኦ ነው! አለቀሰች፡፡ እዬዬ አለች፡፡ ልጅቷን ለማፅናናት፣ የቤቱ ጌታ ያለ የሌለውን የማባበል ጥበብ ስራ ላይ ማዋል ነበረበት፡፡
ማበጠሪያዎች ናቸው፡፡ ኮምፕሌት ማበጠሪያዎችና ተጓዳኝ እቃዎች፡፡ ዘመኗን ሁሉ ስትጐመዣቸው ነበር። በብሮድዌይ ጐዳናዎች ላይ ባሉት መደብሮች ባለፈች ባገደመች ቁጥር ታያቸው ነበር፡፡ በህፃን መጓጓት ነበር ስትመለከታቸው የኖረችው፡፡ እጅግ ያምራሉ፡፡ ከኤሊ ልብስ ብቻ የተሰሩ ናቸው፡፡ ክፈፋቸው በሉሎች ተጊጠዋል፡፡ ውቡ ጸጉሯ ላይ ሻጥ አድርጋ ይበልጥ የምትዋብባቸው ናቸው፡፡ ያ ውብ ጸጉሯ የት ነበር እንኳ የሄደው? ማበጠሪያዎቹ በጣም ውድ እንደሆኑ ጠንቅቃ ታውቃለች፡፡ ከእሷ የመግዛት አቅም በላይ ነበሩ፡፡ መቼም አይኖሯትም ነበር፡፡ የሆነ ነገር እንደማያገኙት ሲያውቁ ደግሞ ያንን ነገር የማግኘት ረሀቡ ለጉድ ይጨምራል፡፡ በቃ እንዲሁ በልቧ ስትቋምጥ እና ስትስገበገብላቸው ኖራለች። በቅናት ስታያቸው ባጅታለች፡፡ አሁን ማበጠሪያዎቹ የሷ ናቸው፡፡ ጸጉሯ ግን የለም፡፡ ተጨማሪ ውበት የተደገሰለት፣ ውብ ጸጉሯ ሄዷል፡፡
ጡቶቿ ላይ ልጥፍ አደረገቻቸው፡፡ አቅፋቸው ቆየች። እንደምንም ቀና ብላ፣ በእንባ በተጋረዱ አይኖቿ ጂምን አየቸው፡፡ ፈገግ ብላ፡- “ጂም ጸጉሬ በጣም በፍጥነት ነው የሚያድገው፡፡” አለች፡፡
ዴላ፣ ድንገት ውስጥ መዳፏን የሚፋጅ ነገር እንዳገኛት ሚጢጢ ድመት ዝልል ብላ፡- “ወይኔ! ወይኔ!” አለች፡፡
ጂም የተዘጋጀለትን ምርጥ ስጦታ እስካሁን አላየም፡፡ ዴላ በታላቅ ጉጉት ተውጣ፣ መዳፏ ላይ አድርጋ፣ ዘርግታ አሳየችው፡፡ ደብዛዛው፣ ውዱ ብረት የልጅቷ ወደር የሌለው የመንፈስ ብርሃን ተጋብቶበት እንደ ማብረቅረቅ ነገር ቃጣው፡፡
“ጂም፣ እጅግ የተዋበ ነገር ነው፡፡ እየውማ፤ ያምራል አይደል? ይህን ለመግዛት ከተማውን ምን ያህል እንዳሰስኩት አልነግርህም፡፡ አሁን በቀን መቶ ጊዜ ሰዓትህን መዥረጥ እያደረግክ ማየት ትችላለህ፡፡ ሰዓትህን አምጣው፤ እሱ ላይ ሲታስር እንዴት እንደሚያምር ልየው፡፡”
ያለችውን አላደረገም፡፡ ሶፋው ላይ ዘፍ አለ፡፡ ሁለት እጆቹን ከኋላ አድርጐ  ተንተራሳቸው፡፡ ሳቅ አለ፡፡
“ዴል፣ የገና ስጦታዎቻችንን ለአሁን ገለል እናድርጋቸው፡፡ ይቀመጡ፡፡ ለጊዜው ልንጠቀምባቸው አንችልም፡፡ ላንቺ ስጦታ ለመግዛት፣ ማበጠሪያዎቹን ለመግዛት ሰዓቱን ሸጬዋለሁ፡፡ አሁን የተከተፈውን ስጋ መጥበሻው ላይ ብታደርጊው ሸጋ ይሆናል፡፡”
እንደምታውቁት ሰብዐ ሰገሎች ጥበበኛ ሰዎች ናቸው። ጥበባቸው እጅግ ታላቅ ነበረ፡፡ በበረት ለተወለደው ህፃን ስጦታ ይዘውለት የሄዱት እነሱ ነበሩ። በገና ስጦታ የመለዋወጥን ድንቅ ልማድ የጀመሩት እነሱ ናቸው፡፡ ምናልባት ስጦታዎቻቸው ተመሳሳይ ቢሆኑ ለመቀያየር እንዲችሉ ተጨማሪ ስጦታ ይዘው እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለም፡፡ ብልሆች ናቸዋ፡፡ የተረኩላችሁ ገድል በአንዲት ክፍል ውስጥ የሚኖሩ፣ ሁለት የዋህ ወጣቶች፣ አንዳቸው ለአንዳቸው መልካም ስጦታ ለማበርከት ሲታትሩ፣ የሚያትት ነው፡፡ በመጨረሻም ለዘመናችን ብልህ ሰዎች ይህቺን ለማለት ወደድን፡- ስጦታ ከሚሰጡ ሁሉ እንደነዚህ ወጣቶች ብልህ የሆነ አንድም ስንኳ የለም። ስጦታ ከሚሰጡና ከሚቀበሉ ሁሉ በየዋህነት  የሚሰጡና የሚቀበሉ ብልሆች ናቸው፡፡ ሰብዐ ሰገሎች ናቸው፡፡

Read 3668 times