Saturday, 02 January 2016 12:17

“...እውን ትዳር ነፃነትን ያሳጣል?...”

Written by  ዮዲት ባይሳ ..ከኢሶግ..
Rate this item
(3 votes)

 ያ የሚመጣው ሰው ባዶውን ሳይሆን የእራሱ የሆነ እውቀት፣ ልምድ፣ ሀብት ወይም በትንሹ የእራሱን ሀሳብ ይዞ ነው የሚመጣው፡፡
አንድ አእምሮ ከሚሰራ ሁለት አእምሮ በጋራ ቢሰራ የሚደመር እንጂ የሚቀነስ ነገር የለውም፡፡
ትዳር ማለት ችግርን ወይም ተግዳሮትን ለሁለት የሚያካፍል፣ ደስታ እና ስኬትን ደግሞ በሁለት የሚያበዛ ወዳጅ ማግኘት ማለት ነው፡፡
በሰው ልጅ እድገት ውስጥ ህፃንነት፣ ልጅነት፣ ወጣትነት፣ ጉልምስና እና እርጅና የማይቀሩ የህይወት ኡደቶች ናቸው፡፡ ታድያ በእነዚህ የእድሜ ደረጃዎች አንድ ሰው ሊያደርጋቸው የሚገቡ ወይም አይቀሬ የህይወት ክንውኖች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ትዳር ወይም ጋብቻ አንዱ ነው፡፡
“...ጉርምስና ከመጣ በኋላ ወንዶች ለሴቶች እንዲሁ ሴቶችም ለወንዶች የሚኖራቸው አመለካከት ቀድሞ ከነበረው የተለየ ይሆናል ወይም በአጭሩ እርስ በእርስ የመፈላለግ ስሜት ይኖራቸዋል፡፡ ይህ ወንድን ወይም ሴትን የመፈለግ ተፈጥሯዊ ስሜት በግዜ ሂደት አድጎ ጋብቻ የምንለው ደረጃ ላይ ይደርሳል፡፡ ስለዚህ ጋብቻ የምንለው አንድ ወንድ እና አንድ ሴት ግንኙነት የሚመሰርቱበት እና ቀጣይ ኑሯቸውን አብረው የሚኖሩበት ጥምረት ወይም አንድነት ነው ማለት እንችላለን፡፡ ወይም በአጭር ቃል ጋብቻ ወይም ከዛ የሚቀድመው የተቃራኒ ፆታ ግንኙነት ተፈጥሯዊ ለሆነ ስሜት ምላሽ መስጠት ነው ብለን ልንተረጉመው እንችላለን፡፡...”
ይህን ያሉን የስነልቦና ባለሙያ የሆኑት አቶ ከበደ በከሪ ሲሆኑ አቶ ከበደ በጋብቻ ዙሪያ በርካታ መፃህፍትን የፃፉ ሲሆን የምክር አገልግሎት በመስጠት የእረዥም አመታት ልምድ አካብተዋል፡፡  ምንም እንኳን በጋብቻ መልካምነት ላይ ብዙዎች ቢስማሙም ጥቂት የማይባሉ ሰዎች በግል ህይወታቸው ከተለማመዱት፣ በአካባቢያቸው ካዩት እና ከሰሙት ነገሮች በመነሳት ስለ ጋብቻ አሉታዊ የሆነ አስተሳሰብን ሊያራምዱ ይችላሉ የሚሉት ባለሙያው የሰዎች ድርጊት በአብዛኛው የሚወሰነው በአእምሮአቸው ውስጥ ባለው አስተሳሰብ በመሆኑ ሰዎች የጋብቻን መልካምነት እንዳይረዱ ብሎም የተሳሳተ አመለካከት እንዲኖራቸው ምክንያት የሚሆኑ አስተሳሰቦች ወይም ልምምዶች በርካታ እንደሆኑም ጨምረው ይጠቅሳሉ፡፡
“...ሁሉም ሰው ጋብቻን አይፈራም፡፡ ነገር ግን ጋብቻን የማይፈልጉ እና ሀላፊነት ወዳለበት ህብረት ለመግባት የሚፈሩ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ እንግዲህ ይህ ፍርሀት ወይም አሉታዊ የሆነ አመለካከት የእራሱ የሆነ መነሻ ምክንያት ይኖረዋል፡፡ የሁሉም ምክንያት ግን ተመሳሳይ ላይሆን ይችላል፡፡...”   
እነዚህ ምክንያቶች እጅግ በርካታ እና የተለያዩ ቢሆኑም የቤተሰብ የኋላ ታሪክ አንዱ እና ግንባር ቀደም ከሚባሉት ውስጥ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ ሰዎች በቤተሰቦቻቸው የትዳር ህይወት ውስጥ ከሚያዩት ነገር በመነሳት ስለጋብቻ መልካም ወይም መጥፎ አመለካከት ሊኖራቸው እንደሚችል አቶ ከበደ ይናገራሉ፡-
“እኛ ባደግንበት ቤተሰብ ውስጥ አባት እና እናታችን ጥሩ የሆነ የባልና ሚስት ግንኙነት ከሌላቸው ወይም ስለ ጋብቻ ስናስብ አርአያ ሊሆን የሚችል ቤተሰብ ከሌለን የእነሱን ችግር እና መጥፎ ግንኑነት በማየት ወደ እንደዛ አይነት ህይወት ላለመግባት በሚል እንሸሻለን፡፡ ነገር ግን በተቃራኒው ጥሩ የትዳር ግንኙነት ያላቸው እና ምሳሌ መሆን የሚችሉ ቤተሰቦች ካሉን እኔም መቼ አግብቼ እንደእነሱ አይነት ህይወት ይኖረኛል? የሚል ጉጉት ሊያድርብን ይችላል፡፡ ስለዚህ የቤተሰባችን የትዳር ሁኔታ እዚህ ላይ የሚኖረው ሚና ይህ ነው የሚባል አይደለም፡፡..”
የሰላም ታሪክ ለዚህ አይነተኛ ማሳያ ነው፡፡ ሰላም በሀያዎቹ መጀመሪያ ላይ የምትገኝ ወጣት  ስትሆን ከአንድ አመት በፊት የነበረውን የትዳሯን አጀማመር እንዲህ ታስታውሰዋለች፡-
“...ከማግባቴ  በፊት ትዳር በጣም የሚያስፈራ ነገር ይመስለኝ ነበር ባጠቃላይ ስለ ትዳር ያለኝ አመለካከት ጥሩ አልነበረም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ቤተሰቦቼ ጥሩ የትዳር ህይወት ስላልነበራቸው ይመስለኛል፡፡ በዚህም ምክንያት ከጓደኛዬ ጋር ሶስት አመት ያህል አብረን ከቆየን በኋላ የትዳር ጥያቄ ሲያቀርብልኝ በጣም ነበር የደነገጥኩት፡፡ እሺታዬንም ቶሎ አልነገርኩትም፡፡ ከብዙ ማንገራገር በኋላም ለማግባት ስወስን የቤተሰቦቼን ተቀባይነት ስላገኘሁ እሱም ሌላ ችግር ነበር፡፡”
ሌላዋ ያነጋገርናት ወጣት ሜሮን ትባላለች ሜሮንም ይህን የሰላም ሀሳብ ብትጋራም ይህ ጫና ወይም ጣልቃ ገብነት የወላጅ ወይም ያሳዳጊ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ከማህበረሰሁ የሚመነጭ ነው ትላለች፡-
“...ይህ አይነቱ ጫና ከቤተሰብ ብቻ የሚመጣ አይመስለኝም፡፡ እንደውም ብዙ ግዜ ከቤተሰብሽ ይልቅ ማግባትሽን ተቃውመው አሉታዊ የሆነ አስተያየት የሚሰጡሽ በአካባቢሽ ያሉ ሰዎች ናቸው፡፡ ሳታገቢ ከዘገየሽም እንደዛው። ለዚህ ምክንያነቱ ምን እንደሆነ በትክክል ለማወቅ ያስቸግራል። ግን አንዳንዱ ገና ልጅ ናት ብሎ ስለሚያስብ ሊሆን ይችላል ወይም ከምታገቢው ሰው ማንነት በመነሳት ሊሆን ይችላል ወይም ሌሎች ምክንይቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ያምሆነ ይህ ግን ተፅእኖ ማድረጋቸው አይቀርም፡፡...”
ቤተሰብ፣ አሳዳጊ እንዲሁም በትልቁ ማህበረሰብ በዚህ እረገድ የሚኖረውን ጫና ወይም ተፅእኖ መካድ ባይቻልም ለዚህ ትልቁን ሀላፊነት መውሰድ ያለባቸው ግለሰቦች እራሳቸው መሆን ይኖርባቸዋል የሚለው ወጣት ሄኖክ ነው፡፡
“...እዚህ ላይ ቤተሰብ ተፅእኖ አያደርግም ማለት አይቻልም ነገርግን እንደ እኔ አመለካከት ወንድ ልጅ ስለ ሴት ወይም በተቃራኒው ሴት ልጅ ስለ ወንድ የሚኖራቸው አመለካከት በእራሱ ሰዎች በጋብቻ አብረው እንዳይኖሩ ወይም ጋብቻን እንዲፈሩ ከሚያደርጉ ምክንያቶች ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዝ ይመስለኛል፡፡ ሌላው ትልቁ ባጠቃላይ ስለትዳር የሚኖረን አመለካከት በእራሱ ተፅእኖ ያለው ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ሰው የሚያስበውን ነው የሚሆነው፡፡...”
እርግጥ ቤተሰብ ወይም አሳዳጊ በዚህ ላይ ተፅእኖ ያደርጋል? ባለሙያው ለዚህ ጥያቄ የሰጡን ምላሽ እንዲህ የሚል ነበር፡-
“...አንዳንድ ግዜ ልጆች ለማግባት በሚወስኑበት ግዜ ቤተሰብ ይህንን ተቃውሞ ጫና ሊፈጥር ይችላል፡፡ ሁሉም ባይሆንም አንዳንዶች ከልጆቻቸው የሚያገኙት ጥቅም ወይም ድጋፍ ይኖርና ልጆቻችን ካገቡ ይህ ጥቅም ሊቀርብን ይችላል ወይም ሊረሱን ይችላሉ ከሚል ስጋት ጋብቻውን ሊቃወሙ ይችላሉ፡፡ እርግጥነው ወላጅ ለልጁ መልካም የሆነውን ነገር ያስባል እንዲሆንም ይፈልጋል ነገርግን አንዳንዴ እንዲህ አይነት ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ እድሜህ/ሽ ገና ነው ወይም ይህ/ች ሰው አይሆንሽም/አትሆንህም በሚሉ ምክንያቶች ወላጆች ልጆቻቸው ወደ ትዳር እንዳይገቡ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ...በዚህ ላይ ወላጆች ምንም አይነት ጣልቃ ገብነት ሊኖራቸው አይገባም ማለት ባይቻልም በዚህ ላይ ትልቁ የመወሰን ሀላፊነት የተጋቢዎቹ መሆን ኖርበታል፡፡...”
የኢኮኖሚ አቅም ሰዎች ጋብቻን እንዲፈሩ ወይም ብቸኝነትን እንዲመርጡ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል በዋነኛነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ምንም እንኳን በኢኮኖሚ እራስን መቻል እና መሰረታዊ የሰው ልጅ ፍላጎቶችን ማሟላት ትዳር ከመመስረቱ በፊት ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ቢሆንም ትዳር በገንዘብ ወይም በቁሳቁስ ላይ መመስረት የለበትም ይላሉ ባለሙያው፡-
“...በቂ የሆነ ገንዘብ የለንም፡፡ ስለዚህ ብቻዬን ብቸገር ይሻላል... የሚሉ አስተያየቶች ብዙ ግዜ ይደመጣሉ፡፡ እንግዲህ ምንያህል ነው ሰውን ሊያኖር የሚችለው? የሚለው አንፃራዊ ነው፡፡ እንደ እይታችን፣ እንደምንኖርበት ማህበረሰብ እና አካባቢ ይለያያል፡፡ ነገርግን መሰረታዊው ጥያቄ እንደ አንድ ሰው ለብቻ መኖር ከቻልን ሌላው ሰው ሲመጣ ለምን ሀሳብ ይሆንብናል? ምክንያቱም ያ የሚመጣው ሰው ባዶውን ሳይሆን የእራሱ የሆነ እውቀት፣ ልምድ፣ ሀብት ወይም በትንሹ የእራሱን ሀሳብ ይዞ ነው የሚመጣው፡፡ ስለዚህ አንድ አእምሮ ከሚሰራ ሁለት አእምሮ በጋራ ቢሰራ የሚደመር እንጂ የሚቀነስ ነገር የለውም ስለዚህ ከአንድ ሁለት ይሻላል።...”
ሌላው የትዳርን አሉታዊ ጎን ከሚሰብኩ ሰዎች የሚያነሱት ምክንያት “ትዳር ነፃነትን ያሳጣል” የሚል ነው፡፡ እውን ትዳር ነፃነትን ያሳጣል? ለሰላም ያነሳንላት ጥያቄ ነበር፡፡
“በዚህ አሳብ በፍፁም አልስማማም ምክንያቱም ትዳር ከያዝኩበት ቀን አንስቶ እስከአሁን ድረስ ነፃነቴን የሚያሳጣ ወይም በጓደኝነት ግዜ ከነበረን ምንም የተለየ ነገር አላየሁም።” እኔእና ባለቤቴ ከመጋባታችን በፊት በጣም ጥሩ የሚባል የፍቅር ግዜ አሳልፈን በሚገባ ተዋውቀናል፡፡ ስለዚህ እንደ እኔ አመለካከት በመጋባታችን ብቻ ምንም የሚፈጠር አዲስ ነገር አይኖርም፡፡ ምንአልባት ይህ አይነቱ ችግር ሊፈጠር የሚችለው በሚገባ ሳትተዋወቂ ወይም ሳትናበቢ ወደ ትዳር የምትሄጂ ከሆነ ብቻ ነው፡፡”
ይህ አይነቱ አመለካከት ከእራስ ወዳድነት የሚመነጭ ነው፡፡ ያለን ደግሞ ሌላው ለዚህ ፅሁፍ ግብአት ይሆነን ዘንድ ሀሳባቸውን ከሰጡን ወጣቶች መካከል ባለትዳር እና የአንድ ልጅ አባት የሆነው ዳንኤል ነው፡፡
“...እኔ ይህንን እንደ እራስ ወደዳድነት ነው የማየው፡፡ በእርግጥ ነፃነቱን የሚጠላ ማንም የለም ነገርግን ትዳር ለእኔ እስር ቤት ማለት አይደለም፡፡ ትዳር ለእኔ ለሌላው በመኖር ልዩ ደስታ የሚገኝበት ህይወት ነው፡፡ በእርግጥ ትዳር ለሌላው በቂ ግዜ መስጠትን ይጠይቃል ምናልባት ሰዎች እንደ ነፃነት ማጣት የሚቆጥሩት ይህንን ሊሆን ይችላል፡፡ ነገርግን እኔን ይበልጥ የሚያዝናናኝ ከባለቤቴ እና ከልጄ ጋር የማሳልፈው ግዜ ነው፡፡...”
የግለሰቦች ምርጫ እንደተጠበቀ ሆኖ ማግባት ካለ ማግባት የበለጠ ጥቅም አለው የሚሉት ባለሙያው አንድ ሰው እድሜው ለትዳር ከደረሰ በኋላ ትዳር መስርቶ ለመኖር ቢወስን እና ቢያገባ ካላገቡ ሰዎች የበለጠ ስኬታማ ህይወት እንደሚኖረውም ይናገራሉ፡፡
“...ትዳሩ በጣም ታስቦበት የተመሰረተ ተጋቢዎቹም በስብእበና፣ በህይወት ግባቸው፣ በህይወት ዘይቤአቸው እንዲሁም በእሴቶቻቸው የሚጣጣሙ ከሆነ ማግባት ካለማግባት በእጅጉ የተሻለ ነው፡፡ ...በአለማችን ላይ ያሉ ስኬታማ የሚባሉ ሰዎች ብዙዎቹ ትዳር ያላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ አልፎ አልፎ ያላገቡ ሰዎችም ሊኖሩ ይችላሉ። ነገርግን ጠቅለል አድርግን እንደ ማህበረሰብ ስንመለከት በህይወት ፍሬያማ ለመሆን በጣም የቅርብ የሆነ፣ የእኔ የምንለው ሰው ያስፈልገናል፡፡ ...ስለዚህ ትዳር ማለት ችግርን ወይም ተግዳሮትን ለሁለት የሚያካፍል፣ ደስታ እና ስኬታችንን ደግሞ በሁለት የሚያበዛ ወዳጅ ማግኘት ማለት ነው፡፡...”

Read 7029 times