Saturday, 02 January 2016 14:21

በ2015 በመላው ዓለም 100 ጋዜጠኞች ተገድለዋል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

- ባለፉት 10 አመታት የተገደሉ ጋዜጠኞች 787 ደርሰዋል
በተጠናቀቀው የፈረንጆች አመት 2015 በአለማችን 100 የተለያዩ አገራት ጋዜጠኞች በስራቸው  ምክንያት ወይም ባልታወቀ ሰበብ መገደላቸውን ሪፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ የተባለው አለማቀፍ የጋዜጠኞች
መብት ተሟጋች ተቋም ባለፈው ማክሰኞ አስታወቀ፡፡ በአመቱ ለህልፈተ ህይወት ከተዳረጉት ጋዜጠኞች መካከል ስድሳ ሰባቱ በስራቸው ላይ እያሉ  ተገድለዋል ያለው ተቋሙ፤
ይህም ባለፉት አስር አመታት ከሙያቸው ጋር በተያያዘ የተገደሉ ጋዜጠኞችን ብዛት 787 እንዳደረሰው ጠቁሞ ሌሎችበሰላማዊ አገራት የሚንቀሳቀሱ በርካቶችም በስራቸው ምክንያት የግድያ ኢላማ መሆናቸውን
አስታውቋል፡፡ በአመቱ 43 ጋዜጠኞች የግድያ ሁኔታቸው ወይም የመገደላቸው ሰበብ ሳይታወቅ መገደላቸውን
የገለጸው ተቋሙ፣ በሙያቸው ጋዜጠኛ ባይሆኑም በዘርፉ የተሰማሩ 27 ግለሰቦችና በሌሎች ሚዲያዎች ላይ የሚሰሩ 7  ሰራተኞች መገደላቸውንም ጠቁሟል፡፡
በአብዛኞቹ ጋዜጠኞች ላይ የተፈጸሙት ግድያዎች ሆን ተብለው የተቀነባበሩ ናቸው ያለው ተቋሙ፣
ለጋዜጠኞች የሚደረገው ከለላ አናሳ መሆኑን ጠቁሞ፣ የተባበሩት መንግስታት በሟቾቹ ላይ ለተወሰደው እርምጃ  የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጡ የሚያስችል አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል፡፡ በ2014 በተለያዩ የአለማችን አገራት ከሞቱት ጋዜጠኞች መካከል ሁለት ሶስተኛ ያህሉ ጦርነት
ባለባቸው አካባቢዎች የተገደሉ እንደነበሩ ያስታወሰው ሪፖርቱ፤ በተቃራኒው በ2015 ከሞቱት ጋዜጠኞች መካከል ሁለት ሶስተኛ ያህሉ ሰላማዊ ተብለው በሚታወቁ አካባቢዎችና አገራት የተገደሉ መሆናቸው ተረጋግጧል ብሏል፡፡ በአመቱ 11 ጋዜጠኞች የተገደሉባት ኢራቅ፣ለጋዜጠኞች አደገኛ የሆነች የአለማችን ቀዳሚዋ አገር  መሆኗን የጠቀሰው ተቋሙ፤10 ጋዜጠኞች የተገደሉባት ሶርያ በሁለተኛነት መቀመጧን፣ በቻርሊ ሄቢዶ መጽሄት ዝግጅት  ክፍል ላይ ሽብርተኞች በፈጸሙት ጥቃት 8 ጋዜጠኞች የተገደሉባት ፈረንሳይም ሶስተኛ ደረጃን መያዟን  ገልጧል፡፡
አይሲስና አልቃይዳን የመሳሰሉ የሽብር ቡድኖች በአመቱ 28 ጋዜጠኞችን መግደላቸው የተነገረ
ሲሆን በተለያዩ አገራት የታሰሩ ጋዜጠኞች ቁጥርም 153 ደርሷል፡፡

Read 1742 times