Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 18 February 2012 10:26

የሙዚቃና የፊልም አሳታሚዎችና አከፋፋዮች ሱቆች እንዲፈርስ ተወሰነ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የኢንዱስትሪውን ዕድገት ወደኋላ ይመልሳል ተብሏል

በአዲስ አበባ ከተማ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ቀበሌ 32 ልዩ ስሙ “ጎንደር በረንዳ” ወይም “ቄጠማ ተራ” እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ከግለሰብ ላይ መጋዘን ተከራይተው የዘፈን እና የፊልም ሕትመቶችን ሲቸረችሩ እና ሲያከፋፍሉ የነበሩ 50 አሳታሚ እና አከፋፋዮች በሦስት ቀን ውስጥ ሱቆቻቸውን እንዲያፈርሱ የተሰጣቸው ማስጠንቀቂያ ተገቢ አለመሆኑን ገለፁ፡፡ ከሁለት ቀናት በፊት በተጠቀሰው ቦታ ተገኝተን ሱቆቹን እንደተመለከትናቸው መጋዘኑ በጥቁር ድንጋይ የተሠራ ሲሆን ውስጡ በኮምፖርሳቶ እና በብረት የተከፋፈሉ ሱቆች ተሠርተውበታል፡፡

አሣታሚ እና አከፋፋዮች እንደሚሉት፤ ቀደም ሲል ይህን ሥራ ይሠሩ የነበሩት መርካቶ አንዋር መስጊድ አጠገብ ሲሆን ሱቆቹ ደግሞ የመስጊዱ ንብረቶች ነበሩ፡፡ ከስድስት ወራት በፊት የመስጊዱ አስተዳደር በሱቆቹ ውስጥ እየተሠሩ ያሉት የሙዚቃ እና የፊልም ሥራዎች ከኃይማኖት ጋራ የማይዛመድ በመሆኑ ለቀው እንዲወጡ በድንገት የተሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ተቀብለው መልቀቃቸውን ይናገራሉ፡፡

በአንዋር መስጊድ አካባቢ በሕገወጥ መንገድ የሚያባዙት እና በሕጋዊ መንገድ የሚሠሩት ተቀላቅለው እንደነበር የገለፁት አሣታሚ እና አከፋፋዮቹ፤ ከመስጊዱ አስተዳደር ውሳኔ በኋላ ሕጋዊ የሆኑት 50ዎቹ ተለይተው እና ተደራጅተው ቦታ ሲያፈላልጉ ቆይተው የአቶ አፍሬም ይርጋ ኃይሌ የግል ንብረት የሆነውን ትልቅ መጋዘን ውስጡን በኮምፖርሳቶ ሸንሽነው፣ እያንዳንዳቸው የመንግሥትን ሕጋዊ ታክስ ከፍለው እና ሕጋዊ ውል አድርገው የአንድ ዓመት ኪራይ በመክፈል ሥራ ከጀመሩ ሁለት ወር እንኳን ሳይሞላቸው ግንባታው ሕገ ወጥ ነው በሚል ሱቆቻቸው ለሦስት ወር ያህል እንደታሸገባቸው ይናገራሉ፡፡

ሱቆቹ ከታሸጉም በኋላ ኮሚቴ አቋቁመው የተደረገው ግንባታ ምንም ዓይነት የይዘት ለውጥ እንዳልተደረገበት፤ የመጋዘኑ ባለቤት አቶ ኤፍሬም ይርጋ ከሁለት ዓመት በፊት በወጣ ጨረታ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የገዙት ንብረት እንደሆነ እና እርሳቸው ከገዙት በኋላ በመጋዘኑ የውጭውም ሆነ የውስጥ አካል ላይ አንድም የይዞታ ለውጥ ሳያደርጉ ለጥበቃ እና አንዱን ሱቅ ከአንዱ ለመለየት እንዲቻል ብቻ በኮምፖርሳቶ እና በመደርደሪያ በመለየት ሲሠሩ እንደነበር ገልፀዋል፡፡

የዴንሳት ሙዚቃ ቤት ባለቤት አቶ ወርቅነህ አደመ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ ከአንዋር መስጊድ አካበቢ ድንገት እንዲነሱ በመወሰኑ፣ ሱቅ እስኪያገኙ ድረስ ለሁለት ወራት ያህል ሥራ ፈተው እንደነበር እና በመጨረሻ አሁን እንዲፈርስ የተባለውን ሱቅ እንደተከራዩ ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ጥረታቸውን አሟጠው ሱቁን ካስተካከሉ በኋላ፣  “አርሂቡ” ቁጥር ሁለት የተሰኘ የተለያየ ድምጻውያንን ዘፈኖች የያዘ ቪሲዲ አሣትመው ለገበያ ለማቅረብ በሚዘጋጁበት በዚህ ጊዜ ከነማስታወቂያው ለሦስት ወር መታሸጉ እርሳቸውን ለከፍተኛ ኪሣራ መዳረጉንና የሙዚቃ ኢንዱስትሪውን መጉዳቱን ገልፀዋል፡፡ ይህንንም በፀጋ ተቀብለው ሱቁን ከፍተው መሥራት ከጀመሩ በኋላ በሦስት ቀን ውስጥ እንዲያፈርሱ ትእዛዝ መስጠቱ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡

የሐበሻ ሙዚቃ ቤት ባለቤት አቶ ፋሲል እሸቱ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ የሙዚቃ እና የፊልም ኢንዱስትሪ በተለያዩ ችግሮች የተሳሰረ መሆኑ ሳያንሰው፤ ያለችውን ትንሽ ተስፋ የሚያለመልሙት፣ በኢትዮጵያ የሚገኘውን የኢንዱስትሪውን 90 በመቶ ንግድ የሚያንቀሳቅሱት እና በመላው ኢትዮጵያ እያሳተሙ የሚያከፋፍሉትን ነጋዴዎችን በአንድ ላይ እንዲዘጉ ማድረግ ኢንዱስትሪው እየተጓዘ ካለበት መንገድ ወደ ኋላ መመለስ ነው ብለዋል፡፡

አያይዘውም፣ ከአንዋር መስጊድ አካባቢ እንዲነሱ የተደረጉት በኃይማኖት አማካኝነት መሆኑን አምነው ተቀብለው ያላቸውን ገንዘብ አሟጠው ተገቢውን የመንግሥት ግብር ከፍለው በንብረቱ ላይ ምንም ዓይነት የይዞታ ለውጥ ሳያደርጉ እየሠሩ ያሉት ሥራ ግንባታው ሕገወጥ ነው እንኳን ቢባል ተቀጥተው ሕጋዊ መስመር ውስጥ ሊገቡ የሚችሉበት መንገድ ሊመቻች ሲገባው አፍርሱ መባሉ ተገቢ አለመሆኑን እና ከመፍረሱ የሚጎዳ እንጂ አንድም የሚጠቀም አካል እንደማይኖር ቦታውን እና አካባቢውን ብቻ በማየት መገመት እንደሚቻል አቶ ፋሲል ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የወረዳ 7 ሥራ አስኪያጅ አቶ ሣህሉ ብርሃኑ በበኩላቸው፤ የቤቱ ባለቤት የተጠቀሱት አሣታሚ እና አከፋፋዮች ሳይሆኑ አቶ ኤፍሬም ይርጋ የተባሉ ግለሰብ መሆናቸውን ገልፀው፤ በማስተር ፕላኑ መሠረት በቦታው ላይ እንዲገነባ የሚፈቀደው ባለ ሦስት ፎቅ ሕንፃ መሆኑን በመጠቆም በተጠቀሰው ቦታ ላይ ግን የተሠራው ቤት ማስተር ፕላኑ ከሚፈቅደው ውጪ በመሆኑ እንዲያፈርሱ መወሰኑን ተናግረዋል፡፡

ውሳኔውንም ከማስጠንቀቂያ ጋር በመስከረም ወር 2004 ዓ.ም ሰጥተዋቸው በጥቅምት ወር ሊያፈርሱ ሲሄዱ ባለቤቶቹ ሱቁን ዘግተው በመጥፋታቸው መታሸጉን እና አሁንም ባለቤቱ አቶ ኤፍሬም ግንባታው ሕገ ወጥ መሆኑን አምነው በሦስት ቀናት ውስጥ ለማፍረስ ተስማምተው በመፈረማቸው ማስጠንቀቂያው ሊደርሳቸው እንደቻለ አስረድተዋል፡፡

“የተጠቀሰውን ችግር ሳንረዳው ቀርተን አይደለም፡፡ የሱቆች በአንድ ላይ አለመሆን በቅጂ መብት መከበር ላይ የሚያመጣውን ተፅዕኖና በነጋዴዎች ላይ የሚያሳድረውን ጫና እንረዳለን፤ ነገር ግን ይህ ቦታ በማስተር ፕላኑ ላይ የተሠራ ዲዛይን አለው፡፡ ከዛ ውጪ የተሠራን ነገር በዝምታ ማለፍ ሕገወጥነትን ማበረታታት ነው፡፡ ሁኔታውን ተረድተን፤ ግንባታውን አፍርሰው በዲስፕሌይ እንዲሠሩ አማራጭ ሰጥተናቸዋል” ብለውናል፡፡ አሣታሚ እና አከፋፋዮቹ ይህንን ሐሳብ ባለመቀበል በዲስፕሌይ ደርድሮ መሥራት ንብረትን ለዘረፋ እንደሚያጋልጥ በመግለፅ፤ ማንኛውም ቀና አስተሳሰብ ያለው መንግሥትም ሆነ ግለሰብ በቦታው ላይ በዲስፕሌይ ደርድሮ መሥራትን ከፈቀደ ውበት ባለው መልኩ የቤቱን ይዞታ ምንም ሳይለውጡ ከልሎ መሥራትን ለመፍቀድ ለምን እንደተቸገሩ በመግለፅ፤ አሁንም ቢሆን የክፍለ ከተማውም ሆነ የወረዳው የበላይ አካል በቦታው ተገኝቶ ሁኔታውን በማየት አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ የአሣታሚዎቹ እና አከፋፋዮቹ በአንድ አካባቢ ተሰባስበው መሥራታቸው ሕገወጥ ቅጂዎች እንዳይስፋፋ በእጅጉ እንደሚከላከል በመጠቆም መንግሥት ከኪሣራ እንዲታደጋቸው ጠይቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦዲዮ ቪዥዋል አሣታሚዎች ማኅበር ሥራ  አስኪያጅ አቶ ኃይላይ ታደሰ በበኩላቸው፤ አሣታሚዎች እና አከፋፋዮች በአንድ ላይ በአንድ አካባቢ ተሰባስበው ሥራ መጀመራቸው ሕገ ወጦችን ከሕጋዊዎች ለመለየት ከፍተኛ አስተዋፆኦ እንዳበረከተ ገልፀው፤ ወረዳው እንዲህ ያለ ውሳኔ ወስኖ ሱቆቹ ለሦስት ወራት ባሸገበት ጊዜ በኪነጥበብ ኢንዱስትው ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡ አሣታሚ እና አከፋፋዮቹ በተለያዩ የክልል ከተሞች የማከፋፈል ሥራን ስለሚሠሩ ለኪነጥበብ ኢንዱስትሪው አንዱ እንቅፋት የሆነውን የስርጭት ችግር መቅረፍ እንደተቻለ ገልፀው፤ ነጋዴዎቹ መጋዘኑን የተከራዩት ከግለሰብ ንብረት ላይ በመሆኑ እና በቤቱ የውጭ እና የውስጥ አካል ላይ ምንም ዓይነት የይዘት ለውጥ ሳያደርጉ ደስ በሚያሰኝ መልኩ ሥራቸውን ብቻ እየሠሩ በመሆኑ መንግሥት ጉዳዩን አጢኖ አስተዳደራዊ መፍትሔ ቢሰጣቸው በርካታ ሰዎችን ከኪሣራ፣ ኢንዱስትሪውንም ከውድቀት ይታደገዋል ብለዋል፡፡

 

 

Read 3729 times Last modified on Saturday, 18 February 2012 10:30